አገር ከልጆቿ ብዙ ትጠብቃለች፤ ተዛዝነን ተባብረን በሙያችን ራሳችንን ሰውተን እንድናገለግላት ከክፋት ከተንኮል ከሀሜት ርቀን አለሁሽ እንድንላት ፤ መልካም መልካሙን እያሰብንና እየሰራን ነገዋን ብሩህ እንድናደርግላት ነው ምኞቷ። አገር ልጆቿን ደሃ ሀብታም፤ አዋቂ አላዋቂ፤ ህጻን ትልቅ ሳትል ሁሉንም በአንድ አይን ነው የምታየው፤ ሁሉም ለሷ እኩል አስፈላጊዎቿ ናቸው። እነዚህ ልጆቿ የሚጠቅማትን ነገር አድርገው ስሟን ሲያስጠሩ ያን ጊዜ አገር በልጆቿ ትደሰታለች፤ ትከብራለች፤ አክባሪዎቿንም ክብር እንዲያገኙ ታደርጋለች።
ታሪክ የሌለው ህዝብ ህዝብ ለመባል አይበቃም ። ታሪኩን ባህሉን ወጉን ጠብቆ ያልኖረውም ቢሆን ያው ነው። ታሪክና ባህልን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ደግሞ የእገሌ ስራ ነው ሊባል የሚችል አይደለም ሁላችንም ሃላፊነት አለብን ። ጥያቄው ይህንን ሃላፊነት በምን መልኩ እንወጣ የሚለው ነው፡፡
የዛሬ የህይወት ገጽታ አምድ እንግዳችን ይህንን የአገር ውለታ ለመመለስ በተለይም ትውልዱ ላይ የአገር የባህልና የወግ ፍቅርን ለማስረጽ ከፍ ያለ ዋጋ እየከፈሉ ብዙ ስራዎችን የሚሰሩ እናት ናቸው ወይዘሮ ጥሩወርቅ ደስታ ። ወይዘሮ ጥሩወርቅ ደስታ የት ተወለዱ? ብዬ ስጠይቃቸው እኔ የተወለድኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ። ንጹህ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኦሮሞም፣ አማራም ፣ ጉራጌም፣ ትግሬም ሌላውንም ሌላውንም ነኝ፤ በጋብቻም በዝምድናም በጓደኝነትም ያልተቀላቀልኩት ብሔር የለም በማለት ይገልጻሉ።
“….እኔ ኢትዮጵያዊነቴን ከምንም በላይ የምወደውና የማከብረው ነገር በመሆኑ የዚህ አካባቢ ተወላጅ ነኝ ማለት አልፈልግም ምክንያቴ ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች አገሬ ላይ ካሉ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተዛምጃለሁ፤ ተጋምጃለሁ ። በመሆኑም እኔ
ኢትዮጵያዊነቴን
ብቻ
ነው
የማውቀው”
ይላሉ።
ወይዘሮ ጥሩወርቅ በተወለዱበት አካባቢ ሚሽን ትምህር ቤት ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያለውን የትምህርታቸውን ተከታትለው አጠናቀዋል። ወይዘሮ ጥሩወርቅ በትምህርታቸውም ቢሆን ጎበዝ ተማሪ ነበሩ። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከገቡ በኋላም ሁለት አመት እንደተማሩ ጎበዝ ተማሪዎች ተመርጠው ወደመምህራን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት እንዲገቡ ይደረግ ነበርና እሳቸውም የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆኑ።
