ከዚህ በፊትም በአንድ ጽሑፋችን እንዳልነው፣ ከአንዳንድ (በተለይም የአፍሪካ) አገራት በስተቀር፣ በአለማችን ደራሲ ክቡር ነው። በተለይም የማስተማሪያ መጻሕፍትን እና መዝገበ ቃላትን ያዘጋጀ ደግሞ የበለጠ ክቡር ነው።
እንደመታደል ሆኖ ሌሎች አገራት (ወይም፣ ሕዝቦች) ለብዕር አለቆቻቸው እማያደርጉላቸው የለም። ሼክስፒር ከሙዚየም ጀምሮ የሌለው ነገር እንደሌለ ሁሉ፤ ፈረንሳይ የዞላን (Émile-Édouard-Charles-Antoine Zola) ስራዎች ለማየት የምትፈቅደው በመስታወት ውስጥ ነው። እሱ ብቻ አይደለም፤ በስራዎቹ በፎቶግራፎቹ እንኳን መቀለድ አይቻልም። እንግሊዝ የመጀመሪያውን መዝገበ ቃላት ያዘጋጀውን Samuel Johnson ”የመዝገበ ቃላት አባት” የሚል ማህበራዊ ማእረግ ሰጥታው እነሆ ዛሬም ድረስ ከነሙሉ ክብሩ ሲታወስ ይኖራል። በሌሎቹም እንዲሁ ሲሆን፤ በተለይ በሩሲያ ጉዳዩ የዋዛ አይደለም።
እንዳለመታደል ሆኖ፣ እዚህ እኛ ጋ ግን ሁሉም ነገር ዜሮ፣ ሁሉም ነገር መና ይሆንና ያርፈዋል። ፅድቁ ቀርቶ … እንዲሉ ጭራሹንም በጎ የሰሩ ሊኮንኑ ሁሉ ይችላሉና ወደ ዛሬው ርእሰ ጉዳያችን ወደ ሆኑት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ እንሂድ።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በሸዋ ክፍለ ሀገር በይፋትና ጥሙጋ አውራጃ በ፲፰፻፷፬ (1864) ዓ.ም ተወለዱ። ለትምህርት ሲደርሱ በአካባቢያቸው የነበረውን የአገራቸውን ትምህርት ተማሩ። በኋላም ወደ ጎንደር ተጉዘው የመጻሕፍትን ትርጓሜ አጠኑ። በጊዜው በነበራቸው የቀለም አቀባበል፣ ምስጢር መመራመርና መራቀቅ ብቃት ምክንያት በጉባኤው «የቀለም ቀንድ» የሚል ቅጽል እንዲያገኙ አስቻላቻው። (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ፣ ብሔራዊ ቢብሎግራፊ (የደራሲያን አጭር የሕይወት ታሪክ)፤ ፲፱፻፺፰ ዓ.ም)
አለቃ ኪዳነ ወልድ ከግዕዝና አማርኛ ሌላ ዐረብኛ፣ ዕብራይስጥ፣ ላቲን፣ ሌሎችንም ቋንቋዎች አጠናቅቀው ያውቁ ነበር። አለቃ ኪዳነ ወልድ በእየሩሳሌም ፳፪ ዓመት ተቀምጠዋል። በዚህም ወቅት ብሉይና ሐዲስን በሦስት ቋንቋ ጠንቅቀው አመሳክረው ተርጕመዋል። ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በ፲፱፻፳፮ ዓ.ም የመጀመሪያውን ”መዝገበ ፊደል” አውጥተው ከልዩ ልዩ ቋንቋዎች ጋር በማመሳከር አሳትመዋል። የኢትዮጵያ ፊደል አመጣጡንና ባህሉን በውል አስተባብረው በማቅረባቸውም በጊዜው ተቋቁመው ለነበሩት ትምህርት ቤቶች መመሪያና መማሪያ ለመሆን በቅተዋል። ቀጥለውም ትንሽ አማርኛ ፊደል ከአረብና ከዕብራይስጥ አቆራኝተው አሳትመዋል። (ዘኒ ከማሁ)።
ስለ ቋንቋና የቋንቋ እውቀት አብዝተው የሚጨነቁት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በተለያዩ ዘይቤዎች ያቀርቧቸው የነበሩት ግጥሞች (‹‹ያማርኛ ሠምና ወርቅ››፣ እንዲሁም መዝገበ ፊደል፣ ገጽ 28 – 32 ላይ ያሉትን ግጥሞቻቸውን ይመለከቷል) ለትውልድ ታላቅ ጥቅም የሚሰጡ ናቸው። እንዲያውም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪቃ የብዙ ሺሕ ዘመናት ነጻ አገር፣ ባለ ፊደልና ቋንቋ የሆነች እሷ ብቻ ስለሆነች ትውልድ ያገሩን ትምህርት በመጀመሪያ እንዲማር ያካሂዱት የነበረው ቅስቀሳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
