ዶክተር ልደቱ ዓለሙ በኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት አካዳሚክ ዲን እንዲሁም በዋናነት የኦርጋናይዜሽናል ሊደርሺፕ መምህር ናቸው፡፡ የማስተር ኦፍ አርትስ ሊደርሺፕ ማኔጅመንት ፕሮግራም መሪ ናቸው፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ህክምና ያገኙ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በስነመለኮት ጥናት የማስተር ኦፍ ዲቪኒቲ (Master of Divinity) ከኢትዮጵያ ስነ መለኮት ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት አግኝተዋል፡፡ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ ከአሜሪካን አገር ኢስተርን ዩኒቨርሲቲ በድርጅታዊ አመራር (Organizational Leadership) ይዘዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ መድረኮች ስልጠናዎችን በመስጠት የሚታወቁ ሲሆን፣ ከግጭት አፈታት ጋር ተያይዞ አዲስ ዘመን የዛሬው የወቅታዊ እንግዳ አድርጎ አቅርቧቸዋል፤ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ግጭት መነሻው ምንድን ነው? ሰዎችንስ የሚያጋጨው ነገር ምንድን ነው ? የሚለው ለቃለ ምልልሳችን እንደ መንደርደሪያ እናድርገው፡፡
ዶክተር ልደቱ፡- በሚገባ! ግጭት በሁለት አካላት አሊያም በሁለት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሲሆን በተለያየ መንገድ ሊፈጠር የሚችል የሐሳብ አለመጣጣም ነጸብራቅ ነው፡፡ ግጭት በራሱ ማንነት የለውም፡፡ በአንድ ሂደት ውስጥ የሚያድጉ አመለካከቶችና አስተሳሰቦች አድገው አለመስማማትንና አለመደማመጥን ፈጥረው የሚያመጡት ውጤት ግጭት ነው፡፡
መንስኤው ምንድን ነው? ከተባለ ብዙ ነው። ዋና መሰረቱ ግን የፍላጎቶች መለያየት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሰበቦች መኖራቸው የሚዘነጋ አይደለም፤ ለምሳሌ የፖለቲካ አቋም፣ ኢኮኖሚያዊ አቅም፣ ማህበራዊ መስተጋብሮች እንዲሁም ሃይማኖትም ሰበብ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁልጊዜ ግን ፍላጎት አለ፡፡ የእኔ ፍላጎት ከሌላው ሰው ፍላጎት ጋር መጣጣም ሳይችል ሲቀር ልዩነት ይመጣል፤ ልዩነት ደግሞ ወደአለመስማማት ሲያድግ በዚያን ጊዜ ግጭት ይፈጠራል፡፡
መሰረቱ የስልጣን ፍላጎት ሊሆን ይችላል፤ ወይም የራስ ሐሳብ የበላይ እንዲሆን ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲሁም ሃይማኖት ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ጥላ ናቸው፡፡ የግጭት መሰረቱ ግላዊ ፍላጎት ነው፡፡ ለዚህ ፍላጎቱ ሌላ ሰበብ ይሆነው ዘንድ የብሔር አሊያም የቋንቋ ሽፋን ሊሰጠው ይችላል፡፡ ይሁንና ሁሉም ሰበብ የግል ፍላጎቱ ማሳኪያ ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ያዋጣኛል ብሎ የሚያስበውን ጥላ ማግኘት የግድ ይለዋል፡፡ ያኔ ደግሞ ግጭት ይፈጠራል ማለት ነው፡፡
አንድ በዚህ ጉዳይ የሚጽፉ፣ በሰላም ጉዳይ ላይ የሚሰሩ፣ የሚያስተምሩና ምርምር የሚያደርጉ በአሜሪካ በኢስተርን ዩኒቨርሲቲ ያሉ ፕሮፌሰር ጆን ፖል ሲናገሩ፤ ልክ በቅዱስ መጽሐፍ ላይ በመጀመሪያ ሰማይና ምድር ነበር እንደሚባለው ሁሉ እርሳቸውም ሐሳባቸውን የሚያጋሩት ይህንን ጽንሰ ሐሳብ ወስደው ነው፡፡ እርሳቸው ይጽፉ የነበረው በክርስትና እይታ ውስጥም ሆነው ነው፡፡
ፕሮፌሰሩ በመጽሐፍ ቅዱስ እይታ ግጭት የተጀመረው በኤደን ገነት ውስጥ ነው ይላሉ፡፡ በሌሎች እምነቶች ዘንድ የተለየ ነገር መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ አዳምና ሄዋን ግን አትብሉ የተባሉትን የሕይወት ዛፍ ከበሉ በኋላ እርስ በእርሳቸው መካሰስ መጀመራቸውን እናያለን፡፡ ግጭት የጀመረው በዚያን ጊዜ ነው፡፡ የአዳምና ሄዋን ልጆች ሁለት ብቻ ሆነው ሳለ በመካከላቸው የፍላጎት አለመጣጣም ስለነበር ግጭት ተፈጠረ፡፡ ስለሆነም ግጭት ከሰው ልጅ ጋር የነበረ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ነገር ግን መካከለኛው ነገር ምንድን ነው? ተብሎ ሲጠየቅ የፍላጎት መለያየት ነው። ፍላጎትን አለማስተናገድ ሲከሰት አለመጣጣሞች እያየሉና እየባሱ መጥተው ግጭት ይፈጠራል፡፡ ግጭት ውጤት ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ የግጭት ሰበብ ናቸው ብለው እርስዎ የጠቃቀሷቸው እንደ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ የኢኮኖሚ ድቀት ብሎም ቋንቋ በእርግጥ ወደግጭት የሚወሰዱ ምክንያቶች መሆን ይችላሉ?
