ዶክተር ዲማ ነገዎ የተወለዱት ኢሉአባቦራ ውስጥ ከጎሬ ከተማ ወደ 18 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጉማሮ በተባለች ስፍራ ነው። የልጅነት ጊዜያቸውን ከቤተሰብ ጋር አሳልፈዋል። ቤተሰባቸው በግብርና ሙያ ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ ናቸው። በልጅነታቸው በጣም የሚወዱት ነገር ታሪክና ተረቶችን ከአባታቸው እግር ሥር ቁጭ ብሎ መስማት ነበር ። አባታቸው ባይኖሩ እንኳን ሌሎች ትልልቅ ሰዎች ሳያጫውቷቸው አይውሉም። እሳቸውም ይህንን ጊዜ በጉጉት ይጠብቁት እንደነበር በአንድ ወቅት ከህይወት ገጻቸው ለዝግጅት ክፍላችን ከተናገሩት ላይ ስለእድገታቸው ትንሽ ለማስታወስ ያህል ወስደናል።
ዶክተር ዲማ ነገዎ፤ ከዘመናዊ ትምህርት ጋር የተዋወቁት በጎሬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። በ1960 ዓ.ም በአገሪቱ ብቸኛ በነበረው ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ዓመታትን በስራ ካሳለፉ በኋላ ዳግም ወደ ትምህርት በመመለስ በሴኔጋል ዩናይትድ ኔሽን አፍሪካን ኢኒስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክ ዴቨሎፕመንት ኤንድ ፕላኒግ ውስጥ ገቡ ። በዚህም ኢኮኖሚክ ፕላኒንግ አጠኑ። ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በአሜሪካ አገር ቴኔሲ ዩኒቨርሲቲ በሶሾሎጂ ትምህርት መስክ ተመርቀዋል። በእንግሊዝ አገርም እንዲሁ በግጭትና የሠላም ግንባታ ዙሪያ የስድስት ወር ስልጠና ወስደዋል። በተመሣሣይ ጀርመንኛ ቋንቋ ተምረዋል።
በፖለቲካ ህይወታቸውም ዶክተር ዲማ በኦሮሞ ነጻነት ግንባር( ኦነግ) ውስጥ ትልቅ ስፍራ አላቸው። ወደ አውሮፓ አቅንተው ጀርመን ውስጥ የኦሮሞ ተማሪዎች ማህበርን በማጠናከር ለሦስት ወር ያህል ሰርተዋል። ወደ ሱዳን ሄደው የትጥቅ ትግሉን ተቀላቅለውም 13 ዓመታትን ለማህበራዊ ፍትህ ነጻነት ታግለዋል። የሶማሊያን መንግስት የዌስተር ሱማሌ ሊብሬሽን ፍሮንትና ሶማሊያ ሊብሬሽን ፍሮንት ድርጅቶችን መስርተዋል። በዚያም ውስጥ ብዙ ቁጥር ያላቸው ኦሮሞዎችን አደራጅተው ከእነርሱ በአስተሳሰብ አልስማማ ሲሉ መንግስቱ የሱማሊያን ጥቅም የሚጻረር ሥራ ሰርተሃል በሚል እንዳሰራቸው ከታሪካቸው ከሚጠቀሱት ምዕራፎች ጥቂቶቹ ናቸው።
በዛሬው ዕትማችን የሀገሪቱን ወቅታዊ ጉዳዮች አስመልክቶ ሙያዊ ሐሳብ እንዲያካፍሉን እንግዳ አድርገናቸዋል። በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ አሁናዊ የፖለቲካ ሥሪት እና ፈተናዎቿ፣ መፍትሄ እና መከናወን ስለሚገባቸው ሁኔታዎች እንዲሁም ‹‹አሸባሪው ሸኔ›› እየሄደበት ያለውን የጥፋት መንገድ ለመቃኘት ተሞክሯል። ከዚህም በተጨማሪ የወያኔ የግፍ አገዛዝ ዘመንና ገፅታ እና አሁናዊ ቁመናም በቃለ ምልልሱ አካተናል ።
አዲስ ዘመን፡- የለውጡ ኃይል ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በሀገሪቱ የመጣውን የፖለቲካ ሂደት እንዴት ይመለከቱታል፤ ለውጡ ለኦሮሞ ህዝብስ ምን ይዞ መጣ ?
