የኢትዮጵያን ዘላቂ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ለማሳካት በመንግሥት የተነደፉ የልማት እቅዶች ከፍተኛ የፋይናንስ አቅም የሚፈልጉ ናቸው። ይህን ከፍተኛ የፋይናንስ ፍላጎት ደግሞ ከግብር በሚሰበሰብ ገቢ እና ከውጭ መንግሥታትና ተቋማት በሚገኝ ብድርና እርዳታ መሸፈን ዘላቂና አዋጭ አማራጭ እንዳልሆነ ይታመናል።
ስለሆነም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶች ለማሟላት በሚያግዝ አኳኋን የግል ኢንቨስትመንቱ ከመንግሥት ጋር በጋራ ልማት ስራዎች ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችል ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የግል ኢንቨስትመንትን በተጠናከረ ሁኔታ ለመሳብ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም የተቀናጀ ስትራቴጂያዊ ቁጥጥር በማከናወን በመንግሥት ባለቤትነት የተያዙ ሀብቶች የተሟላና ዘላቂ ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ መፍጠር ይገባል። ይህ አሰራር ደግሞ የመንግሥት ሀብቶችን አስተዳደር በማሻሻልና ተጨማሪ ሀብት በመፍጠር ተጨማሪ የፋይናንስ አቅርቦት ለማግኘት ያስችላል።
ይህን እቅድ ለማሳካት ኃላፊነት የተጣለበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (Ethiopian Investment Holdings) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት አስፈፃሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን ባወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 እንደተቋቋመ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አደረጃጀትና ተግባር የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ እንደሚወሰን በአዋጁ የተደነገገ በመሆኑ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በታኅሳስ ወር 2014 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን ዓላማና ተግባር ለመወሰን በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። በውሳኔው መሰረትም ምክር ቤቱ በስፋት የተወያየበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን ዓላማና ተግባር ለመወሰን የወጣው ረቂቅ ደንብ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ተወስኗል።
ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በዋናነት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ የመንግስት ሀብቶችን ወደ አንድ ተቋም በመሰብሰብ እና ውጤታማ የኩባንያ አስተዳደር በመፍጠር ከእነዚህ ሀብቶች የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻልና ሀብቶቹን አሟጦ በመጠቀም የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ ስትራቴጂካዊ የልማትና የኢንቨስትመንት መሳሪያ እንደሚሆን ታሳቢ በማድረግ ነው።
በፋይናንስ፣ በንግድ፣ በአምራች፣ በሎጂስቲክስ፣ በሆስፒታሊቲ፣ በግንባታና ሪል ስቴት፣ በኬሚካል እና በመገናኛ ዘርፎች የተሰማሩ 27 ተቋማትን ያካተተው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፤ ባለፈው ወር ስራ መጀመሩ ይታወሳል። ተቋሙ የልማት የድርጅቶቹን አቅምና ተወዳዳሪነት በማሳደግ ተጨማሪ ሀብት ለመፍጠር እና የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ተገልጿል። በተለይም ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ይጠበቃል።
በኩባንያው ስር ከሚተዳደሩ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ ሒልተን ሆቴል፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የመሬት ባንክ እና ልማት ኮርፖሬሽን፣ ብሔራዊ አልኮል እና አረቄ ፋብሪካ እና የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ይጠቀሳሉ።
የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሥራውን በይፋ ለመጀመር የሚያስችለውን ጉባኤ ባካሄደበት ወቅት፣ መንግሥት የቀረፀው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ውጤታማ እንዲሆን አስተማማኝ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ወሳኝ ግብዓት መሆኑን ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ይህን ግብዓት ለማሟላት አንዱ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል። መንግሥት የፋይናንስ አቅርቦትን የሚያሳድጉ አማራጮችን ከሀገር ውስጥና ከውጭ ምንጮች ለማግኘት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ እንደሚተጋም ነው ያስታወቁት።
