በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በሺዎች የሚቆጠሩ ሲሆኑ፤ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 350 ደርሰዋል። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ የማህበሩ አባላት ናቸው። የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክ ሙያ ተቋማት ማህበር ዘጠኝ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ያሉት ሲሆን፤ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
ዶክተር ሞላ ፀጋዬ የኢትዮጵያ የግል ከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክ ሙያ ተቋማት ማህበር ፕሬዚዳንት በተጨማሪም የአድማስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ናቸው። በዛሬው ዕትማችን የግል ከፍተኛ ትምህርት ቴክኒክ ሙያ ተቋማት አስመልክቶ ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- የግል ትምህርት ተቋማት ወደ ማስተማር ከገቡ ወዲህ እንደ አገር ምን ለውጥ መጥቷል ብለው ያስባሉ?
ዶክተር ሞላ፡- የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በአጠቃላይ መንግስት የትምህርት ሴክተር በባለሃብቶች እንዲሰራ ክፍት ከተደረገ ወዲህ 20 ዓመት በላይ አስቆጥሯል። በወቅቱ የትምህርት ተደራሽነት ውስንነት በአገራችን ነበር። ጥቂት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ብቻ ነበሩ። ለአብነት በወቅቱ የነበሩት ሐሮማያ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ጎንደር የህክምና ኮሌጅ፣ ባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ፤ ወንዶ ገነት የግብርና ኮሌጅና የመሳሰሉት ብቻ ነበሩ። በወቅቱ የነበረው ህዝባችን ቁጥር ከግምት ውስጥ ሲገባ እና ለከፍተኛ ትምህርት ዕድሜው የደረሰ ዜጋ ሲታይ ከሌሎች አገራት ማነፃፀር ቀርቶ ከአፍሪካ አገራት አኳያም በጣም ያነሰ ነበር።
በአሁኑ ወቅት እንኳን ሲታይ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባት የደረሰው ከጠቅላላ ህዝብ 12 በመቶ ነው። ይህ ጥሩ ዕድገት ቢሆንም ከአንዳንድ አፍሪካ አገራትም ግን ያነሰ ነው። ይሁንና መንግስት በ10 ዓመት የብልጽግና እቅድ ወደ 22 በመቶ ለማድረስ አቅዷል። ይህን ማንሳት የፈለኩት የግል ትምህርት ተቋማት የራሳቸው የሆነ ትልቅ ሚና አላቸው ለማለት ነው። በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ሲታይ የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ወይንም የቀድሞው የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ መረጃ እንደሚነግርን 1ነጥብ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች እስካሁን በግል ትምህርት ዘርፍ ምሩቃን ናቸው። የጥራት ጉዳይ ካነሳን በሂደት የምናየው ጉዳይ ነው።
ከትምህርት ተደራሽነትና ከፍትሃዊነት አኳያ ይህ ትልቅ ዕምርታ ነው። ፍትሃዊነት ስንል ከከተማ ራቅ ብለው ያለው ወይንም በገጠር ነዋሪዎች አኳያ፣ ከፆታ አኳያ ልዩነቱ ሰፊ ነበር። አሁንም ይህ ልዩነት አለ። ይህን በማስተካከል ረገድ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መስፋፋት የፍትሃዊነትን ጥያቄ ከመሸፈንና ከማጥበብ አኳያ ከፍተኛ ሚና ነበራቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን ከግል የትምህርት ተቋማት ተመርቀው በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው በርካታ ዜጎች አሉ። ለምሳሌ የእኛ ምሩቃን በአሜሪካ እስከ ማይክሮ ሶፍትዌር ካምፓኒ እና ከንቲባ ጽህፈት ቤቶች ድረስ ሄደው እየሠሩ ነው። ሁሉም ተቋማት ደግሞ የየራሳቸው ታሪክ አላቸው። በአገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም በግል ትምህርት ተቋማት የተማሩ ናቸው።
የግሉን ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ትተን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ብቻ ስናይ ወደ 305 ደርሰዋል። በዚህ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ዜጎች በርካቶች ናቸው። ይህ የሚያሳየው ትምህርትን ከማስፋፋትና ፍትሃዊነትን ከማረጋገጥ በዘለለ ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠሩ ናቸው። በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ በመሆናቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ታክስ ከፋይ ናቸው። ታክስ በመክፈላቸው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የራሳቸው ሚና አላቸው። በአጠቃላይ የግል ትምህርት ተቋማት ሚና በዚህ መንገድ ጠምረን ማየት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- የግል ትምህርት ተቋማትን በማበረታት ረገድ የመንግስት ሚና እንዴት ይገለፃል?
ዶክተር ሞላ፡- ለግል ሴክተር መፈቀዱ በራሱ ስኬት ነው። ባለሃብቶች በዚህ ዘርፍ መሰማራታቸውም ትልቅ መሻሻል ነው። አዋጆች፣ ፖሊሲ፣ መመሪያዎችን በማዘጋጀትና የግል የትምህርት ተቋማትን የሚቆጣጠሩ መንግስታዊ ተቋማትን ማቋቋሙም ትልቅ ስኬት ነው። በቅርቡ በተለይም ደግሞ ከአራት ዓመታት ወዲህ በግሉ ዘርፍ ላይ ያሉ መምህራን ጥራትን ከማሳደግ አኳያ ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉ፤ የግል ትምህር ተቋማት ላይ የሚሰሩ መምህራንም የማስተርስና ሦስተኛ ድግሪ እንዲማሩ መፈቀዱና ትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄውን መቀበሉ ትልቅ ለውጥና የዘመናት ጥያቄ ባለፉት አራት ዓመታት ምላሽ ያገኙበት በመሆኑ ማህበሩና ሥራ አመራር ቦርዱ ያመሰግናል። በተለያዩ መድረኮችም ምስጋናችን አቅርበናል።
የግል ትምህርት ተቋማት አመራር ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉ፤ ለመንግስት የትምህርት ተቋማት በሶፍት ኮፒ የሚሰጡ መፅሃፍት ለግሉም መሰጠታቸውና፣ የግል ትምህርት ተቋማት ከውጭ ግብዓቶችን ሲያስገቡ የትብብር ደብዳቤ መኖሩ ትልቅ ለውጥ ነው።
በአስር ዓመቱ ፍኖተ ካርታው ላይም የተገለፀው ነገር ቢኖር የከፍተኛ ትምህርት ምጣኔ 22 በመቶ ለማድረስ ከታሰበው በመንግስት ተጨማሪ ዝንባሌ ከመገንባት ይልቅ ለግል ትምህርት ሴክተር ዕድል መፍጠር የሚለው አቅጣጫና ተቋማት ያላቸው ዕይታ የመንግስትን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ የትምህርት ተቋማትን በማስፋፋት ረገድ ከአፍሪካ አኳያ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝና ብዙም ተወዳዳሪ ያልሆነች ናት። ይህ ለምን የሆነ ይመስሎታል?
ዶክተር ሞላ፡- ተወዳዳሪነት መገለጫው በብዙ መንገድ ነው። አሁንም ለከፍተኛ ትምህርት የደረሰ ዜጋ ከአገሪቱ ጠቅላላ ህዝብ አኳያ ሲታይ በጣም ዝቅተኛ ነው። ለምሳሌ ፊላንድን ብናይ እስከ 95 ከመቶ ደርሰዋል። ያደጉት አገሮች ትልቅ ቁጥር ነው ያስመዘገቡት። ከአፍሪካ አኳያም ብዙ ይቀረናል። ከአንዳንድ የአፍሪካ አገራት ደግሞ በጣም እንሻላለን። የእኛ ዜጎች በውጪው ዓለም ሥራ ከማግኘት አኳያ ጥሩ የሚባል ነው። ዜጎቻችን በዓለም ትልልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እያስተማሩ ነው።
ምስራቅ አፍሪካ ያሉትም ከእኛ ጋር የሚወዳደሩ አይመስለኝም። ሌሎች የአፍሪካ አገራትም ከእኛ ያነሱ ናቸው። የእኛ አገር የትምህርት ተቋማት በጣም ይጠበቃሉ፤ ቁጥጥሩም የጠበቀ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የግሉ ሴክተር ላይ የተሰማሩት ኢትዮጵውያን ናቸው። የሌላ አፍሪካ አገራትን ብናይ የውጭ ዜጋ መጥቶ የራሱን ቢዝነስ ሠርቶ መውጣት እንጂ እንደ ኢትዮጵያ በራሳችን ዜጎች ብቻ የሚመራ፣ ረጅም ጊዜ እቅድ ይዞ የሚተዳደርና የሚመራ አይደለም። እኛ ከደቡብ ኮሪያ አኳያ ብናስተያይ ከእኛ አኳያ ሰማይና ምድር ያክል ልዩነት አላቸው። ከ2000 በላይ የግል ትምህርት ተቋማት ያላቸው አገራት አሉ። ከእነዚህ አኳያ ግን እኛ በጣም ይቀረናል። ለከፍተኛ ትምህርት የደረሱትንና ትምህርቱን ያገኙት ዜጎቻችንም ቁጥር ሲታይ የእኛ በጣም አነስተኛ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በግል ትምህርት ተቋማት በርካታ ጥሩ ተግባራትን ታከናውናላችሁ። በዚያው መጠን የሚያስወቅሳችሁን በትክክል ታውቃላችሁ?
ዶክተር ሞላ፡- የትምህርት ተቋማትን ከጥራት አኳያ ያነሳህ መሰለኝ። የግል ትምህርት ተቋማት ችግር አለ የሚለው አስተሳሰብ መስፈኑን እናውቃለን። ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ጥራት ለማስጠበቅ የሚደረገው ጥራት ምንድን ነው የሚለው እንወቅ። በመንግስትም ሆነ በግል ትምህርት ተቋማት ጥራት ለማስጠበቅ ምን እየተሠራ ነው የሚለውን ማወቅ ጥሩ ነው። ጥራት ብዙ ብያኔ የሚሰጠው ነው። እኛ አገር ዓላማውን እስካሳካ ድረስ በሚለው እሳቤ ይዘን እየሠራን ነው። የሚቆጣጠረን አካልም በዚሁ ሁኔታ እየሄደ ነው።
ይህ እንዳለ ሆኖ የጥራት ብያኔ እይታ ህብረተሰቡና ደንበኞች አገልግሎት አኳያ የሚሰጠው አስተያየት የጥራት ብያኔ ይሆናል። ይህን አይተን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ማየት ይገባል። በአጠቃላይ ግን ግብዓት፤ ሂደትና ውጤት ጋር የተያያዘ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። እኛ አገር የጥራት መገምገሚያዎች አሉ፤ ግን ጠንካራ አይደለም። ስለ ጥራት ሲነሳ ሚዲያዎችም ጭምር በዋናነት የሚያወሩት ስለ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ነው። ግን ይህ ብቻ አይደለም። እኛ አገር የጥራት ማስጠበቂያ ሆኖ እየተደረገ ያለው እውቅና እና ዕድሳት፤ ድንገተኛ ጉብኝት እና የውስጥ ጥራት ኦዲት ላይ ነው የሚሽከረከሩት።
እውቅና እና ዕድሳት በደንብ እንመልከተው። አንድ ተቋም አዲስ ፕሮግራም ሲጀምር እውቅና ሳያገኝ መጀመር አይችልም። ይህን ለማግኘት መስፈርቶች አሉ። እነዚህም አነስተኛ የጥራት መስፈርቶች ናቸው። ስለዚህ እነዚህን መስፈርቶች ሲያሟላ እውቅና ይሰጠዋል። አንዱ መመዘኛ ይህ ነው። ከግብዓት፤ ሂደትና ውጤት አንጻር ያልነው አለ ማለት ነው።
እኛ ስለ ጥራት መናገር ምንችለው አንዱ ይህን ይዘን ነው። ሌላው ከሦስት ዓመት በኋላ ዕድሳት ይባላል። በዚህ ጊዜ እድሳት ለአምስት ዓመት ይሰጣል። ዕድሳት ሁለት፣ ሦስት፣ አራት እያለ ይቀጥላል። መስፈርቶቹ በየጊዜው እየጨመሩ ይሄዳሉ። ጥራትም ሂደት ነው፤ በተለይ የትምህርት ጥራት በአንድ ጊዜ አይረጋገጥም። እኛ አገርም፤ አውሮፓም ስለጥራት ያወራሉ። ግን የጥራት ደረጃችን ይለያያል። የምናወራው በእድገታችን ልክ ነው። ከዚህ ውጭ የእኛ አገር ጥራት ለማስጠበቅ እውቅና እና ዕድሳት፤ ድንገተኛ ጉብኝት እና የውስጥ ጥራት ኦዲት በመከተል ይገመገማል። ከዚህም በተጨማሪ ተቋማት በውስጥ ኦዲት ራሳቸውን ይገመግማሉ። ራሳቸውን ገምግመውም ያስቀምጣሉ። የቀድሞው ለከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ወይንም የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ያሉበትን ደረጃ ይልካሉ። በዚህ ሂደት በመሄዳችን ችግሮች ካሉ ይስተካከላሉ። በዚህ ሂደት በማለፋችን ተቋማትን ብቻ ሳይሆን ግለሰቦችን ጭምር መቀየር ችሏል። ይህን ያነሳሁት ጥራታችን የሚለካው በዚህ ዕይታ ነው ለማለት ነው። የምንነጋራቸው ነገሮች ግንዛቤው ሳይኖር ከተነጋገርን ጫፍ ይወጣሉ። ብድግ ብሎ የትምህርት ጥራት ወድቋል ወይንም ጥሩ ነው የሚሉ ትርክቶች ጥሩ አይደሉም።
አዲስ ዘመን፡- በግል ትምህርት ተቋማት ጥራት ከማስጠበቅና ዜጋ ከመገንባት ይልቅ ሙሉ ለሙሉ ንግድ አድርገውታል የሚል ክስ አለ። እርስዎ ምን ይላሉ?
ዶክተር ሞላ፡- የትምህርት ጥራት ችግር በኢትዮጵያ አለ ወይ የሚለው ምላሽ ማግኘት አለበት። አዎ! የጥራት ችግር አለ። በኢትዮጵያ በግልም ሆነ በመንግስት ተቋማት ትልቅ ችግር አለ። ችግሩ እዚህ ነው እዚያ ነው የሚለው ለአገርም ለህዝብም አይጠቅምም። በአገራችን ከመዕዋለ ህፃናት እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ የትምህርት ጥራት ችግር አለ። ምንጩ ምንድን ነው የሚለው በርካታ እና ውስብስቦች ናቸው። አንደኛው ላለፉት 20 ዓመታት የተደራሽነትና የፍትሃዊነት ጥያቄ ነበር።
መንግስት በበጎ እየሰራቸው ግን ደግሞ በሌላ ጎኑ ችግር ፈጥሯል። ለተደራሽነት ሲሠራ ትምህርት ጥራት ላይ ችግር ነበር። ተማሪዎች ዳስ ውስጥ ሲማሩ ነበር። በአንድ ክፍል ውስጥ ከ80 እስከ 90 ተማሪዎች ይማሩ ነበር። የላብራቶሪ ግብዓቶች አለመሟላትም ሌላኛው ችግር ነው። በዚህ የተነሳ የትምህርት ጥራት ላይ ችግር መፈጠሩ ተፈጥሯዊና አይቀሬ ነው። ቀደም ሲል በነበረው ግንዛቤ ለትምህርት ይሰጥ የነበረው እይታ የጠነከረና ትምህርት የሁሉም ነገር ግብ መሆኑ ይታመን ነበር። አሁን ግን አማራጮች ሲበራከቱ ትምህርት ብቻ ለመኖር አማራጭ አይደለም የሚል እሳቤ መፈጠሩም ሌላኛው ጉዳይ ነው። በአሁኑ ወቅት አማራጮች ነግሰዋል፤ የዜጎችም ፍላጎት እየተቀየረ ነው። በዚህ ዘመን አስተማሪዎቻችን ሩጫ ላይ ናቸው። አንድ ቦታ ብቻ በመሥራት ራሳቸውን ማስተዳደር ላይ የተወሰኑ አይደሉም።
የትምህርት ጥራት በመንግስትም ሆነ የግል ትምህርት ተቋማት ችግር መኖሩን ማመን ይገባል። የግሉ ዘርፍ የተለየ ባህሪ አለው። በግሉ ዘርፍ ትምህርት ንግድ ነው፤ ግን እንደ ንግድ እና ትርፍ ማጋበስ ብቻ ማሰብ ከመጣ ዜጋ ማፍራት አይቻልም። በዚህ ረገድ ምን ላይ ያተኩራሉ ብለን ማሰብ አለ። አንዳንዶች ወደ ትርፍ ማግኘት ያመዝናሉ። የተወሰኑት ጥራት ላይ ያተኩራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ሁለቱንም አመዛዝነው ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ። የሆኖ ሆኖ ግን ችግር አለ። ወደ ቢዝነሱ የሚያዘነብሉ የግል ትምህርት ተቋማት ህግ ጥሰው እስከ መሥራት ይደርሳሉ።
አዲስ ዘመን፡- በርካታ የግል ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ጉድለት ብቻ ሳይሆን ውጤት አሰጣጥም በጣም ከተማሪ አቅም በላይ የተጋነነ እንደሆነ ይነገራል። ይህ በራሱ የግል ትምህርት ተቋማት መካከል ያለውን ጤናማ ውድድርን አያውክም?
ዶክተር ሞላ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳኸው። ሁለት ነገር እያወራን ነው። ብዙ ጊዜ የምገነዘበውና በሚዲያ በተደጋጋሚ የሚነገረው ስለትምህርት ጥራት ሲነገር በብዛት የሚነገረው ጥሰቶች ላይ ብቻ ነው። የትምህርት ጥራት ከዚህም ያለፈ ነው። ጥሰት የሚፈፅሙ ተቋም እንዳሉ ሁሉ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው በአግባቡ የሚሰሩ አሉ። ጥራት መመዘኛው ከመነሻ እስከ መጨረሻው ድረስ ያለው ሂደት ነው። ማንኛውም ተቋም የማህበሩ አባል ሆነም አልሆነ ግን የትምህርት ጥራት ላይ ማተኮር አለባቸው። በዋናነት የትምህርት ጥራት ጉዳይ ማስጠበቅ ትልቁ ሥራ የመንግስት ነው፤ ማህበሩ ግን ድርሻ የለውም እያልኩ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- የትምህርት ጥራት በማስጠበቅ ረገድ የማህበሩ ድርሻ ምንድን ነው?
ዶክተር ሞላ፡- ማህበሩ የተቋቋመበት መተዳደሪያ ደንብ አለው። የአብዛኛውን የማህበራትን ሥራ መገመት ትችላለህ። በዋናነት ሴክተሩን በጋራ ማስተዋወቅና ድምፃቸውንም ማሰማት ነው። ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲኖር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በህብረት ለመነጋገር ነው። በተጨማሪም አቅምና ልምድ ለመለዋወጥ፤ ግብዓቶችን በመተጋገዝና በመተባበር ለመጠቀም፤ በተቋማት መካከል የጥቅም ሽኩቻ ሲኖር በአግባቡ ለመፍታት በማሰብ ነው። እዚህ ውስጥ ያልተካተተ እና ወደፊት መሰራት አለበት ብዬ የማምነው ሕግና ሥርዓትን ማስከበር እና የትምህርት ጥራት ማስከበር ላይ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ አለበት ብዬ አምናለሁ።
በጠነከረ መንገድ መወቃቀስና መተቻቸት ላይ አልደረስንም። እርምጃ ተወሰዶብሃል ወደሚለው ደረጃ አልተሸጋገርንም። በዋናነት ይህ ድርሻ የመንግስት ሆኗል። እንደግለሰብ ግን የማህበሩ አሰራር መጠናከር አለበት። የትምህርት ተቋማት በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸውም መስራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡- ፈቃድ ሳይሰጣቸው የትምህርት ክፍሎችን የሚጀምሩና ተማሪዎችን ለእንግልትም የሚዳርጉ የግል ትምህርት ተቋማትም አሉ። ማህበሩ በዚህ ላይ የሚሠራው ምንድን ነው?
ዶክተር ሞላ፡- የማህበሩን ዓላማ ከላይ የነገርኩህ ነው። ግን ከዚህ በላይ መሄድ አለበት ብዬ አምናለሁ፤ ለዚህም መታገል አለብን። ማህበሩ እርምጃ ቢወስድ ጥሩ ነበር። ግን በዚህ መንገድ አልተቋቋመም። ነገር ግን በመንግስት እርምጃ ተወስዶባቸው ማህበሩ መፍትሄ እንዲያመጣላቸው ቅሬታ የሚያቀርቡ አሉ። ማህበሩ ትክክል ከሆነ ይቀበላል ካልሆነ ግን ጥያቄውን ውድቅ ያደርጋል። ከዚህ ባለፈም ከህግ ውጪ ያለአግባብ የሚሄዱ ተቋማት ካሉም ማህበሩ ለሚመለከታቸው አካላት ያሳውቃል። እውቅና ሳይኖረው ለሚያስተምሩትና ላስመረቁት ግን ማህበሩ በመንግስት ሊወስድ የሚችለው እርምጃ መደገፍ እንጂ ጥብቅና አይቆምም።
አዲስ ዘመን፡- የግል ትምህርት ተቋማት አመሰራረት ብሄር ተኮር ናቸው ይባላል። እርስዎ በዚህ ላይ ምልከታዎ ምድን ነው?
ዶክተር ሞላ፡- ይህ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ይዘው መሄዳቸውና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር መናበባቸው የሚጠበቅ ነው። አንድ ካምፓስ በሆነ ቦታ ሲመሰረት በአካባቢው ያሉ ተወላጆች በብዛት እንደሚማርበትና በሥራ ዕድልም የአካባቢ ነዋሪ የመቀጠሩ የሰፋ ነው። በዚህም ብሄር ተኮር ነው ማለት አስቸጋሪ ነው።
በመርህ ደረጃ ወደ ግል ትምህርት ተቋማት የሚመጣው ተማሪም ከፍሎ መማር የሚችል እንጂ ብሄርን መሰረት ያደረገ አይደለም፤ ዋናው ተፈላጊውን መስፈርት ማሟላቱን ነው። ነገር ግን ይህ ነገር ሙሉ ለሙሉ የለም እያልኩ ሳይሆን የመሆን ዕድሉ ጠባብ ነው። ዘመድ አዝማድ በመቅጠር ተቋማትን የሚሞሉ አይኖሩም ማለት አይቻልም። ይህ ከሆነ ከአንድ አካባቢ የመሆን ዕድል ሊኖረው ይችላል ብዬ እገምታለሁ። ከዚህ በዘለለ ደግሞ በርካታ የግል ትምህርት ተቋማት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ቅርንጫፎች አላቸው። በዚህም የተነሳ ብሄር ተኮር ናቸው ብሎ መደምደም አይቻልም፤ በርካቶችም በዚህ ውስጥ የሉበትም። ሰራተኞችም ተወዳዳሪ ካልሆነ ቢዝነሱ ስለሚወድቅ የሚጎዳው ተቋሙ ነው። እንደ ጋዜጠኛ ይህ ዋነኛ ትኩረታችሁ መሆን የለበትም የሚል እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ባላቸው ቁመና የግል ትምህርት ተቋማት ተወዳዳሪና ለአገሪቱ ችግር የመፍትሄ አካል ናቸውን?
ዶክተር ሞላ፡– በዓለም ላይ በስማቸው የሚታወቁ የትምህርት ተቋማት ሲጀመሩ እንደ ኢትዮጵያ ነበሩ። ተወዳዳሪ የሆኑት በአገራት የእድገት ደረጃቸውና ጊዜ ነው። በኢትዮጵያም ከ20 ዓመት በፊት የግል ትምህርት ተቋማት የነበራቸው እሳቤ፣ ዕድገት፣ የትምህርት ጥራት፣ የቢዝነስ አስተሳሰብ ከዛሬው ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ የተለየ ነው።
በአገራችን የግል ትምህርት ተቋማት ከ20 ዓመት በፊት ጥናትና ምርምር አይታወቅም ነበር።፡ አሁን ግን አንዱ ተልዕኮ ሆኖ እያለገለ ነው። ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባዔዎችም በስፋት ተጀምረዋል። ዕድሳትም እና እውቅና የሚሰጠውም እነዚህ ነገሮች እየተጠናከሩና እየተስተካከሉ ሲሄዱ ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የግል ትምህርት ተቋማት ወደ ተሻለ ደረጃ የመሸጋገር ዕድላቸው ሰፊ ነው።
የጥራቱ ጉዳይ አነጋጋሪ ቢሆንም ተቋማት በዓመት ለጥናትና ምርምር በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ወጪ እያደረጉ ነው። የግል ትምህርት ተቋማትም አሁን ለደረሱበት ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የነበረው ሚና እጅግ ትልቅ ነው። ብዙ ነገሮችን ይሠራሉ፤ የመንግስት ሸክምም እየቀለለ ይሄዳል። ዜጎች እየበለፀጉ ሲሄዱ በፈለጉት ተቋማት ከፍለው መማር ይጀምራሉ፤ መንግስትም እፎይታ ያገኛል።
አዲስ ዘመን፡- የግል ትምህርት ተቋማት የበለጠ ተወዳዳሪ ለመሆን ከመንግስት ምን ይጠብቃሉ?
ዶክተር ሞላ፡- ውስጣችን ንጽህና በመጉደሉ መንግስትና ህብረተሰባችንን ቅር እየተሰኙብን ነው። ሁላችንም ወደ አንድ አካባቢ አለመምጣታችን በተለይም ህግና ሥርዓትን አለማክበር፤ ብሎም አስተምሮ እስከማስመረቅ ያለው ሂደት ጥራት ችግር ይስተዋላል። ከዚህ መውጣት አለብን። በህብረተሰቡና በመንግስት ተዓማኒነት ማትረፍ ከተቻለ መንግስትም የራሱን የተሟላ ምላሽ ይሰጣል ብዬ አምናለሁ። የመጀመሪያው የሚሆነው የግል ትምህርት ተቋማት አስተዋጽዖ እውቅና መስጠት ይገባል። በግሉም ሆነ በመንግስት ሴክተር የሚማሩ ዜጎች እኩል መሆናቸው ታይቶ በዚያው ልክ እውቅና መስጠት ይገባል።
የተዛቡ አመለካከቶች አሉ። በግል ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩና የሚማሩ ዜጎች አሉ። የሚከፍሉት ታክስ፣ የፈጠሩት የመማር ዕድል ቀላል አይደለም። የመንግስትን ሸክም ተጋርተዋል። በመሆኑም ትልቅ እውቅና መስጠት ይገባል። የግልና የመንግስት ነው የሚለው የተራራቀ እሳቤ ማስታረቅ ይገባል። የመንግስትም ሆነ የግል ተቋም የመጨረሻ ውጤቱ የአገር ጉዳይ ነው። በመሆኑም አስተዋፅኦዋቸውን በአግባቡ መገንዘብ ይገባል። በዚህ ጊዜ በቂ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይገባል። ይህ በሂደት በቂ የሆነ አመራር እንዲመጣ ያደርጋል። የድጋፍ ሥራዎች ደግሞ በእቅድና በዓላማ መሠራት አለባቸው።
የግል ተቋማት ከሚወቀሱበት አንዱ እዚህም እዚያም ኩሽና በመሰለ ቤት ያስተ ምራሉ የሚል ነው። በማህበሩ ላይ ከሚቀርቡት ጥያቄዎች ግን የመሬት ጉዳይ ነው። ጥሩ ተቋም ለመገንባት መሬት ያስፈልጋል። ትምህርት ከሁሉም ነገር ቀዳሚና መሰረት ነው። ለሆቴል አገልግሎት እና አምራቾች በሚል ቦታ ቅድሚያ ይሰጣል። በዚያው እኩል በማየት መሬት ማመቻቻትና ማቅረብ ይገባል።
አዋጆችና መመሪያዎች ምን ያክል የግሉን ሴክተር ያሠራሉ በሚለው ላይ በሚገባ አይቶ መፍትሄ መስጠት ይገባል። ለምሳሌ ከአዋጁ አንዱን ብናነሳ በመንግስት ተቋማት የጋራ ቅጥር ሲፈቀድ በግሉ ተቋማት ግን አይፈቀድም። ወደታች መመ ሪያዎች ስንመለከት የግሉን ሴክተር ምን ያህል ያበረታታሉ የሚለውን ማየት ይገባል። የግሉ ሴክተር መሰናክሎች እንዲኖራቸው፣ ምቹ ከመሆን ይልቅ ወደ አልተፈለገ መንገድ እንዲገቡ ይገፋፋል። ለምሳሌ የተማሪ ቁጥር ሲነሳ አንድ ተቋም ግብዓት እስካለው ድረስ የተማሪ ቁጥር ትልቅ ጉዳይ መሆን አልነበረበትም። የተቋቋሙት በተመጣጣኝ ዋጋ ዜጎችን ማስተ ማር ነው። አንዳንድ ባለሃብቶችም በዚህ እየተማረሩ ነው። ሌላ ቢዝነስ ውስጥም ለመግባት የሚገ ፋፋቸው ሁኔታ አለ። ዘርፉን ትምህርት ሚኒስቴር ሲቆጣጠረው ቀደም ሲል የተማሪ ቁጥር አይጠየቅም ነበር። መስፈርቶችና ግብዓ ቶች መሟላታቸው ነበር የሚታየው። አሁን ግን ይህ አሃዝ በ50 ተማሪዎች ተወስኗል። ዘልማዳዊ አሰራር መተግበር ጀመረ።
ተቋማት በትምህርት ክፍሉ እንደተባለው 50 ተማሪ ዎችን ብቻ እያስተማሩ ነው ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው። ማህበሩ ይህ እንዲስተካከል እየጠየቁ ነው። ጉዳያችን እስከ ፓርላማ ድረስ መነጋገሪያ ሆኗል።አንዳንድ ነገሮች አያስኬዱም። መሆን ያለበት ቁጭ ብሎ መነጋገር ነው። በእርግጥ አሁን ያለው የመንግስት አሰራር የመረዳትና የማህበሩን ሃሳብ የመቀበል ፍላጎት አለ። መሆን ያለበት ግብዓትና አስፈላጊ ነገሮች መሟላታቸውን ማረጋገጥ ነው። አሁን መመሪዎች እየተከለሱ ነው። በዚህ ዘንድ እየተስተካከሉ ለሚገኙ ነገሮች መንግስትን እናመሰግናለን፤ የተከለሱት ወደ ሥራ እንዲገቡም እንጠይቃለን። በርቀት ትምህርት ላይም የእውቅና አሰጣጡ መስተካከል አለበት።
የግል ትምህርት ተቋማት ብዙ ፈተናዎች አሉበት። ለምሳሌ ማስተርስ ፕሮግራም ላይ የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ‹‹ሃይር ኤጁኬሽን ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተምን›› ካስተዋወቀ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ ያሉትን ሁሉም መምህራን ወደዚህ ቋት ሊገቡ ነው። ወደዚህ ሲገቡ የእነዚህ መምህራን ያሉት በሁለትና ሦስት ግል ትምህርት ተቋማት ሳይሆን ምንጩ በመንግስት ተቋማት ሊሆኑ ነው። ማስተርስ ማስተማር ያለባቸው ፒ.ኤች.ዲ ያላቸው መሆን አለባቸው። በአገሪቱ ያሉት ምሩቃን ደግሞ ጥቂት ናቸው።
ምንጫቸው ሲታይ ደግሞ የመንግስት ተቋም ነው። ስለዚህ መምህራን ወደ ሲቪ (CV) መሸጥ ሊገቡ ነው። አንድ የግል ትምህርት ተቋም ማስተርስ ለመጀመር ሁለት ረዳት ፕሮፌሰር እና ከዚያ በላይ ያለውና አንድ ማስተርስ ያለው መሆን አለበት ይላል። በዚህ ላይ መፍትሄ እንዲመጣ እየጠየቅን ነው። አገራዊ ችግር ስለሆነ መመሪያውን በማሻሻል መፍትሄ ማምጣት ይቻላል። ለመንግስት የተፈቀደው የጋራ ቅጥርን ለግል ትምህርት ተቋማትም መፍቀድ ሌላኛው መፍትሄ ነው። በአጠቃላይ ምህዳሩ አስቻይ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ለቆይታችን አመሰግናለሁ።
ዶክተር ሞላ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 8 /2014