“…..አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ስማር ጥሩ ተማሪ ነበርኩ ፤ ከዚያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገብቼ ሁለት አመት እንደተማርኩ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተመርጬ የመምህራን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት እንድገባ ሆነ፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ሆኜ መምህር ሊያደርገኝ የሚችለውን ስልጠና አገኘሁ” ይላሉ።
ወይዘሮ ጥሩዬ የመምህራን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የአንደኛ ደረጃ መምህርነት ስልጠናቸውን በ1961 ዓም አጠናቀው ወደ መምህርነት ሙያ ገቡ።
“ ….በወቅቱ ኢንስቲትዩት ላይ መግባት ቀላል አልነበረም የሚመረጠውም ተማሪ በትምህርቱ ጎበዝ የሆነ ብቻ ነበር ። እኔም በአንደኛ ደረጃ መምህርነት ሙያ ሰልጥኜ በማጠናቀቅ ከአንድ እስከ ስድስተኛ ክፍል አንዳንድ ጊዜም እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉትን ተማሪዎች አስተምር ነበር”።
በ20 ዓመት እድሜያቸው የተቀላቀሉትን የመምህርነት ሙያ አብዝተው ይወዱት ይጨነቁለትም ነበር፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ህጻናት ተማሪዎችን እንደ እናት ሆኖ በመንከባከብ ብሎም እውቀት ጨብጠው ወደቀጣዩ ክፍል እንዲዘዋወሩ ለማስቻል ብዙ ጥረት ያደርጉ እንደነበር ይናገራሉ። ለቋንቋና ስነ ጥበብ ትልቅ ፍቅር ያላቸው ወይዘሮ ጥሩወርቅ ሲያስተምሩ የቆዩቱም እንግሊዝኛ ቋንቋንና ስዕልን ነበር።
“ ……አባቴ ስዕል ይወድ ነበርና እኔም የእሱ ተጽዕኖ አድሮብኝ ነው መሰል ስዕል መሳል እንዲሁም ማስተማር በጣም የምወደው ነገር ነው ። ለማንኛውም ቋንቋም በጣም ቅርብ ነኝ፤ ቶሎም ይገባኛል። በወቅቱ ስዕል የገቢ ምንጭ ሆኖ ኑሮን ለመግፋት ስለማያስችል ነው በማስተማር ብቻ የተወሰንኩት፤ ነገር ግን በወቅቱ ሌላ የገቢ ምንጭ ቢኖረኝ ኖሮ ሰዓሊ ነበር የምሆነው “ ይላሉ።
በአስተማሪነት ህይወታቸው ለልጆች በጣም ቅርብ እንደነበሩ የሚናገሩት ወይዘሮ ጥሩወርቅ በወቅቱም በተለይም “አንደኛ ክፍል ላይ ያሉ ህጻናት ለሴት መምህራን ብቻ ነበር የሚሰጡት ፤ በዚህም ሁሉንም የትምህርት አይነት ከማስተማራችንም ባለፈ ልጆቹን በማጫወት ትምህርቱን በጨዋታ መልክ እንዲረዱት በማድረግ በቃ እንደእናት እየተንከባከብን ነው ስናስተምር የኖርነው “ይላሉ።
