በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚመረቱ ቡናዎች መካከል አንዱ የጉጂ ቡና ነው፤ ቡናው ባለው ልዩ ጣዕም በዓለም ገበያም በእጅጉ ይፈለጋል:: የጉጂ ቡና ከዚህ ቀደም በሲዳማ ቡና ስም ነበር ለግብይት የሚቀርበው:: አሁን በስሙ ወደ ገበያ እየቀረበ ይገኛል:: የታጠበውም ሆነ ያልታጠበው የጉጂ ቡና በልዩ ጣዕሙ የተነሳ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል:: በዓለም ገበያ ተወዳጅነትን እያተረፈ ሲሆን፣ የቡና አልሚዎችን ትኩረትን መሳብ መቻሉን መረጃዎች ያመለክታሉ::
በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በቡና ልማትና ግብይት በተለይም ቡናን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሚታወቁ በርካታ ቢሆኑም፣ ቡናን ከሚያለማ ቤተሰብ ተገኝተው በቡና ውስጥ ኖረው ቡናን እያለሙ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ግን ጥቂቶች ናቸው:: እነዚህ ሰዎች ለቡና ካላቸው ቅርበት የተነሳ ዘርፉ ምን አንደሚያስፈልገው ጠንቅቀው ከማወቅ ባለፈ ለውጤታማነቱ በብዙ ይተጋሉ:: የዝግጅት ክፍላችንም ቡና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ባስገኘበት በዚህ አመት፣ ለሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ እየሆነ ካለው ቡና ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸውን እንግዳ በዛሬው የስኬት ገጹ ይዞ ቀርቧል::
ተወልደው ያደጉት በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ቅሌንሶ ነው:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚሁ ትውልድ ቦታቸው፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሀዋሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: በግብርናና በንግድ ዘርፍ ከተሰማራ ቤተሰብ የተገኙት እኚህ እንግዳችን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ባጠናቀቁ ማግስት ያደጉበትን የቡና ልማትና የቡና ንግድ መልሰው ተቀላቀሉ:: የዛሬው የስኬት እንግዳችን አቶ አክሊሉ ካሳ ::
አቶ አክሊሉ የናርዶስ ቡና ላኪ እና ቤካ ኮፊ ፕሮሰስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት መስራችና ባለቤት ናቸው:: በጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ አካባቢ ቡናን እንዲሁም እንሰትን በማልማት ቀዳሚ ከሆነ የዘር ሀረግ የተገኙት አቶ አክሊሉ፣ ከቡናው በተጨማሪም በሆቴል ዘርፍ ተሰማርተው በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌሆራ ላይ ቡሌሆራ ሆቴልን ገንብተዋል:: በዚህም 100 ለሚደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል::
የአቶ አክሊሉ አያት አቶ ጭሪሳ ሲሳ ቡናን ጨምሮ እንሰትን ወደ ጉጂ አካባቢ በማምጣት የመጀመሪያው ናቸው፤ በንጉሱ ዘመን በነበራቸው ሰፊ የእርሻ መሬት ላይ ቡናና እንሰትን በስፋት በማምረት ይታወቁ ነበር:: የቡና ምርቱንም ነጋዴዎች ኤኔትሬ በሚባል ገልባጭ መኪና ገዝተው ሲወስዱ ያስታውሳሉ፤ የቡና ልማትና ግብይትን ወላጅ አባታቸው ከአያታቸው፤ እርሳቸው ደግሞ ከወላጅ አባታቸው እየተቀባበሉ እዚህ ደርሷል::