ዶክተር ልደቱ፡– እኔ የማምነው አይደሉም ብዬ ነው፤ ምክንያቱም የበለጸጉ አገሮች ዘንድም ይህን መሰል ችግር አለ፡፡ ይህ ችግር የደሃ አገሮች ጉዳይ ብቻ አይደለም።ለእኛ
ለድሆች ብቻ የተሰራ መሳሪያ አይደለም፡፡ በበለጸጉ አገራትም አይነቱና መጠኑ ይለያይ እንጂ ግጭቶች አሉ። እርግጥ ነው የሰው አስተሳሰብና አመለካከት እየዳበረ በሄደ ቁጥር ግጭቶችን የምንቆጣጠርበት መንገድ በዚያው ልክ እየተሻለ የሚመጣ ስለሚሆን ሰላማዊ የሆነ ነገር እየበዛ መምጣት ይችላል፡፡
ለምሳሌ በአሜሪካ አገር በትራምፕ አስተዳደር ወቅት ግጭቶች ነበሩ፡፡ አሁንም በተወሰነ ደረጃም ቢሆኑ ግጭቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ምን ያህል ተጽዕኖ ያሳድራሉ የሚለው ሲታይ መልሱ ያን ያህል አይደለም ነው። ስለዚህ ከሰው አስተሳሰብ ጋር ይገናኛል ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽኩት ግጭቶች ውጤቶች ናቸው፡፡ ውጤቶች የሚሆኑት የሐሳብ እና የአመለካከት ልዩነቶችን እንደሚገባቸው ማስተናገድ ሳይኖር ሲቀር ነው። እንደሚገባቸው ማስተናገድ የማይቻልበት ምክንያት ደግሞ የሰው ልጅ የአመለካከት ልዩነት፣ ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት፣ የመደማመጥ ባህል እድገትና እነዚህን መሰል ነገሮች ይወስናል፡፡ እነዚህ በዳበሩበት ሁኔታ ግጭቶች ይቀንሳሉ፡፡ ነገር ግን ከግጭት ነጻ መሆን አይቻልም፡፡ መርሳት የሌለብን ነገር ከግጭት ነጻ የሆነ ዓለም ልንፈጠር አለመቻላችን ነው።
ግጭቱ ግን አገር አቀፍ ነው? ወይም ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያፈናቅል ነው? አሊያም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት መስዋዕት ያደርጋል? ማህበራዊ መስተጋብሩ እንዲቃወስ ያደርጋል? የሚለው ሲስተዋል፤ ምላሹ እዛ ደረጃ መድረስ የለበትም ነው። ስለዚህም ዋናው እዛ ደረጃ እንዳይደረስ በመካከል የሚደረገው ሂደት ነው፡፡ እሱ ሂደት የአስተሳሰብ እድገትና ብስለት እንዲሁም የመደማመጡ ባህል በተጨማሪም መካከለኛ የሚሆኑ መዋቅሮች ግጭቶች እንዲቀንሱ ያደርጋሉ፡፡
ቀድሞ እንደተነሳው ዋና ጥያቄ ሲመለስ ቋንቋን፣ ባህልን፣ ብሔርን፣ ኃይማኖትንና መሰል ጉዳዮችን ሰበብ ማድረግ ትክክል አይደለም፡፡ እነሱም ሊፈጥሩት የሚችሉት ነገር አይደለም፡፡ ሁሉም የተለያየ ባህል፣ እምነትና ቋንቋ ሊኖረው ይችላል፡፡ ሁሉም የየራሱን መተግበር የሚያስችለው መብት ካለው እና መብቱ ከተከበረለት እንዲሁም አንዱ በሌላው ላይ ተጽዕኖ የማያሳደር ከሆነ፤ አንዱ ሲናገር ሌላው ካዳመጠ ግጭት የሚመጣበት መንገድ አይኖርም፡፡ ስለዚህ ለግጭት መፈጠር ሰበብ የሆኑ አመክንዮች በእርግጥም ሰበብ መሆን ያልነበረባቸው ናቸው፡፡ ሰዎች ግን ብቻቸውን ሐሳባቸውን ሊያራምዱና ሊያስተናግዱ የሚችሉበት አውድ ስለሚፈልጉ ሁሌ ሰዎች ያንን አውድ ይመርጣሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በየአካባቢው ለሚፈጠሩ ግጭቶች የአካባቢው ሽማግሌዎች ብቻ መፍትሄ ያመጡለት ነበር፤ በአሁን ጊዜ ግን ሽማግሌዎችም ሆኑ የእምነት አባቶች የመደመጣቸው ሁኔታ እየተዳከመ መጥቷልና ይህ ከምን የመነጨ ነው?
