ለረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት አገልግለዋል። ከመምህርነታቸው ባሻገርም በአፍሪካ ቀንድ፣ በሶማሊያ ጉዳዮች ፣በኢትዮጵያ ረሀብና የአስተዳደር ጉዳዮች እንዲሁም በቅርብ ግዜ በፃፏቸው ጽሑፎችና በግጥማቸው ይታወቃሉ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤም መሥራች ናቸው። ከመሥራችነት በዘለለም የሰብዓዊ መብት ታጋይ ነበሩ።
የበርካታ መጽሐፍ ደራሲና ተመራማሪም ናቸው። በፖለቲካው ጎራም ንቁ ተሳታፊ ነበሩ። በጠንካራ አመክኗዊ ትችታቸውም ይታወቃሉ። ያመኑበትን ከመናገርም ወደኋላ ብለው አያውቁም። በራሳቸው አቋም መጽናት ሁነኛ መገለጫቸው ነው። ሁሌም ሙግታቸው ለደሃው፣ ሠራተኛውና አርሶ አደሩ ማኅበረሰብ ነው-። መምህር፣የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ፖለቲከኛው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የተወለዱት በ1922 ዓ.ም አዲስ አበባ ነው። እድገታቸውም እዚሁ አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ አካባቢ ነው። አዲስ አበባ ሊወለዱ የቻሉትም ከሸዋና የጁ የመጡት ወላጆቻቸው ኑሯቸውን በዚች ከተማ በማድረጋቸው ነው። እርሳቸው የአምስት ዓመት ሕፃን ሳሉ ታዲያ ፋሺስት ጣልያን ኢትዮጵያን ወሮ ነበር።
በግዜው ፕሮፌሰር መስፍን አለቃ ታምራት የሚባሉና ልጆችን ሰብስበው ፊደል በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤት ወላጆቻቸው ሊያስገቧቸው ቢሞክሩም ለትምህርት ፍላጎት ስላልነበራቸው ትምህርት እንዲከታተሉ የተደረጉት በግድ ነበር። በዚህ ላይ ደግሞ ኃይለኛና ጨዋታ ብቻ ፈላጊ የነበሩ በመሆናቸው ለትምህርት ብዙም ትኩረት አልሰጡም።
ሆኖም በሂደት ፕሮፌሰር መስፍን ትምህርቱን እየወደዱት ሲመጡና ከክፍል አለቃዎች ውስጥ አንዱ ሲሆኑ ኃላፊነት ስለተሰማቸው ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል ጀመሩ። ዳዊታቸውንም እዛው ደገሙ። የቤተ ክህነት ትምህርታቸውን በመቀጠል ከትምህርት ቤት ጓደኛቸው ጋር አብረው ሆነው ውዳሴ ማሪያም፤ ዜማ፣ ቅዳሴ፣ ድጓና ፆመ ድጓ ተምረዋል። ከእንጦጦ ቁስቋም ቤተክርስቲያንም ድቁና ተቀብለዋል።
ከጣልያን ወረራ በኋላ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ዳግም ሲከፈት ፕሮፌሰር መስፍን ዘመናዊ የቀለም ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደዚህ ትምህርት ቤት ገቡ። ገና እንደገቡ ትምህርቱ በብርቱ ፈትኗቸው የነበረ ቢሆንም በሂደት ግን ጠንክረው በማጥናታቸውና ለትምህርቱ ትኩረት ሰጥተው በመከታተላቸው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አምስት ዓመት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ችለዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት በንጉሡ እጅ ሹራብና ብርቱካን ተሰጥቷቸው ካደጉት ተማሪዎችም አንዱ ነበሩ። በአንድ ወቅት በራሳቸው አንደበት እንደተናገሩት ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተማሪ ሳሉ በትምህርት ቤት ውስጥ ለተማሪዎች የሚሰጠው የምግብና ሌሎችም አገልግሎት በቂ አይደሉም በሚል ተማሪዎችን በማነሳሳትና ትምህርት ቤቱ የካቶሊክ እንጂ የኦርቶዶክስ አይደለም እንዴውም ‹‹አፄ ኃይለሥላሴ ካቶሊክ ናቸው›› በሚል ደብዳቤ በመፃፍቸው ከንጉሱ ከባድ ግሳፄ ደርሶባቸዋል። በዚህም እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም በጉዳዩ ውስጥ የነበሩ ተማሪዎች የቀረውን ትምህርታቸውን ወደ ጄነራል ዊንጌትና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተበታትነው እንዲማሩ ተደርጓል።
