የዓለም አገራት በኢኮኖሚ የመበልጸግና የመልማት ታሪክ እንደሚያሳየው፤ የማእድን ሀብት ለኢኮኖሚ ብልጽግናና ልማት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከኢንዱስትሪ አብዮት እስከ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ድረስ ባሉት ሁለት ምዕተ ዓመታት የታዩ ስኬቶችና የአገራት አቅሞች ዕውን መሆን የቻሉት ጥሬ የማዕድን ሀብትን ለተለያዩ ዘርፎች በግብዓትነት በመጠቀም ነው።
እነዚህ ስኬቶች ታድያ ያለ ማዕድን ሀብት የማይታሰቡ ነበሩ፡፡ ለኢኮኖሚ ብልጽግና፣ ለልማትና አጠቃላይ አገራዊ አቅም ግንባታ የተጉ፣ እንዲሁም የሚተጉ አገሮች ከራሳቸው የማዕድን ሀብት አልፈው የጎደላቸውን እና የሌላቸውን ለጥሬ ዕቃ የሚውል ማዕድን ከታዳጊ አገሮች ወስደዋል፤ በመውሰድ ላይም ይገኛሉ።
ከዚህ በተቃራኒው የዓለም አቀፍ አመለካከቶች በታዳጊ አገራት በተለይም በአፍሪካ የማዕድን ሀብት የጥገኝነት፣ የግጭትና የአካባቢ ብክለትና መራቆት መንስኤ፣ በዚህም ሳቢያ የኋላቀርነት ምክንያት አድርገው የሚያትቱ በመሆናቸው ዘርፉ ለዕድገት ያለውን የማይተካ ሚና በአህጉሩ እንዳይጫወት ተገድቦ ቆይቷል። እውነታው ግን ወዲህ ነው፡፡ የግጭት፣ የጥገኝነትና የአካባቢ መራቆት ምንጩ የማዕድን ሀብት ሳይሆን የማዕድን ሀብትን በአግባቡና ከዘርፉ ኃያላን ተጽዕኖ ውጪ የማልማት፤ የማስተዳደርና የመጠቀም ዕድልና አቅም ማጣት ነው።
የኢትዮጵያ ምድር በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ተወዳዳሪ ሊሆኑ በሚችሉና የአገርን ኢኮኖሚ መሸከም በሚችሉ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ባላቸው የማዕድን ሀብቶች የተሞላ መሆኑን በተለያዩ ወቅቶች በተለያዩ አካላት የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ የኢትዮጵያ የማዕድን ልማት ፖሊሲ ሰነድ ላይ እንደተመላከተው፤ በኢትዮጵያ የሥነ ምድር ጥናት፣ እንዲሁም የማዕድን ፍለጋና ምርመራ የተጀመረው በ1831 ሲሆን፣ እስካሁን በተገኙ መረጃዎች መሠረት አገሪቷ ካላት አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ውስጥ 25 በመቶ የሚሆነው የቅድመ-ካምብሪያን (Precambrian) ቅርጸ ልውጥ እና እሳተ-ገሞራ ወለድ ዓለት፣ ተጨማሪ 25 በመቶ የሚሆነው የመካከለኛው ዘመን (Mesozoic) ንብብር ዓለት፣ እና 50 በመቶ የሚሆነው የቅርብ ዘመን (Cenozoic) የእሳተ ገሞራና ንብብር ዓለት የጂኦሎጂ ቅንብር ያለው ነው።
የቅድመ-ካምብሪያን የጂኦሎጂ ቅንብር በተለይም እንደ ወርቅ፣ ብረት፣ መዳብ፣ እና ኒኬል የመሳሰሉ ማዕድናት አለኝታ መሠረት ሲሆን፣ የመካከለኛው ዘመን የጂኦሎጂ ቅንብር ለነዳጅና ብረታ ብረት ነክ ያልሆኑ ማዕድናት መገኛም ነው። በአብዛኛው የአገሪቷን አካባቢ የሚሸፍነው የቅርብ ዘመን የጂኦሎጂ ቅንብር የተፈጥሮ ዘይትና ጋዝ፣ ፖታሽ፣ ጨው፣ የኖራ ድንጋይ፣ ጀሶ፣ የብርጭቆ አሸዋ፣ ዶሎማይት፣ ቤንቶናይት፣ ዳያቶማይት፣ ሶዳ አሽ፣ ፑሚስ፣ ኦፓል እና ዲኝ የመሳሰሉ የኢንዱስትሪ ማዕድናት መገኛ ነው።
ነገር ግን አገሪቱ ከዘርፉ መጠቀም ያለባትን ያህል ተጠቃሚ መሆን ሳትችል ቆይታለች፡፡ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የማዕድን ዘርፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ መሻሻል እያሳየ የመጣ ቢሆንም ዛሬም የሚፈለገው አይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ይህም ቁጭት የሚፈጥር ነው፡፡ አገሪቱ ከዘርፉ መጠቀም ያለባትን ያህል ተጠቃሚ እንዳትሆን ያደረጋት የተለያዩ ምክንያቶች ይነሳሉ። ከእነዚህም መካከል በማዕድኑ ዘርፍ ኢትዮጵያ የመጣችበት መንገድ የእሳቤ ችግሮች እና ሳንካዎች የነበሩበት መሆኑ፣ የጠራ እይታ ያልነበረው መሆኑ፣ የተፈጥሮ ሀብትን እንደ ጸጋ ሳይሆን እንደ ግጭት መንስኤ አድርጎ መቁጠር የመሳሰሉ ችግሮች ነበሩ፡፡ ሌላኛው እስካሁን ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ነገር ግን ዘርፉን ሲፈትን የቆየው በበቂ ደረጃ ክህሎት ያለው የተማረ የሰው ኃይል በዘርፉ አለመኖር እና በዘርፉ ያለው ቴክኖሎጂ ደካማ መሆን ነው፡፡
አንድ ዘርፍ ሊያድግ የሚችለው በዘርፉ የሰለጠነ በቂ የሰው ኃይል ሲኖር ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ውስጥ የተሰማሩት አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን በልምድ የሚሰሩ ናቸው፡፡ በዚህም ራሳቸውም ሆኑ አገሪቱ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም፡፡ ይህ ክፍተት ዘርፉ በዘመናዊ መልኩ እንዳያድግ እና የእውቀት ሽግግር እንዳይኖር እንዲሁም ዘርፉ ቴክኖሎጂን ባማከለ መልኩ እንዳያድግ አድርጓል፡፡ እስካሁን ድረስ በአገሪቱ ውስጥ ያለው የማዕድን ልማትም በአብዛኛው በውጭ አገራት ዜጎች ተይዞ እንዲቆይ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ የማዕድን ልማት ፋብሪካዎች ውስጥ በተለይም እውቀት በሚሹ ሥራዎች ላይ በአመዛኙ ሲሰሩ የሚታዩት የውጭ አገራት ዜጎች ናቸው፡፡ ይህም የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከማሳጣቱም ባሻገር የአገሪቱ ራስ ምታት የሆነውን ሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ለሚደረገው ጥረትም እንቅፋት መሆኑ አልቀረም፡፡