በወቅቱ መምህርነት በጣም የሚከበር ሙያ ነበር ፤ ዘፈኑ እንኳን “የእኛ ልጅ ኩሪ ኩሪ ወሰደሽ አስተማሪ” ነበር የሚባለው ነገር ግን እየዋለ እያደረ የሙያው ክብር ዝቅ እያለ ከዚህ ጋር ተከትሎም የሚከፈለው ክፍያ ወቅቱን ያላማከለ እየሆነ በጠቅላላው መምህር ሆኖ ኑሮን አሻሽላለሁ ማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ እኔም የኑሮ ሁኔታዬን ለማሻሻል አስራ አራት ዓመት የሰራሁበትን የመምህርነት ሙያ ትቼ ወደሌላ የስራ መስክ ዞርኩ ይላሉ።
“…..ያ ትልቅ ስምና ዝና የነበረው የመምህርነት ሙያ አድሮ ጥጃ ከመሆኑም በላይ የሚከፈለው ገንዘብም ለመኖር አስቻይ ባለመሆኑ እሱን ትቼ ወደራሴ ስራ ገባሁ” ይላሉ።
ወይዘሮ ጥሩወርቅ በሙያቸው መምህር ይሁኑ እንጂ የዘርፈ ብዙ ሙያዎች ባለቤት ናቸው። ስዕል ይስላሉ፣ በጨርቅ ላይ ንድፍ እያወጡ በክርና መርፌ በመጥለፍ የተለያዩ የእጅ ስራዎችን ይሰራሉ፤ ዳንቴልና የመሳሰሉ ጌጣ ጌጦችን ይሰራሉ።
መምህርነትንም ካቆሙ በኋላ በቀጥታ ያመሩት የእጅ ስራ ሙያቸውን በመጠቀም የተለያዩ ነገሮችን ወደመስራት ነው።
“…እግዚአብሔር ይመስገን መምህትርነትን ብተውም የእጅ ስራ ባለሙያ ስለነበርኩ ለመኖር የሚሆነኝን ስራ እሰራ ነበር ። ስራዬን አይተው የሚወዱልኝ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር ድረስ ያሉ ደንበኞቼ ደግሞ ስራውን በመግዛት ከፍ ያለ አስተዋጽዖንም አበርክተውልኛል” ይላሉ ሁኔታውን ሲያስታውሱ።
ይህንን ስራ እየሰሩ ባለበት ጊዜ ግን ሌላ የተሻለ እድል አጋጠማቸው እሱም ከአገር ውጥቶ አሜሪካን አገር መሄድ ፤በዚህም አሜሪካን አገር ሄደው ለሶስት ዓመት ያህል ከቆዩ በኋላ እዚህ የተዋቸውን ቤተሰቦች እንዲሁም አገራቸውን በመሻት ወደአገራቸው ተመልሰዋል።
“……አሜሪካን አገር ለኑሮ በጣም ተመችቶኝ ነበር ፤ ነገር ግን የአገሬ ፍቅር ብሎም ከእናቴ ጀምሮ ባለቤቴ ልጆቼ ሙሉ ቤተሰቦቼ ያሉት አገር ውስጥ ነው ። በመሆኑም እነሱን ተነጥዬ ለመቆየት በጣም ስለከበደኝ የራሴን ምቾት ወደጎን በማለት ወደአገር ቤት ተመልሻለሁ” ይላሉ።
ወይዘሮ ጥሩወርቅ በአገራቸው ላይ የመስራት ፍላጎት የነበራቸው በመሆኑ በርካታ ትልልቅ የንግድ ስራዎችን ጀምረውም ነበር፤ ነገር ግን እሳቸው እንደሚሉት አካሄዱን ባለማወቄ ብዙ ጥሪቴን ያፈሰስኩባቸው የንግድ ስራዎች እንዲሁ ቀሩ በማለት ይናገራሉ።
“….አንዳንድ ጊዜ ቀጥተኛ መንገድን ተጠቅሞ የንግድ ስራ በተለይም በርካታ ሰዎችን የሚያስተዳድር ስራን መጀመር ከባድ ነው እኔም የሆንኩት እንደዛ ነው። በስራዬ ላይ ትልቅ ጨረታ ተጫርቼ ባሸንፍም ባጋጠመኝ የአካሄድ መበላሸት (ሙስና ) ምክንያት ስራዬ ተበላሸ” ይላሉ።
በቀን በሺዎች የሚቆጠር እንጀራን በመጋገር ያከፋፍል የነበረና በርካታ ሰራተኞችን የሚያስተዳድረው የወይዘሮ ጥሩወርቅ የንግድ ድርጅት በሰዎች ያለአግባብ ጥቅም መጠየቅ ምክንያት በስራው እንዳይቀጥሉ ሆነ። በዚህ ምክንይት ደግሞ አለኝ የሚሉትን ንብረት ሁሉ ለመሸጥ ተገደዱ ።