እርሳቸውም ጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ገብተው ለሶስት ወራት ከቆዩ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት መልቀቂያ ፈተናቸውን ወስደዋል። በተፈሪ መኮንን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቆይታቸውም በኢትዮጵያ ቁልፍ ቦታዎች ላይ የሠሩና በፖለቲካም ተሳትፎ ከነበራቸው ታዋቂ ሰዎች ጋር የመማር እድል ገጥሟቸዋል። ከነዚህ ውስጥም ዶክተር አክሊሉ ሃብቴን፣ ኮለኔል ተሰማ አባደራሽን፣ አቶ አባተ የኔውን፣ ኢንጂነር አባተ መንክርንና ሌሎችንም ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።
በልጅነታቸው ቁጡና ተደባዳቢ የነበሩት ፕሮፌሰር መስፍን የቡጢ ስፖርትን በትምህርት ቤት ደረጃ ተወዳድረዋል። ነስር አስቸገራቸው እንጂ በግዜው ጥሩ ቡጢኛ መሆናቸውንም አስመስክረዋል።
የብሔራዊ ፈተና መልቀቂያ ወስደውም ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ። ሆኖም ነስርና ራስ ምታት ስላስቸገራቸው በዩኒቨርሲቲው ሊቆዩ የቻሉት ለስምንት ወራት ያህል ብቻ ነበር። በዚህም ትምህርታቸውን አቋርጠው በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት የአራተኛ ክፍል አማርኛና እንግሊዘኛ መምህር ሆኑ። በራሳቸው ተነሳሽነትም ትምህርት ቤቱን በርዕሰ መምህርነት አገልግለዋል።
በመቀጠል ፕሮፌሰር መስፍን ነፃ የትምህርት እድል በማግኘታቸው የመምህርነት ሥራቸውን አቋርጠው ወደሕንድ በማቅናት ከፑንጃብ ዩኒቨርሲቲ በአቢይ የፍልስፍናና ንዑስ የጂኦግራፊ ትምህርት ለሦስት ዓመታት ተከታትለው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተው ወደሀገራቸው ተመልሰዋል። ወደሀገራቸው ከተመለሱም በኋላ የጂኦግራፊና ካርታ አነሳስ ኢንስቲትዩት በመግባት በተባባሪ ዳይሬክተርነት ለጥቂት ወራቶች አገልግለዋል።
ከዛም ወደ አሜሪካ በማቅናት ከርላርክ ዩኒቨርስቲ ገብተው ለሁለት ዓመት የጂኦግራፊ ትምህርት ተከታትለው የሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። በውጪ ሀገር በተለይ ደግሞ በሕንድ ለትምህርት በነበራቸው ቆይታ ‹‹ከመደበኛው ትምህርት በዘለለ ያገኘሁት ትልቁ ትምህርት ግልፅነት ነው›› ሲሉ ሕይወታቸው ከማለፉ በፊት ለኢሳት በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል።
በአሜሪካን ሀገር በነበሩበት ወቅትም ሀበሻዎች በሀገራቸውና ከሀገራቸው ውጪ በነጮች መነፅር እንዴት እንደሚታዩ በሚገባ ለመረዳት እንደቻሉና በተለይ ነጮች በጥቁሮች ላይ የሚያደርሱት የቀለም ልዩነት ሀበሾች ስለማያውቁት ልዩነቱ እንደማይሰማቸው በዚሁ ቃለ ምልልስ ገልፀዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪም ወደሀገራቸው ከተመለሱም በኋላ /vulnerability to famine/ በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፍ ከዚሁ አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ክላርክ ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በጂኦግራፊ መምህርነት ለረጅም ዓመታት አገልግለዋል።
