የተወለዱት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቢሆንም ያደጉትና የተማሩት አሰላ ከተማ ነው:: እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ የቄስ ትምህርት ቤት ገብተው ፊደል ቆጥረዋል:: የመጀመሪያ ደረጃም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት ራስዳርጌ ትምህርት ቤት ነው:: የዘመናዊ እርሻ ፋና ወጊ ከሆኑት አባታቸው ሥር ቁጭ ብለው በእውቀትና በጥበብ ያደጉት እኚሁ ሰው የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ጭላሎ እርሻ ልማት ውስጥ በሹፌርነትና አስተርጓሚነት ተቀጥረው ሰርተዋል:: እንዲሁም በዚሁ ተቋም ውስጥ የእቅድና ልማት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ በመሆን አገልግለዋል:: በነበራቸው ቅልጥፍና እና ታታሪነትም የውጭ እድል አግኝተው ሲዊዲንና ሃንጋሪ በመሄድ በእርሻ፤ በእርሻ ኢኮኖሚክስና በእርሻ ልማትና ማህበረሰብ አቀፍ ግብርና ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ ድረስ ተምረዋል::
በተማሩበት የሙያ ዘርፍ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ እስከ ከፍተኛ ዓመራርነት ድረስ ከአርባ ዓመታት በላይ ያገለገሉት እንግዳችን በዚህም ስራቸው 74ሃገራትን የመጎብኘት እድል ያገኙ ሲሆን በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት ላይ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ ያበረከቱት አስተዋፅኦ በከፍተኛ ደረጃ ይጠቀሳል::
ወደሃገራቸው ከተመለሱም በኋላ በተለያዩ ሃገራት ያካበቱትን እውቀትና ተሞክሮ ለማካፈል እንዲሁም የግብርና ልማቱን ለማገዝ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ቢጠይቁም ጥያቄያቸው ተቀባይነት አላገኘም:: በመሆኑም ፊታቸውን ወደ እርዳታ ድርጅቶች በማዞር በገንዘብና በጉልበት መደገፍ ያዙ:: ከዚሁ ጎን ለጎንም የወላጅ አባታቸውን ታሪክ የሚያትተውን ‹‹ተድላ አበበ- የዘመናዊ እርሻ ፋና ወጊ›› የተሰኘውን መፅሃፍ ከመፃፍ ጀምሮ 16 የተለያዩ ታሪክና ይዘት ያላቸውን እውነተኛ ታኮችና ልቦለዶችን በመፃፍ ለህትመት አብቅተዋል:: ለአብነትም የአክሊሉ ሃብተወልድን ማስታወሻ፣ የአፄ ኀይለስላሴን ትክክለኛ ማንነት እንዲሁም የኢትዮጵያን ውብ ገፅታ የሚያሳዩ መፅሃፍትን በምስል በማስደገፍ ለአንባቢያን ያደረሷቸው መፅሃፍት ተጠቃሽ ናቸው:: አዲስ ዘመን ጋዜጣም እኚህን ታላቅ ሰው የዛሬው የዘመን እንግዳ አድርጎ እንደሚከተለው ይዞላችሁ ቀርቧል::
አዲስ ዘመን፡- የውጭ የትምህርት እድል ያገኙበትን አጋጣሚ ያስታውሱንና ውይይታችን እንጀምር?