“…..ቤት ንብረት ሲሸጥ መኪና ሲሸጥ በእጅ ያለ ነገር ሁሉ ሲጠፋ ጤና ሲጎል በጣም ከባድ ነው ፡፡ነገር ግን እኔ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ዛሬ ላይ ቢኖሩ የት ልደርስባቸው የምችላቸውን ንብረቶቼን ስራዬን ባጣም ፈጣሪዬን አመስግኜ የቀረኝን ለመጠቀም ግን አላመነታሁም “ይላሉ።
ንብረት የለም በጤናቸው ላይ ባጋጠማቸው ችግር እግራቸው እንደልብ አይንቀሳቀስላቸውም፡፡ ነገር ግን ወይዘሮ ጥሩወርቅ በቤታቸው ውስጥ ቁጭ ብለው የሚሰሩት ስራ እጅግ የሚገርም ነው። የእጅ ስራዎችን ይሰራሉ አትክልቶችን ይተክላሉ፤ በራሳቸው ወጪ ችግኝ እየገዙና እያፈሉ የመትከል ፍላጎቱ ላላቸው ሰዎች በተለይም ህጻናት ይሰጣሉ። በጠቅላላው ወይዘሮ ጥሩወርቅ ስራ መፍታት ብሎ ነገር አያውቁም።
“…..ንብረቴን ካጣሁ እግሬን ካመመኝ በኋላ አሁን ምን ቀረኝ ብዬ ሳስብ፤ አዎ የቀረኝ አንድ ነገር ነው እሱም እጆቼ ናቸው። እነዚህን ተጠቅሜ ምን ልስራ ስል ደግሞ አገሬን አረንጓዴ በማልበስ ሂደቱ ላይ የበኩሌን ብወጣስ፤ ልጆችን ሰብስቤ አገራችሁ ኢትዮጵያ የዚህ የዚህ ባህል ባለቤት ነበረች ነችም ፤ በማለት ባስተምር ብዬ ገባሁበት ፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ” ይላሉ።
እንደው በዚህ ልክ በስራዎ ላይ በደል ሲደርስብዎ አላግባብ ጥቅም ተጠይቀው ሃብት ንብረትዎን ሲያጡ ምን አለፋኝ ብለው እንዴት ወደአሜሪካን አገር ሄደው መኖርን አልመረጡም? ስላቸው” ….አይ ለመሄድ አልፈለኩም፤ በእኔ ላይ ችግር የደረሰብኝ እኮ መንግስት ባወጣው አዋጅ አይደለም ፤ ይልቁንም ስግብግብ የሆኑ ሰዎች የግል ጥቅማቸውን ለማካበት የፈጠሩት ችግር ነው፤በመሆኑም አገሬ አገሬ ናት ለእነሱ ብዬ አገሬን የምተውበት ምክንያት የለኝም መሸነፌን ግን አምኜ ፊቴን ወደሌላ የህይወት መስመር አዞርኩ” በማለት ይናገራሉ።
በመሆኑም ወይዘሮ ጥሩወርቅ ልጆቻቸውን ይዘው ቤታቸው ቁጭ ብለው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸው ሲማሩ ባገኙት የእጅ ስራ ሙያ የእናቶች ቀሚስ እየጠለፉ ለተለያዩ ሰዎች በመሸጥ ውጪ አገር ሁሉ በመላክ ጥሩ ገቢን ማግኘት ቻሉ፡፡ ልጆቻቸው ዛሬ ራሳቸውን የቻሉበትን ሙያ ባለቤት እንዲሆኑ አደረጉ፡፡ ዛሬ ላይ ይህ በመሆኑ በጣም ደስተኛ ከመሆናቸውም በላይ ልጆቼን አበቃሁበት የስራ መስክም ከፈትኩላቸው ይላሉ።
