
አዲስ አበባ፡- ቴክኖሎጂ ላይ ከፅንሰ ሃሳብ ጀምሮ ያለውን የተዛባ አመለካከት በመቀየር ከተጠቃሚነት ወደ አልሚነት ለመሻገር የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፖሊሲና ፊውቸር ፕላኒንግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደስታ አበራ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ በሀገሪቱ በቴክኖሎጂ ዘርፉ ላይ የዳበረ የሚባል ዕውቀት ቢኖርም የሚተዳደርበት መንገድ የተዛባ ነበር። ይህን ክፍተት በመሙላት ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ አልሚነት ለመሻገር የሚያስችል አዲስ ፖሊሲ ተቀርፆ ወደ ሥራ ተገብቷል። ፖሊሲውም ከፅንሰ ሃሳብ ጀምሮ በቴክኖሎጂ ረገድ ያለውን ትክክል ያልሆነ አመለካከትን በመቀየር ከተጠቃሚነት ወደ አልሚነት ለመሻገር የሚያስችል ነው።
ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጥሩ የምርምር ተቋም የሚባልበት ደረጃ ላይ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤የምርምር ውጤቶችን ወደ ምርትና አገልግሎት ከመቀየር አንፃር ግን ሰፊ ክፈተት አለ ብለዋል።
የታዩ ክፍተቶችን ለመድፈንና ለዘርፉ ውጤታማነት ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን የተናገሩት አቶ ደስታ፤ በአዲሱ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠ ተናግረዋል።
ፖሊሲው፤ ከመንግሥት ይልቅ የቴክኖሎጂውንና የኢኖቬሽኑን ክፍል የግሉ ዘርፍ ቢይዝ የተሻለ እንደሚሆንና መንግሥት የቁጥጥሩን ሥራ እንዲሠራ የሚያደርግ አሠራር የሚከተል መሆኑን ገልፀው፤ ከፍተኛ የገንዘብና የተለያዩ አቅሞችን የሚጠይቁ የምርምር ዓይነቶች በመንግሥት እጅ ላይ እንዲቆይ ይደረጋል ብለዋል።
በዚህ መንገድም ሀገሪቱን ከቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ወደ አልሚነት በማሻገር ተጠቃሚነቷ እንዲረጋገጥ እየተሠራ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ዳይሬክተሩ በአሁኑ ጊዜ ቴክኖሎጂ መጠቀም ላይ ብቻ እንደሚዘወተር በመጠቆም የግሉን ዘርፍ የካበተ አቅም በመጠቀም ሁኔታውን ማስተካከል እንደሚገባም ተናግረዋል።
በሀገሪቱ በዘርፉ ዕውቀት ያለው የሰው ኃይል፣ ተቋማት እና ሌሎችም ባሉበት ደረጃ በተጠቃሚነት ብቻ መቀጠል አዋጪ ባለመሆኑ የግሉ ዘርፍ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ላይ ተሳትፎ የጎላ እንዲሆን ለማስቻል በፖሊሲ ቀረፃ ላይ ሳይቀር እንዲሳተፉ ተደርጓል ብለዋል።
በተጨማሪም ሀገሪቱ በውስን አቅሟ የምታፈራቸውን የቴክኖሎጂ ምሁራን ክህሎትና ዕውቀት አሟጦ ለመጠቀም የምርምር ሥነ ምህዳሩን ምቹ ማድረግና ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ለዚህም በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ማኅበረሰቡ ሊለሙ የሚችሉ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም አቅም እንዳለው በዳሰሳ ጥናት አረጋግጠናል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህን የሚመጥንና የሀገር ውስጥ አቅምን ያገናዘበ ሳይንሳዊ ምርምርና የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል።
ኢኖቬሽንን ስናስብ የመንግሥትን እጅ ከመጠበቅ ይልቅ በፈጠራ የጎለበተና ለመንግሥት አቅም የሚሆን ዜጋን ማፍራት ስለሆነ ለዚህ የሚያስፈልግ የሀብት ምንጮችን ማስፋፋት ያስፈልጋልም ብለዋል።
እንደ አቶ ደስታ ገለፃ፤ በሀገር ላይ ውጤት ማምጣት ካስፈለገ ኢኖቬሽን ላይ የግሉ ዘርፍ የመሪነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል። በተጨማሪም ታላላቅ የትምህርት ተቋማት በሳይንስና ኢኖቬሽን ዘርፍ ላይ ትልቅ ተሳትፎ ማድረግ አለባቸው።
ኅብረተሰቡ ከዚህ በፊት ከተለያዩ ሀገራት የሚገቡ ጥቅማቸው እምብዛም የሆኑ የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ሲጠቀም መቆየቱን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ጊዜ በኋላ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ ችግር ፈቺና ሊያገለግሉ የሚችሉ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ትመና ተሰርቶላቸው እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።
ውብሸት ሰንደቁ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014