ማዕድን ሚኒስቴር ባለፈው ሚያዝያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው የ2014 በጀት አመት ዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፓርት የሀገሪቱ የማእድን ምርት ሀገራዊ ችግሮችን ተቋቁሞ ከፍተኛ እድገት እያሳየ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።ወርቅን ብቻ ብንመለከት በ2014 በጀት አመት ዘጠኝ ወራት 6ሺ 947 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ቀርቧል፤ አፈጻጸሙ በሀገራዊ እቅዱ ከተያዘው እቅድ አንጻር ሲታይ 106 በመቶ ነው። ከ2013 በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የ12 በመቶ ብልጫ ታይቶበታል።
ወርቅ በስፋት ከሚመረትባቸው ክልሎች መካከል አንዱ በሆነው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ እንደሚመረት ከክልሉ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በክልሉ ወርቅ እየተመረተ ያለው በባህላዊ መንገድ ብቻ ነው።
ክልሉ ሰሞኑን ለባህላዊ ወርቅ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች የእውቅና መርሃ ግብር እና የማእድን ዘርፍ ሲምፓዚየም አካሂዷል፤ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተጠቆመውም፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወርቅን ጨምሮ የተፈጥሮ ሀብት የማልማት አቅሙ እየጨመረ መጥቷል። ለአብነትም በ2014 በጀት ዓመት ብቻ 22 ኩንታል ወርቅ ከክልሉ ወደ ብሄራዊ ባንክ ተልኳል፣ 514 ሺህ ቶን የከሰል ድንጋይ እና 164 ሺህ ቶን እምነበረድ በህጋዊ መንገድ ለምቷል።
በበጀት ዓመቱ ለ183 ወርቅ አምራቾች ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ የወርቅ አምራቾች ብዛትም ከአምስት አመታት በፊት 86 ብቻ እንደ ነበር። የባህላዊ ወርቅ አምራቾች ማህበራት ቁጥርም ባለፉት ሶስት ዓመታት ከነበረበት 26 በ2014 በጀት ዓመት ወደ 234 አድጓል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን እንዳሉት፤ ክልሉ ባለሃብቶችን በወርቅ፣ እምነበረድ፣ ከሰል ድንጋይ እና ሌሎችም ማዕድን ልማት ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፉ አድርጓል።እያደገ የመጣውን የመካከለኛ እና አነስተኛ ወርቅ አምራች ማህበራት ቁጥር ማሳደግ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማደራጀት ሌላው የክልሉ መንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አስታውቀዋል።
ክልሉ ለረጅም ጊዜ በጸጥታ ችግር ሲፈተን መቆየቱንም ርእሰ መስተዳድሩ ጠቅሰው፣ በፈተና ውስጥ ዕድል በመፍጠር የተፈጥሮ ሃብቱን እያለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የእውቀት እና የቁጠባ ባህል ማነስ እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብት ክብካቤ ማነስ የዘርፉ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደሆኑ ገልጸው፤ በጥናት ላይ ተመስርቶ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሰራም ነው ያስታወቁት። በህገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጦ የሚወጣ ወርቅ መኖሩን የጠቀሱት ርእሰ መስተዳድሩ፣ ችግሩን ለመፍታት የተጀመሩ እርምጃዎች እንደሚጠናከሩ መግለጻቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።
የክልሉ ማዕድን ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ናስር መሃመድ በበኩላቸው ባለፉት ሶስት አመታት የወርቅ እና የሌሎች ማዕድናት ምርት በከፍተኛ መጠን መጨመሩን አስረድተዋል። የማዕድን ምርት ሊጨምር የቻለው መንግስት ባለፉት ሶስት አመታት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ውጤቱ እንዲቀጥል ህብረተሰቡ ሰላሙን እንዲጠብቅ መጠየቃቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመልክታል።