በወቅቱ ቡናን ወደ አዲስ አበባ ገበያ አምጥተው የመሸጥ ዕድሉ ያልነበራቸው ወላጅ አባታቸው ቡና ሰብሳቢ በሚል የንግድ ፈቃድ በግላቸው የሚያለሙትን ቡና ጨምረው የአካባቢውን አርሶ አደሮች ቡና በመሰብሰብ ለነጋዴዎች ያቀርቡ ነበር:: የወላጅ አባታቸውን ዱካ በመከተል ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ ያደጉት አቶ አክሊሉም፣ ከልጅነታቸው ጀምረው ከአርሶ አደርነትና ከነጋዴነት የትኛው አዋጭ እንደሆነ ሲያመዛዝኑ አድገዋል:: በመጨረሻም ንግዱ የበለጠ አዋጭ እንደሆነ በማመን የቡና አቅራቢ ፈቃድ በማውጣት ወደ ንግዱ ስራ በይፋ ገቡ::
በወቅቱ የቡና ፈቃድ ከነበራቸው ጥቂት ቡና ሰብሳቢዎችና ቡና ላኪዎች መካከል አንዱ ከነበሩት ወላጅ አባታቸው የተረከቡትን የቡና ንግድ ለማሳለጥ በ1984 ዓ.ም ልክ እንደ አባታቸው ሁሉ እርሳቸውም የቡና ሰብሳቢ ንግድ ፈቃድ አወጡ:: በወቅቱ የግላቸውን ሥራ ጨምረው ወላጅ አባታቸውንም ጭምር በማገዝ ሥራውን በሚገባ ተለማመዱ:: ለዘርፉ ካላቸው ቅርበት የተነሳ በጥራት ሠርተው ውጤታማ መሆን ሲችሉ ከሰብሳቢነት ወደ አቅራቢነት ተሸጋገሩ::
ወደ ቡና አቅራቢነት የተሸጋገሩት አቶ አክሊሉ፤ እሸት ቡና መፈልፈያ ማሽን በመትከል የተፈለፈለውን ቡና ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ለላኪዎች ያስረክቡ ነበር:: በዚሁ ሥራ አዲስ አበባ ሲመላለሱ የሥራውን ስፋትና ጥልቀት እንዲሁም ውጤቱን በሚገባ መረዳት ቻሉ:: የተረዱትን ዕውነትም በተግባር ለማዋል ጊዜ አልፈጁም:: ቡናን ከማልማት ጀምረው ሰብሳቢና አቅራቢ ሆነው አዲስ አበባ በነበራቸው ምልልስ የወጪ ንግዱን በከፊል ተረዱ:: ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› ነውና ብሂሉ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ፍላጎት አደረባቸው::
በ1994 ዓ.ም ብዙ ውጣውረዶችን አልፈው የላኪነት ንግድ ፈቃድ አወጡ:: ቡና ላኪ ለመሆን ብዙ ሂደቶች ያለፉ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ ላይ ቢሮ ከመከራየት ጀምሮ እንደ ኮምፒዩተር፣ ስልክና የመሳሰሉትን ግብዓቶች ማሟላት ከጉጂ ለመጡት ለአቶ አክሊሉ ቀላል ጉዳይ አልነበረም:: ይሁንና አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታዎች በሙሉ አሟልተው ከ1994 ዓ.ም ጀምረው ላለፉት 20 ዓመታት የጉጂ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያስገቡ ይገኛሉ::
አቶ አክሊሉ በላኪነት ብቻ 20 ዓመታትን አስቆጥረዋል፤ በቡና ልማቱና በአገር ውስጥ ንግዱ ግን ነብስ ካወቁ ጊዜ አንስቶ ኖረውበታል:: ሕይወታቸው በሙሉ ከቡና ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው በመሆኑም ዘርፉ ላይ ትኩረት አድርገው ይሠራሉ:: የቡና ሥራ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገውና እንደ አይናችን ብሌን ልንንከባከበው የሚገባ ስስ ብልት ነው ሲሉም ገልጸው፣ ሥራው እርጋታን የሚፈልግ እንደሆነም ይናገራሉ::
የቡና ገበያ ዓለማቀፍ ገበያ እንደመሆኑ አንድ ጊዜ ሲወጣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ይወርዳል የሚሉት አቶ አክሊሉ፣ በከፍታውም ከፍ ማለት እንዳለ ሁሉ ሲወርድም አብሮ መውረድ የግድ ነውና ባሕሪውን ማወቅና በጥንቃቄ መጓዝ የግድ ነው ይላሉ:: ቡና እዩኝ እዩኝ የማይወድና እርጋታን የሚፈልግ ሥራ እንደሆነም ይገልጻሉ::
