በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ማዕድናት እንዳሉ ቢነገርም ላለፉት በርካታ ዓመታት ማዕድናቱን በማልማትና በመጠቀም ረገድ ግን በቂ ሥራ እንዳልተሠራ በስፋት ይነገራል። በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በየአካባቢው የሚገኙ ማዕድናትን በመለየት እንዲለሙና ጥቅም ላይ መዋል እንዲችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በቅርቡም የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ዑማ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ያነሱት ይህንኑ ነው። በአገሪቱ ያለውን የማዕድን ዘርፍ አውጥቶ መጠቀም እንዲቻል በርካታ መመለስ ያለባቸው ጥያቄዎች ስለመኖራቸው በማንሳት በተለይም ባለፉት ዓመታት አገሪቷ ባላት ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት መጠቀም እንዳትችል የፖሊሲና የአዋጅ ጉዳይ የማዕድን ዘርፍን ቅርቃር ውስጥ ከትቶት እንደነበር ተናግረዋል።
በኢኮኖሚና ፖለቲካ ሪፎርሙ የማዕድን ዘርፉ ከአምስቱ የብዝሃ ኢኮኖሚ ግንባታ ምሰሶዎች መካከል አንዱ ሆኖ መምጣቱንና መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አስታውሰዋል። በተለይም በብረት ማዕድን ዘርፍ ያለውን እውነታ ሲያስረዱ ኢትዮጵያ ውስጥ 18 የብረት ፋብሪካዎች እንደሚገኙና ከእነዚህም ውስጥ 14ቱ የብረት ፋብሪካዎች ስሪታቸው በአገሪቷ ስላለው የማዕድን ሀብት ጥናት ያደረጉ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል።
‹‹ፋብሪካዎቹ በአገሪቱ ያለውን የብረት ማዕድን አጥንተው፣ ፈልገውና ለይተው ሀብቱን ማልማትና ማምረት እንዲችሉ አልተደረጉም። ፋብሪካዎቹ በመሠረታዊነት ከውጭ በሚገቡ ብረቶችን ተጠቅመው ጥቃቅን ነገሮችን ብቻ በአገር ውስጥ ተጠቅመው በማምረት ለገበያ ያቀርባሉ። ለዚህም ምክንያቱ የአገሪቷን ሀብት መጠቀም እንዳይቻል ያደረጉ አዋጆችና ፖሊሲዎች ስለነበሩ ነው። አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሪፎርም በማድረግ ለዘርፉ እድገት እንቅፋት የሆኑ ችግሮች መፍትሄ እያገኙ ነው›› ብለዋል።
በመሆኑም በየቦታው ማለትም በሁሉም መስሪያ ቤቶች የሚገኙ ስብርባሪ ብረቶችን በመሰብሰብ ኩባንያዎች በመጠነኛ ዋጋ እንዲገዙ በማድረግ ጊዜያዊ መፍትሔዎች ተግባራዊ እየሆኑ ነው። በዋናነት ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የብረት ማዕድን ፍለጋን በማጠናከር የላብራቶሪ ማረጋገጫ ሥራ መሥራት ነው።በተጨማሪም ለዚህ የሚመጥኑ ኩባንያዎችን የመምረጥና የማወዳደር ሥራ ይሠራል። ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላም መንግሥት ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ባለሀብቶች ጋር በጋራ በመሆን ሀብቱን ጥቅም ላይ ለማዋል የማምረት ሥራ ይቀጥላል ብለዋል።
ማዕድንን ጥቅም ላይ ለማዋል ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል የማዕድን ሀብቱ የሚገኝባቸውን አካባቢዎች መለየት አንዱና ቀዳሚው ጉዳይ እንደመሆኑ በሁሉም አካባቢዎች የሚገኙትን ማዕድናት የመለየት ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሠራ የሚገኝ መሆኑን የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል። በአገሪቱ ከሚገኙ የማዕድን ሀብቶች መካከል በአማራ ክልል የሚገኘው ከፍተኛ መጠን ያለው የብረት ማዕድን ተጠቃሽ ነው። በአካባቢው ስላለው ያለው ማዕድን ዓይነትና ይዞታ እንዲሁም ሀብቱን አልምቶ ለመጠቀም ስለተሠሩ ሥራዎችና በቀጣይ ስለሚጠበቁ ተግባራት ዳሰሳ አድርገናል።
