ዛሬ ታላቁ የረመዳን ጾም ከተጠናቀቀ ሁለት ወር ከአስር ቀን በኋላ በሚከበረው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ላይ እንገኛለን።ህዝበ ሙስሊሙ በዓመት አንድ ጊዜ የሚያከብረው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል የመረዳዳትና የመተሳሰብ በዓል እንደመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ዕለቱን የተራበን በማብላት የታረዘን በማልበስና ለሰዎች ሁሉ በጎ በማድረግ በደስታ ያሳልፋሉ።
እርግጥ ነው የየትኛውም ሃይማኖት አስተምህሮ ለሌሎች መልካም ማድረግን፣ መረዳዳትን፣ መከባበርና መተሳሰብን ያዝዛል።ይሁንና አሁን አሁን እነዚህን ዓይነቶቹ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎች ወደ ጎን እየተተው ኢትዮጵያዊ የሆኑ መልካም እሴቶች እየተሸረሸሩ ይታያል።ያም ሆኖ ቀደም ሲል የነበረውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ጠብቀውና መልካም እሴቶችን አክብረው በመያዝ ለትውልድ እያስተላለፉ የሚገኙ የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታዮች ጥቂት አይደሉም።
ሰዎችን በዘር፣ በሃይማኖትና በጎሳ ከፋፍለው የማይመለከቱ በኢትዮጵያዊ አንድነት ታምነው የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ። የተለያየ ብሔርና ሃይማኖት ያለባት አገር ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ልዩነትን ውበት በማድረግ መኖር ችላለች። ወደፊትም ትኖራለች። ይህን መልካም ኢትዮጵያዊ እሴት ጠብቆ ለትውልድ በማሻገር በኩል የተመሰከረላቸውን አውጥቶ ማሳየት ይገባል።
የዕለቱ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓልም የመልካም እሴቶች መገለጫ የሆኑትን መልካም ነገሮች ሁሉ ለሰው ልጆች በማድረግ የሚከበር ስለመሆኑ የዕለቱ እንግዳችን አቶ አላሚን መሀመድብርሃን ይገልጻሉ። አቶ አላሚን፤ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ መሳለሚያ ቢላል መስጊድ አጠገብ ነው ተወልደው ያደጉት። ባደጉበት አካባቢ ዘር፣ ብሔርና ቀለም ሳይለዩ ከእህት ከወንድሞቻቸውና ከአብሮአደግ እኩዮቻቸው ጋር በሰላምና በፍቅር ኖረዋል።
ከማንኛውም ሰው ጋር በሰላም፣ በፍቅር፣ በመከባ በርና በመተሳሰብ መኖር የመቻላቸው ሚስጥር ደግሞ የወላጅ አባታቸው ሀጂ መሀመድብርሃን መልካምነት መሆኑን ያስታውሳሉ።ልጆች የቤተሰቦቻቸው ፍሬዎች እንደመሆናቸው በተቃኙበት መንገድ ያድጋሉ። አቶ አላሚንም መልካምና ሰው አክባሪ ከሆኑትና የተቸገረን በመርዳት በአካባቢያቸው ከታወቁት ወላጅ አባታቸው ሀጂ መሀመድብርሃን በርካታ መልካም ነገሮችን ወርሰዋል።
በመልካም ስብዕናቸው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቁት ሀጂ መሀመድብርሃን በንግድ ይተዳደሩ ነበር።ከተወሰነ መጠን በላይ ሃብት ማፍራት ወንጀል በነበረበት በደርግ ዘመንም እንደ ሀጂ መሀመድብርሃን ያሉ ሰዎች ተፈላጊነት አልነበራቸውም።እንዲያውም በተንሸዋረረ መነጽር ይታያሉ። ሃብት ንብረታቸውም ይወረሳል። በዚያን ወቅት ብዙ ሃብትና ንብረት ከተወረሰባቸው ባለሃብቶች መካከል የአቶ አላሚን አባት ሀጂ መሀመድብርሃን አንዱ ናቸው።
በጊዜው የመንግሥትን ብትር በመሸሽ ከወላጅ አባታቸው ጋር ስደት የወጡት አቶ አላሚን፤ አጠቃላይ ቤተሰቡ ኑሮውን በጅቡቲ ያደርጋል።ጅቡቲን ጨምሮ በአገር ውስጥ ከ70 ዓመት በላይ በንግድ ሥራ አሳልፈው በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ከተለዩት ሀጂ መሀመድብርሃን የተገኙት አቶ አላሚንም የአባታቸውን ፈለግ በመከተል ከልጅነት እስከ ዕውቀት በንግድ ሥራ ውስጥ ናቸው።