እናት ወይዘሮ ጥሩወርቅ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ትልቅ ህዝብ ያላት ናት ይላሉ ። ነገር ግን ከእለት እለት እየሆነ ያለው ነገር ትልቅነታችንን የሚያጎላ ሳይሆን ዝቅ የሚያደርግ ነው፤በተለይም ልጆቻችን ላይ እየሰራን ያለነው ስራ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ፤በዚህ የተነሳ ደግሞ ልጆቹ የውጭውንም የአገር ውስጡንም በቅጡ ሳያውቁት እንዲሁ እየቀሩ ስለመሆናቸው ይናገራሉ።
ይህንን ሁኔታ ለመቀየርም ልጆች በእረፍት ጊዜያቸው ኢትዮጵያዊውን የኖረ ባህል እንዲያውቁት ከቴሌቨዥንና ከእጅ ስልክ ጨዋታዎች ተላቀው የእጅ ስራ እንዲለምዱ ጭቃ አቡክተው የራሳቸውን አትክልት እየተከሉ እንዲጫወቱ ከዛም ባለፈ እርስ በእርሳቸው እየተዋወቁ እንዲያወሩ በጠቅላላው ኢትዮጵያዊ ሆነው እንዲያድጉ ያላሰለሰ ጥረትን በማድረግ ላይ ናቸው።
ይህንን ለማሳካትም በቤታቸው አጥር ላይ ሳይቀር አትክልቶችን በመትከል ችግኞችን በማፍላት በቤት ውስጥም የተለያዩ የእጅ ስራ መስሪያ ክርና አስፈላጊ ነገሮችን በማዘጋጀት ለትውልዱ ኢትዮጵያዊነትን ሊያስተምሩ በራቸውን ክፍት አድርገው ይጠብቃሉ።
“….እኛ በመልካሙ ጊዜ ነው የኖርነው ትምህርት ቤት ብዙ የእጅ ስራ ሙያዎችን ገብይተናል፤ በቤታችን ውስጥም ኢትዮጵያዊ የሆኑ ባህላዊ ስራዎችን በቤተሰቦቻችን አማካይነት ተምረናል። የእርስ በእርስ ግንኙነታችንም ጠንካራ ስለነበር እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ ጥሩ ነገሮችን እያየን እያሳለፍን ነው፤ ዛሬ ላይ ያሉ ህጻናት ግን እኛው በፈጠርነው ችግር ቢያንስ ከአጥር ጊቢያቸው ወጥተው እንኳን ጎረቤት ሄደው አይጫወቱም፤ በቤታቸው ውስጥም ቢሆን በቴክኖሎጂ ውጤቶች ተከበው ነው የሚውሉት ፤በዚህ የተነሳ ደግሞ ሀሳባቸውን በንግግር መግለጽ እንኳን አይችሉም፤ ሙያ የላቸውም በጠቅላላው ኢትዮጵያዊ ወግና ባህላቸውን ዘንግተዋል፤ እኔ ደግሞ ይህንን ችግር በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ ከቻልኩ በሚል ልጆች እኔ ቤት መጥተው እጅ ስራ እንዲሰሩ ጭቃ አቡክተው አትክልት እንዲተክሉ እርስ በእርሳቸው እንዲገናኙና እንዲያወሩ ለማድረግ እየሞከርኩ ነው” ይላሉ።
አሁንም በቀረችኝ እድሜ በጣም ብዙ ስራዎችን የመስራት እቅድ አለኝ የሚሉት ወይዘሮ ጥሩወርቅ በተለይም ትውልድ ላይ ልሰራ ያሰብኩትን ስራ ደግፎ ከጎኔ የሚቆም ካገኘሁ ኢትዮጵያውያን ህጻናት አገር ውስጥም ውጪም ያሉት ማንነታቸውን በደንብ አድርገው አውቀው እንዲያድጉ የምችለውን ሁሉ ለማድረግ እፈልጋለሁ ይላሉ።
“…..እስከ አሁን በሰራሁት ስራ በርካቶች ከጎኔ ናቸው፤ በተለይም ህጻናት ማንነታቸውን እንዲያውቁ ኢትዮጵያ ከጥንት እስከ አሁን ምን ላይ እንዳለች እንዲገነዘቡ ባለችኝ አቅም የምሰራት ስራ የበርካቶችን ቀልብ ስቧል፤ በዚህም በተለይም ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ ዜጎች ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል”ይላሉ።