የክልሉ የማዕድን ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ናስር መሀመድ በተለይ ለአዲስ ዘመን በስልክ እንዳሉት፤ የእውቅና ፕሮግራሙ አላማ ባህላዊ የወርቅ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች የወርቅ ምርታማነትን የማሳደግ ጥረታቸውን ይበልጥ አንዲያጠናክሩ ለማበረታታት ነው። በባህላዊ መንገድ እያመረቱ 22 ኩንታል ወርቅ ለብሄራዊ ባንክ ማቅረብ መቻል ቀላል አይደለም። ክልሉ ካለው እምቅ የወርቅ ሀብት አኳያ ብዙ ወርቅ ማምረት እንደሚጠበቅ ለማስገንዘብ ተሰርቷል። የአደረጃጀቱ ነገር ጥሩ ሆኖ የሚመረተው ወርቅ ግን በቂ አለመሆኑ ላይ መልእክት ለማስተላለፍ ተሞክሯል፤ ማህበራቱ ገና ብዙ ስራ እንደሚጠበቅባቸው ተጠቁሟል።
በመድረኩ ከአምራች ማህበራት 15 እንዲሁም ከወርቅ አዘዋዋሪዎች 15 የሚሆኑት ሽልማትና ሰርተፍኬት እንደተበረከተላቸውም ዋና ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ። ለሽልማት የበቁት አዘዋዋሪዎች ለብሄራዊ ባንክ ባስገቡት የወርቅ መጠን ሲሸለሙ፣አምራቾቹ ደግሞ በፈጠሩት ሀብትና የስራ እድል ልክ ተሸላሚ ተደርገዋል።
ከዚህ ቀደም በሀገር ደረጃ ይህን አይነት መድረክ የተካሄደ ቢሆንም፣ በክልል ደረጃ ሲደረግ ግን ይህ የመጀመሪያው ነው ይላሉ። ያለፈው መድረክ ለውጥ ማሳየቱን ጠቅሰው፣ አምና 21 ኩንታል፣ ዘንድሮ ደግሞ 22 ኩንታል ወርቅ ማምረት መቻሉን ጠቅሰዋል። ከአምስት አመት በፊት ከ50 ኪሎ ግራም የማይዘል ወርቅ ነበር የሚመረተው ሲሉ ያስታውሳሉ።
‹‹ይህን መድረክ አጠናክረን መቀጠል ከቻልን የበለጠ ለውጥ ማምጣት አንደምንችል ተረድተናል›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አምራቾቹም በመሸለማቸው መደሰታቸውን፣ ጥሩ የማበረታቻ መንገድ አንደ ሆነም በመጥቀስ ምስጋና ለክልሉ ማቅረባቸውን አስታውቀዋል። በመድረኩ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተገኝተዋል፤ መድረኩ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ሁሉም አካላት ማስገንዘባቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፣ ጥሩ ለሰራ ምስጋና በማቅረብ ስራውን እንዲያጠናክር ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት ፤ የክልሉን የወርቅ ማዕድን እምቅ አቅምን በተመለከተ ይህን ያህል መጠን የወርቅ ሀብት አለ ተብሎ የተጠና ነገር የለም። በክልሉ ሶስቱም ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ የወርቅ ማዕድን ይገኛል።በባህላዊ መንገድ እየተካሄደ ባለው የወርቅ ልማት በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች በማህበራት ተደራጅተው እየሰሩ ናቸው፤ የማምረቱ ስራ ግን ኋላ ቀር ሲሆን፣ ቁፋሮው በእጅ ነው የሚካሄደው። ወርቅ የሚገኝበትን ድንጋይ አምራቾቹ የሚፈለፍሉትም እንዲሁ በኋላ ቀር መሳሪያ ነው። ከዚያም ድንጋዩ በወፍጮ እየተፈጨ በውሃ እየታጠበ ወርቁ እንዲወጣ ይደረጋል።
ይህን አመራረት ለማዘመን የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የሚናገሩት። ኩባንያዎች የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እያቀረቡ መሆናቸውን፣ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር እንደ ወፍጮ እና መቆፈሪያ ያሉ መሳሪያዎች ዘመናዊነት የተላበሱ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ያብራራሉ። የማዘመን እገዛው በወፍጮ በመቆፈሪያና በመሳሰሉት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ አመራረቱ በቴክኖሎጂ መታገዝ መጀመሩን ተከትሎ ምርቱም እየጨመረ ይገኛል ብለዋል። ከዚህ ቀደም በጣም ውስን ወርቅ ይመረት እንደነበር ተናግረው፣ ያም ከአሁኑ ምርት አንጻር ሲታይ ዜሮ እንደማለት መሆኑን ያስታውሳሉ።
