የትኛውም ልጅ በልጅነቱ ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ? ተብሎ ሲጠየቅ ዶክተር፣ ፓይለት፣ አስተማሪና ሌሎችንም ይላል:: የሕይወት መንገድ የቀናቸው የተመኙትን ሊሆኑ ይችላሉ:: አብዛኞቹ ግን ህልምና ኑሮ ላይገናኝላቸው ይችላል:: ያም ሆኖ ግን በልጅነት ህልምን ማስቀመጥ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም:: የዛሬ የሕይወት ገጽታ አምድ እንግዳችን በልጅነት ዘመናቸው ይህንን እሆናለሁ ብለው ባያስቡም የሕይወት አጋጣሚ የኑሮ መንገድ መራቸውና ዛሬ ላይ አንቱ ያስባላቸውን ብሎም ለብዙዎች ብርሃን እንዲሆኑ ያስቻላቸውን የህክምና ሙያ ውስጥ ገቡ:: የሰዎችን ሁለንተናዊ ኑሮ የሚያዘውን የዓይን ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ይልቃል አዳሙ ይባላሉ::
ፕሮፌሰር ይልቃል አዳሙ ተወልደው ያደጉት በድሮ ጎጃም ክፍለ ሀገር ቆላ ዳሞት አውራጃ ቋሪት ወረዳ ዘጌ ፅዮን ቀበሌ ነው:: ለቤተሰባቸው ያሉትንም የሞቱትንም ቆጥረው ስድስተኛ ልጅ መሆናቸውን ይናገራሉ::
የአርሶ አደር ልጅ የሆኑት ፕሮፌሰር ይልቃል ትምህርት ለመጀመር ከቀያቸው ርቀው መሄድ ነበረባቸው ነገር ግን ቤተሰቦቻቸውም ለትምህርት ዋጋ በመስጠት ርቀው ሄደው እንዲማሩ እድል አመቻቹላቸው እሳቸውም በወረዳው ብቸኛ በነበረው ቋሪት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ገብተው የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሆነ::
” ……እኔ እድሜዬ ለትምህርት ሲደርስ በምኖርበት ወረዳ ላይ በተለይም ለቤተሰቦቼ ቅርብ በሆነ አካባቢ ላይ ትምህርት ቤት አልነበረም፤ ይህ ደግሞ ከቤተሰቤ ርቄ ሄጄ ትምህርቴን እንድከታተል አስገደደኝ:: በመሆኑም ገና 10 ዓመት እንኳን ሳይሞላኝ ዘመድ ቤት ሆኜ ትምህርቴን መከታተል ተገደድኩ” ይላሉ::
በዚህ ሁኔታም ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን በሦስት ዓመት አጠናቀው እንደ አጋጣሚ ሆኖ እሳቸውና ጓደኞቻቸው ወደ ሰባተኛ ክፍል በሚያልፉበት ጊዜ ትምህርት ቤቱ ክፍሎች ጨምሮ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን እንዲያስተምር ተወሰነለት፤ ፕሮፌሰርና ጓደኞቻቸውን ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን ለመማር ሩቅ ከመሄድ ተገላገሉ::
“…..በወቅቱ ትምህርት ቤቱ እስከ ስድስተኛ ክፍል ብቻ ነበር የሚያስተምረው ነገር ግን የእድል ነገር ሆኖ እኛ ወደ ሰባተኛ ክፍል ስናልፍ ትምህርት ቤቱም ሰባተኛን እንዲያስተምር ሆነ:: በዚህ ጊዜም እኛ ተማሪዎቹ ገንዘብ በማዋጣት ተጨማሪ ሁለት ክፍሎች እንዲሰሩ ተደረገ:: በዚህም አንዱን ክፍል ሰባተኛን ከተማርንበት በኋላ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ አንዱን ክፍል ስምንተኛ ክፍልን ተማርንበት” ይላሉ ሁኔታውን በማስታወስ::