ዶክተር ዲማ ነገዎ፡- ይህ ከባድ ጥያቄ ነው። በእርግጥ ይህ ለውጥ እንዲመጣ የኦሮሞ ህዝብ ታግሏል። በተለይ ወጣቱ ከፍተኛ መሥዕዋትነት ከፍሏል። ይህ ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ ውስጥ ሚናው ከፍተኛ ነው። ሁለተኛ ለውጡም እንዲመጣ ያደረገው ለሀያ ሰባት ዓመታት በኦሮሞ ህዝብና በሌላው ህዝብ ላይ ተንሰራፍቶ የቆየው የወያኔ የጭቆና አገዛዝ ነው። ይህን የጭቆና አገዛዝ መሸከም ስላቃተው መጨረሻ ላይ የህዝብ ኃይልና ቁጣ ገንፍሎ ወጥቶ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ነው ለውጥ የመጣው። ሦስት ዓመት ነው የፈጀው ከዚያም በፊት ትግሉ ሲብላላ ነው የቆየው ፤ ከዚያው አሸንቅጥሮ ጣለው።
ወያኔም ለውድቀቱ ስላልተዘጋጀና ውድቀቱን መቀበል ስላቃተው በሌላ መንገድ ተመልሶ ስልጣኑን ለመቆጣጠር ሞከረ። በተለይ ባለፉት የለውጥ ዓመታት እየታየ ያለው ሁኔታ በአንድ በኩል ለውጡን በማስቀጠል በሚፈልጉ ሃይሎች እና ለውጡን ቀልብሶ ወደ ዱሮው ቦታ ለመመለስ በሚፈልጉ ሃይሎች መካከል እየተደረገ ያለ ትንቅንቅ ነው። ይህ ትንቅንቅ እስከ ጦር መማዘዝ እና የብዙ ኢትዮጵውያን ህይወት የቀጠፈ፣ ብዙ ንብረት እንዲወድም ያደረገ እና ከፍተኛ ንብረትን የህዝብ ሃብት የጠፋበትና በሚሊዮኖች ዜጎች የተፈናቀሉበት መሆኑን ያየንበት ነው። እናም ከፍተኛ የሆነ እና በለውጡም ብዙ ውጤቶች ተገኝተዋል።
ቀድሞ በነበረው የወያኔ ስርዓት ከአራት ዓመት በፊት የነበረውና ዛሬ ያለው የተለየ ነው። ያስገኘው ጥቅም አለ። እንዲያውም ሆኖ ደግሞ ይህ ትንቅንቅ ባይኖር ኖሮ ከአሁኑ የተሻለ ለውጥ ይመጣ ነበር። የኢኮኖሚ እና ሌሎች ለውጦችም ይታይ ነበር። ነገር ግን ለውጡን ለመቀልበስ በሚደረገው ጥረት ምጣኔ ሃብቱን ጎድቷል፤ በተለይ የታችኛው የማህበረሰብ ክፍል ኑሮ ተመሰቃቅሏል፤ በሀገር ውስጥ የምናየው የኑሮ ውድነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጭ ጫናዎች ሁኔታዎች ቢኖሩም በዋናነት የዚህ ትንቅንቅ ውጤት ናቸው። ታሪክ ወደኋላ አይሄድም፤ ለውጡ ይቀጥላል፤ ግን እክሎች አጋጥመውታል ፤ አሁንም ሊያጋጥሙት ይችላል ይህን መገመት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ሸኔ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንጹሃን ላይ የሚፈፅመውን ጭፍጨፋ እንዴት ይመለከቱታል?
