ተወልዶ ያደገው በአማራ ክልል፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ሞረትና ጅሩ ወረዳ፣ እነዋሪ ከተማ ሲሆን፤ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ የተማረውም በዚያው ነው። በ1995 ዓ.ም ከጂማ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኮሌጅ በዲፕሎማ ትምህርቱን አጠናቋል።
የትምህርትን ዋጋ በደንብ ያውቃልና በተማረበት የግብርና ሙያ እየሰራ ትምህርቱን በመቀጠል እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ተምሯል። በፋይናንስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በግብርና የትምህርት መስኮች ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪዎች ባለቤት ነው። በገጠር ልማት አስተዳደር (Rural Development Management) የትምህርት መስክ ደግሞ ሁለተኛ ዲግሪውን ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል። በዛሬው የግብርና አምዳችን ያቀረብነው የመማርን ትርጉም የተረዳው በጋሻው መብራቴ።
በአፋር፣ በቤኒሻንጉል፣ በአማራ ክልሎችና በአዲስ አበባ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም ሀገር በቀልና ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሰርቷል። በጋሻው ከሰራባቸው ተቋማት መካከል የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (USAID) እና ፋርም አፍሪካ (Farm Africa) ይገኙበታል።
በተለይም ግብርናውን ይፈትኑታል ተብለው የሚታሰቡትን በረሃና ሙቀት የሚፈራረቅባቸውን ቦታዎች በደንብ አይቷቸዋል፤ጥሩ ሥራም ከውኖባቸዋል። በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ ባገለገለባቸው ተቋማት ውስጥ ሲሰራ ስራዎቹ ሀገርን የሚጠቅሙና ግብርናውን የሚያሻሽሉ እንዲሆኑ ታትሯል። በእዚህም ብዙ ልምዶችን እንዲቀስም እድል አግኝቷል።
ፊት በግብርና ላይ ያለው እውቀትና ግንዛቤ ውስን ነበር። በስራና በትምህርት አጋጣሚዎቹ ግብርና ማለት አብዛኛው ሰው በተለምዶ ከሚያውቀው ተግባር የሰፋ እንደሆነ ተገነዘበ። ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎች፣ ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና ዘዴዎች ፣ወዘተ. እንዳሉ አወቀ። ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን በግብርናው ዘርፍ ለምን ወደ ኋላ ቀረን›› እያለ በተደጋጋሚ ያስብና ይጠይቅ ነበር።
ተወልዶ ያደገበትን አካባቢ ያለውን የዘመናዊ የግብርና ግብአቶች እጥረት አስተዋለ። ‹‹እኔ ከአንድም ሁለት ዲግሪዎችን ተምሬያለሁ። ይህን ችግር ማቃለል ካልቻልኩ የእኔ መማር ትርጉሙ ምኑ ላይ ነው?›› ብሎ ራሱን ጠየቀ። የአርሶ አደሩን ችግር የሚያቃልልና የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማነት ለማሳደግ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ትልቅ የግብርና ኩባንያ ለማቋቋም ተመኘ።
ግብርናውን በቴክኖሎጂ በማገዝ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሻሻል መስራት እንዳለበት አምኖ ስራውን ለመጀመር ተነሳ። መነሻ ካፒታል ለማግኘትም አማራጮችን ማማተር ጀመረ። በቶኒ ኤልመሉ ፋውንዴሽን የስራ ፈጠራ ውድድር ላይ ተሳትፎ በማሸነፍ መነሻ ካፒታል ማግኘት ቻለ። አካባቢውን፣ የአርሶ አደሩን ሕይወት እንዲሁም ግብርናው ያሉበትን ክፍተቶች ስለሚያውቅ ወደ ትውልድ ስፍራው ተመልሶ በ370ሺ ብር የእህል መውቂያ መሳሪያ ገዝቶ ስራ ጀመረ፤ በጋሻው የተማረ አርሶ አደር መሆን ጀመረ።
