
ፍጥረታዊ የሆነ ስብእናን መለወጥ ቀላል አይደለም፤ በብዙ አድካሚና ዋጋ የሚያስከፍል እንደሆነም ይታመናል። በተለይም የስብእናው ባለቤት ስብእናውን የፍጥረታዊ ማንነቱ መገለጫና አካል አድርጎ ከወሰደው ነገሩ “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” መሆኑ ብዙም የሚያነጋግር አይሆንም።
በተለይም ስብእናው ለራስ ከሚሰጥ የተሳሳተ ግምት የሚመነጭ እና ፍጥረታዊ ማንነት ሆኖ የአእምሮ ቀውስ፤ የልብ ድንዳኔ የሚፈጥር ከሆነ በቀላሉ አይላቀቁትም። የችግሩ ስፋትም ከግለሰብ አልፎ ቤተሰብን፣ ማሕበረሰብንና አገርን ጭምር ከፍ ያለ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል የአስተሳሰብ ነቀርሳ ነው።
በአንድ በኩል ስብእናውን የተገዛበት የአስተሳሰብ መሰረት ጤነኛ አለመሆን፤ ከዛም አለፍ ሲል ችግሩ ከፍ ያለ የበሽታ ምንጭ መሆኑን ባለቤቱ አለማወቁ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስብእናው በግልጽ ይሁን በስውር የሚገለጥባቸው ተግባራት በሌሎች ላይ የሚፈጥረው ጫና እና ጫናው የሚያስከትለው ቤተሰባዊ፣ ማሕበራዊና አገራዊ ተግዳሮት ከጅምሩ መቆጣጠር ካልተቻለ አደገኛነቱ የከፋ እንደሚሆን ይታመናል።
የአሸባሪው ሕውሓት ተጨባጭ እውነታም ከዚሕህ የተለየ አይደለም። ቡድኑ ገና ከውልደቱ ይዞት የተነሳው ዘረኝነት፣ አምባገነናዊነት፤ ከዚህ የሚመነጨው እብሪት እና ማን አለብኝነት፣ ከእኔ በላይ ለአሳር እና ተስፋፊነት፤ ከቡድኑ አልፎ ቡድኑን ታምኖ ለትጥቅ ትግል ወደ በረሃ በገባው የትግራይ ወጣት፣ በትግራይ ሕዝብና በመላው የአገሪቱ ሕዝቦች ላይ ያስከተለው ጥፋት ዛሬም ድረስ የቀጠለ ነው።
እነዚህ የቡድኑ ፍጥረታዊ ባህሪዎች ቡድኑ ለሀገሪቱ ሕዝቦች የሰላም፣ የአንድነትና የብልጽግና መሻት ዋንኛ ተግዳሮት እንዲሆን አድርጎታል። በተለይም በሕዝባዊ አመጽ ከሥልጣን ከተባረረ ማግስት ጀምሮ የሕዝባችንን የሰላም፣ የአንድነትና የብልጽግና መሻት በአደባባይ ነፍጥ አንስቶ እየተገዳደረ ይገኛል።
በሥልጣን በነበረባቸው 27 ዓመታትም የሕዝባችንን ዘላቂ ሰላም የሚፈታተኑ የተጠኑ በፖሊሲና በሕግ የተደገፉ ሴራዎችን ከመፈጸም ባለፈ አገራዊ አንድነቱን የሚገዳደሩ የሕዝቦችን አንድነት አደጋ ውስጥ የሚከቱ እኩይ ተግባራትን ፈጽሟል። በልማት ስምም የአገሪቱን ሀብት ዘርፏል፤ አዘርፏል። በከአገርም በሕገወጥ መንገድ በማስወጣት የሕዝባችንን የመልማት ተስፋ አጨልሟል።
ከፍ ባለ እብሪት ተነሳስቶ ለውጡን ለመቀልበስ የሄደበት የጥፋት መንገድ መሰረታዊ ከሆነው ፍጥረታዊ ማንነቱ የመነጨ ነው። በዚህም አገርና ሕዝብን ያስከፈለው ዋጋም በአገሪቱ የነገ ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ ጥቁር ጠባሳ መሆኑ የማይቀር ነው። የተጀመረውን ለውጥ ከፍ ያለ መንገጫገጭ ውስጥ ከቶት እንደነበርም የትናንት ትውስት ነው።
የቡድኑ የሽብር ተግባሮች እወክለዋለሁ የሚለውን የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ከሌሎች በተለይም ከአማራና ከአፋር ወንድሞቹ ጋር ደም ያቃባና መቼም ቢሆን በኢትዮጵያዊነቱ ተደራድሮ በማያውቀው የትግራይ ሕዝብ ላይ የማንነት ግራ መጋባት የፈጠረ ነው።
ቀደም ባለው ጊዜ በነጻነት ስም የገበራችው ልጆቹ ደም ሳይደርቅ፤ ኀዘኑ ከልቡ ሳይወጣ፣ የተሰበረ ልቡ ስብራት ሳያገግም በሆይሆይታ በፈጠረው ግብታዊነት በብዙ ተስፋና ጣር ያፈራቸውን ተስፋዎቹን ለእልቂት ዳርጎበታል።
ይህ ፍጥረታዊ ማንነቱ ዛሬም ቢሆን በአንድ በኩል ስለ ሰላም እያወራ፤ በሌላ በኩል ስለጦርነት ከአቅሙ በላይ ከበሮ እንዲደልቅ እያደረገው ነው፤ አይኑን በጨው ታጥቦ ከማንም በላይ የጦርነት ገፈት ቀማሽ የሆነውን የትግራይ ሕዝብ ስለጦርነት አስፈላጊነት በአደባባይ እየሰበከ ይገኛል።
ቡድኑ የፍጥረቱ መገለጫ በሆነው ፍጥረታዊ ማንነቱ ዘረኝነት፣ አምባገነናዊነት፤ ከዚህ የሚመነጨው እብሪት እና ማን አለብኝነት ፣ ከእኔ በላይ ለአሳር እና ተስፋፊነት የትግራይን ሕዝብ ለተጨማሪ መከራና ስቃይ ሊዳርገው ሌት ተቀን እየተጋ ይገኛል።
እነዚህን ባህሪዎች የራሱ ፍጥረታዊ ባህሪ አድርጎ መቀበሉ ከዛም በላይ የክብሩ መገለጫ አድርጎ መውሰዱ የአደገኝነቱን ደረጃ ከማሳየት ባለፈ፤ በየትኛውም የቡድኑ አዘናጊ ተግባራት አዘናጊ ክፍተቶችን ላለመፍጠር በጥንቃቄ መጓዝን የሚጠይቅ ነው።
አባቶች “ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ…” እንደሚሉት፤ የቡድኑን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የቡድኑን አደገኛነት በሚመጥን መልኩ በትኩረት መከታተል ወሳኝ ነው። ለዚህም አስፈላጊውን ዝግጁነት በማድረግ ቡድኑ ከራሱ ጋር ሲኦል እስከ መውረድ ድረስ የተማማለበትን አገር የማፍረስ ተልዕኮ ማምከን የግድ ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014