ባለፈው ማክሰኞ የህዝብ እንደራሴዎች ፊት ቀርበው የመንግስትን ወቅታዊ ሁኔታ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በብዙ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥያቄና መልሱ ከቃኟቸው ጉዳዮች መካከል ደግሞ አንዱ የሃይማኖት ተቋማትን የሚመለከት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋማቱን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር ከዚህ ቀደም ብዙዎች ደፍረው ሊናገሩት ያልቻሉትን ጉዳይ አንስተዋል፡፡ እንዲህ አሉ፤ ‹‹በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት የመሬት ሊዝ የማይከፍሉት፣ ኦዲት የማይደረጉትና ታክስ የማይከፍሉት የሃይማኖት ተቋማት እንዳሻቸው ይሁኑ የሚል ህግ ስላለ አይደለም። እንዲህ አይነት ህግ የለም። አሜሪካ ውስጥ ማንኛውም የሃይማኖት ተቋም ቤቱን ይገዛሃል። ቸርች ይገዛል፣ መስጂድ ይገዛል። ዝም ብሎ የሃይማኖት ተቋም ነኝ ብሎ ነገር የለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ የሚሆነው ለምንድነው?፣ የሃይማኖት ተቋማት የውስጥ ማንነት ላይ ይሰራሉ። ሞራል ላይ ይሰራሉ።
ሰላም ወዳድነት ላይ ይሰራሉ። አንድ አንዱ ቢቀርም ግድ የለም፤ መንግስት የማይሸፍነውን ነገር ይሸፍናሉ፤ መሬት ቢቀር፣ ታክስ ቢቀር፣ ኦዲት ባይደረጉ ችግር የለውም። እኛ የማንሰራቸውን ወሳኝ ስራዎች ስለሚሰሩ ይካካሳል ነው እሳቤው። እየሆነ ያለው ግን የተገላቢጦሽ ነው። ከፍተኛ የሞራል ዝቅጠት ያለው የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ነው። ከፍተኛ ምዝበራ ያለው የሃይማኖት ተቋማት ውስጥ ነው። እንኳን የውስጥ ማንነት ሊሰሩ ይቅርና የውስጥ ማንነት በይፋ እያፈረሱ ይውላሉ።››
ለወትሮው የሃይማኖት ተቋማት እንዲህ በቀላሉ ሂስ የሚሰጥባቸው ተቋማት አይደሉም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት የሚሰጡት አገልግሎት ለህብረተሰቡ ያለው ፋይዳ በጣም ከፍተኛና በሌላ በማንም የማይተካ ነው ተብሎ ስለሚታመን ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ተቋማቱ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር እነሱን መንካት ብዙ አላስፈላጊ ውጤት የሚያስከትል በመሆኑ ነው፡፡ ይህ የመንግስት ዝምታ ግን አሁን አሁን በትክክለኛው መልኩ ግንዛቤ የተወሰደበት አይመስልም፡፡
በየሃይማኖት ተቋማቱ የሚታየው የስርአት ጉድለት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አሁን ላይ እንዲያውም በአማኞቹ እንኳ የሚታይ አይን ያወጡ ግድፈቶች በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ እየተስተዋሉ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ችግር የሆነው እና ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ በየሃይማኖት ተቋማቱ ውስጥ መሽጎ የሚንቀሳቀሰው እና ፖለቲካን ከሃይማኖት አዳቅሎ የተሰማራው ጽንፈኛ ኃይል ነው፡፡ ይህ ኃይል የአገር ደህንነት ስጋት ነው፡፡ ለሃይማኖት ተቋማቱ መሰረታዊ ተልእኮ መሳካትም እንቅፋት ነው፡፡
የአማኞችን መንፈሳዊ ሕይወት በማነጽ ረገድም ያለው ድርሻ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ምናልባትም ምንም ድርሻ የለውም ማለት እንችላለን፡፡ ይህ ኃይል አሁን ላይ ኦዲተር የማያየውን እና ባለቤት አልባ የሚመስለውን የሃይማኖት ተቋማት ገንዘብ እየቦጠቦጠ ክፉኛ በመወፈሩ ከመንግስት ጋር አቅም ወደ መለካካት ደርሷል፡፡ ይህ ጽንፈኛ ኃይል ስለ ምእመናን ሞራል ድቀትም ሆነ ስላለበት ተቋም ተልእኮ አይጨነቅም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ የሃይማኖት ተቋማት የመሬት ሊዝ አይከፍሉም፤ ግብርም አይቆረጥባቸውም፤ ኦዲተርም አይጎበኛቸውም፡፡ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ከላይ እንደተገለጸው ነው።