በዘርፉ ሰፊ ኢንቨስትመንት እንዳይኖርም እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተለይም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አነስተኛ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የማዕድን ሚኒስቴር ዘርፉን እየተፈታተኑ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና ዘርፉ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ሚናውን ማበርከት እንዲችል ለማስቻል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከያዛቸው እቅዶች አንዱ በዘርፉ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን በክህሎት በብዛትና በጥራት እንዲኖሩ ማድረግ ሲሆን ከዚህ ጋር በተናበበ መልኩም አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ማግኘት እንድትችል እና ኢትዮጵያዊያን በዘርፉ በስፋት መሳተፍ እንዲችሉ ከአገር ውስጥ እና ከውጭ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ዑማ በቅርቡ የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን ሪፖርት ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ጠቁመዋል፡፡
ከተያዘው ዓመት ጀምሮም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከአገሪቱ ፍላጎት ጋር በሚጣጣሙ የማዕድን ትምህርት ዘርፎች ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች የተወጣጡ 48 የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተከፈተው የኢትዮጵያ ማዕድን ማዕከል እና በውጭ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡
የትምህርት ዘርፎቹ በዘርፉ ያለውን የባለሙያ እጥረት የሚፈታ ሲሆን፤ የትምህርት አሰጣጡ ከንድፈ-ሃሳብ በዘለለ በተግባር የሚሰጥ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል፡፡ በቀጣዮቹ 10 አመታት ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ 675 ተማሪዎችን ለማስተማር እቅድ ተይዟል፡፡
እንደ ኢንጂነር ታከለ ዑማ ማብራሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በውጭ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ካሉት በተጨማሪም በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የእብነበረድ ትምህርት ማዕከል እየተቋቋመ ይገኛል፡፡ ይህን ለመደገፍ ከጣልያን መንግሥት በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ይህም አገሪቱ ከማዕድን ሀብት የተሻለ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስችላት ነው፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከተለያዩ አካላት ጋር በጋራ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ብሎም በማእድን ዘርፍ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ የጂኦሎጂ ዲፓርትመንት ተከፍቶ የነበረ ሲሆን፤ ትኩረት ባለማግኘቱ በዘርፉ የሚፈለገውን ሥራ ሳይሠራ መቆየቱን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርእሰ መስተዳድር በአንድ ወቅት ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረው ነበር፡፡ የማዕድን ሚኒስቴር ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ያቋቋመው የእብነበረድ ትምህርት ማዕከል ይህንን ድክመት በመቅረፍ የክልሉ ወጣች እና አገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ባለሃብቶች እብነበረድ ቋጥኞችን በመውሰድ ሌላ ቦታ እሴት ሲጨምሩ እንደነበር ጠቁመው፤ በአካባቢው የትምህርት ክፍል መቋቋሙ እብነ በረድ እዚያው እሴት ተጨምሮበት ወደ ውጭ እንዲላክ እንዲሁም ወጣቶች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ሥራ እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