ዶክተር ልደቱ፡- ይህን ጉዳይ ዝም ብለን የምንፈታው ጉዳይ አይደለም፡፡ በጣም ጥልቅ ከመሆኑ አንጻር ጥናት የሚጠይቅ ነው፡፡ ስለሆነም የምንናገረው በይሆናል ነው። የአገር ሽማግሌዎች ወይም የእምነት አባቶች ሊደመጡ ያልቻሉት ስለምንድን ነው? ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ አንደኛው የማህበረሰብ ለውጥ ነው። ይህ ለውጥ
የሚመጣው ደግሞ ከተለያዩ ጉዳዮች ነው። በዋናነት ግሎባላይዜሽን ነው፡፡ ግሎባላይዜሽን ብቻ ሳይሆን ድህረ ዘመናዊነት (postmodernism) የሚል ጽንሰ ሐሳብም አለ፡፡ ይህ ጽንሰ ሐሳብ ደግሞ የሚያስተናግደው እውነት የሚባለው ነገር የግል ነው፤ በመሆኑም ሁሉን አቀፍ እውነት የለም፡፡
በሁሉም ቦታና ለሁሉም ሰው የሚያገለግል እውነት የለም፡፡ የአንድ ሰው እውነት የዛ ሰው እውነት ነው፤ የእኔ አውነት ደግሞ የእኔ እውነት ነው፡፡ የእኔም የዛ ሰው እውነት ሊከበር ይገባል የሚል አስተሳሰብ የገነነበት ዘመን ነው፡፡ ይህ ድህረ ዘመናዊነት ወደ አገራችን በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች አማካይነት የማይገባበት መንገድ የለም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከዚህ ነጻ አይደለችም፡፡ ስለዚህ ይህ አስተሳሰብ ባህላችን ውስጥ ገብቶ ይሆን ብዬ አስባለሁ፡፡
ከዚህ በፊት ለአገር መፍትሄ የሆኑ እንዲሁም የሕብረተሰብ ክፍሎች ድርና ማግ ሆነው እንዲቆዩ ምክንያት የሆኑ እሴቶችን እሱ የእናንተ እውነት እንጂ የእኛ እውነት አይደለም የሚል ማህበረሰብ ተፈጥሮ ይሆንን የሚል ይመስላል፡፡ ስለዚህ ከዚህ ከድህረ ዘመናዊነት ጋር በተያያዘ ትውልዱ የራሱን ሐሳብ የሚይዝና የራሱን ሐሳብ የሚያራምድ ሆኖ ተገኝቶ ሊ ሆን ይችላል፡፡
ሁለተኛው ምናልባት የሃይማኖት መሪዎች፣ የእምነት አባቶች ወይም ደግሞ የአገር ሽማግሌዎች ከዚህኛውም ከዚያኛውም ወገን ሳይሆኑ መካከለኛውን ቦታ ይዘው የማግባባት ብሎም የማስታረቅ ሥራ በመሥራት የመካከለኛነት ሚና መጫወት ሲገባቸው ወደአንደኛው ወገን አድልተው የአንደኛውን ወገን ሐሳብ የሚያራምዱና የሚደግፉ ብሎም ለዛ ሐሳብ የሚቆረቆሩ፣ ሌላኛውን የሚወቅሱ አንደኛውን ደግሞ የሚኮንኑ ሆነው ከተገኙስ? የሚል አተያይም አለኝ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የአመለካከት ለውጥ በማምጣት በግልጽ አቋማቸውን ከማስተካከል በስተቀር ችግር ነው፡፡
ጥፋተኛውን ጥፋተኛ ነህ የማለት ጉልበት ካላቸው፣ ትክክል ያደረገውን ደግሞ አበጀህ ማለት ከጀመሩ ያኔ እነርሱ ከዚህ ቀደም ያደሉለትና ያደንቁት የነበረውን አካል ጥፋት ሲያጠፋ ተው ሊሉት ከቻሉ፤ ከዚህ ቀደም ሲኮንኑትና ሲያገሉት የነበረው ጥሩ ነገር ሰርቶ ሲገኝ ጥሩ አደረግህ ማለት ከቻሉ ያኔ የመካከለኝነት ስራቸውን ለመስራት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ቀደም ምናልባት በማስታረቅ የመካከለኝነት ድርሻቸውን ሲወጡ የነበረው ፖለቲካዊ ወገንተኝነት፤ የቋንቋ፣ የዘርና ብሔር ወገንተኝነት ባልነበረበት ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ ወጣቱ ሐሳባቸውን መቀበል የተቸገረ አሁን አሁን የመካከለኛነት