ወይዘሮ ጥሩወርቅ ህጻናት የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ውጪ ያሉትም “እረፍትን በኢትዮጵያ “ እንዲያሳልፉ (vacation in Ethiopia) በማለት በየአመቱ አንድ ዝግጅት ለማድረግም ሃሳቡ እንዳላቸው ይናገራሉ ፤ይህ መሆኑ ደግሞ ልጆች ምንጫቸውን፣ ባህላቸውን፣ እንዲያውቁ የሚያደርግ ስለመሆኑም ይገልጻሉ።
ሃሳቡን እኔ ላምጣው እንጂ ስራው የአገር ነው የሚሉት ወይዘሮ ጥሩወርቅ ምክንያቱም እነዚህ ህጻናት የትም ቢወለዱ አልያም ቢያድጉ መሰረታቸው ኢትዮጵያ ናት፤ እነሱም አይክዱም ነገር ግን ዝም ብሎ ትውልዴ ኢትዮጵያ ነው ከማለት ባለፈ ስለ አገራቸው ሲጠየቁ አፋቸውን ሞልተው መናገር መቻል አለባቸው፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ እንደዚህ አይነት ዝግጅቶች እየተደረጉ አገራቸውን በሚገባ ማወቅ ሲችሉ ነው። ይህ መሰሉ ዝግጅት ደግሞ ህጻናቱን ከመጥቀሙም በላይ እንደ አገርም ብዙ የምናተርፍበት ነው። ምክንያቱም እነሱን ይዞ የሚመጣው ቤተሰብ የሚያመጣው የውጭ ምንዛሪ አለ፤ ከዛ ሲያልፍ ደግሞ አገሩ ላይ የሆነ ነገር ሰርቶ ለመሄድም ይነሳሳል በመሆኑም ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው።
“….እኔ አገሬን እወዳለሁ ልጆች ደግሞ ስለ አገራቸው ብዙ ነገር ማወቅ አለባቸው ብዬ በእጅጉ አስባለሁ፤ በመሆኑም ሌት ተቀን የማስበው በምን መልኩ ነው ላሳካው የምችለው የሚለውን ነው ፤የሚረዳኝ ሃሳቤን የሚረዳ ባገኝ ለልጆች ከእንጀራ መጋገር ጀምሮ ዳቦ እንዴት ይጋገራል ፣ ወፍጮ እንዴት ይፈጫል ፤ሌላም ሌላም የሚሉ የአገሬን ባህል የሚያሳዩ ስራዎችን ሃላፊነቱን ወስጄ ለመስራት እፈልጋለሁ ፤ግን ቀጣይነት እንዲኖረው ድጋፍ ያስፈልጋል “ይላሉ።
ልጆቻችን ከእኛ አብራክ ወጥተው በአገር ውስጥም ያሉት ቢሆኑ ከብት አይተው ነክተው አያውቁም፤ ዶሮ ይበሉ ይሆናል እንጂ አያውቁም፤ ጭቃ አቡክተው የራሳቸውን ፈጠራ እንዲሰሩ አናደርጋቸውም ፤ በዚህ በጣም ልናፍር ነው የሚገባን፤ አሜሪካኖቹ ዛሬ የደረሱበት ስልጣኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ያሳለፉትን ይሰሩ የነበረውን አገራቸው ህዝቡ ምን ይመስል እንደነበር አለባበሱን የገበያውን ሁኔታ አመጋገቡን ብቻ ብዙ ነገር በሙዚየም መልክ አደራጅተው አገሬው ብቻ ሳይሆን መጤውም ገንዘብ እየከፈለ እንዲያይ ያደርጋሉ። እኛ ግን የብዙ ባህልና ትሁፊት መገኛዎች ሆነን ለልጆቻችን እንኳን ማስተላለፍ አቅቶናል ይላሉ።