ሙሉ መጠሪያው “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” ከሆነው ሌላ፤ አለቃ ኪዳነ ወልድ ለሚወዷት አገራቸው ባላቸው ዐቅም ሁሉ በብሔራዊ ስሜትና በእውቀት አለመስፋፋት ቁጭት ተነሳስተው በአገራችን ታሪክና ፍልስፍና ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን አሳትመዋል። በተለይም ከዘጠኝ መቶ ገጾች በላይ የሆነው «የሰዋሰው መጽሐፍ» ግዙፍ ስራቸው እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል።
ወደ ውስጥ ከመዝለቃችን በፊት የመዝገበ ቃላትን ጉዳይ ከአገራችን አኳያ ጨረፍ አድርገን እንመልከተው።
“መዝገበ ቃላት” በቁሙ የቃላት መሰብሰብያ፣ ማከማቻ ወይም መድበል ነው። ቁም ነገሩ ግን እነዚህን በተለያዩ ምክንያቶች የተሰባሰቡት ቃላትን መፍታት ወይም መተርጎሙ፤ እንዲሁም ገላጭ (ዲስክሪፕቲ)፣ ወይም መመሪያ ሰጪ (ፕሪስክሪፕቲ) በሆነ መልኩ (ከሁለቱ በአንዱ ማለት ነው) ማዘጋጀቱ፤ የቋንቋውን ሕግና ስርአት ጠብቆ በየክፍሎቹ (ስም፣ ቅፅል …) መተንተኑ ላይ ነው። ስለዚህ ስለመዝገበ ቃላት ሲነሳ የትኞቹ ቃላት ተመርጠው እንደሚሰበሰቡ፣ ከዛም በምን መልክ እንደሚተረጎሙ አብሮ መታሰብ አለበት። ባህላዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ … ጉዳዮችም እንደዛው። (በመሆኑም ነው የመዝገበ ቃላት ዝግጅት በተቋም ደረጃ እንጂ በግለሰብ የሚሞከር አይደለም የሚባለው። ነገሩ እውነት ነው፤ እነ አለቃ ግን ተወጥተውት አለምን ጉድ አሰኝተዋል።)
“መዝገበ ቃላት” የሚለውም ቃል በ 20ኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ከመለመዱ በፊት ጽንሰ ሐሳቡ “ነገር” እና “መጽሐፈ ግስ” በተባሉት ቃላት ውስጥ ተካቶ ነበር የሚለውን የኅሩይ አብዲን ማብራሪያም ከዚሁ ጋር አያይዞ ማስታወስ ጠቃሚ ነው።
ኅሩይ አብዱ ”የመጀመሪያዎቹ ከ1600ዎቹ በፊት የተዘጋጁ የግእዝ-አማርኛ መፍቻዎች ዓላማ በግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ከግሪክ ወይም እብራይስጥ የተገለበጡ ቃላትን ወደ አማርኛ መተርጎም ነበር። እንደዚህ ዓይነት ድርጊት የማያሳዩ (ግስ ያልሆኑ) ቃላቶች በግእዝ ሰዋስው “ነባር” ይባላሉ። አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚሉት ’ዘርነት የሌለው፣ ከዘር አንቀጽ የማይገኝ የቋንቋ ቤተሰብ እየኾነ በውጥንቅጥነት የሚገኝ ጥሬ ቃል ኹሉ ’ነባር’ ይባላል፤ ትርጓሜውም የማይፈልስ፣ የማይናወጥ፣ የማይጠፋ፣ የማይለወጥ ስም ማለት ነው።’ […] በመቀጠል ከ17ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን በተዘጋጁ የሰዋስው ብራናዎች ላይ የምናገኘው “ነገር” በሚል ምደባ ቃላትን እየከፋፈለ ከግእዝ ወደ አማርኛ የሚተረጉም መዝገበ ቃላትን ነው። […] የቅኔ ቤት ግሥ በአብዛኛው የሚገኘው በ19ኛው እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን በተዘጋጁ ብራናዎች ላይ ነው። ይህ አይነት መዝገበ ቃላት የተዘጋጀው በቃላቱ መድረሻ ፊደል ቅደም ተከተል ስለሆነ ቅኔ እና ሌሎች ግእዝ ግጥሞችን ለመድረስ ይረዳል።” (ግንቦት 2009 ዓ.ም) የሚል አስተያየት በጥናታቸው ተካትቶ የምናገኝ ሲሆን ይህም ስለ አለቃ የሚለው አለና አንስተነው ማለፉ ተገቢ ይሆናል።
የ#መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ$ በአለቃ እጅ መግባት?
መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ (፲፰፻፲፯-፲፱፻) በዘመናቸው የግዕዝ – አማርኛ መዝገበ ቃላት ማዘጋጀት ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም ጅምራቸውን ከዳር ሳያደርሱት ሞት እንደሚቀድማቸው ስላወቁት ይህንን ኑዛዜ ለአለቃ ኪዳነ ወልድ ትተውላቸው ማለፋቸው ይታወቃል።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ወደ ግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላቱ ሥራ እንዴት ሊገቡ እንደቻሉ? ለሚለውም “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” መግቢያ ላይ የመምህራቸውን ኑዛዜ እንዲህ አቅርበውታል (በኅሩይ ጥናትም ላይ ሰፍሯል።)
“[…] ኋላም በጊዜ ሞት አስር ዓመት ምሉ ከርሳቸው ጋራ ለነበረው ለአገራቸው ልጅ ለተማሪያቸው እንዲህ ብለውታል፤ ‘ልጄ ሆይ ይህንን ግስ ማሳተም ብትፈልግ እንደ ገና ጥቂት ዕብራይስጥ ተምረኽ ማፍረስና ማደስ አለብኽ፤ በመዠመሪያው አበገደን ጥፈኽ የፊደሉን ተራ በዚያው አስኪደው። አንባቢዎችም እንዳይቸገሩ ከፊደል ቀጥለኽ አጭር ሰዋስው አግባበት፤ የጐደለውና የጠበበው ኹሉ ሞልቶ ሰፍቶ ሊጣፍ ፈቃዴ ነው፤ ከሌላው ንግድ ይልቅ ይህን አንድ መክሊት ለማብዛትና ለማበርከት ትጋ፣ ዘር ኹን፣ ዘር ያድርግኽ፤ ካላጣው ዕድሜ አይንፈግኽ፤ ለአገርኽ ያብቃኽ’ ብለው ተሰናበቱት።”
ከላይኛው አንቀፅ ብዙ ሀሳብ በማውጣትና በመተንተን ብዙ ነገሮችን ማሳየት፤ በተለይ ”…አንባቢዎችም እንዳይቸገሩ ከፊደል ቀጥለኽ ዐጭር ሰዋስው አግባበት፤ የጐደለውና የጠበበው ኹሉ መልቶ ሰፍቶ ሊጣፍ ፈቃዴ ነው …” የሚለውን ወስዶ እራሱን የቻለ ስራ በመስራት የመምህር ክፍለ ጊዮርጊስን ልሂቅነት ማሳየት ይቻላል።
ዲልማን (August Dillmann) የተሰኘ ጀርመናዊ የቋንቋ እና መጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ በርካታ የግእዝ መጻሕፍትን በመመርመር በ1857 ዓ.ም “Lexicon Linguae Aethiopicae” የተሰኘ የግእዝ-ላቲን መዝገበ ቃላት አዘጋጅቶ ነበር። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም የዲልማንን መዝገበ ቃላት አይተው፣ “ሥራን መንቀፍ በሥራ ነው እንጂ በቃል ብቻ መንቀፍ አይገባም” ብለው የጀርመናዊውን መዝገበ ቃላት በሥራ ነቅፈው አዲስ ግስ (መዝገበ ቃላት) የጀመሩት አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚነገሩን ምጽዋ በስደት ሳሉ ነበር የሚለው የኅሩይ ጥናት ሌላውና ተጨማሪ የመምህር ክፍሌን ምጥቀት ማሳያ ነው። በተለይ ዲልማን ማን እንደሆነ ለሚያውቅ ሰው እሱን ከመገዳደርም አልፎ ስራዎቹን በጥናትና መርምር ለመጣል መነበሳት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለተገነዘበ ጉዳዩ መግረም ብቻም ሳይሆን፤ ከጊዜው አኳያ ለማመን ሁሉ ሊያስቸግር ይችላል። (ምናልባት ስለ መምህር ክፍለ ዮርጊስ በሌላ ዝግጅት መመለስ ሳያስፈልግ አይቀርምና ያኔ በስፋት ማየት ይቻላል።)