ድርሻቸው በተለያዩ ምክንያቶች በመጥፋቱ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን በጉዳዩ ላይ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የተለያየ አመለካከት ይዘው ወዲህና ወዲያ የሚሳሳቡትን የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲቀራረቡ ለማድረግ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሚና የት ድረስ መዝለቅ ይችላል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ልደቱ፡- የተቋቋመው የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሶስት ነገሮች ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንደኛው የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በአዋጅ የተፈቀደላቸው ልክ ድረስ መንቀሳቀስ እስከቻሉ ድረስ ለውጥ ይመጣል፡፡ ያ የተሰመረላቸው መስመር ድንበር ከሌለውና ሁሉንም ወገን በእኩል ሁኔታ ለማመካከር የሚችል ከሆነ ውጤታማ ሊሆን ይችላል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ጉዳዩ የሚመለከታቸው እነርሱ ብቻ ባለመሆናቸው ሐሳብ የሚያቀርብ ክፍል አለና ህብረተሰቡ በተሳተፈበት ልክ ይሆናል፡፡ በህብረተሰብ ዘንድ የማይናቁ የተለያዩ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚያ እሴቶች ለምክክር ኮሚሽኑ የመመካከሪያ ሐዲድ መሆን ሲችሉ ማለትም ሐሳብ መንሸራሸር ሲችል ውጤታማ መሆን ይችላል፡፡
ኮሚሽኑ መስራት አለበት ብዬ የማምነው የማንም ወገን ሳይሆን የመካከለኝነትን ስራ ነው፡፡ የዚህኛውም የዚያኛውም ወገን አለመሆን ማለት ነው፡፡ እያንዳንዳችን የግላችን የፖለቲካ አቋም፣ እምነት ሊኖረን ይችላል፤ እርሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ለያዙት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ምንም አይነት የተለየ ዝንባሌ ሳያሳዩና ምንም አይነት የወገንተኝነት ስሜት ሳይንጸባረቅባቸው ሁሉንም ሐሳብ እስከቻሉ ድረስ ማዳመጥ ያሻል፡፡ የተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሐሳባቸው የግድ ስፍራ እንዲያገኝ ከመፈለግ አንጻር ብቻ ሳይሆን በእርግጥም አገራዊ እርቀ ሰላም እንዲመጣ የሚጠበቅባቸውን ለአገራቸው እንደሚያበረክቱ ቆጥረው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል፡፡
ገዥው ፓርቲም እንደአስፈጻሚና ሜዳውን እንዳዘጋጀ አካል ገና ለገና ገዥ ነኝ ብሎ ሳያስብ እሱም እንደሌላው ሁሉ ማዳመጥ ሲችል፤ ሌሎችም ነገሮች መስመራቸውን ጠበቀው እንዲካሄዱ ከተደረጉ እንደታሰበው ኮሚሽኑ አጠናቅቃለሁ ብሎ በያዘው የጊዜ ገደብ ውስጥ ግሩም የሆነችውን ኢትዮጵያን ማየት እንችላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት ለመፍታት በዋናነት ምን አይነት አካሄድን መከተል ይመረጣል? ከዚህ አንጻር የሌሎች አገሮች ልምድ የሚያሳየው ምንድን ነው?