ከፍተኛ መጠን ያለው የብረት ንጥረ ነገር ያለበት አካባቢ ስለመሆኑ በስፋት በሚነገርለት አማራ ክልል፣ ዋግኽምራ፣ ሰቆጣ አካባቢ የሚገኘውን የብረት ንጥረ ነገር የጥንት አባቶች ሲጠቀሙበት እንደነበር የአካባቢው ማኅበረሰብን ዋቢ በማድረግ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ማኅበረሰቡ በአካባቢው የሚገኘው ቀይና ጥቁር አፈር የብረት ንጥረ ነገር ያለው ስለመሆኑ በተግባር ማረጋገጥ የቻለ ቢሆንም ከማዕድን ሀብቱ ግን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዳልሆነ ነው የሚነገረው።
የአካባቢው ሰዎች አፈሩን ጭረው እንደ ማረሻ የመሰሉ የግብርና መሣሪያዎችን ይሠሩ እንደነበርም የአካባቢው ማኅበረሰብ ምስክርነት ይሰጣል። በአካባቢው የነበሩ የቀድሞ አባቶች የግብርና ሥራቸውን ለማቀላጠፍ የሚያስችላቸውን ገጀሞ፣ መጥረቢያ፣ መቆፈሪያ አካፋና የመሳሰሉትን መሣሪያዎች በአካባቢያቸው ከሚገኘውና የብረት ንጥረ ነገርን በውስጡ ከያዘው አፈር ተጠቅመው በባህላዊ መንገድ ሠርተው መጠቀማቸውንና አሁንም እየተጠቀሙ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
በአካባቢው መጠነ ሰፊ የሆነ የብረት ማዕድን እንዲሁም ሌሎች የከበሩ ድንጋዮች ስለመኖራቸው ምን ያህል ይታወቃል፤ የማዕድን ሀብቱንስ ለማልማትና ለመጠቀም ምን የተሠራ ሥራ አለ፤ በማለት ላነሳነው ጥያቄ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑ ባለሙያን አነጋግረናል።
በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ምድር ትምህርት ቤት የአለት እና ማዕድናት ተመራማሪ እና መምህር አቶ አየናቸው አለማየሁ፤ እንደ አገር የተጠኑ ጥናቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ ጥናቱም የሚያመላክተው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የሆነና በዓይነትም የተለያዩ ማዕድናት እንደሚገኙ ይናገራሉ።በአማራ ክልል ሰቆጣ አካባቢ የሚገኘው የብረት ማዕድንም በአገሪቱ አሉ ከተባሉ የብረት ማዕድናት አንዱና ትልቁን ድርሻ የሚይዝ እንደሆነና ይህንንም በቦታው በመገኘት ማረጋገጥ እንደቻሉ ነው ያስረዱት።
ሳይንሳዊ ጥናቶቹም የራሳቸው የሆኑ አመላካቾች ያሏቸው መሆኑን የጠቀሱት መምህሩ፤ የብረት ማዕድናቱ ክምችት በምን ያህል መጠን፣ ጥራትና በምን ያክል የቦታ ስፋት ላይ ይገኛሉ የሚሉት ጥያቄዎችንም በባለሀብቶች ዳሰሳ ተመልሷል። በአካባቢው የዳሰሳ ጥናት ያደረጉትም አክሰስ ካፒታል እና ሰቆጣ ማይኒንግ የተባሉ ካምፓኒዎች ሲሆኑ እነዚህ ካምፓኒዎችም በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል።
ካምፓኒዎቹ ያደረጉትን የዳሰሳ ጥናት ሪፖርቶች መመልከት የቻሉት መምህሩ፤ ሪፖርቱ በርካታ ግኝቶችን የያዘ ስለመሆኑም አስረድተዋል።ለአብነትም በአካባቢው የሚገኘውን ብረት የተባለ ንጥረ ነገር በቦታው ስለመኖሩ አረጋግጠዋል። ከኩባንያዎቹ በተጨማሪ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ መምህራን ባደረጉት የመስክ ምልከታም በአካባቢው የብረት ማዕድን ሀብት መኖሩ ተረጋግጧል።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ በአማራ ክልል የሚገኙ የማዕድን ሀብቶችን አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየሠራ የሚገኝ ሲሆን፤ ለአብነትም በወሎና በምሥራቅ ጎጃም ለኮንስትራክሽን ግብአት ማለትም ለሲሚንቶ ፋብሪካ የሚጠቅም ሀብት ያለበት አካባቢ በጥናት በመለየት የተገኘውን ውጤት ማስረከብ እንደቻሉ ነው መምህሩ የተናገሩት።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የማዕድን ዓይነቶች መካከል በተለይም የኖራ ድንጋይ ከፍተኛ ክምችት መኖሩንና በትሪሊየን ብር የሚገመትና ለበርካታ ዓመታት የሚያገለግል ነው። ይህ የኖራ ድንጋይም የሲሚንቶና የጠመኔ ማምረቻዎችን ጨምሮ የኖራ ግብዓቶችን የሚጠቀሙ ፋብሪካዎችን መትከል ያስችላል።ለዚህም አስፈላጊ የሆኑ ጥናቶች እየተደረጉ ነው።