ዶክተር ዲማ ፡- ወለጋ ውስጥ እንዳልኩት ከአራት ዓመት በፊትም ህዝብ ሲጨፈጨፍ ነበር። ይህ አዲስ ነገር አይደለም። ነገር ግን ማንም ቢሆን በማንም ላይ ይህ ድርጊት መፈፀም የለበትም ብዬ አምናለሁ። የብዙ ንፁሃን ዜጎች ደም ሲፈስ ነበር። ወደ ኋላ ከሄድን ረጅም ነው። 100 ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ነበር፤ ልማት አላካሄድንም። በተለይ ደግሞ ንጹሃን የፖለቲካ ግጭት ውስጥ ምንም ሚና የሌላቸው ህዝቦች፣ ዜጎች እዚህ ውስጥ መማገድ የለባቸውም። ማንም ድርጅት የፖለቲካ ዓላማ ካለው በሰው ፍጡር ላይ ወንጀል መፈፀም የለበትም። የፖለቲካ ዓላማ አለኝ፤ ህዝባዊ ዓላማ አለኝ የሚል በማንም ላይ ይህ መሰል ድርጊት መፈፀም የለበትም።
በእኔ አረዳድ በኢትዮጵያ ውስጥ በብሄሮች አለመግባባት አለ የሚል እምነት የለኝም። ያለው የፖለቲካ አለመግባባት ነው። የሚስተዋለው ግጭትም የፖለቲካ ግጭት ነው። በአፍሪካ ውስጥ ግጭቱን የጎሳ ግጭት የሚያደርጉት የውጭዎቹ ናቸው። ዱሮ ሊሆን ይችላል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካ ውስጥ አለመግባባትና አለመጣጣም አለ። ግማሹ በብሄር፤ ግማሹ በሃይማኖት፣ ግማሹ በተወለደበት አካባቢ ለመደራጀት ይሞክራል። ማንነት ደግሞ በቀላሉ ሰዎችን ለማንቀሳቀስ ስለሚቀል ይጠቀሙበታል። አንዳንድ አካላት ግጭቶችን የሚያራግቡት በዚህ ውስጥ ድጋፍ ለማሰባሰብ ነው።
የወያኔ ፕሮግራም ከዱሮ ጀምሮ ይታወቃል። አንድም ብሄር አንድ እንዲሆን አይፈለግም። በተለይ አማራ እና ኦሮሞ አንድ እንዳይሆን በደንብ ሰርተዋል፤ በዚህም መቀጠል ይፈልጋሉ። ይህ በተወሰነ ደረጃ አሻሽለው ለመቀጠል ሰርተዋል። ኦሮሞ እና አማራ፣ ሱማሌ እና አማራ፣ ሱማሌ እና አፋር ለማጋጨት ብዙ ሠርተዋል። በተወሰነ ቦታ ተጠቅመውበታል። ከአራት ዓመት በፊት በነበረው ግጭት ከሱማሌ እና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል። አሁንም ወያኔ ይህን ለማስቀጠል ነው የሚሰራው ። በዚህ ሁሉ ውስጥ የመጨረሻ ውጤት ገፈት ቀማሽ ግን የትግራይ ህዝብ ነው። ለወያኔ ስልጣን ብለው መሳሪያ እየሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ዘመናትን እንዳሳለፈ ሰው በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል፤ በክልሉ ሠላምን እንዴት ማስፈን ይቻላል ብለው ያምናሉ ?
ዶክተር ዲማ ፡- በኦሮሚያ ክልል የሚታየው ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። ሠላም ከደፈረሰ ሰነባብቷል። በወቅቱ መፍትሄ ቢፈለግ ይህን ያክል ችግር አይፈጥርም ነበር። አሁን እየተስፋፋ ነው፡ ወደ መሃል ሀገርም ተንሰራፍቷል። ይህ ሁኔታ እንደማስበው በሌላ ቦታ ካለው ችግር ጋርም ይያያዛል። ብዙ ሰው ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ችግር ለብቻ ለይተው ያያሉ። ይህን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር አደረገው በሚል ነው የሚወራው። በእርግጥ ኦነግ በኦሮሞ ህዝብ የሚወደድ ድርጅት ነው። ለህዝቡ መብት ታግሏል። ነገር ግን አሁን የሚታየውና ዱሮ የነበረው ለየቅል ነው።
ወያኔ ለ27 አመታት ስልጣን ላይ በቆየበት ወቅት ዋነኛ የትኩረት ቦታው እና አቅጣጫው የነበረው ኦሮሚያ ክልል ነው። ኦሮሚያን መቀማት ላይ ነው ያተኮረው። ስልጣን ከመያዛቸው በፊት የኦሮሞ ሀቀኛ ሃይል እያለ እውነተኛ ታጋዮችን በማግለል የሚፈልጉትን ስራ ሲሰሩ ነበር። ይሁንና የኦሮሞን ህዝብ እንቅስቃሴ መግታት አልቻሉም። በመጨረሻም ህዝብ አስወግዶታል። በሺዎች መሥዋዕት ከፍለው ነው ለዚህ መብቃት የተቻለው። የኦሮሞ ታማኝ ድርጅቶች ውስጥ በመግባት የራሳቸውን ሴራ በመሸረብ ዓላማቸውን ለማሳካት ጥረዋል። ለኦሮሞ እውነተኛ ተቆርቋሪዎችን በማግለል የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚያግዙትን አካላት በዘዴ አስቀምጠዋል።