በድርጊቱ ብዙዎች ተገረሙ። ‹‹ጥሩ ክፍያ የምታገኝበትን ስራህን ትተህ እንዴት እንደዚህ ታደርጋለህ?›› ብለው የጠየቁት ነበሩ። ‹‹አብዷል›› ያሉትም ነበሩ። በትልልቅ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ደመወዝና በትልቅ የኃላፊነት ቦታ መስራትን በመተው ወደ ገጠር ተመልሶ አርሶ አደር መሆን ለአካባቢውም ሰው የሚዋጥ አይደለም። ለእርሱ ግን ወደ አካባቢው መመለሱም ሆነ ስራውን መጀመሩ የሚገጥሙትን መሰናክሎች ሁሉ ተቋቁሞ በማለፍ ያሰበውን ዓላማ ለማሳካት መሰረት የሚሆነው ተግባሩ ነውና በጥያቄውና በወቀሳው ሳይበገር በስራው በረታ።
ሙያው ሰርቶ ማሳየትን የሚፈልግ ነውና ወደ አርሶ አደሩ ዘንድ በመዝለቅ በስራና በትምህርት ልምድ ካገኘው ተሞክሮ ስለግብርና ቴክኖሎጂ ማስተማር ጀመረ። ጎን ለጎንም መሬት በኮንትራት ወስዶ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እና በምርምር ስራ ላይ ተሰማራ። ለምርምሩ መነሻ የሆነውም በአካባቢው በስፋት ይስተዋል የነበረው የምስር በሽታ ነው። የዘር እጥረት ችግርን ለማቃለልም ምርምር ያደርጋል። አርሶ አደሩን የማስተማር፣ አትክልትና ፍራፍሬ የማልማት እንዲሁም የምርምር ስራዎቹ መልካም ውጤቶችን አስገኝተውለታል።
በጋሻው በክረምት ወራት ቀደም ሲል በአካባቢው ያልተለመዱ እንደ ጥቁር አዝሙድ፣ ካሮትና ሱፍ የመሳሰሉትን በአንድ ላይና አሰባጥሮ በመዝራት ለአካባቢው ማህበረሰብና ለአርሶአደሩ ማስተማሩን ቀጠለ። ይህ ተግባሩም የአካባቢው ሕዝብ በክረምትም ሆነ በበጋ የአትክልትና ፍራፍሬ እጥረት እንዳይገጥመው ከማድረግ ባሻገር ያልተለመዱና በውድ ዋጋ የሚሸጡ እንደ ጥቁር አዝሙድ ያሉ ቅመማ ቅመሞችን በቀላሉና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝም አድርጓል።
ንብ በማነብ ሥራ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ስራ ውጤታማ እንዲሆን በሚልም የሱፍ አበባን ከአትክልትና ፍራፍሬው ጎን ለጎን ያለማል፤ ምርቱንም አሽጎ ያከፋፍላል። ይህ ተግባር ለአካባቢው ውበት የሚሰጥ በመሆኑ ብዙዎች እንዲማረኩበትና በተለይም ወጣቶች ግብርናን እንዲወዱ አደረጋቸው። አርሶ አደሩም የበጋሻውን ፋና በመከተል የአትክልትና ፍራፍሬ ዘር ማሳው ላይ እንዲያመርትም አስችሎታል።
የተማረውን ሙያ በሚገባ በተግባር ላይ አለማየቱና ለአገሩ ያለው ልዩ ፍቅር አርሶአደሩ ዘንድ ወርዶ እንዲሰራ እንዳነሳሳው የሚናገረው በጋሻው፤ የግብርና ባለሙያ መሆን መሪም ሰሪም መሆን ነው ብሎ ያምናል። መሪነቱ ደግሞ በእውቀትና በተግባር መታየት እንዳለበትም ይገልጻል።
በጋሻው እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ ሲማር ከግብርና ስላልተለየና ሥራውን በተማረው ልክ በማከናወኑ ውጤቱን ለመመልከት ብዙ ዓመታት አልፈጀበትም። የእርሱ የእርሻ ስራ ሰርቶ ማሳያ የሆነላቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ስራውን ተመልክተውና ልምዱን ወስደው የግብርናቸውን ጎደሎ ሞልተውበታል። የአካባቢው አርሶ አደሮች በበጋ ወራት በመስኖ ማምረትን ሰፋ አድርገው የያዙት ከበጋሻው ትምህርትና ተሞክሮ ወስደው ነው። በተለይ በክረምት ወቅት ለብዙ ወጣቶች የስራ እድል ፈጥሯል።
አርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ ምርቱን መጨመርና ሕይወቱን ማቅለል የበጋሻው ትኩረት ነው፤ ለእዚህም አርሶ አደሮች ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ቀንና ሌሊት ይተጋል። ‹‹ሁሉም ሰው ቴክኖሎጂን ተከትሎ መጓዝ አለበት፤ ከተቻለ ቀድሞ መጓዝም ያስፈልጋል። ቴክኖሎጂ ማለት አዳዲስ ነገሮችን መከተልና የሚጠቅመውን መርጦ መውሰድ ነው።›› የሚለው በጋሻው፣ አርሶ አደሩ ብዙ ሥራዎቹን ቀላል የሚያደርጉለት የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዳሉ መገንዘብና ማመን እንዳለበት ይናገራል። ‹‹ይህ ሲባል ግን ‹ተቀበል› የተባለውን ሁሉ መቀበል ይገባዋል ማለት አይደለም። ውጤታማነታቸው በሰርቶ ማሳያ የተረጋገጠና ለአካባቢውም ሆነ ለመሬቱ የሚስማሙ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን መተግበር ይገባዋል›› ነው የሚለው። የሚያከናውናቸው ተግባራት ለአርሶ አደሩ የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን የሚያደርጉ እንዲሆኑ ይጥራል።