ከመምህርነት ሥራቸው በተጓዳኝ ፕሮፌሰር መስፍን በፖለቲካው ውስጥ የጎላ ተሳትፎ አድርገዋል። በግዜው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ሲካሄድ ከተማሪዎች ጋር በብዙ መልኩ የቅርብ ግንኙነትም ነበራቸው። በተለይ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት በዩኒቨርስቲ ውስጥ ይነሱ የነበሩ የተማሪዎች ለውጥ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን በግልፅ አሳይተዋል።
ተማሪዎች ንጉሡን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሂዱም አብረው ተሳትፈዋል። በተለይ ደግሞ ‹‹መሬት ላራሹ›› በሚል በ1966 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ከተማሪዎች ጎን ቆመዋል፤ ድጋፋቸውንም አሳይተዋል። ወጣት ሰልፈኞችንም በአድማ በታኝ ፖሊሶች ሊደርስባቸው ከሚችል አደጋ ታድገዋል።
አብዮቱ ሊፈነዳ አካባቢም ፕሮፌሰር መስፍን በ1965 ዓ.ም የጊምቢ የአውራጃ አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመው የነበረ ቢሆኑም ሹመቱን ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ለእስር ተዳርገዋል። ከእስር ከተፈቱም በኋላ ለአውራጃ አስተዳዳሪነት ለመሰልጠን ሃዋሳ አንድ ወር ቆይተዋል። ከዛም በተመደቡበት የጊምቢ አውራጃ በመሄድ የሕክምና ተቋም እንዲሟላ ውሃም እንዲገባ በማድረግና የአስራ አንዱንም የአውራጃው ወረዳዎች ሕዝቦች በማወያየት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚገባ ተወጥተዋል።
አብዮቱ ከፈነዳ በኋላም በዘመነ ደርግ ቀደም ሲል በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት የመርማሪ ኮሚሲዮን ሲቋቋም ዋነኛ ተዋናይ ሆነው ለሁለት ዓመታት በሊቀመንበርነት ሠርተዋል። ሆኖም ስልሳዎቹ ጄኔራሎች በደርግ ሲረሸኑ ከኮሚሲዮኑ ሊቀመንበርነትና አባልነት የመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ።
በመጨረሻም ኮሌኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ሊቀመንበርነቱ ይቅርና በአባልነት ይቀጥሉ ስላሏቸው አባል ሆነው ቀጥለዋል። በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝለትም ከሌሎች ጋር በመሆኑ ብርቱ ጥረት አድርገዋል። በኋላም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት እያገለገሉ ጥናትና ምርምሮችንም ሲያካሂዱ ቆይተው በጡረታ ተገልለዋል።
ከደርግ ውድቀት በኋላም በዘመነ ኢሕአዴግ የሽግግር መንግሥት ሊመሠረት ሲል በለንደን ኮንፍረንስ ከተሳተፉ ምሑራን ውስጥ ፕሮፌሰር መስፍን ተጠቃሽ ናቸው። ኢሕአዴግ ሀገሪቷን ሲቆጣጠርም ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤን አቋቁመዋል።
በኢሕአዴግ ዘመን ሳንሱር በመነሳቱና የመፃፍ እድል በመፈጠሩ ፕሮፌሰሩ በተለያዩ መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ ሃሳባቸውን በጽሑፍ መግለፅ ችለዋል። በ1997ቱ ምርጫም በቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ውስጥ ገብተው ትልቅ ፖለቲካዊ አስተዋፅኦ አድርገዋል። ከዚሁ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው ጋር በተያያዘም ሁለት ግዜ ለእስር ተዳርገዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን ከአፄ ኃይለሥላሴ፣ ከኮለኔል መንግስቱ ኃይለማርያምና ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ማለትም በስልጣን ከተፈራረቁትና ወንበር ከተነጣጠቁት መሪዎች ጋር የመገናኘትና የመወያየት እድልም ገጥሟቸዋል፤ ሦስቱንም ባለስልጣናት በማነፃፀር ተመልክተዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ከምሑርነትና ከሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው ባሻገር ላለፉት በርካታ ዓመታት በኢትዮጵያ በተከሰቱ ጉልህ ክስተቶች የአይን ምስክር ሲሆኑ፤በየማኅበራዊ ጉዳዮችም ቀንደኛ ተዋናይ ነበሩ።
