የፌዴራሉ መንግሥት ለቀጣይ ዓመት የያዘውን በጀት መጠን ይፋ አድርጓል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እንዳስታወቀው ለ2015 በጀት ዓመት ለመደበኛ ወጪ ብር 347.12 ቢሊዮን፣ ለካፒታል ወጪ ብር 218.11 ቢሊዮን እንዲሁም ለክልል መንግሥታት ድጋፍ ብር 209.38 ቢሊዮን እና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ብር 12.0 ቢሊዮን የተያዘ ሲሆን አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥት የ2015 በጀት ብር 786.61 ቢሊዮን ይሆናል። ይህ በጀት ከ2014 በጀት ዓመት በጀት ጋር ሲነጻጸር የብር 111.94 ቢሊዮን ወይም የ16.59 በመቶ እድገት አሳይቷል። ቁጥሮቹ ካለፈው ዓመት አንጻር ሲታዩ ጨምረዋል። ነገር ግን አሁን ካለው የዋጋ ግሽበት አንጻር ሲታይ በጀቱ አነስተኛ ነው ማለት ይቻላል።
ሀገሪቱ ከሚያስፈልጋት በጀት አንጻር ሲታይ ደግሞ በጣም ጥቂት ነው። በጦርነት የወደመ ብዙ መሰረተ ልማት ፤ ድርቅ ፤ የእቃዎች የዋጋ ንረት ፤ ወረርሽኝ ፤ ዓለም አቀፍ ጫና እና ሌሎች በርካታ ችግሮች በየቦታው መደቀናቸውን ላየ ሰው በጀቱ ብዙም የሚያወላዳ እንዳልሆነ መገንዘብ ይችላል። ለዚህም ይመስላል የፋይናንስ ሚኒስትሮቹ ሰሞኑን በተደጋጋሚ በጥቂት በጀት እቅድን ስለማከናወን በተደጋጋሚ ሲያወሩ የሚደመጠው።
የሆነ ሆኖ ብሩ ጥቂት እንደሆነ መተማመን ይቻላል። ስለዚህ ዋነኛው ጥያቄ ያለውን እንዴት አድርገን እንጠቀም የሚለው ነው። በዚህ ላይ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል። ጥቂቶቹን በቅደም ተከተል ማንሳት እንችላለን። የመጀመሪያው ጉዳይ አዋጭ ፕሮጀክቶችን መምረጥ እና የማያዋጡትን ወደ ጎን ማድረግ ነው።
በቅርቡ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሃላፊዎች በአንድ ዘገባ ላይ ሲናገሩ እንደሰማነው ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት ተካሂዶባቸው አዋጭ ባለመሆናቸው ተሰርዘዋል ብለዋል። እንዲህ አይነት አሰራር መጠናከር አለበት። በዘፈቀደ የሚሰሩ ፋይዳ ቢስ ፕሮጀክቶች ሀገርን እዳ ውስጥ የሚከትቱ ናቸው።
ከዚህ ቀደም እንደ ሀገር ገብተንባቸው ከነበሩ ችግሮች መሀከል አንዱ እና ዋነኛው ጀምረናቸው የነበሩት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መጨረስ አለመቻላችን ነበር። ከለውጡ በኋላ መንግሥት ከወሰዳቸው እርምጃዎች መሀከል ቀዳሚውም እነዚህን ፕሮጀክቶች ማጠናቀቅ ነበር። በዚህ መልኩ ተበላሽተው የነበሩ ብዙ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ ተመልሰዋል። አሁን አዳዲስ ፕሮጀክቶች እየተጀመሩ ነው።
እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ አንደኛ ጉዳይ ያስፈልጉናል ወይ ብለን መጠየቅ ያለብን ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ ልንፈጽማቸው እንችላለን ወይ ብለን ራሳችንን መገምገም አለብን። ምክንያቱም እነዚህ ፕሮጀክቶች የሚከናወኑት በዚሁ ትንሽ ነው ባልነው ዓመታዊ በጀት ላይ ነው። ያለንን ጥቂት አቅም በትክክለኛው ቦታ ላይ አውለን በአግባቡ መጠቀም ካልቻልን ያለችውን ጥቂት ሀብትም አባክነን ለከርሞውም እዳ ተሸክመን ልንቀመጥ እንችላለን።
በሁለተኛ ደረጃ ልንጠነቀቅበት የሚገባ ሙስና ነው። የሙስና ነገር አሁንም መላ ሊገኝለት ያልቻለ መሰረታዊ ሀገራዊ ችግራችን ነው። አሁንም ከፍተኛ የመንግሥት በጀት በሙስና ይወድማል። በሙስና ምክንያት ቀላል የማይባል ገንዘብ አላስፈላጊ ፕሮጀክቶች ላይ ይወጣል ወይም ፕሮጀክቶቹ ከሚያስፈልጋቸው ገንዘብ በላይ እንዲወጣባቸው ይደረጋል። በጥናት ፤ በሥልጠና ፤ በምርምር ፤ በሲምፖዚየም ፤ በምክክር መድረክ ወዘተ ስም ይባክናል። ይህን ማስቆም ካልተቻለ ይቺው ጥቂት በጀት የሙሰኞች ሲሳይ ልትሆን ትችላለች። አሁን ላይ ካለው የኑሮ ውድነት አንጻር ግለሰቦች በሕገወጥ መልኩ ገንዘብ ወደ ማግኘት ሊያመዝኑበት የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። ስለዚህም ጠንካራ ቁጥጥር ካልተደረገ ሙስናው አይን ያወጣ የአደባባይ ተግባር ሊሆን ይችላል።