እነዚህንና መሰል ጥናቶችን ለማድረግ መነሻቸው የአካባቢው ማኅበረሰብ እንደሆነ ያነሱት መምህሩ፤ ‹‹ማኅበረሰቡ በዘርፉ ሰፊ ዕውቀት ያለውና ከጥንት ጀምሮ በባህላዊ መንገድ ሲጠቀምበት የነበረ ሀብት ነው። የብረት ማዕድን ሀብቱ በሚፈለገው ልክ መልማትና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ያልቻለ ቢሆንም አሁንም አልረፈደምና ይህን ተዝቆ የማያልቅ ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል›› ብለዋል።
ከ50 ዓመታት በፊት ማኅበረሰቡ በአካባቢው የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት በተለይም ብረቱን እያነጠረ ማረሻን ጨምሮ የተለያዩ የእርሻ መሣሪያዎችን እየሠራ ተጠቅሟል። ይሁንና ማኅበረሰቡ የብረት ማዕድን ሀብቱን እየተጠቀመበት ያለው እጅግ ኋላ ቀርና ባህላዊ በሆነ መንገድ ነው። ስለሆነም ዘመናዊ በሆነ መንገድ ብረቱን ማልማት ቢቻልና የብረት ፋብሪካ ቢተከል ከክልሉ አልፎ ለአገርም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ ነው።
ዩኒቨርሲቲው አስቀድሞ መሠራት ያለበትን የማዕድን ሀብቱ መኖሩን አረጋግጧል ያሉት አቶ አየናቸው፤ ከዚህ በተጨማሪም ሀብቱ ምን ያህል ጥራትና ብዛት አለው በማለት ሳይንሳዊ በሆነ ዕውቀት አስደግፎ ጥናቱን ያከናወነ ሲሆን፤ የጥናቱን ሪፖርትም አቅርቧል። በአካባቢው ያለው የማዕድን ሀብት ምን ያህል እንደሆነና የብረት ፋብሪካ ተተክሎ ብረቱ እየተነጠረ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል ቢደረግ ከአካባቢው ባለፈ አገሪቷም ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል መንግሥትን ጨምሮ ለባለሀብቶች፣ አልሚ ለሆኑ ድርጅቶችና ለሌሎች ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጥናታቸው መክረዋል።
ባለሀብቱም ይህንን ጥናት ተመርኩዞ የተለያየ የአዋጭነት ጥናት በማጥናት የማዕድን ሀብቱ በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውልና ማኅበረሰቡም በተለያየ መንገድ ከሀብቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። ለዚህም ምሁራኑ ቀደም ሲል ማኅበረሰቡ የሚያውቀውን እውነታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የመተንተን፣ ማብራሪያዎችን የመጨመርና የማረጋገጥ ሥራውን እያከናወኑ እንደሆነ ያመላከቱት መምህሩ፣ ከዚህም በላይ በአካባቢው የሚገኘው ሀብት እራሱ አፍ አውጥቶ የሚናገር መሆኑን ጠቁመዋል።
‹‹ከፍተኛ መጠን ያለው የብረት ማዕድን ሀብት በሚገኝበት ዋግኽምራ ሰቆጣ አካባቢ መልከአምድሩ ለግብርና ምርት የማይመች በመሆኑ በአካባቢው የሚገኘው የማኅበረሰብ ክፍል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህ አካባቢ የታደለውን እምቅ የማዕድን ሀብት አውጥቶ በማልማትና በመጠቀም ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል። ለዚህም ኅብረተሰቡ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን የሚጠይቅ በመሆኑ ጥያቄው ሊመለስለት ይገባል።ማኅበረሰቡ አካባቢው የሰጠውን ማዕድን አውጥቶ ማልማት የሚችልበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ተጠቃሚ እንዲሆን መሥራት ያስፈልጋል›› ብለዋል።
ኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ በግብርና የሚተዳደር እንደመሆኑ በርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች በግብርና ሥራ ምርት መስጠት የሚችሉ ናቸው። ማኅበረሰቡም ምርት አምርቶ ከምርቱ እንደሚጠቀም ሁሉ የዚሁ አካባቢ ማኅበረሰብም በአካባቢው ከሚገኘው የማዕድን ሀብት ተጠቃሚ በመሆን ፍትሃዊ የሀብት ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል በማለት ማኅበረሰቡም ለረጅም ጊዜ ሲያነሳው የነበረ ጥያቄ መሆኑንም አቶ አየናቸው ገልፀዋል።