ከቤተሰባቸው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የቡና ልማትና ግብይት እየመሩ ያሉትና በዚህም ሶስተኛው ትውልድ ለመሆን የበቁት አቶ አክሊሉ፤ በጉጂ አካባቢ በ105 ሄክታር መሬት ላይ 200 ቋሚ ሠራተኞችን በማሰማራት ቡና እያለሙ ናቸው:: ቡና በሚደርስበት ጊዜ ደግሞ በቀን ከ400 እስከ 500 ለሚደርሱ ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ:: ከዚህ በተጨማሪም በአካባቢው የሚገኙ አምስት ሺ አርሶ አደሮችን በማሰባሰብ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረጉ አርሶ አደሮቹ የሚያለሙትን ቡና ይረከባሉ:: አርሶ አደሮቹም በዕለቱ በዋለው የቡና ገበያ ዋጋና ባቀረቡት የቡና መጠን ልክ ተከፋይ ይሆናሉ::
አርሶ አደሮቹ የተሻለ ተከፋይ እንዲሆኑ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የግድ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ችግኝ ከማቅረብ ጀምሮ የተለያዩ እገዛዎችን ከናርዶስ ቡና ላኪ ድርጅት እንዲያገኙ አንደሚደረግም ነው የሚናገሩት:: ለአብነትም ችግኝ በማፍላት፣ በጉንደላ፣ በምርት አሰባሰብና በአፈር አጠባበቅ ዙሪያ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ በባለሙያዎች እንዲያገኙ ይደረጋል:: ይህም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ ጥራቱ የተጠበቀና በተፈጥሮ ኦርጋኒክ የሆነውን የጉጂ ቡናን ለዓለም ገበያ ማቅረብ አስችሏቸዋል:: በዚህም ናርዶስ ቡና ላኪ ድርጅት የኦርጋኒክነት መለያን ጨምሮ የጥራት ደረጃቸውን የሚገልጹ የምስክር ወረቀቶችን ማግኘት ችሏል::
እሸት ቡናው እዛው ጉጂ በሚገኘው መፈልፈያ ጣቢያቸው ተፈልፍሎና ደርቆ አዲስ አበባ ይደርሳል:: አዲስ አበባ በሚገኘው መቀሸሪያና ማበጠሪያ ማዕከላቸው ደግሞ ቡናው አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎለት ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ተዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ ይሰናዳል:: ይህ ሥራ በሚከናወንበት ናርዶስ ቡና ላኪ ድርጅት ውስጥ ደግሞ ከ80 በላይ ለሆኑ ሠራተኞች በቋሚነት የሥራ ዕድል ተፈጥሯል::
የዛሬ 20 ዓመት ቡና ወደ ውጭ መላክ ሲጀምሩ ቄራ አካባቢ ቢሮ ተከራይተው ይሰሩ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አክሊሉ፣ በብዙ ልፋትና ጥረት፤ እርጋታና ትዕግስትን ገንዘብ በማድረግ ጭምር ቀስ በቀስ ዛሬ ላይ ደርሰዋል:: በአሁኑ ወቅት ግን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ማሰልጠኛ አካባቢ 4ሺ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ፋብሪካቸውን ገንብተው ቡናውን ለውጭ ገበያ ዝግጁ በማድረግ ይልካሉ:: ሥራውን ከዚህ በበለጠ አስፍቶ ለመሥራትም ማስፋፊያ ጠይቀው በዚሁ ቦታ 8000 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ቦታን አግኝተዋል::
‹‹ቡና የአገሪቱ ትልቅ ሃብት እንደመሆኑ እንደ አይናችን ብሌን ልንንከባከበው ይገባል›› የሚሉት አቶ አክሊሉ፤ የቡናው ዘርፍ ካለፉት ዓመታት በተሻለ አሁን ባለቤት እያገኘ መሆኑንም ነው የተናገሩት:: በዘርፉ መሠራት ያለበት ሥራ አሁንም ገና ብዙ እንደሚቀረው አስገንዝበዋል:: ከሌሎች አገራት ጋር ሲወዳደር በልማቱም ይሁን በወጪ ንግዱ እንዲሁም ዋናው ምንጭ የሆነው አርሶ አደር ላይ ምንም እንዳልተሰራም ይጠቁማሉ:: በማስታወቂያውም ቢሆን እንዲሁ ብዙ ይቀረናል ይላሉ::