እንደ እርሳቸው ገለፃ፣ መንግሥት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማነት ለማሳደግ እየተገበራቸው ከሚገኙ አሰራሮች መካከል አንዱ ዓለም አቀፍ የኮርፖሬት አስተዳደር ስርዓቶችን መዘርጋት ነው። በዚህም የተቋማቱን ትርፍና ገቢ ለመጨመር ተቋማቱን በማቀናጀት ዘመናዊ በሆነ አመራር ለማስተዳደር ድርጅቶቹን በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ስር ማሰባሰብ ተገቢ አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ አሰራር የማክሮ ኢኮኖሚውን ፈተናዎች በማቃለል ዘላቂ የምጣኔ ሀብት እድገት ለማስመዝገብ ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የድርጅቶቹን ውጤታማነትና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ከሀገራዊና ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት አጋሮች ጋር በትብብር ይሰራል። በእነዚህ ትብብሮች አማካኝነትም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞችና የረጅም ጊዜ ምጣኔ ሀብታዊ እቅዶች እውን ለማድረግ እንደሚሰራና መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ማሞ ምህረቱ ‹‹የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተቋቋመው መንግሥት ያስቀመጠውን የረጅም ጊዜ የልማት እቅድ ተግባራዊ ለማድረግና ተጨማሪ የፋይናንስ አቅርቦት ለማግኘት፣ መንግሥት ያሉትን ሀብቶች በተሻለና ዓለም አቀፍ ደረጃን ከግምት ውስጥ ባስገባ ሙያዊ አሰራር እንዲተዳደሩ በማድረግ ተጨማሪ ሀብት ለመፍጠር እንዲሁም መሰረተ ሰፊ የሆነ ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገር ውስጥ ለማምጣት ነው›› ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ኩባንያው የመንግሥት ስትራቴጂያዊ የኢንቨስትመንት መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል። የኢትዮጵያ መንግሥትን ፍላጎት የሚያሟሉ የኢንቨስትመንት ተግባራትን ያከናውናል። በተጨማሪም በስሩ ያሉ የመንግሥት ሀብቶች ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲሰሩ ያደርጋል፤ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ስራዎችንም ያከናውናል። ይህን ዓላማ ለማሳካት ኩባንያው ዓለም አቀፍ መርሆችን ተከትሎ የሚሰራ ተቋም እንደሆነ ማረጋገጫ የሚሰጡና በትልልቅ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ለመሳተፍ የሚያግዙ መደላድሎችን ፈጥሯል።
27ቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተለያየ አቅምና የትርፍ መጠን እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ማሞ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጠንካራ የኮርፖሬት አስተዳደርን ስለሚከተል 27ቱም የልማት ተቋማት የበለጠ አትራፊና ውጤታማ እንዲሆኑ አስተዳደራዊ አሰራሮችን እንደሚተገብር ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዋቄ በበኩላቸው፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶቹ በአንድ ሆልዲንግ ኩባንያ ስር በበላይነት መመራታቸው አስተዳደራዊ ጉዳዮቻቸውን ለማጠናከር፣ ኢንቨስትመንታቸውን ለማሳደግና የተቋማቱን ውጤታማነት በጋራ ለማሳደግ ከመፈለግ የመጣ እንደሆነ ገልጸዋል። የሲንጋፖርንና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ልምድ በመጥቀስ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አሠራር በሌሎች አገራትም ተሞክሮ ውጤት ያመጣ አሠራር እንደሆነ የተናገሩት አቶ ግርማ፣ ያደጉ አገራት በዚህ አካሄድ ተቋሞቻቸውን አጠናክረው የተሻለ ኢኮኖሚ እንደገነቡ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያም የኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥራ ቢዘገይም በቅርቡ ተቋቁሞ ወደሥራ መግባቱ ለአገር የሚበጅ እርምጃ መሆኑንም ተናግረዋል።
አቶ ግርማ ‹‹የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሲቋቋም የእያንዳንዱን የልማት ድርጅት ቦርድ ተክቶ የሚሠራ አለመሆኑን መረዳት ይገባል። 27ቱም የልማት ድርጅቶች ቦርድ ቢኖራቸውም የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሆልዲንግስም ሆነ መንግሥት ኢንቨስትመንት እንዴት ይሻሻላል በሚለው ጉዳይ ላይ በትኩረት በጋራ እንደሚሠሩ ግልጽ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በተለይም የልማት ድርጅቶቹን የካፒታል አጠቃቀም፣ የሥራ ክንውንና የአስተዳደር ሥርዓት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን በማሳደግ ረገድ ከየተቋማቱ ኃላፊዎችና የቦርድ አመራሮች ጋር በቅንጅት ይሰራል። እያንዳንዱ የልማት ድርጅት በሚያቀርበው ዕቅድና አፈጻጸም መሠረት ይበልጥ እንዲጠናከሩ እንዲሁም የአፈፃፀም ድክመት ካጋጠመ እንዴት መሻሻል እንደሚገባው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ይመክርበታል። ይህ አካሄድ እንደአገር በኢንቨስትመንት ዘርፍ ያለውን ክንውን ለማጠናከር ይረዳል›› በማለት አስረድተዋል።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህርና በ‹‹ፍሮንቲየሪይ (Frontieri)›› ጥናትና አማካሪ ድርጅት ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሞላ አለማየሁ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለይቶ በትኩረት ከመስራት አንፃር ለዘርፉ መጠንከር አወንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ይገልፃሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ አሰራሩ በተናጠል ከመንቀሳቀስ ይልቅ ሀብትንና አቅምን አሰባስቦ መስራት የኢንቨስትመንት ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ይረዳል። ፍትሐዊ ስርጭት ያለውና በእቅድ የሚመራ ኢንቨስትመንት እንዲኖርም ያስችላል። ከዚህ በተጨማሪም ለኢንቨስትመንቱ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ዘርፎችን ለመለየትም ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያግዛል።