በአሁኑ ወቅት በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሥም የሚንቀሳቀሱት የወያኔ ተላላኪ ናቸው ። ትክክለኛ የኦሮሞ ወዳጅ ያልሆኑ ናቸው። ይሁንና ለኦሮሞ ህዝብና ነፃነት የሚታገሉ የሉም ማለት አይደለም፡ ከበስተጀርባ ያለውን ሚስጥር አልተረዱትም። ኦሮሚያ ማለት ኢትዮጵያ ማለት ነው። ኦሮሚያ ተበጠበጠች ማለት መላ ኢትዮጵያ ተበጠበጠች ማለት ነው። የሀገሪቱ ትልቁ ሃብት በኦሮሚያ ውስጥ ነው። ኦሮሚያ ማዕከል ናት።
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውና የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙት አብዛኛው መገኛው ኦሮሚያ ነው። በመሆኑም ኦሮሚያን መበጥበጥ ማለት መንግስትን ማዳከም ነው፤ ይህም የወያኔ ስትራቴጂ ነው። በጦርነቱ ማሸነፍ ባለማቻላቸው በተለያየ ቦታ ግጭት በመቀስቀስ ማትረፍ ይፈልጋሉ። በዚህ ብቻ ሳይሆን በአማራ፣ በጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እና ሌሎች አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮች የወያኔ ጥንስስ ናቸው። ወያኔ ላለፉት 27 ዓመታት በርካታ የሚመቿትን ነገሮችን ለራሷ ስትሰራ ነበር።
አሁን እነዚህን አካላት በመከፋፈልና በማነሳሳት እየተጠቀሙ ነው። ይህን አውቀው አብረው የሚሰሩ አሉ። ሳያውቁ የእነዚህን አካላት መሳሪያ እና መጠቀሚያ የሆኑ አሉ። አውቀው የኦሮሞን ህዝብ መብት እናስከብራለን ብለው የሚታገሉ አሉ። ያልተመለሱ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎች አሉ። ለምሳሌ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ላይኛው የመንግስት እርከን የመልካም አስተዳደር መስፈን አለበት። በአሁኑ ወቅት በብዙ የመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉት በወያኔ የአገዛዝ ዘመን የነበሩት ናቸው። ተለውጠው ከሆነ መልካም ነው። ግን አሁንም በቀድሞው አሰራር የሚሄዱ አሉ።
ይህ የህዝቡ ጥያቄ ነው። በርካታ ጥያቄዎች አሉ። በመሆኑም እምነት በሚጣልባቸው ሰዎች መመራት አለበት። በዚህ የተነሳ የሚታገሉ ሰዎች አሉ ብሎ መገመት ይቻላል። በክልሉ ውስጥ ያለውን ችግር በተወሰነ የፖሊስ ኃይል ብቻ ስለማይመለስ በተገቢው መንገድ መመለስ ይገባል። ህዝቡ የአሸባሪው ሸኔን እንቅስቃሴ እየደገፈ ነው የሚል እምነት የለኝም። ግን የጦር መሳሪያ ይዘው ከመጡበትና የሚከላከልበት ከሌለ ምንም ሊያደርግ አይችልም። በሌላ በኩል የመንግስት አካላት አሸባሪ እየመገባችሁ ነው ብለው ህዝቡን ይጠይቃሉ። በዚህ መሃል ተጎጂው ህዝብ ነው። በመሆኑም እልባት ለመስጠት ሌላ ተጨማሪ አሠራር መከተል ይገባል። የእምነት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ ሃዳ ስንቄዎች፣ ሴቶችና ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ ውይይት ያስፈልጋል። በዚህም ችግሩን እንዴት መፍታት ይቻላል በሚለው ላይ በጥልቀት መሥራት ይገባል። ለዚህም ስትራቴጂ መንደፍ ይገባል። መንግስትም በተደጋጋሚ የሠላም ጥሪዎችን እያደረገ ነው፤ ይህን ቢጠቀሙ መልካም ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከገዳ ሥርዓት አንፃርስ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?