በሶስተኛ ደረጃ ተቋማት የተመደበላቸውን የስራ ማስኬጃ በጀት የሚጠቀሙበትን መንገድ ማስተካከል በጣም አስፈላጊ ነው። የብዙዎቹ ተቋማት ለስራ ማስኬጅ የሚሰጣቸው በጀት ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው። ይህ የሚበረታታ እና የሚያስፈልግ ነው። ነገር ግን ብዙዎቹ ተቋማት በየጊዜው በጀታቸው የመጨመሩን ያህል አገልግሎት አሰጣጣቸው ሲጨምር አይታይም። ይህ ምክንያቱ ብዙ ቢሆንም የብዙዎቹ ተቋማት በጀት ግን የሚያልቀው አገልገሎትን በማሻሻል ላይ እንዳልሆነ እርግጥ ነው።
ዓላማ የሌላቸው ስብሰባዎች ፤ የማይተገበሩ ጥናቶች ፤ ስፍር ቁጥር የሌለው አበል ፤ ተደጋጋሚ ድግሶች ወዘተ.. መንግሥትን ለስራ የመደበውን የመስሪያ ቤቱን በጀት ሙጥጥ አድርገው ሲበሉት በተደጋጋሚ ታይቷል። ስራው አንዲት እርምጃ ሳይራመድ የስራ ማስኬጃው በጀት ካለቀ ይህ የብዙ ችግር ምልክት ነውና ይህን ማየት እና ማስተካከል አስፈላጊ ነው።
በመቀጠል ሊታይ የሚገባው ጉዳይ የበጀት አጠቃቀሙን ግምገማ በየጊዜው በቋሚነት ማካሄድ አስፈላጊ ነው። ብዙውን ጊዜ እንደታየው የመንግሥት በጀት አንዴ ከተለቀቀ በኋላ ተመልካች የሌለው ዝርው በጀት ነው። የብዙ ተቋማት የበጀት አጠቃቀም ግምገማ ገለልተኛ በሆነ አካል የማይታይ ሲሆን መንግሥት የመደባቸው ኦዲተሮችም የበጀት ግምገማቸው ውጤት ምን ላይ እንደደረሰ ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው። እንደ አሰራር የመንግሥት ተቋማት በጀት በየጊዜው ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ መከታተያ ሥርዓቶች ቢኖሩም እነዚህ ሥርዓቶች በሚገባ ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው በጀቱ በከፍተኛ ደረጃ መባከኑን ቀጥሏል። ስለዚህም በቀጣዩ ዓመት ያለችንን አነስተኛ በጀት በቅጡ መጠቀም ከፈለግን የተሻለ ጠንካራ የበጀት ክትትል ሥርዓት መፍጠር አስፈላጊ ነው።
በመጨረሻም የበጀት አጠቃቀማችን ሁነኛ ውጤት እንዲያመጣ ከተፈለገ የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኛ መሆን አለበት። ከላይ የተባሉት ሃሳቦችም ሆነ ሌሎች የተሻሉ የበጀት አጠቃቀሞችን ለመፍጠር የፖለቲካ አመራሩ በሕዝባዊነት እና ሀገር ወዳድነት መንፈስ እየተመራ ውሳኔዎችን መወሰን አለበት። የፖለቲካ አመራሩ ሕዝባዊነትን ሲላበስ ለሀገር እና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን ብቻ ይተገብራል።
የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኛ ከሆነ ሙስና አይፈጽምም ፤ ለሙስና እና ለሙሰኞች የሚሆን ትእግስትም የለውም። የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኛ ከሆነ በየተቋሙ የሚመደበው በጀት ምን ላይ እንደዋለ ይከታተላል ፤ ይወስናል። ከሁሉም በላይ የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኛ ከሆነ የበጀት አጠቃቀሙን ሂደት በቋሚነት ይከታተላል። ብክነት ሲኖርም ያርማል ፤ አጥፊዎችንም ይቀጣል። ስለዚህም የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው። አልያም አሁን እንደሚደረገው በውስጣዊ ግምገማ እና ቦታ በመቀያየር ብቻ የሚያልፍ ከሆነ ይህ አዲሱም በጀት ከዚህ ቀደም እንደነበሩት በጀቶች የሚባክን ይሆናል።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2014