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ለመቀጠል ወደ አውራጃው ትምህርት ቤት መሄድ ነበረባቸውና ወደዛ ሄዱ:: ነገር ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በወጉ እንዳይማሩ ያደረጋቸው ሁኔታ ተፈጠረ ይኸውም የአባታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ነበር:: ስለዚህም የዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን ለአንድ አመት አቋረጡ፤ በኋላም እንደገና የዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ትምህርት ቤት ተመለሱ::
“….የአባቴ መሞት የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቴን ለአንድ ዓመት እንዳቋርጥ አስገደደኝ :: እናቴ ያለአባት ብዙ ልጆችን ማሳደግ ስለነበረባት እኔም ከትውልድ አካባቢዬ ርቄ ስለሄድኩ ትምህርቴን በአግባቡ ለመከታተል ከፍ ያለ ችግር ውስጥ ነበርኩ ” ይላሉ ::
ሳይደግስ አይጣላም ነውና ብሂሉ ፕሮፌሰር ይልቃል የዘጠነኛ ክፍል ትምህርታቸውን የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት እንዳጠናቀቁ የስራ ማስታወቂያ አዩ እድሜያቸው ለስራ ያልደረሰም ቢሆን ስምንተኛ ክፍልን ያጠናቀቀ ይል ስለነበር እድሜያቸውን ከፍ አድርገው ለውድድር ተመዘገቡ::
“…..የተመዘገብነው ስራ የጤና ረዳት የሚል ነበር:: በወቅቱ ፈንጣጣ ከአገራችን የጠፋበት ጊዜ ስለነበር እና፤ የዓለም ጤና ድርጅት ለጤና ጥበቃ እርዳታ በመስጠት በዚህ ዘመቻ የተሳተፉትን ወጣቶች በብዛት በጤና ረዳትነት እንዲሰለጥኑ ሲደረግ ፤ ጤና ጥበቃ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ከየትምህርት ቤቱ ፤ ከጦር ሰራዊት፤ ከፖሊስ፤ ከመንግስት እርሻዎችና ከተለያዩ ቦታዎች ወጣቶችን መልምሎ በጤና ረዳትነት ለማሰልጠን የወጣ ማስታወቂያ ነበር:: በወቅቱም ውድድሩን በማለፌ ለስልጠና ታጠቅ ጦር ሰፈር ገባሁ” ይላሉ::
ስልጠናውን ለአንድ ዓመት ያህል ከወሰዱ በኋላ በቀጥታ የተመደቡት 155 ብር ደመወዝ ጎንደር ክፍለ ሀገር ሁመራ ሆስፒታል ነበር:: ቀስ ብሎም ደመወዛቸው ወደ 182 ብር ከፍ አለላቸው:: በዚህ ሆስፒታል ላይ ለሶስት ዓመት ያህል ሰሩ:: እንዳሰቡትም እናታቸውን ለመደገፍ እድሉን አገኙ::
” ….የጤና ባለሙያ እሆናለሁ ብዬ በልጅነቴም አልተመኘሁም እንደውም እኔ አስብ የነበረው የሒሳብ ትምህርት እወድ ስለነበር የኢንጂነሪንግ ተማሪ እሆናለሁ ብዬ ነበር:: ነገር ግን ጤና ረዳትነትን ስማር በተለይም ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ልምምድ ሳደርግ የህክምና ተማሪዎችንና መምህራኖቻቸውን በቅርብ የማየት እድል ሳገኝ ለሙያው ፍቅርና ቅናት አደረብኝ:: በትምህርቴም ጥሩ ስለነበርኩ መምህራኖቼም በዚሁ መቅረት እንደሌለብኝ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ሊያዩን እንደሚፈልጉ ደጋግመው ይነግሩኝ ስለነበር ሐኪም መሆን እንዳለብኝ ያን ጊዜ ነው የወሰንኩት” ይላሉ::
ፕሮፌሰር የህክምናን ሙያ ካዩት በኋላ ራሳቸውን አሻሽለው ትልቅ ደረጃ መድረስ እንዳለባቸው ወሰኑ:: ይህንንም ለማሳካት ቤተሰባቸውን እየረዱ ራሳቸውን እያሸነፉ ብዙ ትግል አደረጉ:: ፕሮፌሰር መሻሻልን ስንቅ ስላደረጉ በስራ ቦታቸው ተመድበው እየሰሩ በተልዕኮ ትምህርት ከዘጠነኛ እስከ 11 ክፍል ያለውን ትምህርታቸውን ቀጠሉ::