ዶክተር ልደቱ፡- በቅርቡ ባደረግሁት ጥናት መሰረት የተለያዩ አገሮች ተሞክሮ ምን ይመስላል? የሚለውን ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ለዚህ ጉዳይ በተዘጋጀ አንድ የምክክር ጉባኤና የፓናል ውይይት ላይ ጽሁፍ አቅርቤያለሁ፤ ጽሁፍ በቤተክርስቲያን ደረጃ የተዘጋጀ ስለሆነ የቀረበውም በዛ ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ ይሁንና እነዚያን ጉዳዮች ማየት ብንችል ጥሩ ነገር ማግኘት እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ለምሳሌ ኒካራጓ የተደረገውን ብናይ፤ የዛሬ አስራ ምናምን ዓመት የነበረ ሂደት ውስጥ ከመንግስት ጋር መስማማት ያልቻሉ አካላት ነበሩ፡፡ እነዚህም የራሳቸው አቋም ያላቸው ናቸውና በመካከላቸው ለስምንት ዓመታት የዘለቀ መራራ ጦርነት ተካሂዶ ነበር፡፡ የሚገርመው ነገር ግን ጦርነቱ እየተካሄደ ውይይቶች መካሄድ ቻሉ፡፡ እርግጥ ነው በዚህ ውስጥ የመካከለኝነትን ሚና የሚጫወቱ ተቋማት ነበሩ፡፡ እነዚህ የመካከለኝነትን ሚና የሚጫወቱ ሰዎች ሁለቱን አካላት ለማዳመጥ ይሞክሩ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሳ ይህ ነው የማይባል መስዋዕትነትን ከፍለዋል። ቢሆንም ከስምንት ዓመት ደም አፍሳሽ ጦርነት በኋላ ወደሰላም መምጣት ተችሏል፡፡ ስለዚህም መደማመጥ ትልቅ ነገር ነው፡፡
ሁለተኛዋ አገር ሶሪያ ናት፤ ሶሪያ እርስ በእርስ በመናቆር ግሩም የሆነ ማንነቷ ቢበላሽም፤ የዛሬን አያድርገውና ጥሩ የምትባል አገር ነበረች፡፡ በመከራ ውስጥ ሆና በነበረበት ጊዜ መልካም የሆኑ ነገሮች ነበሩ፡፡ በሚያሳዝን መልኩ ተግባራዊ መሆን አልቻለም፡፡ መደማመጥን ገዥው መንግስት በጄ ሊል አልቻለም፡፡ በተለይ አንዲት አባቷ ዲፕሎማት የሆነች ሃይንድ የምትባል ሶሪያዊት፣ አገሯ ውስጥ ሰላም ይሰፍን ዘንድ ትሻ ነበርና ለዚህ ሰላም መስፈን ምቹ መደላድልን ለመፍጠር ትጥር ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የሙግት ልምድ እንዲኖር ማድረጓ ነው፡፡ ሙግቶች ሲካሄዱ ማዳመጥ እንደ ልማድ ይቆጠር ነበር፡፡
ይህች ሴት በአገሯ ምድር ንግግር እንዲያደርጉ ትጋብዛቸው ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ እስራኤላዊ የሆነ ሰው ነው፤ እስራኤላዊ መሆኑ ብቻ አይደለም፤ የአይሁዶች እምነት መምህር የሆነ እና በዜግነቱ ደግሞ አሜሪካ የሆነን ሰው ነበር፡፡ በእርግጥ የግጭት ልውጠት ባለሞያም ነው። ሶሪያ ከተማ ውስጥ እስከ ሶስት ሺ ሰዎች በሚካፈሉበት በትልልቅ መድረኮች ይህ ሰው ተጋብዞ እርሱ የእስራኤልን፤ እርሷ ደግሞ የሶሪያን አመለካከት ያቀርቡ ነበር፡፡ ሶሪያ እንብርት ላይ ይህ ውይይት ይከናወን ነበር፡፡ እርሱ የእስራኤልንና የአይሁድን ሐሳብ ሲያጸባርቅ እርሷ ደግሞ የሶሪያ ስታንጸባርቅ ምን አይነት መደማመጥ እንደነበር ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ይህ የሆነው ሶሪያ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ከመግባቷ በፊት ነው፡፡
እኔ እዚህ ላይ ያለኝ ሐሳብ ሶሪያውያን ይህን ወርቃማ እድል አልተጠቀሙበትም የሚል ነው፡፡ ካለመጠቀማቸውም የተነሳ አሁን የደረሰባቸውን ዘግናኝ ነገር ሊገጥሟቸው ችሏል፡፡ በወቅቱ የመደማመጥ ባህል ነበራቸው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ስኬት ብቻ ሳይሆን ውድቀትም ልንማርበት ይገባል፡፡ ይህን አይነት ወርቃማ ተሞክሮ ለአንገብጋቢ ጉዳያቸው ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ የሃይንድ ዓላማ መልካም ነው፤ ስትራቴጂዋም አብዮት ማስነሳት አይደለም፡፡ የመድረኩ ዓላማ መሪዎች ዘንድ እንዲደረስና እነርሱም ወደመደማመጥ እንዲመጡ ነው፡፡
በአንድ ወቅት ይህቺ ሴት፣ የሶሪያን ቀዳማዊት እመቤትን አግኝታ ፕሬዚዳንት ባሽር አላስድን አንድ ጥያቄ እንድታቀርብላት ለመነቻት፡፡ ይኸውም ‹በፊትዎ ሁለት እድል አለ፤ አንድም የዘር ጭፍጨፋ ፈጽሞ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደቀረበው እንደዩጎዝላቪያው
መሪ ስሎቦዳን ሚሎሶቪች መሆን ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የሰላም አባት ተብለው እንደታወቁት እንደ ደቡብ አፍሪካው መሪ እንደማንዴላ መሆን ነው፡፡ ስለዚህ ከሁለቱ የቱን ትመርጣለህ?› ስትዪ ጠይቂልኝ አለቻት። አክላ የእርሷ ምኞት እንደማንዴላ እንዲሆን ስለነበር ‹እባክሽን እንደማንዴላ ሁን በይው› ስትልም ተማጸነቻት። መሪዎቹ ሰምተው ቢሆን ኖሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሶሪያውያን አይፈናቀሉም ነበር፤ የሰው ሕይወት አይጠፋም ነበር፡፡ እነዚያ የሚያማምሩ ከተሞች ዶግ አመድ አይሆኑም ነበር። የሶሪያውያን መሪዎች ግን ይህን መጠቀም ባለመቻላቸው የከፋ ነገር ሊከሰት ግድ ሆነ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምናልባት ከአህጉር አንጻር ቅርባችን የሆነውን ተሞክሮ ለማንሳት ያህል ከደቡብ አፍሪካ የምንወሰደው ልምድስ ምን ሊሆን ይችላል?