“….በእኔ እድሜ ያሉ ብዙ የተማሩ ነገር ግን ምን እንደሚሰሩ ግራ ገብቷቸው ቤታቸው ቁጭ ያሉ ብዙ ናቸው ፤ በእነዚህ ሰዎች መጠቀም ብንችል ብዙ ትርፍ ይገኛል፤ በተለይም ህጻናት የአገራቸው ፍቅር እንዲያድርባቸው ስለ አገራቸው ተቆርቋሪ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል” ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ ስራ
በ1990ዎቹ አካባቢ ኤች አይ ቪ ኤድስ በአገር አቀፍ ደረጃ እጅግ ተስፋፍቶ ነበር ፤ በዚህ ምክንያት በርካታ ህጻናት ያለ ወላጅና አሳዳጊ ቀሩ። በወቅቱ ኑሯቸው ደብረብርሃን ከተማ ላይ የነበረው ወይዘሮ ጥሩወርቅ የደብረ ብርሃን ከተማ ንግድ ምክር ቤት ሰብሳቢ የነበሩ በመሆኑ ‹‹እባክሽ እነዚህን ልጆች የሚረዳ ሰው ፈልጊ መባላቸው›› ወደ በጎ አድርጎት ስራ አስገባቸው ። በዛ መሰረት አፈላልገው ልጆቹን የሚረዳ አካል ያገኛሉ። እሳቸውም የበኩሌን ልወጣ በማለት ከቤታቸው አንድ ክፍል ለህጻናቱ ማረፊያ ይሰጣሉ።
በዚህም ህጻናቱ እየመጡ በውጭ አገር አሳዳጊ እየተገኘላቸው በርካታ ልጆች ጥሩ ደረጃ የደረሱ ቢሆንም በተለይም በውጭ አገር በጉዲፈቻነት የሚወስዱት ሰዎች ከአምስት አመት በላይ የሆኑ ልጆችን እንቀበልም በማለታቸው ወይዘሮ ጥሩወርቅ ቤት ውስጥ አምስት ህጻናት በጉዲፈቻ የሚወስዳቸው አጥተው ቀሩ። እሳቸውም የወለደ አንጀታቸው አልችል ቢላቸው እነዚህን ህጻናት ሰብስበው በማሳደግ ዛሬ ላይ ለትልቅ ቁምነገር አብቅተዋል።
መልዕክት
በአገር ደረጃ የተጀመሩ ስራዎች እጅግ ድንቅ ናቸው። አረንጓዴ ልማት አገራችንን ወደቀድሞ የአየር ጸባይዋ እንድትመለስ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። እኔም በምችለው ሁሉ ይህንን ሁኔታ ለማገዝ በቤቴ ውስጥ በራሴ ወጪ ችግኞችን እያፈላሁ ለሚፈልግ እየሰጠሁ የጓሮ አትክልቶችን እያለማሁ ብዙ ስራዎችን እየሰራሁ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ትውልድ የማነጽ ስራ ላይ በትኩረት እየሰራሁ ሲሆን ይህንን ስራ ከጎኔ ሆኖ የሚደግፈኝ ግን እፈልጋለሁ።
በተለይም የእኔን ሃሳብ የሚረዳኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ነው፤በነገራች ላይ እሳቸው ከሚሰሩትና ከሀሳባቸው ትልቅነት አንጻር አልኩ እንጂ ሁሉም በየቦታቸው ጥሩ ይሰራሉ፤ የሚሉት ወይዘሮ ጥሩወርቅ በእሳቸው ስራ ወዳድነት እኔንና የእኔ አይነቶችን ማግኘት ቢችሉ ኢትዮጵያን በብልጽግና ማማ ላይ እናስቀምጣታለን ይላሉ።
በመሆኑም ህጻናቶቻችንን እናድን ትርፎቻችን እነሱ ናቸው። አገራችንን የሚረከቡትም እነሱ ብቻ ናቸው። በመሆኑም ልጆቻችችን ከእጃችን ሳይወጡ አገራቸውንም ሳያቁ እንዳይቀሩ እንስራ እንበርታ እንረዳዳ ይላሉ።
እፀገነት አክሊሉ
ዘመን ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም