ልጆች እንደምን አላችሁ፤ ዕረፍት ተጀመረ አይደል? መቼም ደስተኛ ሆናችሁ እያሳለፋችሁ እንደሆነ አምናለሁ። በተለያየ መንገድ ጊዜያችሁን እያሳለፋችሁ እንደሆነም እርግጠኛ ነኝ። ይህ ክረምት ከባለፉት ክረምቶች ከበድ ያለ ስለሆነ መጠንቀቅ አለባችሁ እሺ ? ከቤተሰባችሁ ጋር ካልሆነ የትም እንዳትሄዱ። ለማንኛውም ዛሬ ለእናንተ ሳይሆን ለወላጆቻችሁ የሚጠቅም ነገር ነው የምንነግራችሁ። ስለዚህም ተራውን ለቤተሰባችሁ ልቀቁላቸው እሺ? ጎበዞች።
ወላጆች ልጆች በክረምት ወቅት ማድረግ ያለባቸው በርካታ ተግባራት እንዳሉ ታውቃላችሁ። ምክንያቱም አሁን የዕረፍት ጊዜያቸው ላይ ናቸው። ትዝታ የሚፈጥርላቸው ነገር ይፈልጋሉ። ይህንን ዕድል የምትሰጧቸው ደግሞ እናንተ ናችሁ። ልጆች የዕረፍት ጊዜያቸው ላይ ብዙ መሰላቸት ይገጥማቸዋል። ምክንያቱም ይህንን ጊዜ ያለ ትምህርት ቤት ፣ ያለ ምንም ሥራ ካሳለፉት ጭንቀት ይለቅባቸዋል። ስለሆነም በክረምቱና በእረፍታቸው እንዳይሰለቹ ብዙ ነገሮች ያስፈልጋቸዋልና የእናንተ ድርሻ ብዙ ነው።
ብዙ ተግባራትን እንዲከውኑ መፍቀድ ደግሞ ይኖርባችኋል። ታዲያ ይህንን ስታደርጉ ምን ዓይነት መንገድ መከተል አለባችሁ፤ ምንስ ዓይነት ነገሮችን ማድረግ ይጠበቅባችኋል? ከተባለ ከተለያዩ መረጃ ምንጮች ያገኘሁትን ሀሳብ ላጋራችሁ። አንዱ ከወትሮው በተለየ መልኩ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲዝናኑ መፍቀድ ሲሆን፤ እንቅስቃሴዎችን ለማቀድ የተወሰነ ጊዜ ማውጣት ይገባችኋል። ይህ ሲሆን ግን እንደ ዕድሜያቸው፣ እንደጣዕማቸው ወይም እንደ ብስለታቸው፣ ልዩ ልዩ አማራጮች ማቅረብ ያስፈልጋል።
ከዚያ ባሻገር የተለያዩ ተግባራትን እንዲፈጽሙ ማበረታትም ይገባል። ለምሳሌ፡- አብረውን ምግብ እንዲያበስሉ መፍቀድ፣ እጅ ሥራና የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያደርጉ መጋበዝ ደስተኛ ያደርጋቸ ዋልና እንጠቀምበት።
ሌላው መደረግ ያለበት ነገር የቀጣይ ትምህርታቸውን የሚያጠኑበትንና እውቀታቸውን የሚያዳብሩበትን የተለያየ ዕድል መስጠት ነው። ለአብነት የቀጣይ ክፍል መማሪያ መጽሐፍትን እንዲያነቡ መጋበዝና የሚወዱትን ትምህርት በተግባር እንዲለማመዱት ማበረታታት በዋናነት ይጠቀሳል። በተጨማሪም የተለያዩ እውቀት የሚያስጨብጡ ትምህርታዊ ፊልሞችና መሰል የጨዋታ አይነቶችን እንዲያዩ መፍቀድም ለቀጣይ ጉዟቸው እጅግ ጠቃሚ ነው። ሌላው ወላጆች ማድረግ ያለባቸው ይህንን የክረምቱን ጊዜ ልጆቻቸው እንዴት ማሳለፍ እንዳለባቸው ማወቅ ነው።
ለመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ክረምትን እንዴት ማሳለፍ እንዳለባቸው ያውቃሉ? እንዴትስ እንዲያሳልፉ ያደርጓቸዋል? ከተባለ በብዙ መልኩ የሚል ምላሽ ይኖራል። እንደውም አንዳንዱ ተገቢነት የሌለው እንደሆነ ማንሳት ይቻላል። ከእነዚህ መካከል አንዳንድ ነገሮችን እንበላችሁ። ቤተሰብ ልጆቻቸው ትምህርት ከተዘጋ በኋላ እንዴት እንደሚያሳልፉ የሚጨነቁ ናቸው። ግን እነዚህ ቤተሰቦች ብዙ ዓይነት ባህሪ ያሳያሉ።
የመጀመሪያዎቹ ልጆቻቸው በመዝናናት ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ የሚፈቅዱ ሲሆኑ፤ በበጋው ጊዜ አዕምሯቸው ደክሟል ብለው ያስባሉና የተለያዩ መጫዎቻዎችን በመግዛትና የተለያየ ቦታ በመውሰድ እንዲዝናኑ ብቻ ይፈቅዱላቸዋል። ይህ መሆኑ ደግሞ ልጆች ምንም አይነት የግል ብቃታቸውን የሚያዳብሩበት ትምህርትና ጊዜ እንዳያገኙ ከማድረጉም በላይ አዕምሯቸው እንዲሰለብና ጨዋታ ብቻ ወዳድ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።
ሁለተኞቹ አይነት ወላጆች ደግሞ የክረምቱን ጊዜ ምንም አይነት መዝናኛ ጊዜ ሳይሰጧቸውና አዕምሯቸውን እንዲያሳርፉ ሳያደርጓቸው በቀጥታ ትምህርት እንደተዘጋ ሥራ ላይ የሚጠመዱ ናቸው። ወሩን በሙሉ በሥራ እንዲያሳልፉ ያስገድዷቸዋል። በዚህም ከትምህርትም ሆነ ከአዕምሮ እረፍት እንዲርቁ ይሆናሉ። ይህ ደግሞ ለቀጣይ የትምህርት ዝግጅታቸውም ሆነ የመቀበል አቅማቸው እንዲሁም ለሥራ ያላቸው ፍላጎት አዳጋች ነገሮችን የሚፈጥር ነው።
ሦስተኛው አይነት ወላጅ ጨዋታና መዝናናት አያስፈልግም ብለው የሚያምኑ ሲሆኑ፤ ሙሉ ጊዜያቸውን ለትምህርት እንዲሰጡ የሚያስገድዱ ናቸው። በተለይም የክረምት ትምህርት ጭምር እንዲጀምሩ ያደርጓቸዋል። በዚህም ተማሪዎች ከትምህርት ወደ ትምህርት ስለሚገቡ የጭንቀት ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ።
አራተኛው ለልጆቻቸው ምንም ግድ የሌላቸው ወላጆች ሲሆኑ፤ ጊዜያቸውን የት እንደሚያሳልፉ የማይጠይቁ፣ የማያመቻቹ ቸልተኛ የሆኑ ወላጆች ናቸው። በዚህም ልጆቹ የራሳቸውን መስመር እንዲመርጡ ይገደዳሉ። ይህ ደግሞ አንዳንዶችን ዱርዬ፣ አንዳንዶችን ሱሰኛና አልባሌ ቦታ የሚያሳልፉ ያደርጋቸዋል። ለማንም የማይታዘዙና ሥራ የማይወዱ ጭምር የሚያደርጋቸውም ነው። እናም ከላይ የጠቀስናቸው አይነት ወላጆች በሙሉ ልጆችን የሚገነቡ አይደሉም። ክረምቱን ተጠቅመው ተገቢውን ተግባር እንዳይከውኑም ያደርጓቸዋል። ስለሆነም ወላጆች እነዚህን ባህሪት መላበስ የለባቸውም። ሁሉንም አመጣጥኖ የሚያይ ወላጅ መሆንም ይጠበቅባቸዋል።
ከትምህርታቸውም ሆነ ከጨዋታ እንዳይርቁ ሚዛናዊ እቅድ ማውጣት ትልቁ የወላጆች ተልዕኮ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ልጆችን ማሳተፍ ከምንም በላይ ይጠቅማል። ልጆች ከወላጆች ጋር ተግባራትን መከወናቸው ብዙ ጠቀሜታ አለው። ለአብነት እቅድ ማውጣት ላይ መሳተፋቸው ልጆች እቅድ ማውጣትን አውቀው በዚያ መጓዝን እንዲለምዱ ያደርጋቸዋል። ኃላፊነትን መወጣት እንዲችሉም ያስተምራቸዋል። ምክንያቱም እቅድ ለስኬት የመጀመሪያ መንገድ ነውና።
ሌላው የጊዜ ዋጋን እንዲረዱ ያደርጋቸዋል። ከእቅዳቸው ውስጥ ደግሞ ሃይማኖታዊ ነገሮች እንዲካተቱ ማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ከትምህርቱ ባሻገር የሚለምዱት ብዙ ነገር ይኖራቸዋል። አንዱ ግብረገብነት ነው። ዓለማዊ እውቀትን ከመንፈሳዊው ጋር ማጣጣም እንዲችሉም እድል የሚሰጣቸው ነው።
ሌላው ወላጆች ልጆችን እቅዳቸው ውስጥ ማካተት እንዳለባቸው ማመን ያለባቸው ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን የሚያሰፉበትን ሁኔታ ሲሆን፤ ጎረቤትና ዘመድ መጠየቅን ልምዳቸው እንዲያደርጉ ማበረታት አለባቸው። አገራቸውን እንዲያውቁ ከቻሉ የተለያዩ ቦታዎችን ቢያሳዩዋቸው መልካም ነው።
በተመሳሳይ አንዳንድ ገደቦችንም ሊጥሉባቸው እንደሚገባ መዘንጋት የለባቸውም። አንዱ ክረምት ላይ ተዘውትሮ የሚታይ የፊልምና ቴሌቪዥን ጉዳይ ሲሆን፤ ለእነርሱ የሚመጥነውን መርጦ ማሳየትና ጊዜ መገደብ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ወላጆች ለልጆቻቸው መጠንቀቅ አለባቸው ሲባል ለእድሜያቸው የሚመጥነውን ነገር ማድረግ ይኖርባቸዋል። እኛ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያገኘናቸው ሀሳቦችም ጠቃሚ ናቸውና ተጠቀሙባቸው በማለት ለዛሬ ተሰናበትን። መልካም ሰንበት!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3 /2014