ዶክተር ዲማ ፡- በገዳ ሥርዓት ይህ ፈጽሞ አይፈቀድም። ጦርነት ውስጥ ከተገባ የራሱ ህግ አለው። ይህ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደረገው ነገር አግባብ አይደለም። ይህን አድርጎ የተገኘ የሚቀጣበት፣ የሚመራበትና የሚፈታበት የራሱ የሆነ ህግ አለው። መሰል ድርጊት የሚፈፅም ከህብረተሰቡ መገለል ይደርስበታል።
አዲስ ዘመን፡- ለኦሮሞ ህዝብ ቆሜያለሁ ከሚል ቡድን በንጹሀን ላይ የሚያደርሰውን ግፍ እንዴት ይታያል?
ዶክተር ዲማ ፡- መጀመሪያ እኮ ሸኔ ጥቃት የጀመረው በኦሮሞ ህዝብ ላይ ነው። ስንት ዓመት ሙሉ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈፅም አልነበረም እንዴ? እኛ እኮ እናውቃለን፤ እንሰማለን። ድርጊቱን መፈፀም የጀመረው በኦሮሞ ህዝብ ላይ ነው። አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ቢኖር በማንም ህዝብ ላይ ወንጀል የሚፈፅም ሰው በራሱ ህዝብ ላይም አይተውም፤ ድርጊቱ ወንጀል ነው። ሌላ ህዝብ ላይ እጁን ያነሳ መጨረሻ ላይ ኦሮሞን ነው የሚያጠፋው።
አዲስ ዘመን፡- በሀገራችን ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበት ሰፊ ዕድል እና ሥርዓት እያለ አሸባሪው ሸኔ በህዝብና በሀገር ላይ ይህን ግፍ የሚያደርሰው ከምን የመነጨ ይመስልዎታል ?
ዶክተር ዲማ ፡- ሸኔ ሲባል የከተማው ሰው የሆነ ጭራቅ ይመስለዋል። ከዚህ ህብረተሰብ የወጣ ነው ፤ አዲስ ሰው አይደለም። ምንም ከመፈለግ አይደለም። መሳሪያ ያነሳ ማንኛውም ቡድን ሥርዓት ከሌለው እንዲህ ዓይነት ወንጀል ከመፈፀም ወደ ኋላ አይልም። የተደራጀ፤ በሥነምግባር የታነፀ አንዳንዴ ፀጥታ ኃይሎችም እኮ ህገወጥ ተግባር ሊፈፅሙ ይችላሉ። መሳሪያ ያነገበ ሰው በህግ የሚመራው ለዚህ ነው። ማንኛውም የታጠቀ ቡድን ዓላማው ምንድን ነው፤ ዓላማው በመንግስት ላይ ካመፀ የመጀመሪያ ዓላማው ህዝብና መንግስትን ማጣላት ነው። አንደኛ መንግስት በሥርዓት እንዳያስተዳድር፣ ህዝብ ደግሞ ለመንግስት እንዳይገዛ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን ልዩነት ማስፋት ነው። ይህ የማንኛውም የወታደራዊ ፖለቲካ ዓላማ ያነገበ አካል ሴራ ነው። ከዚያ ደግሞ በሂደት ህዝብና ህዝብን ማጣላት ነው። በመሆኑም አሁን እየተካሄደ ያለው አንደኛ መንግስት የህዝብን ሰላም እና ደህንነት መጠበቅ አልቻለም ለማሰኘት ጭምር ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ቡድን ዛሬም ይሁን ነገ ለኦሮሞ ህዝብ ከፍተኛ የሥጋት ምንጭ መሆኑን እንደማይቀር ብዙዎች ይናገራሉ። እርስዎ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ዲማ ፡- ሸኔ ለኦሮሞ ህዝብ ይህን ያክል ከፍተኛ ስጋት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም አሸባሪው ሸኔ በሌሎች ስትራቴጂ የሚመራ እና የራሱ ስትራቴጂ የሌለው በመሆኑ ከጀርባው ያለው ኃይል እየተዳከመ ከመጣ እሱም ቦታ አይኖረውም።
አዲስ ዘመን፡- በአሸባሪው ሸኔ ላይ በተለያዩ የፀጥታ ሃይሎችና በህዝብ ድጋፍ ጭምር ነው ዘመቻ የተካሄደበት። ይህ በቂ ነው ይላሉ?