የሁመራ ቆይታቸውንም አጠናቀው በጭልጋ አውራጃ አይከል ጤና ጣቢያ ተቀየሩ:: ይህ ሁኔታ ግን ፕሮፌሰር ላይ ቅሬታን ፈጠረ ፤ ምክንያቱም ሁመራ ላይ ሶስት ዓመት ስለሰሩ ይጠብቁ የነበረው ዝውውር ጎንደር ወይም ደብርታቦር ከተሞች ላይ ነበርና ቅር አላቸው:: ያም ቢሆን ግን ወደተመደቡበት አካባቢ ሄደው ለስድስት ወራት ስራቸውን ሰሩ:: ከዛ ግን ስራቸውን ትተው ወደ ባህርዳር በመሄድ ጣና ሐይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በመደበኛው መርሀ ግብር አጠናቀቁ::
“…..ትምህርቴን ከዘጠነኛ ክፍል አቋርጬ ወደስራ ከገባሁ ጀምሮ ቢያንስ እናቴን ምንም ነገር አላስቸገርኩም ፤ ራሴን ችያለሁ፤ ሁለተኛ ደግሞ ሁመራ ላይ የበረሃ አበልም ስለነበረው ፤ በባህርዬም ቁጥብ ስለሆንኩ ገንዘቡን በአግባቡ አጠራቅሜ ከሁለት ዓመት በኋላ ቤተሰቤን ለመጠየቅ ስመለስ ልብስ ገዝቼ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ አድርጌ በጣም ተደስተው ነበር:: እንደውም የአካባቢያችን ሰዎች ይልቃል “አካባቢውን የሃብታም ፍየል አስመሰለው” እስኪባል ድረስ አዘንጫቸው ነበር፤ በመሆኑም ጤና ረዳት መሆኔ በጣም ጠቅሞኛል” ይላሉ::
ፕሮፌሰር ይልቃል በዛ በለጋ እድሜያቸው የሰሩትን የጤና ረዳትነት ስራ እስከ አሁን ላለው ሕይወታቸው እጅግ እንደጠቀማቸው ነው የሚናገሩት:: ምክንያቱም ገና በልጅነታቸው ብዙ ጠንካራ ውሳኔዎችን እንዲወስኑም ስለማስቻሉ ነው የሚናገሩት::
“…… የጤና ረዳት ሆኜ ስራ የጀመርኩት ከ18 ዓመት በታች በነበረ እድሜዬ ነው:: በዛን ወቅት ደግሞ ራሴን ችዬ በርካታ ጠንካራ ውሳኔዎችን ወስኛለሁ:: ምናልባት አሁን ቢሆን የማልደፍራቸውን ውሳኔዎች ወስኛለሁ:: ለምሳሌ ትምህርቴን አቋርጬ ወደስራ የገባሁት ማንንም ሳላማክር በራሴ ውሳኔ ነው:: ስራዬን ትቼ ባህርዳር የ12ኛ ክፍል ትምህርቴን የተከታተልኩት ለማንም ሳልናገር ነው:: እነዚህ ሁሉ ለእኔ በእድሜዬ ትልልቅ ውሳኔዎች ናቸው”::
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በጥሩ ውጤት በማጠናቀቅ ጎንደር የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ተመደቡ:: ብልሁ ይልቃልም በስራ ላይ እያሉ ያፈሩትን ንብረት በመሸጥና ገንዘቡን ባንክ በማስገባት እየቆጠቡ ራሳቸውን እየረዱ የሕክምና ትምህርታቸውን መማራቸውን ይናገራሉ:: በዚህች ባስቀመጧት ገንዘብም በሳቸው ደረጃ እንደልብ በሚባል መልኩ ለእስክርቢቶ ፤ ለወረቀት፤ ለልብስና ለጫማ መግዣ ሳይቸገሩ መማራቸውን ይናገራሉ::
ሕይወቴን የመራሁት በጣም በዕቅድና በፕሮግራም ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ይልቃል ይህንን ዓይነት ሰው እንድሆን እድሉን የከፈተልኝ ደግሞ ጤና ረዳትነት ስልጠና መሄዴ ነው:: ይህ ባይሆን ኖሮ ብዙ እቸገር ነበር በማለት ይናገራሉ::
በጎንደር ሕክምና ሣይንስ ኮሌጅ (ያኔ አዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር እንደነበረ ልብ ይሏል) ሕክምናን የተማሩት ፕሮፌሰር ይልቃል የትምህርት ቆይታቸውም ጥሩ እንደነበር ይናገራሉ:: እንደውም መጀመሪያ የጤና ረዳትነት ስልጠናን መውሰድዎ ምን ያህል አገዘዎት ጎበዝ ተማሪ አደረገዎት? ብዬ ላነሳሁላቸው ጥያቄ ሲመልሱም “…ስልጠናው አግዞኛል ለማለት አያስደፍርም፤ ግን ደግሞ ለትምህርቱ እንግዳ እንዳልሆን አድርጎኛል ፤ እኛ በጤና ረዳትነት 1 ዓመት የሰለጠነውን ዩኒቨርሲቲው ላይ በአንድ ቀን ልንማረው እንችላለን:: ነገር ግን 12ኛ ክፍልን ተፈትነው በቀጥታ ዩኒቨርሲቲውን ከተቀላቀሉት ተማሪዎች እንሻል ነበር፤ ውጤት እስከመቀየር ድረስ የሚያደርስ ግን አልነበረም” ይላሉ፡፡
በህክምና ትምህርት ቤት
ውስጥ የነበራቸው ውጤት
መካከለኛ ነበር:: ስራ ላይ የነበሩ መሆናቸው ደግሞ ብዙ እንዳይጨነቁ እባረራለሁ ብለው ሰግተው ሌት ተቀን እንቅልፋቸውን እንዳያጡ አድርጓቸዋል፤ ይህም ቢሆን ግን ዝቅ ያለ ውጤትም ላለማምጣት የቻሉትን ያህል ያጠኑም ነበር::
የጎንደር ሕክምና ሣይንስ ኮሌጅ የህክምና ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የተመደቡት ከንባታና ሃድያ አውራጃ ውስጥ ሽንሽቾ ጤና ጣቢያ ነው:: ባለ ብዙ እቅዱ ፕሮፌሰር ይልቃል እዚህ ቦታ ላይ ከ26 ቀን በላይ መስራት አልቻሉም:: ምክንያቱ ደግሞ ወደ ኤርትራ ዝመት መባላቸው ነበር:: ነገር ግን በተፈለጉበት ሰዓት መድረስ ባለመቻላቸው ሌላ ሰው ተላከ:: ይህ ዘመቻ ቢያልፋቸውም ለሌላ ዘመቻ ታጠቅ ማገገሚያ ማዕከል እንዲዘምቱ ሆነ:: በዚህ ቦታ ላይ ሶስት ያህል ወራቶችን እንደሰሩ ኢህአዴግ አገሪቱን በመቆጣጠሩ ታጠቅን ለቀው አዲስ አበባ ገቡ::
በወቅቱ ስድስት ኪሎ ፖለቲካ ትምህርት ቤት ( አሁን የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩሊቲ ) ተብሎ በሚታወቀው ግቢ ውስጥ የደርግ ባለስልጣናት በእስር እንዲቆዩ ተደረገ፤ በግቢው ውስጥ የነበሩት የጦር ምርኮኞች ወደሌላ ማገገሚያ እንዲሄዱና እሳቸው ደግሞ እዛው ጤና ጣቢያ በማቋቋም የደርግ ባለሰልጣናትን እንዲያክሙ ሆነ::
“….. አዎ በወቅቱ በስድስት ኪሎ ፖለቲካ ትምህርት ቤት ቁስለኞችን አክም ነበር፤ ነገር ግን የመንግስት ለውጥ በመደረጉ ቦታው ላይ የደርግ ባለስልጣናት እንዲገቡና ቁስለኞቹ ወደሌላ ማገገሚያ ማዕከል እንዲዞሩ ሆነ:: እኔም እዛው ጤና ጣቢያ አቋቁሜ ባለስልጣናቱን ለስድስት ወራት ያህል እያከምኩ ከቆየሁ በኋላ ሰንዳፋ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሌጅ እንድንዞር ተደረገ” ይላሉ::
ከእነዚህ አገርን ሲመሩ ከነበሩ እሳቸውም ሆነ አብዛኛው ህዝብ በሩቅ እንጂ በቅርብ አይቷቸው አግኝቷቸው ከማያውቅ የደርግ ባለስልጣናት ጋር ሦስት አመታት በህክምና ሙያቸው የማገልገል እድልንም አግኝተዋል::
“…በወቅቱ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እና ጣሊያን ኤምባሲ ከተጠለሉት በቀር ሁሉም የእኔው ታካሚ ነበሩ:: እነ ሻምበል ፍቅረ ስላሴ ወግደረስ፣ ሌተናል ኮሎኔል ፍሰሃ ደስታን ጨምሮ ብዙዎቹ በስም የምናውቃቸው ሁሉ ነበሩ:: ከመቶ በላይ ጀነራሎችና ሚኒስትሮችም እንደዛው:: በእድሜ ልጅ(ወጣት) ስለነበርሁ ብዙዎቹ በስራዬ ላይ ሲያዩኝ ታግዬ ከኢህአዴግ ጋር የመጣሁ ስለምመስላቸው በጣም ይጠነቀቁ እንደነበር በኋላ አጫውተውኛል”::
