እኛ መልከ ብዙ፣ ልምደ ብዙ አገር ነን።ታሪክና ብዙ ተሞክሮችን የቀመርንና ለሌላ የምናካፍልም እንደሆንን ብዙዎች ይመሰክሩልናል።ለዚህም አንዱ ማሳያ ተፈጥሮ ካሳመረልን ውጪ በራሳችን አረንጓዴ ምድር ለመፍጠር የምናደርገው ጥረት ነው።የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ችግር ለመመከትም ከሌሎች አገራት በይበልጥ የምንተጋ ሕዝቦች ነን።
ይህ አገርኛ ልማዳችን መቼ ጀመረ? ከተባለ የተለያዩ ጥናታዊና ታሪካዊ ጽሑፎች እንደሚያመላክቱት በ14ኛው ክፍለ ዘመን በንጉሥ ዘረ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት ነው።ለረጅም ዓመታት በዘመቻ ችግኝ ተተክሏል፤ እንክብካቤም ተደርጎለታል።ይህ የሆነውም በራሱ በሕዝቡ አማካኝነት እንደነበር ከአረንጓዴ ልማት ጋር በተመለከተ ብዙ ጥናትና ምርምሮችን ያደረጉት ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረእግዚአብሔር ይናገራሉ።
ኢትዮጵያውያን የአካባቢ እንክብካቤን የሚያደርጉት ለዘመናዊው ትውልድ ጭምር የሚያስተላልፉት ልምድ እንዲኖር በማሰብ ነው የሚሉት ዶክተር ተወልደብርሃን፤ መሬቱ እንዳይሸረሸር እርከኖችን ይሠራሉ፤ ዛፎችን ተክለውም ይንከባከባሉ።በዚህም ባሕልና ተፈጥሮን ማጣመር የሚችሉ ሕዝቦች ናቸው።በራሳቸው ተነሳሽነትም ምድሪቱን አለምልመዋታል።መጀመሪያ ከታች ወደላይ በማምጣት ከዚያ ደግሞ ከላይ ወደታች በማውረድ ተግባሩን የከወኑ ድንቅ ሕዝቦች መሆናቸውንም ያነሳሉ።
‹‹ Status, Challenge and Opportunities of environmental Management in Ethiopia›› በሚል በታተመ ጆርናል ላይ በንጉሥ ዘረ ያዕቆብ ዘመን በዘመቻ ከተተከሉና ተጠብቀው ከቆዩ ደኖች ወፍ ዋሻ፣ ጅባት፣ መናገሻ እና የየረር ተራሮች ጥብቅ ደኖች ይጠቀሳሉ።በመንግሥት ደረጃ ችግኞችን አፍልቶ መትከል የተጀመረው ግን በአጼ ልብነ ድንግል ዘመን እንደነበር ይነሳል የሚሉት ተመራማሪው፤ ይህም በ16ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ልብነ ድንግል ከወፍ ዋሻ ዘርና ችግኞችን ወስደው ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በሚገኝ መናገሻ ሱባ የሚባል ሥፍራ የሃበሻ ጽድ የተከሉበት ነው።በመቀጠል አፄ ምኒልክ ባህርዛፍን ከአውስትራሊያ በማስመጣት ተክለዋል። በአገሪቱ ያለውን የማገዶና የቤት መሥሪያ ቁሳቁስ እጥረት ለመቀነስም የባህር ዛፍ ተክልን ከአውስትራሊያ አስመጥተው በመትከልና በማስተከል አፄ ምኒልክ «ዘመናዊ» እፅዋትን ለኢትዮጵያ አስተዋውቀዋል።በወቅቱ የደን መጨፍጨፍን ለመከላከል «ሁሉም በግለሰብ መሬት ላይ ያሉ ዛፎች የመንግሥት ንብረት ናቸው» ሲሉ አውጀው እንደነበር በዚሁ ጆርናል ላይ መጠቀሱን ያብራራሉ።
ደኖች የሕዝብ ሀብት እንደሆኑ በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ እንደነበር ይነግረናል።ከዚያም በኋላም ቢሆን ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ መሪዎች የተለያዩ ስልቶችን እየተጠቀሙ ችግኞችን በዘመቻ ተክለዋል።ለዚህም ምስክር የሚሆኑት በቤተክርስቲያንና መስጊዶች እንደነበሩም ይናገራሉ።
በዘመነ ነገሥታት በተለያዩ ምክንያቶች ነገስታቱ መናገሻቸውን ይለዋውጡ እንደነበር ይታወቃል።ለዚህ ማሳያው ደግሞ አፄ ምኒልክ ሲሆኑ፤ መኖሪያቸውን ሲለዋውጡ አብረው ችግኝ መትከልን እንደዋና ተግባራቸው አድርገው ይጓዙ ነበር።በፍጥነት ማደግ የሚችልና ራሱን በፍጥነት የሚተካውን ባህርዛፍን በአማካሪያቸው አማካኝነት የመረጡትም ለዚህ እንደነበር ታሪክ ይነገራል።