እስራኤል እያሉ፣ በዘመኑ ኢትዮጵያ አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ የነበሩትን አለቃ ልዑል ራስ ተፈሪ፤ “ትችል እንደሆነ መጥተህ ሕዝቅኤልን ተርጉምልኝ” ብለው በጻፉላቸው ደብዳቤ መሰረት፣ በ1912 ዓ.ም ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ […] በታዘዙት መሰረትም ሕዝቅኤልን ንባቡን ከሙሉ ትርጓሜው ጋር አሳትሙ። ከዛስ? ወደ መምህር ጊዮርጊስ ኑዛዜና የግዕዝ – አማርኛ መዝገበ ቃላትን ዝግጅት ገቡ። ወደ መምህር ክፍሌ እንመለስ።
መምህር ክፍሌ:-
መምህር ክፍሌ በ1870ዎቹ መጀመርያ የግእዝ-አማርኛ ግሳቸውን (መዝገበ ቃላት) ረቂቅ ሲልኩ ይህንንም መልእክት አብረው ልከው ነበር፤
“የዚህ ግሥ ሥራው አልተጨረሰም፤ ስምና ግዕዘ ብሔር ቀርቶታል። ጊዜ ቢገኝ ሲታተም ይጨረሳል። ተራም ቤቱን ሳይለቅ አንዳንድ የፊደል ተራ ተዛውሮ ይገኛል። ኋላ ይቀናል። አማርኛው ለሰው እንዲሰማ የአገረ ሰብ አማርኛ አለበት፤ ‘ሥር፣ ሥራ’ በብዙ አንድ አማርኛ ይሆናሉ። ሥራ ሲበዛ ሥሮች፣ ሥርም ሲበዛ ሥሮች ይባላል። እንዲህ ያለ ሲገኝ ያለ መምህር ለሁሉ አይሰማም። ስለዚህ ሥራ ብሎ በብዙ ‘ሥራዎች’ እንደ ማለት ያለ ይጥፋ። እንዲሰማ ነው እንጂ መልካም አማርኛ አይደለም።
“ሦስቱ ‘ሀሐኀ’፣ ሁለቱ ‘ሠሰ’፣ ሁለቱ ‘አዐ’ እንዳይሳሳቱ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አለዚያ ተራ ይበላሻል። የፊደልም ተራ ‘ሀላዊ’ ሳይል ‘ሀለደ’ አይልም። ከ‘ላ’‘ለ’ ይቀድማል ብሎ ‘ሀለደ’ ይቅደም ቢል ከ‘ዊ’‘ደ’ አይቀድምም ይላሉ። ሁሉ እንዲህ ነው፣ ቤቱን ካለቀቀ ግዕዝ ሐምስ ቢቀዳደሙ ግድ የላቸውም። ሦስተኛው ፊደል ያለ ተራው እንዳይገባ ይጠብቃሉ።
ፍችም አእማሪ ‘ያወቀ’፣ አእማሪት ‘የወደደች’፣ እንዲህ ያለ ፍች አለው፡ ያንዱ ፍች ለሁሉ ይሆናል። የፊደል ግድፈት ተጠንቅቃችኁ ተመልከቱ፤ ዕለቱን ተጨርሶ ሳይታረም መጥቶላችኋል። ሰላመ እግዚአብሔር የሀሉ ምስሌክሙ አሜን።”
መምህሩን ባናያቸውም ያየናቸው፤ ባናውቃቸውም ያወቅናቸው፤ አጠገባችን ሁሉ ያሉ እስኪመስለን ድረስ መልእክታቸው ዘልቆ ተሰምቶናልና ላቀበሉን ሰዎች ምስጋናችን ይድረሳቸው።
ይህንን ከባድ ኃላፊነት ለመወጣትም የአለቃ ኪዳነ ወልድን ተግባርና ኃላፊነትን የመሸከም ብቃት ”ቀን ከሌት ሳይሉ ይሰሩ ጀመር፡፡ በሥራ ውለው ማታ ንፋስ በመቀበል ጊዜ አንድ ሃሳብ ቢያገኙ በማስታወሻ ለመፃፍ ከውጭ ወደ ቤት ይመለሳሉ፡፡ በምሳ ወይም በራት ጊዜ አንድ ትርጓሜ ቢታሰባቸው ምግቡን ትተው ብድግ ይላሉ፡፡ ሌሊትም ተኝተው ሳሉ አንድ ምስጢር ቢገጥማቸው ከመኝታቸው ተነስተው መብራት አብርተው ይጽፋሉ” በማለት አለቃ ደስታ ያገልፁታል፡፡
አለቃ ደስታ ስለ የእድሜና የእውቀት ታላቃቸው ሲመሰክሩም፤ “የግዕዝን መሰረት ያወቅሁት ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ነው፤ አሁን ያዘጋጀሁትን ሰፊ ያማርኛ መዝገበ ቃላት ለመጻፍ የበቃሁትም ከርሳቸው ባገኘሁት ትምህርትና እውቀት ነው” ማለታቸው ታሪካዊ ስፍራውን ይዞ ይገኛል።
በተወለዱ በ፸፪ ዓመታቸው ሰኔ ፳፬ ቀን ፲፱፻፴፮ ዓመተ ምሕረት ዐርፈው ደብረ ሊባኖስ የተቀበሩት አለቃ ኪዳነ ወልድ ለበርካታ ዓመታት በዚህ ሁኔታ ቢሰሩም መዝገበ ቃላቱን ከፍፃሜ ለማድረስ እድሜ እንደሚገድባቸው ስለተረዱት አለቃ ደስታን ለደቀ መዝሙርነት መረጡ (እዚህ ላይ በእምነት የተሞላ የትውልድ ቅብብሎሽ መኖሩን፤ ይህ እራሱን የቻለ አገራዊ እሴትም እንደሆነ ልብ ይሏል)። ጊዜ ሞታቸው ሲቃረብም ከመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በጅምር የተቀበሉትንና እርሳቸው ያስፋፉትን የግእዝ መዝገበ ቃላት ሥራ በተራቸው ለአለቃ ደስታ ተክለ ወልድ አስተላልፈው አረፉ፡፡”
(በተፈሪ መኮንን ማተሚያ ቤት የተጀመረው ትውውቅና የተወጠነው ምሁራዊ ጓደኝነት ድሬዳዋ በሚገኘው በቅዱስ ዐልአዛር የላዛሪስት ማተማያ ቤትም ቀጥሎ ሁለቱ (አለቃ ኪዳነ ወልድ እና አለቃ ደስታ) በእውቀት ሰንሰለት የተሳሰሩ ሰዎች ለአስራ ስድስት አመት አብረው መስራታቸውን የአዲስ አድማሱ ባየህ አስነብቧል።
አለቃ ደስታ በበኩላቸው፤ መሟላት ያለበትን ሁሉ አሟልተው፣ መዝገበ ቃላቱን አድሰውና አርመው “መጽሐፈ ስዋስወ ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” በሚል ርዕስ በ1948 እንዲታተም አደረጉ፡፡ ይህ 908 ገፆች ያሉት የግእዝ – አማርኛ መዝገበ ቃላት ደራሲ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መሆናቸው በመጽሐፉ የተገለፀ ሲሆን፤ ደስታ ተክለወልድ በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ማሳተማቸውም ተጠቁሟል። ይህም በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የተጀመረው፤ ለአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የተላለፈው፤ የሁለት ቀደምት ሊቃውንት ልፋት፣ እልህ አስጨራሽና ትውልዶችን የተሸጋገረ ድካም በአለቃ ደስታ ተክለወልድ ፍፃሜ አግኝቶ ለህልውና በቃ። (አለቃ ደስታ ያዘጋጁት መዝገበ ቃላት የተደራጀው እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሁሉ በአበገደ ፊደል ተራ መሰረት መሆኑን፤ ማለትም የቃላቱ ቅደም ተከተል የሚጀምረው በ”ሀ” ፊደል ሳይሆን በ”አ” ፊደል ነው፡፡ በዚህ አካሄድ “ሀ” አምስተኛ ፊደል እንዲሁም “ለ” ሠላሳኛ ፊደል ሲሆን የመጨረሻው ፊደል ደግሞ “ተ” ይሆናል።)
በመጨረሻም፣ ለሁሉም ነገር ምስክሩ ስራ ነው። ሌላው ሁሉ ከዛ በኋላ ነው። ዛሬ እዚህ የምናወራላቸው ቀደምት ልሂቃን እኛ ከምናወራላቸው በበለጠ ስራቸው እራሱ አፍ አውጥቶ ይናገራልና ነፍሳቸውን በገነት ያኑርልን። አሜን
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 /2014