ከአስራ አንድ ወንድምና እህቶቻቸው ጋር ያደጉት አቶ አላሚን፤ ወላጅ አባታቸው በትምህርት አጥብቀው ያምኑ እንደነበር በማስታወስ እያንዳንዳቸው ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እንደተማሩ ይናገራሉ። ከትምህርት ቀጥ ለውም ቤተሰቡ የሚተዳደርበትን የንግድ ሥራ ተቀብለው እየነገዱ ይገኛሉ።
አባታቸው ሥራ ወዳድና ታማኝ ነጋዴ እንደነበሩ የሚያስታውሱት አቶ አላሚን፤ በስደት ከሄዱበት ጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ በ1987 ዓ.ም ከአባታቸው ጋር ተመልሰዋል።ሌሎች ወንድም እህቶቻቸው ደግሞ ወደ አሜሪካ ሲጓዙ አቶ ነቢል መሀመድብርሃን የተባሉት ወንድማቸው እዛው ጅቡቲ በመቅረት የንግድ ሥራቸውን አስቀጥለዋል። ይህም የአባታቸውን ፈለግ ተከትለው ላስቀጠሉት ንግድ ትልቅ አቅም ፈጥሯል። በአሁኑ ወቅትም በአገር ውስጥ የሌሉ ምርቶችን ከውጭ የማስገባት ትልቁን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ።
አስመጪ ነጋዴ የነበሩትን ወላጅ አባታቸውን ተክተው በአገር ውስጥ አቶ አላሚን፤ ከጅቡቲ ደግሞ አቶ ነቢል በጋራ በመሆን መሀመድብርሃንና ልጆቹ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅትን በጋራ እየመሩ ይገኛሉ። ዘይትን ጨምሮ የተለያዩ በአገር ውስጥ የማይመረቱ ምርቶችን ወደ አገር ውስጥ ገበያ ያስገባሉ። በአገር ውስጥ ያስገቧቸውን ምርቶችም ለጅምላ አከፋፋዮች በማቅረብ ንግዳቸውን እያቀላጠፉ ይገኛሉ።
በአሁኑ ወቅትም ከውጭ አገር ወደ አገር ውስጥ ከሚገባው የዘይት ምርት መካከልም 50 በመቶ ድርሻ ያለው መሀመድብርሃንና ልጆቹ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት የሚያስገባው ነው።አገሪቷ ካለባት የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳም መንግሥት በቅርቡ ፍራንኮቫሉታን በመፍቀዱ ምክንያትም ድርጅቱ የራሱን ዶላር በመጠቀም በአገር ውስጥ የሌሉና ከውጭ አገር የሚገቡ ምርቶችን ያስገባል።ወደ አገር ውስጥ ከሚያስገቡት ምርቶች መካከልም ዘይት፣ ዱቄት፣ ስኳር፣ ለተለያዩ ምርቶች የሚውሉ የፋብሪካ ጥሬ ዕቃዎችንና አልፎ አልፎም መኪና ይገኝበታል።
መሀመድብርሃንና ልጆቹ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ዋና የንግድ ጣቢያው ጅቡቲ ሲሆን፤ ማናቸውም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች የሚሰራጩት ከጅቡቲ በአቶ ነቢል አማካኝነት ነው።ምርቶቹ አዲስ አበባ ሲደርሱ ደግሞ አቶ አላሚን ተቀብለው ሁሉንም በየፈርጁ ያስተናግዳሉ።ድርጅቱ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የአስመጪነትን ሚና ብቻ እየተወጣ ያለ ቢሆንም፣ የቦለቄ ምርትን ወደ ውጭ አገር በመላክ የውጭ ምንዛሪ ለአገር ያስገባ እንደነበርም አቶ አላሚን አጫውተውናል።
ፍራንኮቫሉታ ተፈቅዶለት በተለይም ዘይትን በስፋት እያስገባ የሚገኘው መሀመድብርሃንና ልጆቹ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት፤ ትላልቅ ንግዶች ላይ የተሰማራ እንደመሆኑ በቀጥታ ማህበረሰቡ ጋር መድረስ አይችልም።በአሁኑ ወቅት ባለው የኑሮ ውድነት ምክንያት በተለይም በዘይት ምርት የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የተለያዩ ዕቅዶችን ይዟል።