ዶክተር ልደቱ፡- በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት ከተገረሰሰ በኋላ ኔልሰን ማንዴላ ወደ ስልጣን በሚመጡበት ጊዜ አገሪቱ ውጥረት ውስጥ ነበረች፡፡ በዚህ ወቅት አንድ ወሳኝ የሆነ ተቋም ተመሰረተ፡፡ ተቋሙም ‹እውነትና እርቅ ኮሚሽን› የሚል መጠሪያ የነበረው ነው። ይህን ሐሳብ ያቀረቡት ሰው በጊዜው የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩ ናቸው፡፡ ሌሎች አካላትም ለተቋሙ እውቅና ሰጡት፡፡
ኮሚሽኑ በወቅቱ ሁለት አማራጮች ነበሩት፡፡ አንደኛው በአፓርታይድ ስርዓት ውስጥ በዘር መድልዎና በዘር ጭፍጨፋ ንቁ ተሳትፎ ያላቸውን ሰዎች በሙሉ አስፈላጊ ሰነዶችን በማሰናዳት ለፍርድ ማቅረብ የሚል ነበር፡፡ ይህ ግን ሲያስቡት ጊዜና ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ ተሰማቸው፡፡ ስለዚህ ሁለተኛ አማራጭ ብለው የያዙት ሁሉም ነገር እንዳልሆነ አሊያም እንዳልተፈጠረ ለምን አንቆጥረውም የሚል ነበር፡፡
እንዳልተፈጠረ ነገር መርሳት የቅርብ ጊዜ ክስተት በመሆኑ ቁስሉ ያልሻረ ነውና የማይሆን ነገር ነው። ሁሉንም ለፍርድ ማቅረቡ ደግሞ ጊዜና ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ነው።ስለዚህ ሁለቱም አካሄዶች ይቅሩና በደል የደረሰበት ሰው ይምጣና ይንገረን፤ በደል አድራሹ ደግሞ በደል ማድረሱን ይምጣና ይመን፤ ከዚያም ለሰራው ጥፋት ይቅርታ ይጠይቅ፡፡ ይቅርታ ተጠያቂውም ይቅር ይበል፡፡ ‹አይ! ይህ አይሆንም› የሚሉ ካሉ ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት ሂደት ይሂዱ ወደሚለው ሐሳብ መጡ፡፡
ስለዚህ በዚህ አይነት መንገድ እውነትን በመናገር እርቅን ማውረድ ይቻላል ተባለ፡፡ በዚህ አይነት አካሄድ በመጓዛቸው በሰላሟም ሆነ በኢኮኖሚዋም ጠንካራ የሆነችውን የአሁኗን ደቡብ አፍሪካ ለማየት ተችሏል፡፡
በወቅቱም ደቡብ አፍሪካዊው የፀረ አፓርታይድ ታጋይ ሊቀ-ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ‹የዛሬ አሸባሪ የነገ አገር መሪ ሊሆን ይችላልና እንደማመጥና ሰላም ለማምጣት እንትጋ፤ አንድ ቀን ተቀምጠን መነጋገራችን ላይቀር ያልሆነ ስም አንሰጣጥ› ብለው ተናግረው ነበር፡፡ ‹ያለ ይቅርታ ነገ የሚባል ነገር የለም› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው ላይ የሰጡት አንድ ምሳሌ ‹እኛ ደቡብ አፍሪካውያን እንደ ሁለት ተናካሽ ውሻዎችን መምሰል የለብንም፡፡ (እኛ ሲሉ የጠሩትም ጥቁሩንም ነጩን በአንድ ላይ ነው)፡፡ እርስ በእርስ እልህ መጋባት የለብንም፡፡ በደልን እያሰብን ቂም አንያዝ፤ ደግሞም ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ጊዜው የእኛ ነው በሚል ያልተገባ ድርጊት አንፈጽም ሲሉ ነበር። እውነትና እርቅ ኮሚሽን ስራውን ሲሰራ የነበረው እንዲህ በማድረግ ነበር፡፡