ከምኒልክ ቀጥሎ አፄ ኃይለሥላሴም ቢሆን ችግኝን ለመትከልና ለመንከባከብ ብዙ የለፉ ናቸው።የደን አዋጅን በማውጣት በርካታ ሥራዎች ከውነዋል።ለአብነት ‹‹አጼ ኃይለሥላሴ ችግኝ መትከልን እንደ አንድ የመንግሥት ሥራ አድርገው ወስደውት እንደነበር ይወሳል።በተጨማሪ እርሳቸው ደን መጠበቅና ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ፓርኮች እንዲቋቋሙ ምክንያትም ነበሩ።ለዚህም ማሳያው አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ነው።
ወደ ደርግ ዘመነ መንግሥት ስንገባም ይህ ኢትዮጵያዊ ባህል የአካባቢ ጥበቃን የተመለከቱ ፖሊሲዎች ጭምር ተቀርፀውበት የቀጠለ ነው። ዋነኛ ትኩረታቸው ግን የዱር እንስሳት ጥበቃ ላይ እንደነበር ጥናቶች ያሳያሉ። በተለይ በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 1973/74 (1966 ዓ.ም) በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የተከሰተው ርሃብና ድርቅ፤ አካባቢ ጥበቃ ላይ ጠንክሮ ለመሥራት እንዳነሳሳ ይጠቀሳል። በአጠቃላይ ደን ሥራ ላይ ከፍተኛና የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ዝግጅት ተደርጎ፣ ቦታዎች ተመርጠው፣ ችግኞች ተፈልተው፣ ለማኅበረሰቡ አነስተኛ ድጎማ በማድረግ፤ በተራቆቱ ቦታዎች ችግኞች እንዲተከሉ መደረጉም ይወሳል።
ኢህአዴግ ላይ ስንገባ ደግሞ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ማንሳት ግድ ይለናል።በተለይ ዋናው የትኩረት አቅጣጫ የአየር ንብረት ለውጥ እንደነበር ይታወሳል።ችግኝ መትከልና አካባቢን መንከባከብ እንደ አንድ ትልቅ ሥራ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።ይህ ወቅት የልማትና የአካባቢ ጥበቃ ተቋማት የተመሠረቱበትም ነው። በፖሊሲ ደረጃም ሥነ ምህዳርን፣ አካባቢን፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን በሚመለከት ግብ ተቀምጦለት እንቅስቃሴ ተጀምሮበት ነበር፡፡
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉት ዶክተር ዐቢይ አሕመድም ‘አረንጓዴ አሻራ’ በሚል የተደረገው አገር አቀፍ የችግኝ መትከል ዘመቻ ይህንኑ የሚያጠናክር እንደሆነ ማንም አይክደውም።ዘመቻው በፍላጎት ላይ የተመሠረተ እና በስፋት በርካታ ችግኞች የተተከሉበት መሆኑ ደግሞ ልዩ ያደርገዋል።ይሁን እንጂ እንደቀደመው ጊዜ ባህል አድርጎ ማኅበረሰቡ ችግኞችን መትከል ይገባዋል።ምክንያቱም አሁን ላይ ከከተሞች መስፋፋትና ሥልጣኔ ጋር ተያይዞ ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ ችግር እየታመሰች ነው።ኢትዮጵያም ብትሆን የገፈቱ ቀማሽ እየሆነች መጥታለች።ለዚህ ደግሞ መፍትሄው አንድናአንድ ሲሆን እርሱም ችግኝን መትከል ነው።እናም ቀስቃሽ ሳንሻ ይህንን ማድረግ የውዴታ ግዴታችን ሊሆን ይገባል።
ማኅበረሰቡን ማነሳሳትና ወደ ቀደመው ባህሉ ማሻገር አስፈላጊ ነው።አገርኛ ባህላችን ደግሞ እንዲጎለብት ከዚህ አማራጭ ውጪ ሌላ ሊመጣ የሚችል ነገር አይኖርም።ስለሆነም ሪከርድ በተያዘበት ጊዜ በአንድ ጀንበር የተተከሉት ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደነበሩን ሁሉ አራት ቢሊዮን ችግኝን ተክለን አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ሊሸፍን የሚችል የአገር ሀብት ማምረት እንደምንችል በማመን ወደ ተግባሩ መግባት ይጠበቅብናል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በአንድ ወቅት ባወጣው ዘገባ እንዳስቀመጠው፤ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነስ በመምጣት አሁን ላይ ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት 15 በመቶ ወይም 17 ሚሊዮን ሄክታር ብቻ መሸፈኑን በቅርቡ የወጣው “Mass tree planting Prospects for a green legacy in Ethiopia“ የተሰኘ ሪፖርት ያሳያል።ከዚህ ውስጥ ደግሞ 15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታሩ የተፈጥሮ ደን ነው።የተቀረው በችግኝ ተከላ የተሸፈ እንደሆነም ጥናቱ አመላክቷል።በተጨማሪም አገሪቱን በደን ምንጠራ ባዶ የሆነና ደንን መልሶ ለማልማት ምቹ የሆነ 18 ሚሊዮን ሄክታር ባዶ መሬት እንዳላት ሪፖርቱ ያሳያል።እናም ችግኙ ፀድቆ ደን መሆን ሲችል የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በአንድ በመቶ ሊያድግ እንደሚችል ይገመታልና ያንን ማድረጉ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ድርሻ ይሆናል።
ኢትዮጵያ በአቶ መለስ ዜናዊ ይፋ በተደረገው «ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ» ስትራቴጂን ቀርፃ መንቀሳቀስ ላይ መሆኗ ሲታወቅ የበርካታ አገሮችን ቀልብ ስባ ነበር።በተለይም ከበለፀጉ አገሮች መካከል ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይና አሜሪካ የመሳሰሉ አገሮች ኢትዮጵያ እየተገበረችው ላለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ድጋፋቸውን ከሰጡ መካከል ይገኛሉ።ስለዚህም ከአገራዊ ልምዷ ባሻገር የምትነድፋቸው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂዎች ጭምር ሌሎችን የሚያስቀና እንደነበር መረዳት ይቻላል።
ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ የምታከናውናቸው ሥራዎች የራሷን ልማትና ዕድገት የሚያፋጥኑ፣ ለዓለም ሥጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከልና አደጋዎቹን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅዖ እንደሚኖረውም በእጅጉ ታምኖበታል።ለአየር ንብረት ለውጥ መባባስ ትልቅ ሚና የነበራቸው አገሮች ሳይቀሩ እንኳን አገራችን ለምታከናውነው የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ድጋፋቸውን ለመስጠት የወሰኑት ችግሩ ያስተሳሰራቸውና የጋራ ጥቅም ወደሚያስገኝ መፍትሔ የሚወስዳቸው ሆኖ በማግኘታቸው መሆኑን መገመት አይከብድም።
ኢትዮጵያ የያዘችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ዝቅተኛ የካርበን ልቀት መጠን እንዲኖር የሚያደርግ አብዮት ነው።ስትራቴጂው በአንድ ጎን ልማትና ዕድገቷን የሚያፋጥንና ዘላቂነቱን አስተማማኝ የሚያደርግ አካባቢ እንደሚፈጥር ጥናቶች ይጠቁማሉ።ተፈጥሮን ከመንከባከብና ተጠቃሚ ከመሆን በተጨማሪ ለብክለትና ለውድመት ከሚዳርጉ አደጋዎች ጠብቆ ለማቆየትም ሁነኛ መፍትሔ ያዘለ ሆኗል።
በ2017 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ2025) መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ራዕይ ሰንቃ በመንቀሳቀስ ላይ የምትገኘውን ኢትዮጵያ፣ በተለይ አረንጓዴ ልማት ለሕዝቧ የሕልውና እና የኑሮ መሠረት በመሆኑ፣ እየተሠራ ያለው ሥራ ዓለም ጭምር በሞዴልነት እየወሰደና እየሠራበት እንደሚገኝ የዘርፉ ምሁራንና ጥናቶች እያረጋገጡ ያሉት።
የአገራችን የደን ሀብት ታሪክ በጣም ወደኋላ ብንሔድ የምድሪቱ 120 ሚሊዮን ሄክታር 60 በመቶ በሚሆን ደን ተሸፍኖ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ።ቀደም ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከ1375 እስከ 1404 አገሪቱን ያስተዳደሩት አፄ ዳዊት የደን እንስሳትንና ገደብ የለሽ የአደን ጨዋታን ለመከላከል አገሪቱን ለሰባት የአካባቢ ጥበቃ ጣቢያዎች ጠባቂ ሰው በመመደብ ከፋፍለውት እንደነበር ዜና መዋዕላቸው ይነግረናል።በተመሳሳይም ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብም የጅባትን ደንና የወፍ ዋሻን ውኃ-በል (watershed) የደን ክምችት እንዲጀመር አድርገው ነበር።የወጨጫንና የየረር ጋራዎችን በደን በማልማት እንዲሁም ‹‹የንጉሥ የደን ክልል›› በማድረግ አገሪቱን በደን የማልበስ ተግባር በስፋት እንደፈጸሙ ታሪካቸው በስፋት ያወሳል፡፡
የደን ሀብትን ጠቃሚነትን በእጅጉ የተገነዘቡት ዐፄ ምኒልክም፤ ‹‹የንጉሥ የደን ክልል›› የሚለውን እሳቤ አጽንዖት በመስጠትም በዘመናቸው የመጀመሪያውን የደን ሥርዓት መሥርተው ነበር።ዐጤ ምኒልክ የመጀመሪያውን የደን ሕግ ለማርቀቅም የውጭ አገር ባለሙያዎችን ቀጥረው እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።ይህም ሕግ ደን ሁሉ የመንግሥት ንብረት እንዲሆን ይደነግጋል።
አገሪቱን በደን ለማልማት ካላቸው ቅንአት የተነሣም በፍጥነት የሚያድጉ ዛፎችን ከሌሎች አገር ያስመጡ ነበር።ንጉሡ የደን አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ለማቋቋም ካላቸው ፍላጎት የተነሣ የውጭ አገር ዜጋም ቀጥረው ነበር።ከዚህ በተጨማሪም ሕዝብ የተፈጥሮ የደን ሀብትን እንዲንከባከብ ያበረታቱ ነበር።ንጉሡ የደን አጠባበቅን በተመለከተ ያወጡት ሕግ ደንን አላግባብ የሚጨፈጭፉ ሰዎችን ንብረታቸውን በመውረስና እስከ ሞትም በሚያደርስ የቅጣት ርምጃ የጠነከረም ነበር፡፡
‘የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ’ በማስቀጠል ረገድም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በስፋት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።እንደ አብነትም ዶክተር ዐቢይ በመዲናችን በአዲስ አበባ ያስጀመሯቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች አረንጓዴ ኢኮኖሚን፣ የአካባቢ ጥበቃንና የተፈጥሮ ሀብት መንከባከብን ትኩረት ያደረገ መሆኑን ልብ ይሏል።የተፈጥሮ ሀብትም ሆነ የዕፅዋቶችና የደኖች መመናመን ጉዳይ በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለው ጥፋትና ቀውስ ከፍተኛ መሆኑ ከግምት ውስጥ ያስገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መላው የአገራቸውን ሕዝብ ከጎናቸው በማሰለፍ የአረንጓዴ ልማት ዐርበኛ በማድረግ ረገድ ትልቅ ስኬትን እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡
ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከምሁር እስከ አፈ ነቢብ… ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈው የችግኝ ተከላ ዘንድሮም በስፋት ቀጥሏል።ኢትዮጵያን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ/ልማት ሞዴል አድርጓታልም።የደን ሀብቶቻችን ሊያበረክቱ የሚችሉትን እምቅ ጠቀሜታዎችም ግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለራሱ፣ ለልጆቹና ለመጪው ትውልድ ሲል በዚህ የአረንጓዴ ዘመቻ ላይ በስፋት እንዲሳተፍ በተደጋጋሚ ላስተላለፉት አገራዊ ጥሪ ከሁሉም የማኅበረሰሰብ ዘንድ ተግባራዊ የሆነ ምላሽን እየተቸረው ነው፡፡
አገራችን ካሏት እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችና የመልሚያ ዕድሎች አንዱ የደን ሀብት ሲሆን፤ የደን ሀብቶቻችንን መጠበቅ፣ ማልማት እና በዕቅድ ጥቅም ላይ ማዋል ኢኮኖሚያዊ፣ ሥርዓተ-ምሕዳራዊና ማሕበራዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ።ጃሬድ ዳይመንድ (Collapse – ውድቀት በተሰኘ መጽሐፉ) «የተፈጥሮ ሀብቶቻቸውን በተገቢው መንገድ የማይዙ እና ጥቅም ላይ የማያውሉ ማኅበረሰቦች ላልታሰበ ሥርዐተ-ምሕዳራዊ አጥፍቶ የመጥፋት አደጋ ይጋለጣሉ፤» ይላል።
የደኖች መመናመን፣ የዕፅዋት ዓይነት እና ብዛት መቀነስ፣ የደን ለበስ መሬቶች መራቆት፣ ሚዛን ያልጠበቀ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ለተጠቀሰው አደጋ ምክንያት መሆናቸውን ከምድረ ገጽ የጠፉ ማኅበረሰቦች ታሪክ ያስረዳል።ስለሆነም ከዚህ አደጋ ለመትረፍ ዛፍ መትከል አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሊሆን ይገባዋል፡፡
የብዝሀ ሕይወት ሀብትና ሥርዓተ ምሕዳር በፕላኔታችን የሰው ልጅን ጨምሮ ለሌሎች ሕይወት ላላቸው ነገሮች አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም።ከዚያም ባሻገር የተለያዩ አስቸጋሪ የበሽታ ወረርሽኞችን ከመከላከልና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚደርሱ ጉዳቶችን በመቀነስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አላቸው።እናም ኢትዮጵያውያን አረንጓዴ ውበትና አረንጓዴ ሕይወት ይኖራቸው ዘንድ ችግኝ መትከል፣ ዕፅዋቶችን መንከባከብ፣ ደኖቻችንን ከጭፍጨፋ መከላከል የሁሉም ሰው ኃላፊነት ነው።በዚህ ክረምትም ሁሉም ሰው ችግኝ በመትከልና የተተከሉትንም በመንከባከብ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።ይህ ጊዜ አገር በቀሉን ልምዳችንን በመጠቀም እኛም ከችግራችን የምናላቀቅበት ነውና ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ አረንጓዴ አሻራችንን ለራሳችን፣ ለአገራችን፣ ለትውልድ ማሳረፊያ እናውለው በማለት ለዛሬ የያዝነውን ሀሳብ ቋጨን።ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1/2014