ድርጅቱ ከውጭ የሚያስገባውን የዘይት ምርት ለአከፋፋይ ነጋዴዎች የሚሸጥ በመሆኑና አከፋፋዮች ደግሞ የራሳቸውን ትርፍ ይዘው ለቸርቻሪዎች እያለ ማህበረሰቡ ጋር ሲደርስ ከፍተኛ ጭማሪ ይኖረዋል ያሉት አቶ አላሚን፤ ድርጅታቸው ይህንን ሰፊ ክፍተት ለማጥበብና ምርቱን በቀጥታ ለማህበረሰቡ ተደራሽ ማድረግ በሚቻልበት መንገድ እየተጓዘ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ለዚህም ሀሳባቸውን ለመንግሥት በማቅረብ በተለይም የዘይት ምርትን ለመንግሥት በማቅረብ በመንግሥት በኩል ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የተጀማመሩ ሥራዎች አሉ። በርካታ ሰዎች ያላቸውን የሥራ እንቅስቃሴ በመረዳት አቅርቦታቸውን በቀ ጥታ ለማህበረሰቡ ማድረስ የሚችሉበትን አሰራር ባመላከቷቸው መሰረት ወደ ሥራው ገብተ ዋል። የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም ፈቃደ ኝነታቸውን በተግባር ማሳየት ከቻሉ በተለይም ከውጭ አገር የሚያስገቡትን የዘይት ምርት በቀጥታ ለመንግሥት ለማቅረብ ያላቸውን ዝግጁነት የጠቀሱት አቶ አላሚን፣ አሁን ያለው የንግድ ስርዓት ግን ጤናማ አለመሆኑ ሀሳባቸውን ፈታኝ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል።
‹‹ሰዎች እየሰረቁ ቢዝነስ ሠራሁ የሚባልበት ዘመን ላይ መድረሳችን አሳዛኝ ነው›› የሚሉት አቶ አላሚን፤ ንግድን ታማኝና ሀቀኛ ከሆኑት አባታቸው ሲማሩ ጨዋነትንና መልካም ስነምግባርንም አብረው የተማሩ ታማኝ ነጋዴ ስለመሆናቸው ይናገራሉ።ይሁንና አሁን ያለው የንግድ ስርዓት ደግሞ አብዛኛው ጤናማ አይደለም። ስለዚህ መንግሥት ጤነኛውን ከታማሚው መለየት የሚያስችለውን ስርዓት ዘርግቶ ሊሰራ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል።
‹‹አባታችን በደግነቱ፣ ሁሉን እኩል አድርጎ በማየትና በሀቀኝነቱ ይታወቃል›› የሚሉት አቶ አላሚን፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው የአካባቢውን ህጻናት ‹‹የማን ልጅ ነህ፣ ማነህ፣ ምንድነህ›› ሳይሉ ማስተማራቸውንም ያስታውሳሉ።‹‹ከንፈርና ጥርስ ተደጋግፎ ያምራል›› የሚለውን አባባል የሚያዘወትሩት ሀጂ መሀመድብርሃን፤ ሰው ለሰው ተከባብሮ፣ ተረዳድቶና ተደጋግፎ መኖር ያለበት መሆኑን በማመን ብዙዎችን በመርዳት መልካምነትን አስተምረው ማለፍ የቻሉ ታላቅ አባት ስለመሆናቸውም ከልጆቻቸው በላይ የአካባቢው ማህበረሰብ ምስክር መሆኑንም ሰምተናል።
በአካባቢያቸው የተሰሩ የኮብልስቶን መንገዶችን አስተባብሮ በማሰራት ቀዳሚ ያልነበራቸው ሀጂ መሀመድብርሃን ልጅ አቶ አላሚን ንግድን ጨምሮ መልካምነትን ከወላጅ አባታቸው ቀስመዋል።አላሚን እና ወንድማቸው አቶ ነቢልም እንዲሁ ከንግድ ሥራቸው ጎን ለጎን ምግባረ ሰናይ የሆኑ ተግባራትን ያከናውናሉ። የተራበን በማጉረስ፤ የታረዘን በማልበስና በተለያዩ በጎ ሥራዎቻቸውም ይታወቃሉ።
አቶ አላሚንና ወንድማቸው አቶ ነቢል መሀመ ድብርሃን፤ የወላጅ አባታቸውን ፈለግ በመከተል ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል።ይሁንና ‹‹የሚሰጥ ለፈጣሪ ያበድራል፤ ቀኝ እጅህ ሲሰጥ ግራ እጃችሁ እንኳን አይመልከት›› እንዲል ታላቁ መጽሐፍ በዝርዝር ማስረዳት አልፈለጉም።