ዶክተር ጌታቸው፡- ጭላሎ እርሻ በ18 ዓመቴ በሹፌርነትና በአስተርጓሚነት ተቀጥሬ በምሰራበት ወቅት በዋናነት ሞዴል ገበሬዎችን እንከታተል ነበር:: አንድ ዓመት ተኩል እንደሰራሁ ሪፖርት ፃፉ ተባለ:: ይሄ ነው እንግዲህ የህይወት አቅጣጫዬን ሙሉ ለሙሉ የቀየረው:: በመሰረቱ እኔ ከዚህ በፊት ሪፖርት እንዴት እንደሚፃፍ አላውቅም ነበር:: በመሆኑም ጸሃፊዋን ከዚህ ቀደም ተፅፎ ከሆነ ጠየኳትና ሰጠችኝ:: በነገራችን ላይ ከእኔ ጋር የሚሰሩት ሌሎቹ አራቱ ሰዎች አለማያ ኮሌጅ የጨረሱ ሲሆኑ እኔ ብቻ ነኝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ያጠናቀኩት:: ግን የሚገርምሽ የቀደሙትን ሪፖርቶች እያየሁ የራሴን ሪፖርት ቆንጆ አድርጌ ሰርቼ ለዳሬክተሩ ሰጠሁት:: እሱም የሌሎቹን እናየዋለን ግን የጌታቸውን ዩኒቨርስቲ ስላልጨረሰ እኔ እሞላበታሁ አለ:: ሃሙስ እለት ይህንን ብሎኝ ሲያበቃ ሰኞ እለት አስጠራኝና ከመቀመጫው ተነስቶ አቅፎ ሳመኝ:: እንዲህ አይነት ሪፖርት ማንም የፃፈ የለም፤ እጅግ በጣም ጥሩና ትክክለኛውን የፕሮጀክቱን ገፅታ የሚገልፅ ሪፖርት ነው የፃፍከው አለኝ::
በወቅቱ ታዲያ ከአለማያ ኮሌጅ የመጡት ባለሙያዎች ይከፈላቸው የነበረው 550 ብር ሲሆን እኔ የማገኘው ደግሞ 275 ብር ነበር:: ዳይሬክተሩ በዚያ ሪፖርት በመደሰቱ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ደውሎ ስለምሰራው ስራ ጥሩነትና ደመወዝ ከሌሎቹ እኩል እንዲከፈለኝ ቢጠይቅም በወቅቱ የነበሩት ሃላፊ ለዩኒቨርስቲ ምሩቃን እንጂ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለጨረሰ ሰው አይሰጥም አሉ:: ይሁንና የትምህርት እድል እንዲሰጠኝ ተስማሙ:: እናም ያቺ ሪፖርት ሲዊዲን ሃገር ነፃ የትምህርት እድል እንዳገኝ በር ከፈተችልኝ:: የመጀመሪያ ዲግሪዬን እንደጨረስኩኝ ተመልሼ ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ልክ እንደ ጭላሎ እርሻ (ካዱ) አይነት ፕሮጀክት ወላይታ ሶዶ ላይ ዋዱ የተባለ ፕሮጀክት እንዳቋቁም የእርሻ ማናጀር ሆኜ ተመደብኩኝ::
ስምንት ወር ከሰራሁ በኋላ አንድ ቀን እንደተለመደው የከረመ ጋዜጣ ሳገላብጥ ሃንጋሪ በእርሻ ትምህርት የማስተርስ ዲግሪ ለመማር የሚፈልግ ካለ ማመልከት እንደሚችል የሚገልፅ ማስታወቂያ አነበብኩኝ:: የሚገርምሽ ጋዜጣው ከወጣ አንድ ወር ያለፈው ቢሆንም እድሌን ልሞክር ብዬ ኢምባሲ ስደውል አንድም ሰው እንዳላመለከተ ነገሩኝ:: ያ የሆነበት ምክንያት በንጉሱ ዘመን አሜሪካና ሌሎች የምዕራብ ሃገራት እንጂ እንደሃንጋሪ ያሉ ኮምዩኒስት ሃገር ለመማር የሚያስበውም አልነበረም:: መልቀቂያ አስገብቼ እርሻ ሚኒስቴር በኩል አመለከትኩኝ:: ሀንጋሪ እንደሄድኩኝ ሁለት መኝታ ቤት ያለው አፓርትመንት ተሰጠኝ፤ ሶስት ወር ቋንቋዉን የምታሰለጥነኝ ሴት ተመደበችልኝ፤ የአራት ፕሮፌሰሮች ደመወዝ የሚያክል ገንዘብ ተከፈለኝ፤ በዚያ ላይ ትምህርቱ እንደሰጋሁት በሃንጋሪኛ ሳይሆን በእንግሊዘኛ መሆኑ ትልቅ እረፍት ሰጠኝ:: በአጠቃላይ ለመግለፅ በሚቸግር ሁኔታ ማንም የማያገኘው እድል ነው የተሰጠኝ::
ማስተርሴን እንደጨረስኩኝ ዶክትሬትን እዛው ለመስራት ሳመለክት ግን በኢትዮጵያ መንግስት በመለወጡ ምክንያት በአዲሱ መንግስት እውቅና ካልተሰጠኝ እንደማልቀጥል ተነገረኝ:: እኔም ፈጠን ብዬ በወቅቱ አመራር ለነበሩት ዶክተር ፀጋአምላክ አሳወኩዋቸውና ዶክትሬቴን እንድቀጥል ተፈቀደልኝ:: ትምህርቴን ልጨርስ ስል ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር የሚባል ነገር ተከሰተ:: በዚያ ወቅት ደግሞ ሚስት አግብቼ ልጆችም ወልጄ ስለነበር እንዴት እመለሳለሁ ብዬ ሳስብ ሌሎችም ሰዎች እንዳልመለስ መከሩኝ:: በዚህ መሰረት ቤተሰቤን ይዤ ወደ ሲዊዲን ተመለሰኩና በተማርኩት ትምህርት ዘርፍ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቀጠርኩ:: ሌሴቶ የሚባል ሃገር ተመደብኩ፤ በመቀጠልም ታንዛኒያ፤ በተከታታይ 17 ሃገራት በቋሚነት ተመድቤ የሰራሁ ሲሆን 74 የአለም ሃገራትን ደግሞ በስራ አጋጣሚ እየተዟዟርኩኝ ለማየት ችያለሁ:: ብዙ ጊዜዬን የአለም አቀፉ የምግብ ድርጅት ውስጥ ነው የሰራሁት፤ በመቀጠል ግን የአለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት ውስጥ አገልግያለሁ::
አዲስ ዘመን፡- እስቲ አሁን ደግሞ ስለእርዳታ ሥራዎት በጥቂቱ ያብራሩልን?
ዶክተር ጌታቸው፡– በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ 45ዓመት አገልግዬ ወደ ተወለድኩባት ሃገር ከተመለስኩ በኋላ ሜቄዶኒያ በመሄድ ድርጅቱ በሁለት እግሩ እስከሚቆም ድረስ ከየድርጅቱና ባለሃብቱ ገንዘብ እየለመንኩ የበኩሌን ድጋፍ ሳደርግ ቆይቻለሁ:: በመቀጠልም እድገት የተባለ የህፃናት መርጃንም በተመሳሳይ እናትና አባት የሌላቸውን ህፃናትን ሙሉ ጊዜዬን በመስጠትና የቦርድ አባልም ሆኜ እየሰራሁ ነው ያለሁት:: ከዚህም ባሻገር የማሳትማቸውን መፅሃፍት ገቢ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ለእነዚህ ድርጅቶች ነው ያስረከብኩት:: በቅርቡም ሁለት መፅሓፌን አሳትሜ በቀጥታ ለሜቆዶንያ ሰጥቻለሁ:: የመጨረሻ መፅሓፍቶቼን ደግሞ አምባ ለሚባል የህፃናት ማሳደጊያ ሙሉ ለሙሉ ሰጥቻለሁ:: አሁንም ቤቴ ውስጥ የማሳድጋቸው ሁለት ልጆች አሉኝ:: ይህንን የማደርገው እኛ ረጅሙን መንገድ ጨርሰናል፣ ነገ አገር ተረካቢ የሆነውን ዜጋ ግን የመደገፍና የማብቃት ሃፊነት አለብን ብዬ ስለማምን ነው:: በቀጣይም አቅሜ የቻለውን ያህል የማደርግ ነው የሚሆነው::
አዲስ ዘመን፡- የግብርና ባለሙያ ሆነው ሳለ በርካታ መፅሓፍትን በመፃፍ ለንባብ አብቅታዋል:: ከዚህ በመነሳት እንዳው የተደበቀ የስነ-ፅሁፍ ተሰጥኦ አሎት ማለት እንችላለን?