በቀጣይም በዘርፉ የሰለጠነ እና ብቁ የሰው ኃይል ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጡት ኢንጂነር ታከለ፤ የማዕድን ዘርፍም ወጣት በሆነ በዘርፉ ተገቢው የትምህርት እና የሙያ ዝግጅት ባላቸው ለቴክኖሎጂ ቅርብ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች መመራት አለበት ተብሎ እንደሚታመን ጠቁመዋል፡፡ ይህን ለማሳካትም ተገቢው ትኩረት ይሰጣል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የሚደረገው ጥረት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የተናገሩት ሚኒስትሩ፤
አገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንድትችል በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት የተጀመረው መልካም ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በየአካባቢው መሰራት አለበት፡፡ በየአካባቢው ያሉ የማዕድን ሀብቶችን በመለየት የማዕድን ሀብቶቹ በሚገኙባቸው አቅራቢያዎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በማዕድኖቹ ዘርፍ ሊሰሩ የሚችሉ ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት አለባቸው፡፡
ከዩኒቨርሲቲዎች ባሻገር የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት አገራዊ ስትራቴጂ መዘርጋት አለበት፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተማሪዎችን በማሰልጠን ብቻ የአገሪቱን የማዕድን ዘርፍ የኢኮኖሚ አለኝታ ማድረግ አይታሰብም፡፡ አገሪቱ ያላትን የማዕድን ዘርፍ የሚመለከት እና ማዕድን ፋይዳዎች ዙሪያ የሚያተኩሩ ትምህርቶች ከታችኛው የትምህርት ክፍሎች ጀምሮ የትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲካተት መደረግ አለበት፡፡
በተለያዩ የማዕድን ንዑስ ዘርፎች ለፋብሪካና ማእድናቱን በጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ የቴክኒክና የቴክኖሎጂ ክህሎቶችን፣ ጥናትና ምርምሮችን ማዳበርና በሥራ ላይ ማዋል የሚችል የሰለጠነ እና የበቃ የሰው ኃይል ለማልማት የሚያስችል አጭር እና የረጅም ጊዜ ስልጠናዎች በየጊዜው መሰጠት አለበት፡፡
በዘርፉ የሚስተዋለው የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ክህሎት እና እውቀት ያላቸው አዳዲስ ባለሙያዎችን በማሰልጠን ብቻ የሚፈታ አይደለም፡፡ ዘርፉን የተቀላቀሉትን እና የሚቀላቀሉትንም በዘርፉ ማቆየትን ይጠይቃል፡፡ አዳዲሶች እየገቡ ነባሮቹ የሚወጡ ከሆነ በቀዳዳ በርሜል ውስጥ ውሃ እንደመጨመር ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የዘርፉ ባለሞያዎች በያዙት ሥራ ላይ እንዲቆዩ ለማስቻል ተገቢ የሆነ የማበረታቻ ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡
የዘርፉን ልማት በብቃት እንዲሁም በኃላፊነትና ተጠያቂነት ለማስተዳደር በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ወሳኝነት ያለው እንደመሆኑ ስልጠናው እና የትምህርት አሰጣጥ ቀጣይነት ያለው መሆን አለበት፡፡ ቀጣይነት ያለው የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ሥራ መከናወን አለበት።
ከዚያ ጎን ለጎን በማዕድን ዘርፍ ሊደርስ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመቋቋም እና ማዕድኑ የሚመረትባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ማህበረሰቦች በተሻለ መልኩ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ማዕድኑ በሚገኝባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች የማዕድን ዘርፍ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ላይ ትኩረት ያደረጉ የቴክኖሎጂ እንክዩቤሽን ማዕከላትን ማቋቋምም ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ የቴክኖሎጂ እንክዩቤሽን ማዕከላት በአንድ በኩል የአካባቢው ነዋሪዎች በማዕድን ዘርፉ ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ በሌላ በኩል በማዕድን ልማት ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ያስችላቸዋል፡፡
መላኩ ኤሮሴ
የተፈጥሮአዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014