እነዚህን የደቡብ አፍሪካና የኒካራጓ ተሞክሮ ትልቅ ምሳሌያችን ማድረግ የሚቻል ሲሆን፣ ሶሪያ ደግሞ ባለማድመጧ ከደረሰባት ውድቀት መማር እንችላለን የሚል እምነት አለኝና እኛ መምረጥ ያለብንን መምረጥ ያለብን ከወዲሁ ነው፤ ያለነው መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው። ብልሆች ብንሆን ከባህሎቻችን፣ ከእምነቶቻችን ውስጥ ያሉ ወርቃማ የሆኑ እሴቶቻችንን በማውጣት መደማመጥ ይኖርብናል፡፡ ዘግናኝ የሆነ ነገር እንኳ ቢነገረን ለማዳመጥ እንሞክር፡፡ የሁሉንም በማዳመጥ ወደ እርቅ እንሂድና አዲስ የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት እድላችንን እንጠቀምበት፡፡ አለበለዚያ እንደሶሪያ የማንሆንበት ምክንያት አይኖርም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አንጻር ፖለቲከኞች ድርሻቸው ምን መሆን አለበት? በምንስ አይነት አግባብ ነው መንቀሳቀስ ያለባቸው?
ዶክተር ልደቱ፡- እዚህ ላይ ማንሳት የምፈልገው ጽንሰ ሐሳብ አለ፡፡ ሁለት የሃርቫርድ ፕሮፌሰሮች ብዝሃነትን እንዴት አድርገን ማስኬድ እንችላለን ብለው ሲያስቡ ሶስት ጽንሰ ሐሳቦችን ለማስቀመጥ ችለዋል፡፡ አንደኛው ማግለል ይቅርና ፍትሃዊ እንሁን የሚል ነው፡፡ አንድ ሰው ከእኛ የተለየ በመሆኑ ብቻ እንደእኛ አልሆነም በሚል አናግልለው የሚል አመለካከት ነው፡፡ ይህን ጽንሰ ሐሳብ ኢትዮጵያ አልፋበታለች፡፡ ሁለተኛው ጽንሰ ሐሳብ ደግሞ ከእኛ ሌላ የሆነው አካል የፈለገውን እንዲያደርግ እንፈቀድለት የሚል ነው፡፡
ይህን ስናደርግለት እምነቱን፣ ባህሉን፣ ቋንቋውን በነጻነት ይለማመዳል፡፡ እንደ እኔ ይህንንም ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች ነው ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ ሶስተኛውና ምርጡ ጽንሰ ሐሳብ ግን ከሁለቱ የተለየ ነው። ሶስተኛው ለብዝሃነት ያስፈልጋል ከምንለው ሌላ ሶስተኛ አካል ምንድን ነው ልዩ የሆነው እሴቱ? ምንስ ውበትና ቁም ነገር አለው? ከዛ ቁምነገረ ስለምን እኛ አንማርም? ያንን ባህል ስለምን ባህላችን አናደርገውም? የሚል ነው፡፡ በዚህ አካሄድ ደግሞ አንድ መልካም የሆነ እሴት የአንድ ቡድን ብቻ መሆኑ ይቀርና የሁላችንም ጭምር ይሆናል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ከሲዳማ አፊኒ (እንደማመጥ) የሚለው እና ከጋሞ አባቶች የሚወሰዱ ግሩም የሆኑ እሴቶች አሉ፤ ስለዚህ ይህን ግሩም እሴት የሁላችን ብናደርገውስ?