ዶክተር ዲማ ፡- በቂ አይደለም። ከዚህ በፊት ለተለያዩ አካላት በተደጋጋሚ ተናግሬያለሁ። ይህንን በፀጥታ ኃይል ብቻ መፍታት ስለማይቻል ሌሎች ፖለቲካዊ ዘዴዎችን ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የአሸባሪው ሸኔ አሁናዊ የጥፋት መንገድ ኦነግ ለኦሮሞ ህዝብ የታገለለትን እና የከፈለውን ዋጋ ማሳነስ አይሆንም?
ዶክተር ዲማ ፡- የተፈለገውም ይህ ነው። የተፈለገው ነገር ቢኖር ያንን የመሰለ ከፍተኛ መስዋዕነት ከፍሎ የኦሮሞን ህዝብ ትግል እዚህ ደረጃ ላይ ያረሰውን ኃይል ለማጠልሸት ነው። ቦታ ለማሳጣት፣ ስሙን ለማጥፋት የተደረገ ነው። ሆን ብለው ወያኔ ያደረገችው ስራ ነው። ወያኔ የኦሮሞን ህዝብ እንቅስቃሴ ለማጥፋት እና ለማሸነፍ ስላቃታት ከውስጥ ቦርቡራ ስሙንም አጠልሽታ በህዝብ ዘንድም አስጠልታ ለማጥፋት ነው ይህን ስትራቴጂ የነደፈችውና ሥራ ላይ ያዋለችው።
አዲስ ዘመን፡- መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር በሠላማዊ መንገድ ለመፍታት እየሄደበት ያለውን የሰላም መንገድ እንዴት አገኙት?
ዶክተር ዲማ ነገዎ፡- ጥሩ ነው! እደግፋለሁ። በሚቻለው መጠን ማንኛውንም ዓይነት ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሞከር ጥሩ ነው። ችግሩ ግን መንግስት ብቻ የሚፈልገው ሳይሆን ያኛውም ወገን የሚፈልገው መሆን አለበት። በጦርነት ያልተገኘውን በሰላማዊ ድርድር መፍታት ነገሮችን ማቻቻል ያስፈልጋል የሚል ነገር ይኖራል ብዬ አምናለሁ ። ነገር ግን እኔ ሰዎቹን እስከማውቃቸው ድረስ ማቻቻል የሚባል ነገር የሚያውቁ አይመስለኝም። በባህሪያቸውም ማቻቻል የሚለውን ቋንቋ አያውቁም።
አዲስ ዘመን፡- ሌላ ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ዕድሉን እንስጥዎ?
ዶክተር ዲማ ፡- እኔ ብዙ የምለው ተጨማሪ ነገር የለም። በሰሜኑም ሆነ በየትኛም የሀገሪቱ አካባቢ እየተደረገ ያለው ጦርነት መጠኑ ቢበዛም ቢያንስም የህዝብ ህይወት እየቀጠፈ እና እያፈናቀለ ነው። የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እየጎዳ ነው። በአንዳንድ አካባቢ እርሻ እየታረሰ አይደለም። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ለርሃብ ተጋልጧል። ይህ የሀገሪቱንም ገፅታ እያበላሸ ነው። ስለዚህ ይህ በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲያገኝ ቢደረግ በተቻለ መጠን ደግሞ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት ለሀገሪቱ መፀዒ ዕድል ወሳኝ ነው። በመሆኑም የተጀመረው የእርቅ መንገድ መደገፍ የሚገባው ነው የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ለነበርዎት ቆይታ በአንባቢያን ስም እናመሰግናለን።
ዶክተር ዲማ ነገዎ፡- እግዜር ይስጥልኝ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሰኔ 27 /2014