ዶክተር ጌታቸው፡- እውነት ለመናገር በተለይ ከውጭ እንደተመለስኩኝ ግብርና ሚኒስቴርም ሆነ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት በመሄድ በሙያዬ ሃገሬንና ህዝቤን ለመደገፍ ጥያቄ አቅርቤ ነበር:: ሆኖም የሚቀበለኝ አላገኘሁም:: እንደሚታወቀው የመጣሁት በወያኔ ጊዜ ነው፤ እዚህ ሃገር ዓለም-አቀፍ ተሞክሮ ያለውና ብዙ እውቀት ያካባተ ባለሙያ ላግዝ ሲል ለምን እንደሚከለከል አይገባኝም:: እንደነገርኩሽ በርካታ የዓለም ሃገራትን ጎብኝቻለሁ፤ ከ147 በላይ ነጮች በስሬ ስመራ የነበርኩ ሰው የገዛ ወገኖቼን ልደግፍ ባልኩኝ እንዴት ተቀባይ ማግኘት እንዳልቻልኩ ለእኔ ዛሬም ድረስ እንቆቅልሽ ነው:: በወቅቱ ከነበሩ የመንግስት ሰዎች ምላሽ በኋላ ምላሽ በማጣቴ አዲስ አበባ በሚገኘው የዓለም የምግብ ድርጅት ውስጥ የሥራ አስኪያጁ ዋና አማካሪ ሆኜ አንድ ዓመት ተኩል ሰርቻለሁ::
ከዚያ በኋላ ግን ቁጭ ከምል ብዬ መፃፍ ጀመርኩኝ፤ በቅድሚያም የአባቴን ታሪክ ፃፍኩና አሳተምኩኝ:: ቀጠልኩና ሁልጊዜ የሚሳዝኑንኛ ዓለም ያላወቃቸው ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ አክሊሉ ሃብተወልድን ታሪክ ‹‹የአክሊሉ ማስታወሻ›› ብዬ ከፃፍኩኝ በኋላ የቀድሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት እንድሪያስ እሸቴን ጠይቄ አምስት ፕሮፌሰሮች ድጋፍ አግኝቶ ታተመ:: ይህ መፅሃፍ ከጠበኩት በላይ በብዙ ሺ ኮፒ ነው የተሸጠው:: ከዚያ በኋላ ደግሞ የራሴን የህይወት ታሪክ ፃፍኩኝ:: በመቀጠልም የሰባት ዲያስፖራዎች ታሪክ የያዘ ‹‹ከዝታ ጓዳ›› የተሰኘ መፅሃፍ አሳተምኩኝ:: በዚህም አላበቃሁም፤ ሃንጋሪ ሳለሁ አንድ አባስዩም ጎይቶም የሚባሉ ሰው ያጫወቱኝን ታሪክ በመፅሓፍ መልክ አሳትሜዋለሁ:: እቅድ 27 የተባለ ልብወለድ ፤ በኮሪያ የዘመቱ ጀግኖቻችንን የሚያወሳ አንድ መፅሃፍ ለአንባቢዎች አድርሻለው::
በተጨማሪም ሁልጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ በአለም ላይ ጦርነትና ረሃብ ብቻ ይታወቃል? ለምን ጥሩ ገፅታችንን አላሳይም? ብዬ የሃገራችንን ጥሩ ጥሩ ጎኖች የሚያሳዩ 500 የሚሆኑ ፎቶግራፎዎችን አሰባስቤ ከነማብራሪያው የሚያሳይ ትልቅ መፅሓፍ ከኢትዮጵያ አየር መንድ ጋር በመተባበር ዶባይ አምስት ሺ ኮፒ ታተመ:: በመቀጠልም ‹‹ የማያባራው ጦስ›› የተሰኘ ልብ ወለድ ፅፊያለሁ:: በነገራችን ላይ ልቦለዶቹን ጨምሮ አብዛኛው መፅሓፎቼ እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ናቸው:: ከእነዚህም መካከል ተነጣጥለው ሲዊዲንና ኢትዮጵያ ያደጉ ሳይተዋወቁ የኖሩ መንትያ ዶክተሮች ላይ ያነጣጠረው ‹‹መንታ ነፍሶች›› የተባለው መፅሓፌ ተጠቃሽ ነው:: እናም በዚህ መልክ አሁን ድረስ ቀጠለና ላይ 16ኛ መፅሓፌን ለማስመረቅ እየተሯሯጥኩ ነው ያለሁት::
አዲስ ዘመን፡- በጎንደሬው ነጋዴ ላይ ተመስርተው ስለፃፉት መፅሃፍ እስቲ በቅጡ ያብራሩልኝ?
