
አዲስ አበባ፡- የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽን በመተግበር እኤአ በ2030 የግብርናው ምርታማነት በእጥፍ ለመጨመር እንደሚሰራ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የግብርና ሚኒስቴር ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ሀገር አቀፍ የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀት ትናንት የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በወቅቱም የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን እንደገለጹት፤ የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ በመጪዎቹ ስምንት ዓመታት በእጥፍ ለመጨመር የዲጂታል ግብርና ስርዓትን መጠቀም አስፈላጊ ነው ። የዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽን የመረጃ አያያዝ ስርዓታችን ችግር የመፍታት አቅም ስላለው የምርት ስርጭትን ያሳድጋል። በተናጠል መንገድ ቴክኖሎጂው ላይ የሚሰሩ አካላትን አሰባስቦ በአንድ እንዲሰሩና የምርት ብክነትን እንዲቀንስ በማድረግ ምርትን በእጥፍ ለማሳደግ ይጠቅማል።
ፍኖተ ካርታው ቴክኖሎጂዎች ወደ አርሶ አደሩ እንዲደርሱ ያደርጋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የግብርናውን ሥራ የሚደግፉ እንደ ዓለም ባንክና ቢልና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በቀላሉ ተቀናጅተው ድጋፍ እንዲያደርጉ ይረዳል። እንዲሁም ኢትዮጵያ ያለባትን የምርታማነት ችግርና የግብርና ምርቶች የዝውውር ስርዓት ይፈታል። የመረጃ ፍሰትንና አርሶ አደሩ ጋር ያሉ ችግሮችን በመፍታት ምርት የት እንዳለ በቀላሉ ማወቅ ይቻላል። ይህ ከሆነ የኢትዮጵያ ግብርና ወደ መዘመን ስርዓት ይሸጋገራል ብለዋል።
ከቀበሌ እስከ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ድረስ የግብርናን መረጃ መሰብሰብ ከባድ ችግር ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ምርትን ለመጨመር ለአርሶ አደሩ ቅድሚያ ሰጥቶ ምርት ሊጨምር የሚችልበትን ሙያዊ ምክረ ሀሳብ ማግኘት መቻል አለበት። ይህን የሚመጥን መረጃ በፍጥነት ከቀበሌ ወደ ማዕከል እንዲደርስ የሚያደርግ ቴክኖሎጅን በመዘረጋት ላይ ነው ብለዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ግብርና ለሀገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ዘርፉን ለማዘመን በሀገር ደረጃ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው። ምርትን ከቀበሌ እስከ ማዕከል ለማሳለጥ ጠንካራ መሰረተ ልማትን መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ዲጂታል ኢኮኖሚውን በፍጥነት በጋራ መገንባት ይገባል ያሉት ሚኒስትሯ፤ለዚህም ይረዳ ዘንድ መሰረተ ልማቶች እየተገነቡ ነው። ግብርናው ትልቅ ገቢ ያለው በመሆኑ ቅድሚያ በመስጠት ለማዘመን ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያን ወደ እድገት ለማሻገር ዘርፉን ወደ ዲጂታል በመቀየር ከዚህ በፊት የነበረውን የምርት ዝውውር ማነቆ በመፍታት ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የዓለም ባንክ ተወካይ ፓርመሽ ሻህ ኢትዮጵያ በዲጂታል አገልግሎት እንድትዘመን ለማድረግና ፍኖተ ካርታውን ለማሳካት ዓለም ባንክ ድጋፍና ክትትል ያደርጋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራትን ወደ ዘመናዊ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ለማሸጋገር እየተሰራ ነው። በኢትዮጵያ ያሉ አነስተኛ አርሶ አደሮችን ዲጂታል ቴክኖሎጅን ተጠቅመው በግብርናው ዘርፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ዓለም ባንክ እገዛ ያደርጋል ብለዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014