አገሪቱን በከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ ሆነው ሲመሩ የነበሩ ሰዎች ከፍተኛ የጦር ጀነራሎችና ሌሎችንም ማከም ለእርስዎስ ምን ስሜትን ፈጠረብዎት? ስላቸው “……እነሱ ትልቅ መሆናቸው የሚፈጥረው ስሜት እንዳለ ሆኖ እኔ ልጅ ሆኜ የተወለድኩበት ወረዳ ሲያምጽ ከመንግስት ጋር ተዋግቷል፤ አባቴ የሞተው በዚሁ ምክንያት ነው፤ ስለዚህ የደርግ ስርዓት አባቴን ገሎብኛል ማለት ነው ፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ በቀጥታ አባቴን ባይገሉትም በስርዓቱ ውስጥ የነበሩ ናቸው የአባቴ ገዳዮች ነበሩ፤ ይህም ቢሆን ግን ለራሴ ደጋግሜ እነግረው የነበረው በእኔና በቤተሰቤ ላይ የደረሰውን ነገር ሁሉ ረስቼ በሙያዬ የሚፈልጉትን አገልግሎት መስጠት እንዳለብኝ ነበር፤ በመሆኑም የልቤ ሀዘን ተጽዕኖ አድርጎብኝ የገባሁትን ቃል ኪዳን እንዳላፈርስ ጥንቃቄ አደርግ ነበር” ይላሉ ሁኔታውን ሲያስታውሱ::
ይህ የልባቸው መሻት ተሳክቶላቸውም ባለስልጣናቱን ለሶስት አመታት ያለምንም ችግር የጤና ሁኔታቸውን ሲከታተሉ የባሰ ነገርም ሲያዩ ተጨማሪ ህክምናን እንዲያገኙ ወደ ሆስፒታሎች ሲልኩ በባለሰልጣናቱም አብዝቶ ሲወደዱና ሲመሰገኑ ቆዩ:: በዚህ ሙያዊ ስነ ምግባራቸው ደግሞ እስከ አሁንም ድረስ ሲያገኟቸው በፍቅር የሚያዩቸው ተደዋውለው የሚጠያየቁ ቤተሰቦችን ለመፍራት ችለዋል::
ፕሮፌሰር ባለስልጣናቱን እያገለገሉ ባሉበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት አቡነ ጳውሎስ እስረኞቹን ለመጎብኘት ወደ ስፍራው ይሄዳሉ ፤ በወቅቱ ያሏቸውን ነገር እስከ አሁን ድረስ ያስታውሳሉ፤” …..አቡነ ጳውሎስ አስረኞቹን ለመጎብኘት ወደ ስፍራው መጡ እነሱን ጎብኝተው ከጨረሱ በኋላ እኔን ጠርተው አንተ እግዚአብሔር እነዚህን ሰዎች እንድትንከባከብ እንድታገለግል መርጦሃል ፤ እነዚህ ሰዎች እራሳቸውን መከላከል የማይችሉ በሰው ቁጥጥር ስር ያሉ ስለሆኑ ከፍተኛ እንክብካቤ ይፈልጋሉ አንተም ይህንን እንድታደርግ ” ብለውኝ ሲሄዱ በእውነት ትልቅ ሃላፊነት ነበር የተሰማኝ ያንንም ለመወጣት የምችለውን ሁሉ አድርጌያለሁ” ይላሉ::
“…..እነሱን ማየት ማናገር እንደሚፈልግ እንደማንኛውም ዜጋ እኔም በዛ እድሜዬ ከእነሱ ጋር ማውራት መተያየት መቻሌ እንዳለ ሆኖ ከዛ በላይ ግን ብዙ አይነት እውቀቶችን ያገኘሁበት ወቅት ነበር፤ አብሬያቸው ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተምሬያለሁ፤ በየሳምንቱ ትምህርታዊ ጽሁፎች እየተዘጋጁ በየሙያቸው ገለጻ ሲደረግ ተከታትያለሁ፤ በዚህም ለሕይወቴም ትልቅ ትምህርት የሚሆነኝን ስንቅ አግኝቻለሁ” ይላሉ::
ከሶስት ዓመት ቆይታ በኋላ ይህ ማቆያ ተዘጋና ባለስልጣናቱም ወደማዕከላዊና ከርቸሌ ሄዱ:: በዚህ ወቅት የባለስልጣናቱ ጥያቄ ዶክተር ይልቃል አብሮን ይዘዋወር የሚል ነገር ፤ እሳቸው ግን ከፍ ያለ የትምህርት ፍላጎት ስለነበራቸው ቢጠየቁም ፍቃደኛ አልሆኑም ፤ በአንጻሩ ሆስፒታል መግባት እንደሚፈልጉና ከእነሱ ጋር እንደማይሄዱ አሳወቁ:: በዚህም ራስ ደስታ ሆስፒታል ተመደቡ:: ለአንድ አመት ተኩል ሙያዊ አገልግሎታቸውን ከሰጡ በኋላ የድረ ምረቃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አቀኑ::
ፕሮፌሰር ይልቃል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት ምርጫቸው የዓይን ህክምና አደረጉ:: ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያታቸው ገጠር ላይ ያሉ በዓይን ህመም የሚሰቃዩ ሰዎች ነበሩ:: ችግሩን ለመቅረፍም የዓይን ሐኪም መሆንን ተቀዳሚ ምርጫቸው አደረጉ::
“…..በእኛ አካባቢ ሰዎች በዓይን ህመም ምክንያት ብዙ ሲቸገሩ አይ ነበር:: በተለይ የዓይን ማዝ (ትራኩማ) የሚባለው በሽታ የብዙዎችን ዓይን አጥፍቷል:: በተለምዶ ፀጉር በቀለ በሚል የሰዎች የዓይን እይታ ሲጠፋም አይ ነበር:: ይህንን ለመቅረፍ ደግሞ የዓይን ሐኪም መሆን አስፈላጊ ሆኖ ይሰማኝ ነበር” ይላሉ የዓይን ህክምና ትምህርት ክፍል የገቡበትን ምክንያት ሲያስረዱ::
በመጀመሪያም ፈልገው የተቸገረ ወገናቸውን እረዳበታለሁ ብለው የጀመሩት የዓይን ህክምና ትምህርት ከገቡበት በኋላ እጅግ ወደዱት:: ፕሮፌሰር ደግሞ በባህርያቸው ረጋ ያሉ ለሚያደርጉት ነገር ጥንቃቄን የሚያስቀድሙ መሆናቸው በጣም ስስ የሆነውንና ከፍ ያለ ጥንቃቄን የሚፈልገውን ዓይንን ለማከም ትክክለኛው ሰው ሆኑ::
“…..የዓይን ህክምና ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው ፤ እኔ ጊዜ ወስጄ በምፈልገው መንገድ ጥንቃቄ አድርጌ በቻልኩት መጠን ለመስራት ነው የምሞክረው ከዚህ አንጸር ደግሞ ባህርዬም ረድቶኛል መሰለኝ እስከ አሁን በስራዬ በጣም ደስተኛ ነኝ” ይላሉ::
ለብዙ ዓመታት በተወለዱበት ወረዳ ላይ ብቸኛው የሕክምና ዶክተር ሆነው የዘለቁት ፕሮፌሰር ይልቃል፤ በዚህም ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ለማየት በሄዱበት አጋጣሚም ሆነ በሌላ ጊዜ የአካባቢውን ህብረተሰብ በሙያቻው ሳያገለግሉ ተመልሰው አያውቁም:: የዓይን ሐኪም ከሆኑ በኋላም ቢሆን ያላቸውን እውቀት እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን ጭነው በመሄድ ለብዙዎች መፍትሔ ሰጥተው ነው የሚመለሱት::
ፕሮፌሰር የሰብ ስፔሻሊቲ ትምህርታቸውን አሜሪካን አገር ነው የተማሩት ፤ እዛ በትምህርት ላይ ሳሉም ወዲያው ጨርሰው አገራቸው መመለስን ነበር የሚያስቡት ምክንያቱም እዚህ ብዙ የእሳቸውን ህክምና የሚፈልግ የአገራቸው ልጆች እንዳሉ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ::
“….አሜሪካን አገር ለትምህርት ስሄድ ገና ወጣት ነበርኩ፤ አላገባሁም ምንም ወደኋላ የሚያስቀረኝም ነገር አልነበረም፤ ግን እዛ ቀርቼ ከማገኘው የኢኮኖሚ ጥቅም ይልቅ እውቀቴን ይዤ አገሬ ብገባ ምን ያህል ዜጎችን እንደማገለግል ለአገሬም አልኝታ እንደምሆን አውቅ ነበር በመሆኑም ብዙ ሰዎች እንድቀርና ጥሩ ሕይወት እንዲኖረኝ ቢያግባቡኝም እኔ ግን አልፈለኩምና ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ ወደአገሬ ነው የገባሁት” ይላሉ::
በሌላ በኩል ደግሞ ይላሉ ፕሮፌሰር ” …ከዚህ ስሄድ ትልቅ ሃላፊነት ይዤ ነው የሄድኩት ፤ ተመልሼ ካልመጣሁ መታከም የማይችሉ በሽተኞች ነበሩኝ፤ እንዲሁም እኔ የተላኩት እውቀት ይዤ መጥቼ እንዳስተምር ፣ እንዳክም ነው ተከፍሎልኝ ነው የተማርኩት፤ በመሆኑም ይህንን ውለታ መብላት አልፈለኩም:: ከምንም በላይ ደግሞ እዛ ብቀር ለገንዘብ ነው የእኔን አገልግሎት የአሜሪካን ህዝብ ይፍልጋል ማለት አይቻልም፤ የአገሬ ስዎች ግን ከምንም በላይ አስፈልጋቸዋለሁ ብዙ አገልግሎቴን የሚሹ አሉ ለአገሬም ጥሪት ነኝ” ይላሉ::
“….አሁን በአገራችን የዓይን ህክምና አሰጣጥ ላይ የሚታዩ እድገቶችና ለውጦች ሰፊ ናቸው:: ከዚህ ቀደም አገር ውስጥ የማይሰጡ ህክምናዎች አሁን በራሳችን ባለሙያዎች መሰራት ጀምረዋል:: ለዓይን ህክምና ጆሮ መሰጠት ተጀምሯል:: ይህም ህክምና እንዲያድግ እያደረገው ከመሆኑም በላይ አሁን ባለንበት ሁኔታም ህክምናው መነቃቃትና መሻሻል ይታይበታል የዓይን ሐኪሞችም በቁጥርም በምንሰጠው አገልግሎትም እየበዛን ነው”ይላሉ::
በአገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዓይን ሐኪም ያለው ዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ነው:: ይህ የዓይን ትምህርት ክፍል ደግሞ የድረ ምረቃ ትምህርት መስጠት ከጀመረ 42 ዓመት ሆኖታል:: እዚያ ያለን ብዙዎቻችን ብዙ ልምድ አካብተናል፤ ውጭ አገር ሄደን ተምረናል፤ ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ ሲሰሩ ያልነበሩ የቀዶ ህክምና ስራዎች እንዲጀመሩ የራሳችንን አስተዋጽኦ አድርገናል ይላሉ::
ፕሮፌሰር ይልቃል እንዳሉትም እሳቸው ብቻ እንኳን በሰብ ስፔሻሊቲ (ኦኩሎፕላስቲክስ ) ሙያ ማለትም ዓይን አካባቢ መበላሸት፣ ለምሳሌ የዓይን ሽፋሽፍት መታጠፍ፣ የእንባ ቧንቧ መዘጋት፣ ዓይን አካባቢ ማሳመር፣ እጢዎች ከዓይን ጀርባ፣ ጎንም ሆነ ፊት ለፊት ቢወጡ በቀዶ ህክምን ማስተካከል ላይ የመጀመሪያው ሰው በመሆን በብቸኝነት በርካታ ዓመታትን አገልግለዋል::
የመጀመሪያም እንደመሆናቸው መጠን ሙያው እንዲስፋፋ ሌሎች ባለሙያዎችም በዘርፉ እንዲሰሩ ችግሩ ያለባቸውም ሰዎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ አበርክተዋል:: አሁን ላይም በዘርፉ ከሰባት ያላነሱ ባለሙያዎች ሊኖሩ ችለዋል:: በቀጣይ ደግሞ ትምህርቱን በአገር ውስጥ ለመስጠት ዝግጅትም በማድረግ ላይ ናቸው::
ዳግማዊ ምኒልክ ውስጥ እሳቸውን ጨምሮ ከሳቸውም በፊት የነበሩ እንደውም የእሳቸውም መምህራን ሁሉ በሙያቸው ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አድርገዋል:: ብዙ ዜጎች ውጭ አገር እየሄዱ ይታከሙ የነበሩትን በማስቀረት አገር ውስጥ ታክመው እንዲድኑም አስችለዋል::
በዓይን ህክምና ሕይወት ላይጠፋ ይችላል ነገር ግን ለዓይን ሐኪም ዓይን መጥፋትም እንደ ሕይወት መጥፋት ነውና በዚህ ልክ ያዘኑበት ጊዜ ነበር? ፕሮፌሰር “…..እስከ አሁን የሰራኋቸው ስራዎች ሁሉ የተሳኩ ነበሩ ማለት አይደለም፤ ያልጠበቅነው ነገርም ሊያጋጥም ይችላል ፤ እንደዚህ አይነት ነገር ሲያጋጥመኝ እንቅልፍ አልተኛም፤ በተቻለ መጠን ወደ ኦፕሬሽን ክፍል ሳልገባ ከታካሚዎች ጋር ቁጭ ብዬ እነጋገራለሁ፤ ከወጡ በኋላም እንደዛው፤ ነገር ግን ለማከም ጥረት በሚደርግበት ጊዜ የሚያጋጥም ችግር ያለ ነው መጽሐፍ ላይም ተጽፏል፤ አንዳንዱ ጉዳት ደግሞ ምንም ሊደረግለት የማይችል የሚሆንበት አጋጣሚም አለ፤ ልቤን ከሚሰብሩት ነገሮች መካከል ግን ዓይን ላይ ወይም ዓይን አካባቢ እጢ ወጥቶ ወደካንሰርነት ተቀይሮ አይኑን አጥፍቶ በጣም ቆስሎ፤ በጣም ሸቶ፤ ትል አፍርቶ የሚመጡ ሰዎች ናቸው:: እነዚህ ሰዎች ምናልባትም ሆስፒታል እስከሚደርሱ ረጅም ጊዜ የቆዩት አንድም በግንዛቤ ማነስ ወይም በአቅም ማነስ ወይም በሁለቱም ምክንያት ነው፤ እንዲያውም የድህነታችን መገለጫ ሁሉ ይመስለኛል፤ በመሆኑም እነዚህን ሰዎች የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቼ ነው ከችግራቸው ለማላቀቅ የምጥረው” በማለት በስራቸው ላይ ስለሚመለከቱት ነገር ይናገራሉ::