ዶክተር ጌታቸው፡– እኚህ ነጋዴ ከስማቸው ጀምሮ አስገራሚ ታሪክ ያላቸው ሰው ነበሩ:: የሚገርምሽ እኚህ ሰው ጎንደሬ ናቸው፤ የአባታቸውም ስም ጌታቸው ነበር፤ ከጎንደር ወደ አስመራ እየሄዱ እህል፤ ከአስመራ ደግሞ ጨው እያመጡ ይሸጡ ነበር:: እኚህ ነጋዴ እንደልባቸው እንዲገቡ እንዲወጡ ጌታቸው የሚለውን የአባታቸውን ስም በመተው ወደ ጎይቶም ቀይረውታል:: አንድ ቀን ማርዮ የሚባል ጣሊያናዊ ከአስመራ ምፅዋ ይወስዳቸዋል፤ ‹‹ሲጋራ ግዛ›› ብሎ 10ሺ ሊሬ ይሰጣቸዋል:: በወቅቱ የ17 ዓመት ጎረምሳ የነበሩት እኚሁ ሰው በተባሉት መሰረት ሲጋራውን ገዝተው ሲመለሱ ውሃ ላይ የሚንሳፈፍ ቤት ያያሉ፤ ያለመሰረት ውሃ ላይ በሚናኘውን ቤት መሳይ ነገር ተደንቀው ጠጋ አሉት፤ ሰዎች ወደ ውስጥ ሲገቡ አይተውም ተከትለው ገቡ:: አንድ ነጭ መርከበኛ ያገኛቸውና ‹‹ለነጭ ብቻ የተፈቀደ ነው ምን ትሰራለህ›› ብሎ ያፈጥባቸዋል፤ ማርዮ የተባለ ሰው ሲጋራ ግዛ ብሎ ልኳቸው እንደሆነና መውጫው እንደጠፋባቸው ይናገሩታል:: ያ ሁሉ ሲሆን ታዲያ አንድ ሰዓት ተኩል ያህል ጊዜ በመርከብ ተጉዘው እንደነበር አላወቁም ነበር:: በዚያው ተልከው ወጡ ሚላኖ አረፉ፤ በመቀጠልም ቡዳ ፔስት፤ ኦስትሪያ እየተዘዋሩ ሰርተዋል::
እኚህ ሰው በጉርምስና እድሜያቸው ከሃገራቸው ከወጡ በኋላ ጃንሆይም ሆነ መንግስቱ ሃይለማርያም አግኝቷቸዋል:: ጃንሆይ በሚሰሩበት የባሬስታነት ስራ ሃገራቸው ሆነው መስራት እንደሚችሉ ነግረዋቸው ሊወስዷቸው ቢጠይቋቸው አሻፈረኝ ብለዋል:: እንዳውም ‹‹አይነፋም›› ብለው ሲመልሱላቸው ንጉሱ ክፉኛ ደንግጠው ነበር:: በነገራችን ላይ አሁን የአራዳ ቋንቋ ብዙ ሰው የሚመስለው ይህ ቃል በጎንደር የተለመደና አይሆንም እንደማለት ነው:: ያን ጊዜ በነጋዴው ስደተኛ ምላሽ ንጉሱ መደናገጣቸውን ያዩት የአትሌቲክስ አሰልጣኙ ወልደመስቀል ኮስትሬ ትርጉሙን ነግረው ነው ያረጓጓቸው:: መንግስቱን በተመሳሳይ ሁኔታ ‹‹አይነፋም›› ብለውታል:: እናም የእኚህን ሰው የህይወት ታሪክ በመፃፍ ለህትመት አብቅቻለሁ::
አዲስ ዘመን፡- አንድ ኮሌጅ ሄደው ካጋጠሞት ነገር ተነስተው ስለፃፉት መፅሓፍ ደግሞ እስቲ በጥቂቱ ያብራሩልኝ?
