
አዲስ አበባ፡- የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ሊያሳድጉ የሚችሉ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማዕከል ጥሪ አቀረበ፡፡
የኢንዱስትሪ -የትምህርት ተቋማት ትስስር ውጤት እያስገኘ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው ረጋሳ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከተጋረጠባቸው ችግሮች አንዱና ትልቁ የሰለጠነና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል እጥረት ነው፡፡ የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ሊያሳድጉ የሚችሉ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡
ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኮሌጆችና ከኢንዱስትሪዎች ጋር የምንፈጥረው ግንኙነት የክህሎት ክፍተቱን ለመዝጋት ትልቅ እድል ይሰጣል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ማዕከሉ ከህፃናት አድን ድርጅት በሊዌይ ፕሮጀክት ጋር በተጀመረው የእቅም ግንባታ ፕሮጀክት ውጤታማ ሥራ አግኝተንበታል ብለዋል፡፡ ብዙ መምህራን በኢንዱስትሪዎች በነበራቸው ቆይታ የሙያ ልምድ ብቻ ሳይሆን የኢንዱስትሪ ባህልን ጭምር በማየት ለተማሪዎቻቸው ለማስተላለፍ ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪና የተቋማትን ትስስር ሥራ ተቋማዊና አገራዊ ለማድረግ መንግሥት ብዙ ሥራ እየሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ በፖሊሲ የተደገፈ እንዲሆን በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በኩል የኢንዱስሪት ፖሊሲ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስቴርና በትምህርት ሚኒስቴር በኩልም የተቀረጹ ፖሊሲዎች ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ለኢንዱስትሪዎች አቅም ግንባታ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ተቋማት በመናበብ በትስስርና በመቀናጀት እየሠሩ መሆኑን አስታውሰው፤ ፖሊሲ ከማውጣት ጀምሮ ተግባራዊ እስኪሆኑ ድረስ ዝርዝር የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት ተቋማዊ አቅም ለመፍጠር ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪና የትምህርት ተቋማት ትስስር ተፈጥሮ ተማሪዎች ወደ ኢንዱስትሪዎች ሲላኩ አሰልጣኞችንም ሆነ ሰልጣኞችን ለመቀበል ማሽን ያበላሹብናል በሚል እሳቤ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሰልጣኞችም በሥራ ሰዓት አለመገኘት፣ የሥራ አልባሳትን በአግባቡ አለመጠቀምን ጨምሮ ኢንዱስትሪዎች በሚፈልጉት ልክ ራሳቸውን አዘጋጅተው ያለመምጣት ችግሮች ይስተዋሉ ነበር፡፡ እነዚህን ክፍተቶች ለመፍታት በተሠራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ጥሩ ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ መተማመኑ ስለተፈጠረ ኢንዱስትሪዎች በራቸውን ከፍተው ሰልጣኞች በነጻነት ስልጠናቸውን እንዲወስዱና እንዲለማመዱ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህም አልፎ በተፈጠረው መተማመን ኢንዱስትሪዎች ሰልጣኞችን እስከመቅጠር ደርሰዋል፡፡ ይህንን በማሳደግ በአገር ደረጃ እንዲሰፋና ተቋማዊ አቅም ተፈጥሮበት እንዲሠራ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የሰው ሀብት አንዱ የአገር ትልቁ ሀብት ነው ያሉት አቶ አስፋው፤ በራሱ አቅም ፈጥሮ በሌሎች ላይ አቅሙን የማስተላለፍ ሥራ መሥራት የሚችል ብቁ ዜጋ ማፍራት ያስፈልጋል፡፡ የሚስተዋሉ የክህሎት ክፍተቶችን ለመቅረፍ ኮሌጆች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎችም የስልጠናና ምርምር ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
የዚህ ሥራ አካል የሆነና ከአራት የአዲስ አበባ ኮሌጆች የተውጣጡ 120 አሰልጣኞች በኢንዱስትሪዎች የ15 ወራት የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና እንዲወስዱ መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህን መልካም ተሞክሮ ተቋማዊ ለማድረግና ለማስፋት በትኩረት እንደሚሠራ ተጠቁሟል፡፡
ከኢንዱስትሪዎች ሥልጠናውን በመስጠት በማዕከልነት የተመረጡት የኢትዮ-ኢንጂነሪንግ ግሩፕ አንዱ ኩባንያ የሆነው ፓወር ኢኩዩፕመንት ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ አምቼ አውቶሞቲቪ ኢንዱስትሪ፣ ፀሐይ ኢንዱስትሪ እና ቢ እና ሲ አልሙኒየም ኢንዱስትሪ መሆናቸውን ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 10 /2014