የእርሻ ባለሀብት የመሆን ራእይ ያለው በጋሻው፤ አሁን ብዙ ተግባራትን እየከወነ ይገኛል። በዚህ ፍጥነት ከተጓዘ በጥቂት ዓመታት ውስጥም ራእዩ እውን እንደሚሆንም ያምናል። በሀገሪቱ በግብርና ሥራ ፈጠራ ዙሪያ የሚፈለገውን ያህል ስላልተሰራ እርሱና ጓደኞቹ ይህን ሁኔታ ለመቀየር እንደ ባለሙያ ጥረቶችን እያደረጉ እንደሆነ ይናገራል።
‹‹በጋሻው ፋርም ቴክኖሎጂ (B Farm Tech)›› በተባለው በግሉ በከፈተው ድርጅት በኩል የመውቂያ ማሽን አቅርቦት አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማገዝም እየሰራ ነው። በዚህ ተግባሩም መውቂያ እና ትራክተርን የሚያገናኝ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) በማሰራት ላይ ነው። ይህ ሥራ ልክ እንደራይድ አገልግሎት ፈላጊው ደውሎ አገልግሎቱን የሚያገኝበትን አሰራር የሚፈጥር ነው። በተጨማሪም የግብርና መሳሪያዎች ሁሉ ከውጭ እየመጡ አገልግሎት የሚሰጡ በመሆናቸው አገርንም አርሶአደሩንም መጥቀም ባለባቸው ልክ እየጠቀሙ ባለመሆኑ መሳሪያዎቹን በአገር ውስጥ ለማምረት ጥረት እያደረገ ነው።
‹‹የተለየ ጥረት የተለየ ስኬትን ይሰጣል›› ብሎ የሚያምነው በጋሻው፤ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ‹‹ንስር አግሪ ቴክ›› የሚባል ድርጅትም አቋቁሟል። በዚህ ድርጅት በኩል እስካሁን ካከናወናቸው ተግባራት የላቁ ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት አቅዷል። ድርጅቱን የመሰረቱት ባለሙያዎች የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ደግሞ ይህን ዓላማ ከማሳካት የመነጨ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። በግብርና ላይ የተሰማራው በጋሻው፣ በኤሮስፔስ (Aerospace) ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪ ካለው እና ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ ጓደኞቹ ጋር በጥምረት የተቋቋመው ይህ ድርጅት በግብርናው ዘርፍ ለአገር የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተስፋ አላቸው።
በአሁኑ ወቅት የበጋሻውና ጓደኞቹ ዋና ትኩረት የግብርናውን ምርታማነት የሚያሻሽል ድሮን (Drone) ጥቅም ላይ ማዋል ነው። በዚህ ተግባራቸውም በድሮን የሰብል፣ አትክልትና ፍራፍሬ በሽታዎችን የመለየት፤ የመድኃኒት ርጭት እና አንበጣ የማባረር ተግባራትን ለማከናወን እየጣሩ ነው። ሥራቸው እውቅና ተሰጥቶት ወደ ተግባር እንዲገቡ የተፈቀደ ቢሆንም፣ ድሮንን ለማብረር ሕግና ፖሊሲ አለመኖሩ ግን እንቅፋት ሆኖባቸዋል።
‹‹ግብርና ሥራ ሲያጡና ሥራ ሲፈቱ የሚገባበት ሙያ አይደለም፤ የራስ ገነትን መፍጠሪያ እንጂ። ምክንያቱም ተፈጥሮን እየተመገቡ ተፈጥሮን ለሌላ መመገብ የሚቻልበት መስክ ግብርና ነው።›› የሚለው በጋሻው፣ ይህ እውን የሚሆነው በእውቀትና በፍላጎት ሲሰራ ብቻ ነው ይላል።
‹‹እኔ አሁን ባለሁበት ደረጃ የመውቂያ ማሽን በማከራየትና በሌሎቹ የግብርና ስራዎቼ በወረዳ ደረጃ ማንም ሰው የማይከፈለውን ደመወዝ በወር አገኛለሁ። ከፋዩ ደግሞ ራሴ ነኝ። የምናተርፈው ብዙ ጊዜና ነጻነት እንዳለ ማወቅም ይገባናል። ሙያንና ልምድን ማካፈልም እጅግ አስፈላጊ ነው›› የሚለው የግብርና ባለሙያው፤ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባና በተለይም የግብርና ባለሙያዎች ይህን ቢጠቀሙ አትራፊ እንደሚሆኑ ይናገራል።
በጋሻው ግብናውን ለማዘመንና የአርሶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል ላከናወናቸው ተግባራት ሽልማቶችን አግኝቷል። ስራው ከአካባቢው አልፎ በክልል ደረጃ በመልካም ተሞክሮነት የሚጠቀስ ለመሆን በቅቷል።
በጋሻው ግብርና ከተለመደው አሰራር የተሻለና በሙያ የታገዘ አሰራር እንደሚያስፈልገው በፅኑ ያምናል። እንደ እርሱ ገለጻ፤ አመራሩ አርሶ አደሩን አሳምን ተብሎ ያልተገባ ነገር ማስተማር የለበትም። ኮርጆ ማስኮረጅም ይህ አይደለም። ምክንያቱም በዚህ ዓይነቱ አካሄድ አርሶ አደሩ በብዙ መንገድ ተጎድቷል። መሬቱ ሳይመረጥ ይህንን ዝራ ተብሎ ዋጋ እየከፈለ ነው። በተለይ ዛሬ ላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንኳን መጠቀም እንዳይችል ሆኗል። እናም መስጠት ያለብን የሚጠቅመውን እንጂ የማይስማማውን መሆን የለበትም። ባለሙያውን እንዲሰማና ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀም ለእያንዳንዱ መልከአምድር የሚስማማውን ነገር ማጥናትና መስጠት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የግብርና ባለሙያዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። የሚጠቅመውን ለማሳየት መጣርና መመራመርም ይገባቸዋል።
የግብርና ባለሙያዎች የራሳቸው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማስቻል ላይም በሚገባ አልተሰራም ይላል፤ በጋሻው። ይህ ቢሆን ኖሮ ለአንድ ቦታ ብቻ የተሰጠውን ተክል ሌላ ቦታ ላይ በማላመድ የምግብ ችግራችንን መቅረፍ እንችል ነበር። ሆኖም ውጭውን እንጂ ራሳችንን እንድናይ ሆነን ስላላለፍንና አምነንበት ቁርጠኛ ሆነን ወደ ሥራው ስላልገባን ችግሩ እንዲቀጥል አድርጎታል። ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ጥናት ተደርጎ ሊሰራበት እንደሚገባም ያሳስባል።
‹‹ … ሰው የሚሠራው አለቃው ያዘዘውን ነው። ሳይንስ ተኮርም አይደለም። ግብርና ደግሞ ፍላጎትንና እውቀትን ይሻል። እውቀቱና ሙያው የሌለው ሰው ቦታውን እየመራው፤ ባለሙያው ደግሞ በምንቸገረኝነት ሥራውን እየከወነው ውጤት መጠበቅ ሞኝነት ነው። እናም ከዚህ የአሰራር ችግር ካልወጣን ግብርናውን ማዘመን አንችልም። ሙያን በአግባቡ መጠቀም ከጥገኝነት መላቀቅ ብቻ ሳይሆን ለራስ ነጻነትን መስጠት ነው። አዳዲስ ፈጠራዎችን ለመስራት ራስን ነጻ ማድረግ ይገባል›› በማለት ያስረዳል።
የተማረ ሰው ብር ጠባቂ ሳይሆን ብር ፈጣሪ መሆን እንዳለበት የሚያምነው በጋሻው፤ በተለይም ቢሮ ላይ ያሉ ሰዎች ተጨማሪ የሙያቸው ሰራተኛ መሆን እንደሚገባቸው ይመክራል። በተለይም የግብርና ሰራተኞች የኃላፊያቸው ትዕዛዝ አስፈጻሚዎች መሆን ብቻ እንደሌለባቸውና እውቀት የሚጠይቁና በአርሶ አደሩ ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ መፍጠር በሚችሉ የዘርፉ ተግባራት ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው በአፅንዖት ይመክራል።
‹‹ ብዙ ችግሮች ካሉና ብዙ የሚማረር ሰው ካለ ያንን ችግር መፍታት የሚችል ኃይል ስለሚያስፈልግ ብዙ የሥራ እድል አለ ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ ቅርብ የሚሆነው የተማረውና የተመራመረው ነው። እናም ራስን የዚያ አካል ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው። በፈለጉት መልኩ ለመሥራት ያለንበትንና ወደ ፊት መሆን የምንፈልገውን ማወቅ አለብን። ከዚያም ሀሳባችንን ለመተግበር ቁርጠኛ እንሁን። ተስፋ ባለመቁረጥ ውስጥ አዳዲስ ፈጠራዎችን እንሞክር። ያን ጊዜ ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የምንተርፍበትን መንገድ እኛገኛለን›› ይላል።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2014