እሳቸው አንደሚሉት፤ እነዚህ ሁሉ ሥራዎች በሚገባ ባይሠሩም የኢትዮጵያ ቡና በአሁኑ ወቅት በራሱ ጊዜ ገፍቶ እየወጣ ነው:: በዘርፉ የሚታዩ ክፍተቶችን በመድፈን በተለይም ቡና አምራቹ ዘንድ ወርዶ መሥራት ከተቻለ የኢትዮጵያ ቡና ከዚህም በበለጠ ውጤታማ መሆን ይችላል::
ከቡና መዳረሻ ሀገሮች አኳያም ሲያብራሩ በአሁኑ ወቅት ቻይናን ጨምሮ ብዙ በርካታ የዓለም አገራት የኢትዮጵያን ቡና እንደሚፈልጉ ይገልጻሉ:: ስለዚህ ይህን ዕድል መጠቀም እንዲቻል ቡናን በመጠንና በተሻለ ጥራት ማምረት የግድ መሆኑን ያመለክታሉ::
የናርዶስ ቡና ላኪ ድርጅት የገበያ መዳረሻዎችን አስመልክወተው ሲገልጹም በመላው ዓለም ተደራሽ እንደሚሆን ነው የተናገሩት:: አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ኤዢያ በተለይም በአሁኑ ወቅት ቻይና የጉጂን ቡና ተመራጭ በማድረግ አንደኛ ገዢ እየሆነች መጥታለች:: ዘንድሮ ናርዶስ ቡና ላኪ ብቻውን ሶስት ሺ ቶን ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ እቅዱን ማሳካት ችሏል ብለዋል::
አቶ አክሊሉ እንዳሉት፤ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ሰፋፊ ማህበረሰብ አቀፍ ሥራዎችን ሰርተዋል:: በትውልድ አካባቢያቸው መንገድ፣ ድልድይ፣ ውሃ፣ ትምህርት ቤቶችን በስፋት ሠርተዋል፤ በቡሌ ሆራ ቅሌንሶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሚማሩ ሴት ተማሪዎች የሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ያቀርባሉ:: ቁሳቁሱ ቡና ገዢ ከሆኑት አገራት መካከል አንዷ ከሆነችው ኒዮርክ ጋር ስምምነት በማድረግ ለዓመት የሚበቃውን አንድ ጊዜ በማምጣት ያቀርባሉ::
የሴቶች ንጽህና መጠበቂያው መልሶ ጥቅም ላይ የሚውልና የሚታጠብ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ተማሪዎቹን በማሰልጠን ራሳቸው እንዲያመርቱት እየተደረገም ነው ብለዋል:: ለዚህም አስፈላጊውን የስፌት መኪኖች፣ የተለያዩ ጨርቆች፣ ክሮችና ሌሎች ቁሳቁስ በማሟላት ተማሪዎቹ ሠርተው መጠቀም እንዲችሉ አድርገዋል:: አቶ አክሊሉ በማንኛውም አገራዊ ጉዳዮች መንግሥት ለሚያደርገው ጥሪ ምላሽ እየሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ይህንኑ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል::
እሳቸው እንዳሉት ናርዶስ ቡና ላኪ ድርጅት አሁን ለዓለም ገበያ እያቀረበ ካለው የቡና መጠን በላይ ለማቅረብና የጥራት ደረጃውንም ከፍ ለማድረግ ራዕይ ሰንቆ እየሠራ ነው:: ለተግባራዊነቱም ዋናው ሥራ የሚሠራው ታች አርሶ አደሩ ዘንድ መሆኑን በማመን አርሶ አደሩ ጋ ወርደን እንሠራለን ብለዋል:: መንግሥትን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ከታች ከመነሻው አርሶ አደሩ ላይ ብዙ መሥራት እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት::
እናም በወጪ ንግድ ቀዳሚ ከሆነው ቡና አገሪቷ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንድታገኝ፣ የታመመው ኢኮኖሚ እንዲያገግም ብሎም ዘርፉ እያስመዘገበ ያለው ውጤት ይበልጥ እንዲሻሻል መንግሥትን ጨምሮ የዘርፉ ተዋናዮች በሙሉ የቤት ሥራቸውን እንዲወጡም ነው የጠየቁት:: አበቃን::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2015