ግዙፍ ሀብት ያላቸውን ተቋማት በአንድ ተቋም ስር አሰባስቦ ማስተዳደር በሌሎችም አገራት የተለመደ አሰራር መሆኑን በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር እና የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ጥናትና ምርምር ዘርፍ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ ግርማም ይገልጻሉ።
‹‹ሀብትን በጋራ በማሰባሰብ መስራት የሀብት ብክነትን ለመቀነስ፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሳደግ እና የድርጅቶቹን ትርፋማነት ለመጨመር ያግዛል›› ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ፣ በትርፋማነታቸው የላቀ አፈፃፀም ያላቸው አባል ተቋማት ለሌሎቹ እያበደሩ አቅማቸው እንዲጎለብት መልካም እድል የሚፈጥር መሆኑንም ነው የሚገልጹት። እስከ አሁን ገንዘብን በጋራ የማንቀሳቀስ የዳበረ ልምድ እንደሌለም ጠቅሰው፣ ይህ አሰራር በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ነው የሚገልጹት።
ከኢንቨስትመንት ዘርፉ ማነቆዎች መካከል የፋይናንስ አቅርቦት ችግር አንዱ መሆኑንም አመልክተው፣ ትልቅ የካፒታል አቅም ያላቸውን ተቋማት በአንድ ላይ ሰብስቦ መምራት የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ምንጭን በማስፋት የኢንቨስትመንት ስራዎችን ለማሳደግ አወንታዊ ሚና እንደሚኖረው ይገልፃሉ።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መንግሥትን ዋስ በማድረግ ከውጭ አካላት ብድር እንደሚያገኙ ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ መቋቋሙ አባል ተቋማት የብድር ፍላጎታቸውን ወደ ሀገር ውስጥ እንዲያዞሩ ሊያደርግ እንደሚችልና የሀገሪቱን የውጭ ብድር ጫና ለማቃለልም አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ነው ያስረዱት። ከዚህ በተጨማሪም አንዱ ድርጅት ለሌላው ድርጅት ብድር በመስጠት የወለድ ገቢ (Interest Income) የሚያገኝበት እድል እንደሚፈጠርም ይናገራሉ።
ትልቅ ሀብት ያላቸውን ግዙፍ ተቋማት ሰብስቦ ማስተዳደርና መምራት ከፍተኛ ብቃት እንደሚጠይቅ አይካድም። በአገሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ የመንግሥት ሃብቶችን ወደ አንድ ተቋም በመሰብሰብና ውጤታማ የአስተዳደር ሥርዓት በመፍጠር ከሃብቶች የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻልና የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ስትራቴጂካዊ የልማትና የኢንቨስትመንት መሣሪያ ለማድረግ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥም ከዚህ አንፃር ትልቅ ኃላፊነት አለበት።
ዶክተር ሞላ በዚህ ረገድ ‹‹ተቋማትን ሰብሰብ አድርጎ በማስተዳደር ረገድ ከዚህ ቀደም ከታዩ ክፍተቶች ልምድ መውሰድ ያስፈልጋል። መንግሥት ጠንካራ የክትትልና ግምገማ ስርዓት መዘርጋት ይኖርበታል። የተቋማቱን የስራ አፈፃፀምና ክፍተቶችን በጥልቀት በመመልከት ጠንካራ አፈፃፀሞችን አጠናክሮ ማስቀጠልና ክፍተቶችን ማረም ይገባል›› ይላሉ። ከዚህ ቀደም የታዩ የአፈፃፀም ድክመቶች እንዳይደገሙ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባም ይመክራሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር ሀብታሙ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሚመራበት ጠንካራ ስርዓት ሊኖረው እንደሚገባ ያሳስባሉ። ‹‹ድርጅቶቹን ሰብስቦ በመምራትና በማስተዳደር ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ትርፍ የሚያስመዘግቡት ድርጅቶች ተጎጂ እንዳይሆኑና በአንፃራዊነት ዝቅ ያለ አቅም ያላቸው ደግሞ ጥገኛ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ይላሉ።
የእያንዳንዱ ድርጅት ውጤታማነት በዋናነት የሚለካው ባስመዘገበው ትርፍ እንጂ ለሌሎች በመስጠቱ ወይም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣቱ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ የተቋማቱን ግንኙነት ግልፅ በሆነና ውጤታማነትን ሊያሳድግ በሚችል አሰራር መምራት እንደሚያስፈልግ ነው የሚመክሩት።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የሚመራበት ጠንካራ ስርዓት ሊኖረው ይገባል፡፡ ድርጅቶቹን ሰብስቦ በመምራትና በማስተዳደር ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ትርፍ የሚያስመዘግቡት ድርጅቶች ተጎጂ እንዳይሆኑና በአንፃራዊነት ዝቅ ያለ አቅም ያላቸው ደግሞ ጥገኛ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የእያንዳንዱ ድርጅት ውጤታማነት በዋናነት የሚለካው ባስመዘገበው ትርፍ እንጂ ለሌሎች በመስጠቱ ወይም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣቱ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የተቋማቱን ግንኙነት ግልፅ በሆነና ውጤታማነትን ሊያሳድግ በሚችል አሰራር መምራት ያስፈልጋል
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14 ቀን 2014 ዓ.ም