‹‹በእርግጥ አካባቢው ላለፉት በርካታ ዓመታት የጦርነት ቀጠና የነበረ በመሆኑ የመልማትና የመበልጸግ ዕድል አላገኘም። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ በእጁ ያለውን ሀብት ተጠቅሞ መልማትና መበልጸግ የሚያስችለው በመሆኑ ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ማኅበረሰቡ የአካባቢውን ሀብት መጠቀም መጀመር አለበት›› ያሉት አቶ አየናቸው፤ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የሚያበረታታ እንደሆነም ተናግረዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፣ ከግብርና ቀጥሎ ሁለተኛው የዕድገት ዘርፍ ሆኖ የተለየውን የማዕድን ዘርፉን ማልማትና መጠቀም እንዲቻል መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ መቀጠል አለበት። የማዕድን ሚኒስቴር የጀመረውን ጥሩ ሥራ ማስቀጠልና በተለይም ጥናት በተደረገባቸው አካባቢዎች ኢንቨስት ማድረግ፤ እንዲሁም የማዕድን ሀብቱ በዘላቂነት ለረጅም ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲችል አመላካች በሆኑ ቦታዎች ሁሉ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ጥናቶችን ማካሄድ ያስፈልጋል።
የተጠኑት ጥናቶችም በሚገባ ተደራጅተው ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መተላለፍ ይገባቸዋል። ከዚህ ባለፈም ወጣቱ ትውልድ በአገሪቱ ያለውን ሀብት እንዲያውቀውና እንዲጠቀምበት የማስተማር ሥራ መሠራት ይኖርበታል። ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ በመስኖ እርሻ ወጣቱ መሰማራት የሚችልበትን ዕድል ይፈጥራል። ስለዚህ አሁን እየመጣ ያለውን የማዕድን ዕድልም ወጣቱ እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዲቻል ግንዛቤ በመፍጠር ማኅበረሰቡን ማንቃት ያስፈልጋል።
በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኘውን ዕምቅ የማዕድን ሀብት ማልማትና መጠቀም ያልተቻለበት አንዱ ምክንያት በዘርፉ የሰለጠነና ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ባለመኖሩ እንደሆነ ስለሚነሳው ሀሳብ ሲያስረዱም ‹‹በአገሪቱ ከሚገኙ 46 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት ስለ ማዕድን ዘርፍ የሚያጠና ጂኦሎጂ ወይም ስነምድር የሚባለው የትምህርት ክፍል እንዳላቸው መረጃዎች ያሳያሉ። የጂኦሎጂ ወይም የስነምድር ትምህርትን ማስፋፋት ተገቢ ነው። የትምህርት ክፍሉን ከማስፋፋት ባለፈ በተመረጡ አካባቢዎች የተደራጁ ላብራቶሪዎች፣ ብቁ የሆኑ ባለሙያዎች በተለይም ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ። ይህንንም ዩኒቨርሲቲዎች ትኩረት ሰጥተው በአጭርና በረጅም ጊዜ ስልጠና በመስጠት መምህራኖችን ማብቃት ያስፈልጋል። እንደ አገር ያለው የትምህርት ጥራት ችግር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ቢሆንም በየዓመቱ በማዕድን ዘርፍ በርካታ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ እንደመሆኑ ተማሪዎቹ በዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ በመሆን መፍትሔ ያመጣሉ የሚለውን ለመመለስ የትምህርት ተቋማቱ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እና በተመረጡ አካባቢዎችም በማዕድን ዘርፍ የልዕቀት ማዕከልን አቋቁሞ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ለነገ የሚተው ሥራ አይደለም።
ፍሬሕይወት አወቀ