ኢትዮጵያውያን ግን የምናውቀው ከአንዱ ጥሩ የሆነ የምግብ አሰራር ባህልን መውሰድን ነው፡፡ የጉራጌ ክትፎ፣ የኦሮሞ ጨጨብሳ፣ የትግሬ አንባሻ እና የሌሎችንም እያልን ወስደን ኢትዮጵያዊ ባህል አድርገናቸዋል፡፡ የአገራችንን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የውጭውንም እንደ ላዛኛና ፒዛ የምግብ አሰራርን እንጋራለን፡፡ ምግብን በዚህ ደረጃ የምንጋራ ከሆነ ጥሩ እሴትን ስለምን አንጋራም? የፖለቲካ ተፎካካሪዎች ከዚሁ ባህል የተቀዱ ሰዎች ናቸው፡፡ ሁሉም ከየመጡበት ብሔር ያለውን እሴት ብቻ ከሚያንጸባርቁ የሌሎችንም ቢጋሩ መልካም ነው፡፡
ይህን ለማድረግ ደግሞ በመጀመሪያ መደማመጥ የግድ ይለናል፡፡ ምናልባት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ያልሆኑ ትርክቶች ሊሆኑ ይችላሉና ስንደማመጥ ግን ለይተን ለማወቅ እድሉን እናገኛለን፡፡ ያኔ በከንቱ ያጣሉን የነበሩ ነገሮችን ሁሉ ማወቅ እንጀምራለንና ከትልቅ ይቅርታ ጋር ለፖለቲከኞችም ሆነ ለማህበረሰብ አንቂዎች የማስተላልፈው መልዕክት ቢኖረኝ እንደማመጥ የሚል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከሰላም መስፈን አኳያ ሲታይ የሃይማኖት አባቶች ትልቁን ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ነው የሚታሰበው፤ ይሁንና ሃይማኖተኞች የሚባሉት ከፖለቲካው ጋር ተደባልቀዋል፤ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዶክተር ልደቱ፡- ግልጽ ነው፤ ሚናቸውን እንደ ሚገባው እየተወጡ አይደሉም፡፡ ስለዚህም ከወገንተኝነት ነጻ መውጣት አለባቸው፡፡ ከየትኛውም ዘር ቢመጡም መጫወት ያለባቸው የመካከለኝነትን ሚና ነው፡፡ ሲሰሩ ደግሞ በመጀመሪያ ማድረግ ያለባቸው ከራስ መጀመርን ነው፡፡ በየቤተ እምነታቸው ውስጥ እየሰጡ ያለውን የአመራርነት ሚና መፈተሸ አለባቸው። ስለዚህም ግጭትን መፍታት መጀመር ያለባቸው ከቤታቸው ነው። የቤታቸውን ችግር ካልፈቱ ወደውጭ መውጣት አይችሉም፡፡ ስለዚህም ጥቅም ተኮር ከሆነ አሰራር ይውጡና የእምነት ክፍሎቻቸውን ወደማበጃጀት ይግቡ። የእኔ ወገን ስልጣን ማግኘት አለበት ከሚለው አስተሳሰብ ይውጡ፡፡ ይህንንም በተግባር ያሳዩን፡፡ ያኔ የመካከለኝነት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ምንም እንኳ አዎንታዊ ሚና ቢኖረውም፤ ለግጭት መፈጠር ትልቁን አስተዋጽኦ በመጫወት ላይ ይገኛል፤ ከአሉታዊ ጎኑ ይልቅ ህብረተሰቡ በአሉታዊ ጎኑ ለመጠቀም ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ዶክተር ልደቱ፡- በአገር መሪዎችና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል መደማመጥ ቢኖር የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጾች ምን ሌላ ነገር ሊያወሩ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ሰዎች ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መንገዶች ነበሩ። ለምሳሌ ቀልዶች ነበሩ፡፡ ይህ ማለት ህብረተሰቡ ሐሳቡን የሚገልጽበት መድረክ ሲያጣ የሆነ መንገድ መፈለጉ አይቀርም፤ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ለሐሳቡ መግለጫ የሚሆን ነገር አምጥቶ በህብረተሰቡ እጅ ላይ አደረገ እንጂ።እንዳልተደመጠ የሚያስብና ልዩነት አለኝ ብሎ የሚያምን ሰው በተፈጠረለት እድል ሁሉ ሐሳቡን ይገልጻል፡፡
ነገር ግን መደማመጥ በመሪዎቻችን መካከል ቢኖር ኖሮ ግን አፍራሽ የሆነ ሐሳቦች የመኖር እድል አይኖራቸውም። ሌላው ደግሞ አፍራሽ የሆነ ሐሳብ ቢመጣ እንኳ በመንግስት ይደመጣል፡፡ ወደ መፍትሄም መምጣት ይችላል፡፡ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ የፖለቲካ መድረክ መሆኑ ይቀርና አገባሁ፤ ወለድኩ፤ ተመርቅኩና መሰል መረጃዎች የሚጻፉበት ይሆናል፡፡ በዚህም የመረጃ ምንጭ መሆን ይጀምራሉ እንጂ የጦርነት ምንጭ አይሆኑም። ስለዚህ አሁንም እንደማመጥ፤ ስንደማመጥ አገር አትጠፋም፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የጠቢቡ ሰለሞንን ጥቅስ ብጠቅስ ደስ ይለኛል፤ ይኸውም ‹ብዙ ምክር ባለበት ድል አለ› ይላል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን እንመካከር፡፡ ይህን ስናደርግ ውብና ግሩም ህዝቦች መሆን እንችላለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ዶክተር ልደቱ፡- እኔም ስለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014