የአገሪቱ ህገ መንግስትም መንግስት እና ሃይማኖት ፈጽሞ የተለያዩ መሆናቸውንና አንዳቸው የሌላቸው የውስጥ ጉዳይ ላይ እንደማይገቡ ይደነግጋል፡፡ ይህ የግብር እና የኦዲት ነጻነትም ከዚህ እሳቤ ጋር የሚሄድ ነው፡፡ ታዲያ ግን አሁን ባለው ሁኔታ መንግስት እና የሃይማኖት ተቋማት መስመራቸውን ጠብቀው እየሄዱ ነው? መልሱ አይደለም ነው፡፡ በሃይማኖት ተቋማት በኩል መንግስት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ እየገባብን ነው የሚል ስሞታ አለ፡፡
በመንግስት በኩልም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የተደበቀ የፖለቲካ ኃይል አለ የሚል እምነት አለ፡፡ የሁለቱን ክርክር ወደ ጎን ትተን በአይናችን ያየነውን ብንናገር በሃይማኖት ተቋማት መድረኮች የሚደረጉ ስብከቶች፤ በቴሌቪዥናቸው የሚተላለፉ ፕሮግራሞች፤ በአደባባይ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ የሚያመለክቱት ሃይማኖታዊ ስራው ሁለተኛ ሆኖ ቀዳሚው ጉዳይ ፖለቲካ እየሆነ ነው፡፡ ይህን የሚደርገው ደግሞ ከላይ የገለጥነው ለጊዜው አቅም የገነባ የመሰለው ጽንፈኛ ሀይል ነው፡፡ ይህ አደገኛ ችግር አለው፡፡
ከችግሮቹ ዋነኛው እና ቀዳሚው ግን የዚህ ሀይል የአገር ደህንነት ስጋት መሆን ሳይሆን ተቋማቱ መሰረታዊ ተልእኮአቸውን እንዲስቱ ማድረጉ ላይ ነው፡፡ የሃይማኖት ተቋማቱ መሰረታዊ ተልእኮቸውን በመተዋቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉት አይነት የሞራል ዝቅጠት እየዋጣቸው ነው፡፡
የሞራል ዝቅጠቱን በሁለት መልኩ ልናየው እንችላለን፡፡ አንደኛው በተቋማቱ ውስጥ ያለ ሲሆን ሁለተኛው በአማኞቻቸው ዘንድ ያለው ብለን፡፡ በተቋማቱ ውስጥ ያለው የሞራል ዝቅጠት በአማኞች ገንዘብ ሚሊየነር የሆኑ አገልጋዮችን እና የቤተ እምነት መሪዎችን ከመፍጠር አንስቶ የሃይማኖት ተቋማቱን እንደ መንፈሳዊ ስፍራ ሳይሆን እንደ አንድ ሁነኛ የንግድ ተቋም እስከመቀየር የደረሰ ነው፡፡
ድሀ በሆነች አገር ፤ ለእለት ገቢያቸው በሚታገሉ ምእመናን ተክቦ ቅንጡ መኪና መንዳት ፤ በዘመናዊ ቤት መኖር ፤ በጠባቂዎች ታጅቦ መንቀሳቀስ የተለመደ ትእይንት ሆኗል፡፡ ትናንት የነበሩን የሃይማኖት አባቶች የግላቸውን ኑሮ የሚኖሩ፤ ስባሪ ሳንቲም ከሃይማኖት ተቋም የማይወስዱ ፤ በተቃራኒው ከመሬታቸውም ከንብረታቸውም ቆርሰው ለህዝብ ጥቅም የሚውል ቤተ መቅደስ ወይም መስጊድ እንዲሰራ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ ዛሬ የዚያን ተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡
የሞራል ስብራቱ በውጭ ስናየው ደግሞ በሃይማኖት ተቋማት መዳከም በአገር ደረጃ ስርአት አልበኞች እንዲፈለፈሉ አድርጓል፡፡ ሰውን በአደባባይ ቀጥቅጦ መግደል ፤ የሃይማኖት ተቋማትን ማቃጠል ፤ በቀን ብርሃን መዝረፍ ፤ ህጻናትን ማፈን ፤ ሴቶችን እና አረጋውያንን አስገድዶ መድፈር ወዘተ…የመንግስት መዳከም ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ተቋማት ሀዲድ መሳት ውጤት ነው፡፡
እነዚህ ችግሮች ላይ አሁን ከቁጥጥር በላይ የሆነው ሙስና ፤ ከአመት አመት እያሻቀበ ያለው ፍቺ ፤ ወጣቱን የሰለበው ሱሰኝነት እና ሌሎችን ማህበራዊ ችግሮች ልንጨምር እንችላለን። እነዚህ ሁሉ የሚያመለክቱት የሃይማኖት ተቋማት ከታክስ እና ከኦዲት ነጻ እንዲሆኑ ያረጋቸውን መንፈሳዊ ተልእኮ እያጡት እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህም አሁን ውይይት መጀመር ያስፈልጋል። ውይይቱ ምናልባትም የሃይማኖት ተቋማት ታክስ ይከፈሉ ወይም ኦዲት ይደረጉ የሚል ላይሆን ይችላል።
ነገር ግን ተቋማቱ እንዴት በአቅማቸው እና በተልእኳቸው ልክ እንዲንቀሳቀሱ እናድረጋቸው የሚል ሊሆን ይገባል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ሃይማኖታችንን እንወዳለን ፤ እንፈልገዋለንም፡፡ ነገር ግን ሃይማኖታችንን የምንፈልገው ከነጠንካራ ተቋሙ እና ከሞራል ልእልናው ጋር ነው፡፡ ስለዚህም አሁን ወደ ተልእኳችን መመለስ ያለብን ትክክለኛው ጊዜ ነው፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኔ 13 /2014