ከመሳለሚያ ወደ 18 ማዞሪያ በሚያወጣው የመንገድ ግንባታ በርካታ መኖሪያና የንግድ ቤቶች ፈርሰው ተመልክተናል።መንግሥትም አቅም ላላቸው ምትክ የጋራ መኖሪያ ቤት በመስጠት አቅም ለሌላቸውም ባለው አቅም እያስተናገደ ይገኛል። ይሁንና በአካባቢው በበጎ ሥራ ለሚታወቁት መሀመድብርሃንና ልጆቹ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅትም የሁለት አባወራ ቤቶችን እንዲገነባ የቤት ሥራ ሰጥቷል። ይህንንም የቤት ሥራ በደስታ ተቀብለው የሁለት አባወራ ቤቶችን እየገነቡ እንደሆነ መመልከት ችለናል። ለግንባታውም ከመቶ ሰባ አምስት ሺ እስከ ሁለት መቶ ሺ ብር በጀት መያዛቸውን አጫውተውናል።
የመኖሪያ ቤት ግንባታውን ጨምሮ የኮብልስቶን መንገድ ሲሰሩ እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካሞችን ሲመግቡና ሲያግዙ የወረዳ አራት የሥራ ኃላፊዎች መረዳት የሚገባቸውን ዜጎች ከመመልመል ጀምሮ የተለያዩ እገዛዎችን እያደረገላቸው በመሆኑ አቶ አላሚን ለወረዳ አራት የሥራ ኃላፊዎች በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
መልካምነት ለራስ ነው እንዲሉ ስለሚያደርጉት በጎ ሥራ ብዙ መናገር ያልፈቀዱት አቶ አላሚን፤ መንግሥት ለሚያደርገው ጥሪ ሁሉ ፈጣን ምላሽ እየሰጡ እንደሆነና በቀጣይም ለማንኛውም አገራዊ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኞች ነን ብለዋል።የድርጅቱ አብዛኛው ሥራ የሚከ ወነው ከጅቡቲ በሚጀምረው አስመጪነት እንደመሆኑ ጸሐፊ፣ መልዕክተኛና ጉዳይ አስፈጻሚ ለሆኑ አምስት ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
በአሁኑ ወቅትም በአገሪቱ የአስመጪነትን ሚና በብርቱ እየተወጣ ያለውና ስረ መሰረቱን ከቤተሰብ ያደረገው መሀመድብርሃንና ልጆቹ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በቤተሰቡ በተባበረ ክንድ የሚመራ ነው።በመሆኑም በቀጣይ ቤተሰቡን በማስተባበር በሌሎች የሥራ ዘርፎች የመቀላቀል ዕቅድም አለው።ዕቅዳቸውም ተወልደው ባደጉበትና በብዙ መልካም ሥራቸው በሚታወቁበት መሳለሚያ ቢላል መስጊድ ከሚገኘው ሰፊ ግቢያቸው ቡናን ቆልተው፣ ፈጭተውና አሽገው ወደ ውጭ ገበያ መላክ ነው።
ለዚሁ ዕቅዳቸውም አስፈላጊውን መሰረተ ልማት በማሟላት ላይ ይገኛሉ። ቡናን ቆልቶ የሚፈጭ ማሽንም ወደ አገር ውስጥ እያስገቡ ነው።ገበያውን አስመልክቶም ሳውዲ አረቢያን ጨምሮ ለኩዌትና ለጃፓን ለማቅረብ የገበያ ትስስር ፈጥረዋል።ሥራው ሲጀመርም ከ50 እስከ 60 ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል።
አቶ አላሚን የስደትን መጥፎ ገጽታና በአገር ውስጥ ያለውን ነጻነት በሚገባ ማጣጣም ችለናል፤ አሁን ደግሞ ስደት ሰልችቶናል ይላሉ። ይሁንና ቤተሰቡ በደርግ ዘመነ መንግሥት የደረሰበትን መገፋት ሸሽቶ ክፉ ጊዜን ያሳለፈው በጅቡቲ እንደመሆኑ ጅቡቲን እንደሚወዳትም ይናገራሉ። ‹‹ይሁን እንጂ ከአገር የሚበልጥ ምንም ነገር የለምና በማንኛውም ነገር አገርን አስቀድመን ለአገር እንሰራለን›› ብለዋል።
ሰዎች እርስ በእርስ መረዳዳት ከቻሉና እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ ለእኔ ብቻ ከማለት ለእኛ በማለት መረዳዳትና መተሳሰብ ከተቻለ ማንኛውም ችግር ይፈታል፤ የራቀው ይቀርባል፤ የማይቻል የሚመስለው ሁሉ ይቻላል በማለት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል የሰላም፣ የፍቅር፣ የመረዳዳትና የመተሳሰብ እንዲሆን በመመኘት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። እኛም መልካም በዓል እንዲሆን በመመኘት አበቃን!
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም