የለውጡ መንግሥት ወደ መሪነት ከመጣ በኋላ በአገሪቱ የሥልጣን መንበር ላይ ቁንጮ የነበረው ሕወሓት ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር የነበረው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ ሄዶ ጦርነት እስከ መክፈት ደርሷል። ቀድሞም ሕወሓት እየሄደበት ያለው መንገድ ትክክል አለመሆኑን ለማሳወቅ እና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማንም እንደማይበጅ ለመጠቆም ለአገር የሚበጀውን በመምረጥ የፌዴራል መንግሥት ተደጋጋሚ የሠላም ጥሪዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል።
ከ11 ጊዜ ያላነሰ የሰላም ጥሪ የተደረገለት ሕወሓት የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎች እና የእናቶችን ጥሪ አሻፈረኝ በማለት በእምቢተኛነቱን ቆይቷል። ከዚያም አለፍ ብሎ በትግራይ የተናጠል ምርጫ ማካሄድን ጨምሮ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ማደፍረሱን ተያያዘው። የየዕለቱን ውጥረት ከማባባስ አልፎም በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ትግራይ ክልል ውስጥ አብሮት ከ20 ዓመታት በላይ በኖረው፣ በማህበራዊ ጉዳይና በበጎ አድራጎት ሥራ ከጎኑ ሆኖ ሲያገለግለው የኖረውን የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ፈፀመ። ድርጊቱ ቅጽበታዊና አስደንጋጭ፤ መንግሥትም በዚያው ልክ ዝግጅት ያላደረገበት ቢሆንም ግን ከሦስት ሳምንታት በላይ ባልቆየ ሕግ የማስከበር እርምጃ ሕወሓትን መቆጣጠር ተችሏል።
የፌዴራል ሠራዊት በሕወሓት የሽብር ቡድን ላይ የበላይነትን ተቀናጅቶ መቀሌን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ ጊዜያዊ አስተዳደር ቢቋቋምም ክልሉ መረጋጋት አልቻለም። የሽምቅ ጥቃት መቀጠሉን ተከትሎ የክልሉ ሕዝብም እንዳይጎዳ በማሰብ ለሰላም ሲል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል አስወጥቶም ነበር።
ነገር ግን መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ የማሰላሰያ ጊዜም እንዲሁን የሰጠውን የሰላም መንገድ ጥሶ ሽብር ቡድኑ በአገሪቱ ሰላም እንዳይሰፍን በየአቅጣጫው ትንኮሳውን ተያያዘው። የትግራይ አዋሳኝ የሆኑት የአፋርና የአማራ አካባቢዎች በመውረር ጦርነቱን አስቀጠለ። በዚህም በሁሉም ቦታ የብዙዎች ሕይወት ተቀጠፈ። በሕወሓት የጥፋት ቡድን ከፍተኛ ቁሳዊ ውድመት ደረሰ። የደሴና የኮምቦልቻ ከተሞችን በመቆጣጠር ከሸኔ ጋር በመተባበር ወደ መሃል አገር ለመግባት በተለይ በአፋር በኩል ቁልፍ ከተማ የሆነችውን ጭፍራን ይዘው አዲስ አበባን ከጂቡቲ ጋር የሚያገናኘውን መንገድ ለመቆጣጠር ቢዋጉም አልተሳካላቸውም። በተቃራኒው የፌዴራል መንግሥቱ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ በመጀመሩ በመጡበት እግራቸው መልሰው ወደ ኋላ ፈረጠጡ። የአፋር እና የአማራ ክልልን መልቀቅ ግዴታ ሆነባቸው። ነገር ግን አሁንም ድረስ የችግሩ ሰንኮፍ አልተነቀለም። የትግራይ ሕዝብም ከስቃይና ረሀብ ተላቆ የሰላም እንቅልፍ አላገኘም።
ይሁን እንጂ ሕወሓት በሌላ በኩል ደግሞ ሸኔን በደንብ በማገዝ እና በማደራጀት የኦሮሚያ ክልልን ማመስ ሥራዬ ብሎ ተያያዘው። በኦሮሚያ ክልሉ የተለያዩ ዞኖች አርሶ አደሮችንና ሌሎች ሰላማዊ ወገኖችን ጭምር መግደል፣ መዝረፍና ማገት እንዲሁም የከፋ ችግር ማድረስ የየዕለት ዜና ሆነ። በክልሉ በሚኖሩ ሕዝቦች አሰቃቂ ግድያና ዘረፋ ሲያካሂድ በአሸባሪው ሸኔ የጥፋት ቡድን በርካታ ዜጎችን መግደል እና ማቁሰልን፤ ወንድ ሴት ሕፃን ሳይል በአሰቃቂ ሁኔታ የዜጎችን ሕይወት ማጥፋት አንዳንዴም የዘር ፍጅት እንዲነሳ በሚቀሰቅስ መልኩ ግድያን መፈፀም ተዘወተረ።
‹‹ኢትዮጵያውያን ወገኖችም የራሳቸውን ችግር ለመፍታት እስከፈቀዱና ለመተባበር እስከቆረጡ ድረስ የሰላም ጉዞው የቱንም ያህል ዋጋ ቢጠይቅ ለስኬት እንደምንበቃ ጥርጥር የለንም። ›› ያለው መንግሥት ለሰላም ሲል ዝምታን ቢመርጥም በተቃራኒው ለጥፋት አላማ የቆመው አካል ፈቃደኛ ባለመሆኑ አሁን ደግሞ በርካታ ንጹሀን ዜጎች በሸኔ የሽብር ቡድን ሕይወታቸው እያለፈ ይገኛል።
መንግሥት ተደጋጋሚ የሠላም ጥሪዎችን ያቀርባል፤ በሰሜን በኩል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም፣ በደቡብም ሆነ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በጋምቤላም ሆነ በሌላ አካባቢ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ሰላም ይሻላል በሚል በሆደ ሰፊነት ነገሮችን በትዕግስት ለማለፍ ሞክሯል። ሆኖም ለሰላም ብቻ ቅድሚያ መሰጠቱ ወንጀለኞች እና ክፉ ድርጊት ፈፃሚዎች ከሰላም ይልቅ ጥፋት ብቻ የሚታያቸው አሸባሪዎች የልብ ልብ እየተሰማቸው የበለጠ ወንጀል እየፈፀሙና ሕዝብ እየተጎዳ፤ የሰዎች ሕይወት እየጠፋ መሆኑን በመጥቀስ መንግሥት እርምጃዎች ላይ መጠንከር አለበት በማለት የሚሰጠውን አስተያየት በሚመለከት እና በዚህ ቀውስ ላይ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ከታከለ ምን ያህል ጥፋት ሊያስከትሉ ይችላል? እንዲሁም በዋናነት መፍትሔው ምን መሆን አለበት ስንል ከፖለቲካ ፓርቲዎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር መብራቱ ዓለሙ ጋር የነበረንን ቆይታ እንሆ ብለናል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም የሰጠውን ትኩረት አሁንም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እያደረገ ያለውን የሰላም ሂደት እንዴት አገኙት?
ዶክተር መብራቱ፡– እንግዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ላይ እየሠራሁ ነው ይላል። በደንብ ትኩረት መስጠቱን ለማሳወቅ የሰላም ሚኒስቴር አቋቁሟል። ነገር ግን መንግሥት ሠርቻለሁ እያለ ባለው ልክ ሰላም መጥቷል ወይ ? የሚል ጥያቄ ከተነሳ መልሱን የትኛውም ኢትዮጵያዊ ሊመልሰው ይችላል። ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ ከሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ይደረጋል። ከልሒቃን ጋርም ተደጋጋሚ ውይይቶች እየተደረጉ ናቸው። ነገር ግን ተጨባጭ ሰላም ማምጣት ላይ ግን ብዙ የተሔደበት አይመስልም። በዚህ የተነሳ አሁንም ድረስ የዜጎች ሞት እና መፈናቀል መቆም አልቻለም።
አዲስ ዘመን፡- ትክክል ነዎት! አሁንም የዜጎች ሞት እና መፈና ቀል አላቆመም። ነገር ግን መንግሥት ተደጋጋሚ የሠላም ጥሪዎችን ከማቅረብ አልተቆጠበም። ለምሳሌ ለሕወሓት የሽብር ቡድን ከ10 ጊዜ በላይ የሃይማኖት አባቶችን፣ ሽማግሌዎችን፣ ታዋቂ ሰዎችን እና እናቶችን… በመላክ ከጦርነት ይልቅ ሁሉም ነገር በሠላም እንዲያልቅ ተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቧል። አልፎ ተርፎ ለሰላም ባለው ፍላጎት የታሰሩ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮችን ጭምር ፈትቷል። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም በተደጋጋሚ ሰዎች ከሚያልቁ በሠላም እንጨርስ በማለት ተደጋጋሚ ዕድል ከፍቷል። ከእዛኛው ወገን ያለው ምላሽ ግን ሁሉም እንደሚያየውና እንደሚሰማው ነው። አሁንስ ምን ሊሆን ይችላል ብለው ይገምታሉ?
ዶክተር መብራቱ፡– እውነት ነው። የአንድ ወገን ሰላም መፈለግ ብቻ አዋጪ አይሆንም። የሌላኛውን ፍላጎት በደንብ መረዳት እና ማየት ተገቢ ነው። ሁለተኛ የሰሜኑ ጦርነትን በተመለከተ መንግሥት የወሰደው እርምጃ ትክክል ነው። ጥቃት ሲፈፀም ቢያንስ የአፀፋ መልስ መስጠት የአንድ መንግሥት ግዴታ ነው። ነገር ግን ከዛ ጋር ተያይዞ ማህበረሰቡ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ቶሎ መፍታት ተገቢ ነው የሚል እምነት አለኝ።
በመንግሥታት ወይንም በፖለቲካ ልሒቃን መካከል በሚፈጠር ግጭት ብዙ ሕዝብ እና ማህበረሰብ መጎዳት የለበትም። አሁን እንደሚታወቀው የትግራይ ሕዝብ መብራት፣ ስልክም ሆነ ውሃ ምንም የለውም። ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ እንኳ የሚታወቅ ነገር የለም። ሕወሓት በፈጠረው ችግር የትግራይ ሕዝብ መበደልም ሆነ መጎዳት የለበትም። የትኛውም ማህበረሰብ ሰላሙ ሊከበርለት እና ሊጠበቅለት ይገባል። ከዚያ አንፃር አሁንም ብዙ ምስቅልቅል ያለባቸው ነገሮች ከፊታችን ያሉ ይመስለኛል። ስለዚህ እንደተባለው በትክክል ሰላም ማስፈን የሚቻለው በአንድ ወገን ብቻ አይደለም። በሁለቱም ወገን የሰላም ፍላጎት መምጣት አለበት። ይህ ደግሞ ሊመጣ የሚችለው በድርድር፣ በሽምግልና ወይም ወደፊት ይመጣል ተብሎ በሚታሰበው አገራዊ ምክክር በመግባባት ችግሮች ይፈታሉ፤ ወይም ይቀረፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡- መንግሥት በደቡብም ሆነ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላም ሆነ በሌላው አካባቢ በሚከሰቱ የሰላም መደፍረሶች የሚወስደው እርምጃ በቂ ነው ይላሉ? በተለይ የሰዎችን በሕይወት የመኖር መብት ከማስጠበቅ አንጻር እንዴት ያዩታል?
ዶክተር መብራቱ፡- መንግሥት የመጀመሪያ ተልዕኮ መሆን ያለበት የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ዜጎችን ማረጋጋት እና የመኖር ዋስትናን ማረጋገጥ ነው። በዚህ ረገድ ሥራ አልተሠራም ማለት አይቻልም። ነገር ግን የምናየው ደም መፋሰስ እና የሰዎች እልቂት አሁንም ድረስ አላቆመም። ይሔ ደግሞ የሚያሳየን መንግሥት መሥራት ያለበትን ያክል ወርዶ አለመሥራቱን ነው። ለምሳሌ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል አካባቢ ጅምላ ጭፍጨፋዎች እና የሰዎች ሞት እንዲያውም ጅምላ ቀብር ሁሉ ነበር። በክልሉ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ነበር። የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ሦስት ዓመት ቢሞላውም አሁንም የዜጎች ሞት መቆም አልቻለም። መፈናቀልም አልቆመም።
መሻሻሎች ቢኖሩም ችግሩ አሁንም አልተቀረፈም። የፀጥታ ኃይሎችም እየተጎዱ እና እየሞቱ ነው። ስለዚህ በፍጥነት ወደ አገራዊ ምክክር ተገብቶ ተፋላሚ ኃይሎችም ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መጥተው ሰላም እና እርቅ ይፈፀማል የሚል እምነት ነበረኝ። ነገር ግን ብሔራዊ ምክክሩም ወደ ኋላ እየተጎተተ ነው። ስለዚህ መንግሥት እየወሰደ ያለው እርምጃ ችግር ሲከሰት ችግሩ እንዴት
ላስቁመው እያለ ነው። አስቀድሞ ለመከላከል ብዙ ትኩረት እየተሰጠ አይደለም። ችግሩ ሲከሰት ሔዶ ማዳፈን እና ማፈን፤ እዚያ አካባቢ ያለውን መረጃ መደበቅ ትክክል አይደለም። ይህ ከአሁኑ ማስተካከያ ካልተደረገለት የእዚህች አገር ዕጣ ፈንታ ወደ ቀውስ ያመራል። ስለዚህ መንግሥት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ባለድርሻ አካላት ማለትም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኃን እና በአጠቃላይ ሁሉም ተረባርቦ ካልሠራ የወደፊት እንቅስቃሴያችን ውጤት ካለማምጣት ባሻገር ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ትንሽ የሚያሰጋ ይመስለኛል።
አዲስ ዘመን፡- ቀድሞ መከላከልን በተመለከተ ሁለት ሃሳቦች ይሰጣሉ። አንደኛው መንግሥት ከእርምጃ ይልቅ ሰላም ላይ ትኩረት ማድረጉ ችግሩ የበለጠ እንዳይባባስ ረድቷል የሚሉ ቢኖሩም በተቃራኒው ለሰላም ቅድሚያ መስጠት በሚል ሰበብ መንግሥት ፈጠን ብሎ እርምጃ አለመውሰዱ እንዲያውም ድርጊቱን ፈፃሚዎች የልብ ልብ እየተሰማቸው የበለጠ ወንጀል እንዲፈፅሙ ሕዝብ እንዲጎዳ እና የሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ እያደረገ ነው የሚሉ ወገኖችም አሉ። እርሶ ቀድሞ መከላከል ሲሉ ምን ማለትዎ ነው? በደንብ ያብራሩልኝ።
ዶክተር መብራቱ፡– ቀድሞ መከላከል ማለት የትኛዎቹም ታጣቂ ኃይሎች ከመንግሥት ጋር ጥላቻ ያላቸው የተደራጁ ኃይሎች ሊሆኑ ይችላሉ ወይንም የውጭ ኃይሎችም ሊሆኑ ይችላሉ እነዚህ አንድ ማህበረሰብ ውስጥ ገብተው የሆነ ጉዳት እና ጥቃት እስኪፈፅሙ ድረስ የእኛ የፀጥታ መዋቅር ምን ላይ ነው? የክልሉ ፖሊስ አለ፤ ፌዴራል ፖሊስ አለ፤ ልዩ ኃይል አለ፤ መከላከያ አለ፤ ኮማንዶ አለ። ይህ ሁሉ ባለበት አገር አንድ ሰፈር ተገብቶ ብዙ ሰዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል። ነገር ግን ይሔ አሰቃቂ ተግባር ተከሰተ ተብሎ ዜና ከመሠራቱ በፊት የደህንነት ተቋሙ ምን ይሠራል የሚል ጥያቄ ማንሳት ይቻላል። ሁለተኛም ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ በደንብ ተከናውኗል? ብዬ አላምንም የተለያዩ የማህበረሰቡ ጥያቄዎች አሉ።
ከሕዝቡ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ይኖራሉ። መንግሥት እነዚህን ጥያቄዎች እስከታች ድረስ ወርዶ መመለስ ካልቻለ ማህበረሰቡ የሽፍታ መደበቂያ ዋሻ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ማህበረሰቡ የሚፈልገው ለውጥ መጥቶለታል? የተባለው ለውጥስ በእርግጥ ማህበረሰቡ ላይ ለውጥ አሳይቷል ወይ? በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው በትክክል በንቃት ኅብረተሰቡ እየተሳተፈ ነው? ወይንስ ምንድን ነው? የወጣቱ ፍላጎትስ እንዴት ይታያል? የወጣቱ ቁጥር እየጨመረ እና ሥራ አጥ እየተበራከተ ነው። በሌላ በኩል የኑሮ ውድነት አለ። ይሄ በሙሉ ማህበረሰቡን እያንገሸገሸው ነው። እነዚህ ሁኔታዎች በሙሉ ችግሮችን ሊያባብሱ ይችላሉ። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ ነገሮች አስቦ በማስተዋል ምንድን ነው? ብሎ ተቀምጦ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ሊያግዙን ይችላሉ? ሲቪክ ማህበረሰቡ ምን ሊያግዘን ይችላል? ዓለም አቀፍ ተቋማት ምን ሊያግዙን ይችላሉ? ብሎ አቅዶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል።
አሁን ግን ከታች ሲነድ እሳቱን የማዳፈን እና የማጥፋት እንቅስቃሴዎች እየታዩ ናቸው። ስለዚህ መንግሥት ይህንን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት አለበት። እኛም የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥትም ላይ ጫና ፈጥረን፤ ማህበረሰቡ ንቁ እንዲሆን ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ ብንሠራ ምናልባት የችግሩ ስፋት እና ጥልቀት እየቀነሰ ይሔዳል የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- በጋምቤላም ሆነ በኦሮሚያ ወለጋ ላይም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች እየታየ እና እየተፈፀመ ያለው ድርጊት ብዙ ኢትዮጵያውያንን ስጋት ውስጥ መጨመሩ አይታበልም። በዚህ ላይ ሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግር ከተባባሰ እና ከቀጠለ አደጋው እስከምን ደረጃ ሊደርስ ይችላል ይላሉ?
ዶክተር መብራቱ፡– እኔን የሚያስጨንቀኝ የጥላቻ ንግግሩ አይደለም። የጥላቻ ንግግሩን ያመጣው ምንድን ነው? የሚለው ነው። የጥላቻ ንግግርን ያመጣው የጥላቻ ፖለቲካ ነው። ሌላው በሕዝብ እና በመንግሥት መካከል እምነት ከሌለ የጥላቻ ንግግሮች እጅግ በጣም እየሰፉ ይሔዳሉ። የጥላቻ ንግግር እና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ የወጡ ሕጎች እንደሚታዩት ገና በደንብ ተግባራዊ ሆነው እርምጃ እየተወሰደ አይደለም። ስለዚህ የጥላቻ ንግግሮች ለምን ይፈጠራሉ? የሚፈጥራቸውስ ማን ነው? ኅብረተሰቡስ ለምን ይቀበላቸዋል? እነዚህ የሀሰት መረጃዎች እና የጥላቻ ንግግሮችስ ለምን ይሰራጫሉ የሚለው ላይ በደንብ መታሰብ አለበት። ይህ ደግሞ የመጣው ትክክለኛ መረጃ ለኅብረተሰቡ መገናኛ ብዙኃኑ እያቀረቡ ስላልሆነ ነው።
መንግሥት ለምን ይፈራል? ምዕራብ ወለጋ እና ጋምቤላ ላይ የተፈፀመው ነገር መገናኛ ብዙኃኑ እዚያው ቦታው ላይ ሆነው ያለውን እውነታ ቢገልፁ ችግሩ ምንድን ነው? ሕዝቡ የሚፈልገው እውነታውን ነው። ተቸገርኩ እርዱኝ ቢባል የእኛ ሕዝብ ይረዳል፤ ያግዛል። የእኛ ሕዝብ ለአገሩ እና ለሃቅ ሟች ነው። ከዚያ አንፃር እኔ አውቅልሃለሁ ፖለቲካን ማስቆም ካልቻልን ፊታችን ላይ ብዙ ተስፋ አይታየኝም። ስለዚህ የጥላቻ ንግግር እንዳይበራከት መንግሥት የጥላቻ ፖለቲካን በማጥፋት እና መረጃዎች በትክክል ሕዝቡ ጋር በማድረስ በኩል መሥራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- የተጠያቂነት ሁኔታን በሚመለከት ከላይ የደህንነት መዋቅሩ ምን ይሠራል? ብለው ነበር። በአጠቃላይ በአካባቢው የነበረው የፀጥታ ኃይልም ሆነ አጠቃላይ አደረጃጀቱ ተጠያቂ መሆን አለበት። ያለበለዚያ የጥፋት ድርጊቱ ይቀጥላል የሚሉ ወገኖች አሉ። እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር መብራቱ፡– ማንኛውም ሰው ከሕግ በታች ነው። ሁላችንንም የሚገዛን አገራዊ ሕግ አለ። ስለዚህ በፈፀሙት ልክ ተጠያቂ መሆን አለባቸው። ተጠያቂ የሚሆን አካል እያየን አይደለም። ተጠያቂዎች እየመጡም አይደለም። ስለዚህ ተጠያቂነትን ማስፈን ላይ መንግሥት በጣም ሊገፋበት ይገባል። እኛም እየታገልን ያለነው የአካባቢያቸውን ፀጥታ ፣ ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ ያልቻሉትን መንግሥት ራሱ ተጠያቂ ያድርጋቸው እያልን ነው።
መንግሥት ሕዝብን ሊያወያይ ይገባል። ሕዝብ ተጠያቂውን ያውቃል። ማን ተጠያቂ ነው? ቢባል ሕዝቡ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጠዋል። እንደአገር እንደመንግሥት ተጠያቂነትን ለማስፈን ምን እንደቸገረን እኔም ብዙ አላወቅኩም። ምክንያቱም ብዙ ሀብት እና የተማረ የሰው ኃይል አለን። ጥሩ ጅማሮ ላይ ነበርን። አሁን ተመልሰን ለምን ወደ ቀውስ እንደገባን አላወቅንም። እርሱ በደንብ መታየት አለበት ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥም ጥፋቱ ቆመ ሲባል መልሶ ይቀጥላል። እስኪ በዋናነት መፍትሔ ይሆናል የሚሉት ምንድን ነው?
ዶክተር መብራቱ፡- አሁን ላለው የሰላም መደፍረስ መፍትሔው አገራዊ ምክክሩን ቶሎ መጀመር ነው። ጊዜ ሳይባክን አገራዊ ምክክሩን ለማካሔድ በአስቸኳይ ወደ ሥራ መገባት አለበት። ተፋላሚ ኃይሎች በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመጡ መደረግ አለበት። ምንም ዓይነት ነገር ተደባብቀን እና ተሸፋፍነን ሳይሆን የየራሳችንን ፍላጎት የሆነ ቦታ ቁጭ አድርገን ይህችን አገር እንዴት ወደ ፊት እናሻግራት ብለን መነጋገር አለብን። በብዙ ነገሮች ላይ ልዩነቶች አሉ። በታሪክ ትርክት ላይ፤ በባንዲራ ላይ፣ በአገር ግንባታ ላይ፣ በፌዴራሊዝሙ ላይ ፣ በሕገመንግሥቱ ላይ በአብዛኛው መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ልዩነቶች አሉ። እነዚህን ልዩነቶች ማጥበብ እና ወደ አንድነት ማምጣት የምንችለው በአስቸኳይ ወደ ብሔራዊ ምክክሩ ስንገባ ነው። ለእኔ ዋነኛ መፍትሔ የምለው ይሔንን ነው።
ሌላው መንግሥት ከተፋላሚ ኃይሎች ጋር መነጋገር፣ መደራደር እና ወደ ሽምግልና መግባቱ ትክክል ነው። እንዲያውም ቶሎ መጀመር አለበት። የታጠቁ ኃይሎችም ውጊያቸውን አቁመው በጠረጴዛ ዙሪያ ጥያቄያቸውን ማቅረብ አለባቸው። በተከታዮቻቸውም በኩል ቢሆን ጥያቄያቸውን ማቅረብ አለባቸው። ይህ ከሆነ መፍትሔ ሊመጣ ይችላል። በዚህ አሁን ያለውን ቀውስ መቀነስ ወይም አስቀድመን መከላከል እንችላለን። ለፖለቲካ ለውጡም ሽግግር ይሆናል። ዋናው መፍትሔ ብሔራዊ ምክክር ነው። ሽምግልናው እንደ ግብአት ሊሆን ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ከላይ እርሶ እንደገለፁት በፍጥነት አገራዊ ምክክሩ ካልተጀመረ፤ ተጠያቂነት ካልሰፈነ እና አሁን የሚታየው በዚሁ ከቀጠለ መጨረሻችን ምን ይሆናል?
ዶክተር መብራቱ፡– ሥርዓት አልበኝነት ይነግሳል። የብሔር ግጭት ውስጥ ልንገባ እንችላለን። በኋላ ወደማያባራ እልቂት እናመራለን። ሩዋንዳም ቢሆን የተጀመረው በዚሁ መልኩ፤ ቀስ በቀስ በጥላቻ ንግግር ነው። ስለዚህ ወደማያባራ ችግር ከማምራታችን በፊት ከወዲሁ መፍትሔ ማበጀት የተሻለ ነው። ያለበለዚያ ሕዝቡ በብሔር ተከፋፍሎ ወደ ግጭት ያመራል። በዚህ ጊዜ ደግሞ አገር ቀውስ ውስጥ ትገባለች። ማንም የጎበዝ አለቃ እየተነሳ ዘራፊ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ከምንገባ ከአሁኑ አካሔዳችንን ማስተካከል አለብን ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ዶክተር መብራቱ፡- እኔም ስለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2014