አልከደን ብሎ የመጣ አይን እንዲከደን፣ የተከደነው ሲከፈት፣ ወደአንድ በኩል የተጣመመውን ወደቦታው እንዲመለስ ማድረግ ትርፍ ነገር ካለ አንስቶ ማሳመር ፕሮፌሰር ከተካኑባቸው ብሎም ለዓመታት በብቸኝነት ከሰሯቸው የህክምን ስራዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው:: ሆኖም በዚህ ስራ ሰዎችን እንደሚፈልጉት አድርጎ ማስደሰቱ ለእሳቸውም ደስታ ቢፈጥርላቸውም ያን ያህል ግን አብሮ የሚቆይ ወይም ደግሞ ከባድ የዓይን ችግሮችን ይዘው መጥተው እንደሚሰሩላቸው ሰዎች እርካታ እንደማይፈጥርባቸውም ነው የሚናገሩት::
ፕሮፌሰር ትዳር የመሰረትኩት ቆየት ብዬ ነው ይላሉ፤ ከወራት በኋላም 15 ዓመት የጋብቻ ዘመናትን ያስቆጥራሉ:: በእነዚህ ዓመታት ደግሞ ፋርማሲስት ከሆኑት ባለቤታቸው አንድ ወንድና ሁለት ሴት ልጆችን ወልደዋል:: ምንም እንኳን ልጆቹ ህጻናት ሆነው መጨረሻቸው የታወቀ ባይሆንም አንዷ” እንደ አባቴ የዓይን አካሚ ነው የምሆነው” ትላለች:: ሌላዋ የልብ ሐኪም የመሆን ፍላጎት አላት በማለት የልጆቻቸውን ሁኔታ ይናገራሉ::
መልዕክት
ሁልጊዜ የምናገረው ነገር ነው:: ሰው የሚወደውን ስራ ሲሰራ ውጤታማ ይሆናል፤ ነገር ግን ገንዘብ አገኝበታለሁ ብሎ የማያዋጣ የትምህርት መስክ ወይም የስራ መስክ ለመምረጥ ብሎ መሄድ የተሰጠውን መክሊቱ አለማወቅ ነው:: በተለይም የህክምና ሙያ ፍቅር የሚጠይቅ በመሆኑ በገንዘብ መተመኑ አዋጭ አይደለም:: እኔ እንኳን ዛሬ ላይ ዋጋዬ ስንት እንደሆነ አላውቀውም:: የማንንም ዋጋ መተመንም ከባድ ነው:: የህክምና ስራ ማለት እንደማንኛውም የቢሮ ስራ ተጥሎ የሚወጣ ነገ እጨርሰዋለሁ የሚባል አይደለም፤ አብሮ ቤት ድረስ የሚሄድ፤ ዛሬ እረፍት ላይ ነኝ አልሰራም፤ ተኝቻለሁ አልቀሰቀስም፤ ማለት የማያስችል ነው::
በመሆኑም ሐኪም የራሱን ምቾት እያሰበ ህክምና እሰራለሁ ካለ አይሆንም፤ በመሆኑም ለስራው እራስን ያለምንም ስሌት መስጠት ይጠይቃል:: ወጣቶች ማንኛውም ሙያ ላይ ሲሰማሩ ስራን ለአለቃ ወይንም ለገንዘብ ሳይሆን ለህሊናቸውና ለፈጣሪያቸው ታማኝ በመሆን መስራት ከቻሉ ስኬት ላይ የማይደርሱበት ምንም ምክንያት አይኖርም::
የበጎ ፈቃድ ስራዎች
ፕሮፌሰር ከማከም ከማስተማር ባለፈ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ይሳተፋሉ:: ከዚህም መካከል በትውልድ መንደራቸው ጤና ጣቢያ እንዲቋቋም ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ ሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤት እንዲከፈት ጓደኞቻቸውንና የተለያዩ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ሰርተዋል:: ቤተ መጽሐፍት አሰርተዋል፤ ቴክኒክና ሙያ አካባቢው ላይ እንዲኖር የራሳቸውን ድርሻ አበርክተዋል::
በሌላ በኩልም ጸረ-ወባ ማህበርን ከመሰረቱት ኢትዮጵያውያን አንዱ ናቸው፤ በአገር አቀፍ ደረጃም በተለያዩ ኮሚቴዎች ማለትም በጤና ሚኒስቴር የዓይነ ስውርነት መከላከል ኮሚቴ አባል ናቸው፤ በዳካ ናሽናል ድራግ አድቫይዘሪ ኮሚቴ ላይም ለረጅም ዓመታት አባል ሆነው ሰርተዋል:: የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅትም የዳኞች ኮሚቴ አባል ሆነው ያገለግላሉ:: በተጨማሪም ፕሮፌሰር ይልቃል በአገር ውስጥና በውጭ አገር በሙያቸው በአማካሪነት ይሰራሉ፡፡
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 10 ቀን 2014 ዓ.ም