መረጃዎች አንደሚጠቁሙት፤ በወርቅ ማምረቱ ባህላዊ አምራቾችና ኩባንያዎች እየተሳተፉ ሲሆን፣ የባህላዊ አምራቾቹ ድርሻ ከፍተኛ ነው። በኢትዮጵያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በወርቅ ማውጣት ስራ ተሰማርተዋል። ከእነዚህ መካከልም ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ሰፊውን ድርሻ ይይዛሉ። በየአመቱ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው የወርቅ ምርት ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚመረተው በባህላዊ መንገድ ነው።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደግሞ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ በባህላዊ መንገድ ብቻ እያመረተ ነው። በርካታ አባላት ያሏቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ማህበራትም ይገኛሉ። ይህን አቅም በማዘመን የወርቅ ምርታማነትን ማሳደግ እንደ ሀገር በማዕድን ዘርፍ ለማከናወን መስራት ይገባል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ይህን እያደረገ ይገኛል።
እንደ አቶ ናስር ገለጻ፤ በክልሉ የወርቅ ምርታማነትን ለማሳደግ ብዙ እቅዶች አሉ፤ ክልሉ የልማት ድርጅት አቋቁሟል፤ የተለያዩ የልማት ድርጅቶችም አሉ፤ እነዚህ አካላት የተሻለ ቴክኖሎጂ እንዲያቀርቡና በባህላዊ መንገድ የሚመርትበትን መንገድ በማዘመን የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ይሰራል። በእዚህ በኩል በጋራ ለመስራት ነው እየተሞከረ ያለው።
በግብይቱም ላይ በሰጡት ማብራሪያ ለወርቅ አዘዋዋሪዎች ፈቃድ እየተሰጠ እንደሚሰራ ነው የተናገሩት፤ እነሱ ወርቁን በአሶሳ በብሄራዊ ባንክ ውክልና ለተሰጠው አካል ያቀርባሉ ይላሉ። ከዚህ በመለስ ግን በግብይቱ ላይ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ስለመኖራቸውም ይጠቁማሉ።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ክልሉ ከሱዳንና ደቡብ ሱዳን ጋር ይዋሰናል፤ ወርቁ የሚመረተው በአብዛኛው በእነዚህ ጠረፍ አካባቢዎች ነው። በግብይቱ ላይ ጥቁር ገበያውና ኮንትሮባንዲስቶች ችግር እየፈጠሩ ናቸው። በእነዚህ ድንበሮች አካባቢ የወርቅ ህገ ወጥ ንግድ ይስተዋላል። ይህን ችግር ለመፍታት ግብረ ሀይል ተቋቁሞ በቁጥጥርና ክትትል እየተሰራ ይገኛል። ችግሩን የመፍታቱ ስራ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራን በስፋት ይጠይቃል።
የፌዴራል መንግስት የማዕድን ፓሊሲ እያዘጋጀ ነው፤ ይህም የማዕድን ልማቱንና ግብይቱን መምራት የሚያስችል ነው፤ እኛ ድንበር አካባቢ እንደመገኘታችን እንደ ክልል ሁሉም የጸጥታ ተቋማት በግብረ ሀይል ውስጥ ይሰራሉ። መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ጉምሩክ ከኛ ጋር በግብረ ሀይል አብረን እየሰራን ነው። አስፈላጊውን ቁጥጥር እንዲያደርጉ ሁሌም አብረን እንመክራለን። ጠንካራ ፍተሻ እየተደረገም ይገኛል። ይህም ህገወጥ የወርቅ ዝውውሩን ለመቆጣጠር አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
ይህ ሀብት የአምራቹን ህይወት እንዲቀይር፣ የክልሉን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያሳድግ እየተሰራ መሆኑንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የጠቆሙት። ይህ ህብረተሰብ ወርቅ ላይ ተቀምጦ የሚቸገር ነው ሲሉ ገልጸው፣ እኛ ማዕድኑ የህብረተሰቡን ህይወት እንዲቀይር ምኞታችን ነው፤ አቅሙ ያላቸው ባለሀብቶች፣ ቴክኖሎጂው ያላቸው አካላት ወደ ክልሉ መጥተው ከህብረተሰቡ ጋር እንዲሰሩ እንፈልጋለን ሲሉም አስታውቀዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ናስር ገለጻ፤ የባህላዊ አምራቾቹ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እንደ ክልል ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው። በኩባንያ ደረጃ በዘመናዊ መንገድ በክልሉ ወርቅ እየተመረተ አይደለም። ባለሀብቶች በወርቅ ማምረት ስራ ለመሰማራት ቦታዎችን ከአመታት በፊት ቢወስዱም ፣ ባለፈው ስርአት ቦታ መያዝ እንጂ ማልማት ውስጥ መግባት ብዙም አይታይም ነበር። አሁን ባለሀብቶቹ ወደ ልማቱ አንዲገቡ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ናቸው። ክልሉ እያደረገ ያለውን ጥሪ ተከትሎም ሌሎች ባለሀብቶች ወደ ክልሉ እየመጡ ይገኛሉ።
እንደ ሀገር ሰላምና ደህንነቱ ከተረጋጋ የማዕድን ሀብቱ የሚለማበት አቅጣጫ እየተቀመጠ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከአራት አመት በፊት ማዕድን ብዙም ትኩረት የተሰጠው አልነበረም ይላሉ፤ አሁን ግን ከቡና ቀጥሎ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ተጠቃሹ መሆን መቻሉን ነው የተናገሩት።
አምራቹ ከወርቅ ምርቱ የሚያገኘውን ሀብት በአግባቡ እንዲጠቀምበት፣ ህይወቱን እንዲቀይርበት ወደ ተሻለ ማምረት ስራ መግባት እንዲችል ለማድረግ ቁጠባ ላይ እየተሰራ መሆኑንም ይገልጻሉ። ከወርቅ የሚገኘው ብር የማያልቅ አርጎ የመጠቀም ጎጂ ባህል አለ ሲሉ ገልጸው፣ ይህን ባህል ማስቀረት ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ ነው የተናገሩት።ይህን ስራ የክልሉ ማዕድን አጄንሲ ብቻውን ሊሰራው እንደማይችልም አስታውቀዋል፤ ስልጠና በተከታታይ እንዲሰጥ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረናል፤ የቁጠባ ባህልን ለማሳደግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየመከርን ነው። በትምህርትና ስልጠና ግንዛቤ ለማስጨበጥ እየተሞከረ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።
ቁጠባ አስፈላጊ ነው። ይህ ማለት ግን ቁጠባ ጨርሶ የለም ማለት አይደለም፤ ከነበሩበት ሁኔታ አኳያ ሲታይ ትልቅ መሻሻል አለ። የቁጠባን ባህል በማሳደግ በኩል እየተሰራ ነው። በማዕድን ሚኒስቴር በኩልም ግንዛቤ በማሳደግ በኩል እየሰራ ነው። በሶስት አመታት ውስጥ ያልነበረ ነገር ማምጣት ተችሏል።
‹‹ለውጡን ለማበላሸት የሚደረግ ሙከራ አለ፤ በጸጥታ በኩል ገባ ወጣ የሚል ችግርም ይስተዋላል›› የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይሄ የአምራቹ ትልቁ ተግዳሮት መሆኑን ነው የጠቀሱት። ተግዳሮቱ አምራቾቹ ወርቅ የማምረቱን ስራ ያዝ ለቀቅ እንዲያደርጉት እያስገደዳቸው ነው ይላሉ። መንግስት በጸጥታ ማስፈኑ በኩል ጥሩ እየሰራ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህ ችግር ይፈታል የሚል እምነት አላቸው። ሁለተኛው ችግር በቴክኖሎጂ በኩል ለሚቀርብ ጥያቄ በቁጠባዎች በኩል ፈጣን ምላሽ አለመስጠታቸው ነው።በእዚህ ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል። በተረፈ ግን ሁኔታዎች በጥሩ ደረጃ ላይ ናቸው ብለዋል።
በአስር አመቱ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሪ እቅድ ላይም የማዕድን ዘርፍ ከአምስቱ የእድገት ማእዘኖች አንዱ እንደመሆኑ ክልሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ እያመረቱ ለሚገኙት ለባህላዊ ወርቅ አምራቾች የሰጠው እውቅናና ማበረታቻ ተገቢና ወቅታዊ ነው። ለአምራቾቹ የሚደረግ የትኛውም ድጋፍ አምራቾቹን ከማትጋት ባሻገር እንደ ሀገር እና ክልል ከወርቅ ማዕድን ለማግኘት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የበኩሉን ሚና ይጫወታል።የባህላዊ አምራቾችን የማምረት አቅም በቴክኖሎጂና በስልጠና በማሳደግ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ምርታማነት ማሳደግም ይገባል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2014