ዶክተር ጌታቸው፡- አንድ ወቅት ላይ አንድ ኮሌጅ ሄጄ ስለጀግንነታችን ሳወራ የእኛ ወታደሮች እንኳን እዚህ ኮርያ ሄደው ጀግንነታቸውን ያሳዩ መሆናቸውን ገለፅኩኝ:: ይህንን ጊዜ አንድ ተማሪ ተነሳና ‹‹እኛ ከኮሪያ ጋር በድንበር ሆነ በክልልም ሳንዋሰን ለምንድነው እዛ ሄደን የተዋጋነው?›› የሚል ጥያቄ በጩኸት አቀረበልኝ:: ይህም ትውልዱ ስለሃገሩ ታሪክ እንደማያውቅ እንድገነዘብ አደረገኝ:: ከዚህ በመነሳት የዘመቱ ጀግኖችን በማነጋገር ሰፊ ጥናት አካሄድኩኝ:: ፎቶግራፋቸውን አግኝቼም በማያያዝ በኮርያ የተፈፀመውን ጀግንነት የሚያሳይ በጣም ቆንጆ መፅሓፍ አዘጋጀሁኝ:: የሚገርመው ግን ኮርያ ድረስ ሄጄ ነገሩን ከስር መሰረቱ ለማጥናት ስሞክር ኮርያኖቹ የኢትዮጵያንና የጀግኖቿን ውለታ በሚዘክር ሁኔታ ቹንቻን በሚባል መንደር ማዕከል ከፍተው ለትውልድ እንዲተላለፍ ማድረጋቸውን አይቻለሁ:: በእውነቱ በዚህ በጣም ሊመሰገኑ ነው የሚገባቸው::
በተመሳሳይ አንድ ትምህርት ቤት ሄጄ ስለታሪክ እያስረዳሁ ስላ ስለጃኑሄ ተነሳና ተማሪዎቹ ያውቋቸው እንደሆነ ጠየኳቸው:: አንዱ ተነሳና ‹‹አዎ አውቀዋቸዋለሁ፤ ከሰው ይልቅ ለውሻ ምግብ የሚመግቡ ንጉስ ነበሩ›› ሲል መልስ ሰጠኝ:: በሰማሁት ነገር በጣም ነው የተደናገጥኩት:: ሌሎቹም ከወሬ በስተቀር ስለንጉሱ ታሪክ እንደማያውቁ ነገሩኝ:: ስለሆነም በ11ሺ 800 የንጉሱ ፎቶዎች በእጄ ላይ ስለነበረኝ ከእነዚህ ውስጥም 306 ቆንጆ ፎቶግራፎችን መርጬ ለንጉሱ ቤተሰቦች አሳየኋቸው:: የገንዘብ ድጋፍ አድርገውልኝ ታሪካቸውን በምስል ያስደገፈ መፅሃፍ አዘጋጅቼ በቅርቡ ለማስመረቅ እየተሯሯጥኩኝ ነው:: ከዚህ በተጨማሪ ሁለት መፅሓፍቶችን አዘጋጅቻለሁ:: በድምሩ 16 መፅሓፍት ናቸው ያዘጋጀሁት::
አዲስ ዘመን፡- ብዙ ጊዜ ስለወላጅ አባትዎት ሲናገሩ ይደመጣሉ፤ እስቲ እርሶ አሁን ላሉበት ሁኔታ የአባትዎት አስተዋፅኦ ምን እንደነበር ያስታውሱኝ?
ዶክተር ጌታቸው፡- እንደሚታወቀው አባቴ በኢትዮጵያ ዘመናዊ እርሻ ፋና ወጊ የሆኑ ሰው ናቸው:: በንጉሱ ዘመን በትራክተርና ኮምባይነር እንዴት ማረስ እንደሚቻል ያስተዋወቁ ሰው ከመሆናቸውም ባሻገር ከሁለት ሺ ሰዎች በላይ በስራቸው ቀጥረው ያሰሩ ነበር:: የሚገርምሽ አባቴ ምንም እንኳን እስከ አራተኛ ክፍል ብቻ ቢማሩም አዳዲስ ነገሮችን የማሰብና የመቀበል ችሎታቸው ከፍተኛ ነበር:: ከዚህ በተጨማሪም ፈረንሳይኛና ጣሊያንኛ አቀላጥፈው የሚናገሩ ሰው ነበሩ:: ባይማሩም ግን የተማሩ ሰዎች በእሳቸው የግብርና እውቀት በጣም ነበር የሚገረሙት:: ከእርሻው ባሻገር ለአካባቢው ማህበረሰብ ትምህርት ቤት ፤ ክሊኒክ ከፍተዋል:: ንጉሱ እርሻቸውን በጎበኙበት ወቅት አባቴ ያስገነቡት ትምህርት ቤት በአባቴ ስም እንዲሰየም ቢነግሯቸውም እሳቸው ግን የራሳቸውን ስም ማጎላት ስላልፈለጉ በአካባቢው ስም ደነባ ትምህርት ቤት አሉት:: ያ ትምህርት ቤት አሁን ላይ በርካታ ዶክተሮችና ኢንጅነሮችን ማፍራት የቻለ የትምህርት ተቋም ሆኗል:: ብዙዎቹም እረኛ ሆነው ከመቅረት ታድገው ህይወታቸውን የለወጡላቸው መሆኑን ይመሰክሩላቸዋል::
ይሁንና ያ ሁሉ እርሻ፤ ያ በርካታ የአለም ባለሙያዎች የጎበኙት ሥፍራ፤ ለብዙዎች የሥራ እድል የፈጠረ ሃብት በአንድ አዋጅ ብቻ አመድ ሲሆን ማየት በጣም ነው የሚሳዝነው:: ደግሞም ከሁሉ በላይ የሚያሳዝነው ቦታውን ሆነ ቤቱን ይውሰዱ ግን ሲሆን እንዳለ ተረክቦ ማስቀጠል፤ ከተቻለም ማሻሻል ሲገባ ሙሉ ለሙሉ እንዲጠፋ መደረጉ በእጅጉ ልብ የሚሰብር ጉዳይ ነው:: በወቅቱ ከአባቴ ተቀምቶ ለእያንዳንዱ ሰው 10 ሄክታር ከተሰጠ በኋላ ሱማሌ ስትወረን ያ ሁሉ መሬት የተሰጠው ሰው ጦርሜዳ ሄዶ አንድም በህይወት የተመለሰ ሰው የለም:: አጥፍቶ መጥፋት ይሉሻል ይሄ ነው:: በአጠቃላይ ግን በዚህ ጉዳይ ላይ ማውራት አልፈልግም::
አዲስ ዘመን፡- አባቶት ባይማሩም ዘመናዊ ግብርና ባስጀመሩበት መንገድ ቢቀጥል ኖሮ የኢትዮጵያ ግብርና የት ይደርሳል ብለው ይገምታሉ?