በጤና ችግር ውስጥም ሆነው በቆዩባቸው ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ሲከታተሉ ቆይተዋል። በአንድ ወቅትም የሀገሪቱን ወቅታዊ ፖለቲካ አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል። ‹‹ ይሄ በየቤቱ ቁጭ ብሎ ማማቱንና መተማማቱን ትቶ ጉልበቱን እያስተሳሰረና እያስተባበረ በጎሰኛነት ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት እየተባበረ እነሱን ይዞ መውጣት አለበት፤ እነሱን ማጠናከር አለበት። የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁልግዜ ለጉልበተኛ የሚዳርገው ይህ ነው። እልል ብሎ ቤቱ ይገባል። መግባት የለበትም። ቆሞ እነዚህን ሰዎች መደገፍና ማጠናከር አለበት››
ስለሀገራቸው ብዙ የሠሩት በብዙም የተጉት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ስለአበርክቷቸው ከበርካታ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እውቅናና ሽልማት ጎርፎላቸዋል። ብዘዎችም ስለርሳቸው ሲመሰክሩ ዘጠና ዓመታትን በዘለቀው የሕይወት ጉዟቸው ስለ ሀገርና ሕዝብ የሚችሉትን አድርገዋል ይላሉ። ይህ ግን ለርሳቸው የሚያረካ አልነበረም። ምነው ለሀገሬ ከዚህም በላይ በሠራሁ የሚሉ ሰው ነበሩ።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ለእርሳቸው በተዘጋጀ አንድ የእውቅና መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ‹‹አንዳንድ ግዜ ሰዎች ይህን ሠራህ ይህን አደረክ ብለው ሲያመሰግኑኝ ይጨንቀኛል። ግራ ይገባኛል። ከደሞዜ ውጪ ብሠራ፤ ለሰዎች ብዬ ብራብ ፤ለሰዎች ብዬ ብጠማ፤ ለሰዎች ብዬ ብታረዝ ምን ያደርጉኝ ነበር? ምን ያህል ያመሰግኑኝ ነበር? እያልኩ አስባለሁ›› ብለዋል።
ይህችን ዓለም በሞት ተሰናብተው ከመሄዳቸው በፊት ያሳተሙትን ዛሬን አንድትናንትን ጨምሮ አደጋ ያንዣበበት የአፍሪካ ቀንድ፣የክህደት ቁልቁለት፣ መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፣ አዳፍኔ፣ ፍርሃትና መክሸፍ፣ እንዘጭ እምቦጭ፣ የኢትዮጵያ ጉዞ፣ አገቱኒና ሌሎችም ከብዙ በጥቂቱ ለሕትመት የበቋቸው ሥራዎቻቸው ናቸው።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ለሀገራቸው በርካታ ሥራዎችን አበርክተው በ2013 ዓ.ም በተወለዱ በዘጠና ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሥራቸው ግን ዘመናትን ይሻገራል።
እውቀታቸውንና ልምዳቸውን ሳይሰስቱ በመጽሐፍት፣ በመጽሔቶችና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን ቀርበው ለትውልድ ሲያስተላልፉ የኖሩት ፕሮፌሰር መስፍን፤ የሁልግዜ ትኩረታቸው የነገዋ ኢትዮጵያ ጉዳይ ነው። በተለይ የወጣቱ ትውልድ ጉዳይ ሁሌም እንደሚያሳስባቸውና ድፍረቱን አደንቀዋለው የሚሉት ይህ ወጣት በእውቀት የታነፀና ሚዛናዊ እንዲሆን ሲመክሩ ኖረዋል።
ይችን ምድር ተሰናብተው ከመሄዳቸው በፊት ወጣቱን አስመልክተው ‹‹ ስድ አትሁኑ። ለእውቀት ተወዳደሩ። አዋቂዎች ሁኑ። ነገር ግን ደግሞ እናውቃለን ብላችሁ በማታውቁት ነገር አትመፃደቁ፤ መጨረሻውም ክስረት ነው›› ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 29 /2014