ዶክተር ጌታቸው፡- በጣም ቆንጆ ጥያቄ ነው! አንደኛ እንደዚያ ሆኖ ቢቀጥል ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ ዋስትና ጥያቄ አይነሳም ነበር:: ሌላው ቀርቶ ከአባቴም በተጨማሪ ከአለማያ ኮሌጅ የተማሩ ባለሙያዎች እርሻ ስራ ውስጥ ገብተው ነበር:: ቦሎቄና ጥጥ ሳይቀር በስፋት ይመረት ነበር:: ወደ ውጭ መላክም ተጀምሮ ነበር:: አንድ ጊዜ አባቴ ውስኪ ከፈቱና ምነው ብለን ብንጠይቃቸው 26 ብር ይሸጥ የነበረውን አንድ ኩንታል ስንዴ 28 ብር በመሸጣቸው ተደስተው እንደሆነ ነገሩን:: የሚገርምሽ ነጋዴዎቹ እዚያው ድረስ እየመጡ ነበር የሚረከቧቸው:: ሥራም ሆነ መሬት እንደልብ ነበር:: ደርግ የኢትዮጵያን መሬት ሲወርስ 20 በመቶ የሚሆነው መሬት ይታረስ ነበር:: 80 በመቶው ገና አልተነካም ነበር:: ቀሪውን ለሚፈልገው መስጠትና ማሳረስ ሲችል አልሚዎችን ማጥፋት ነበር የተያያዘው:: ያንን ሁሉ መሬት አባቴ በጀመሩት መንገድ ቢታረስ ኖሮ በኢትዮጵያ የምግብ እጥረት አይነሳም ነበር:: ሁለተኛ ህዝቡ በደንብ ጠግቦ ያድር ነበር::
ይህንን ስልሽ ፊውዳል ስርዓት አልነበረም እያልኩሽ አይደለም፤ ግን ደርግ እውቀት ስላልነበረው የሚያርሱና ለብዙዎች የሥራ እድል የፈጠሩ እንዳአባቴ ያሉ አምራቾችን አጠፋ:: በነገራችን ላይ በአባቴ መሬት ላይ የሚያርሱ ሰዎች ራሳቸው አርሶአደሮች ነበሩ፤ ስለሆነም ያ መሬት የተነጠቀው ከፊውዳሉ ሳይሆን ከአራሶአደሩ ጭምር እንደነበር ያሳይሻል:: በእኔ እምነት መውረስ የነበረበት አዲስ አበባ፣ አዳማና ቢሾፍቱ ቁጭ ብሎ እያሰረሰ በየዓመቱ የሚሰበስበውን ፊውዳል ነበር:: ከአራሹ ላይ እንዴት መሬት ይወሰዳል?:: በእርግጥ መጀመሪያ ላይ እኔ ‹‹መሬት ላራሹ›› ሲባል የአባቴ መሬት አይነካም፤ እንዳውም ሌላ መሬት ይሰጣቸዋል የሚል እምነት ነበረኝ:: ምክንያቱም አባቴ አርሶአደር እንጂ ፊውዳል አልነበሩምና ነው:: በኋላ ላይ ግን መሬት ላራሹ ሳይሆን መሬት ለመንግስት ነው የሆነው:: እንዳልሽው ግን በተጀመረው ሁኔታ ከቀጠለ ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደምታድግ የውጭ ፃሃፍት ሳይቀሩ ፅፈውበት ነበር:: በወቅቱ ከኢንዱስትሪ እቃዎች በስተቀር እህልና ምግብ ከውጭ አናስገባም ነበር:: ከዚያ በኋላ ያ ሁሉ ልማት ጠፋና ልመና ውስጥ ተገባ:: አሁን ደግሞ ፈጣሪ ይመስገንና ገበሬው ነቅቷል እየሰራ ነው ያለው:: ግን ከሁሉ በላይ ሰላም ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡- ግን እኮ ደርግ ከሰራቸው ጥሩ ነገሮች በዋናነት የሚጠቀሰው መሬት ለአራሹ መስጠቱ ነው፤ እርሶ ይህንን አይደግፉትም ማለት ነው? አሁን ካለው የመሬት አዋጅ ጋር እያነፃፀሩም ይንገሩኝ?
ዶክተር ጌታቸው፡- በርግጥ ‹‹ደርግ መሬት ላራሹ›› ብሎ ማወጁ የሚደገፍ ነው:: ሆኖም የዚህ ሃሳብ አመንጪ ደርግ ሳይሆን ለለውጥ የጮሁ ተማሪዎች ያመጡት ነው:: ግን መሬት ላራሹ ሲባል ለገበሬው ማለት ነው:: እንዳልሽው በዚህ አዋጅ በርካታ ገበሬዎች ተጠቃሚ ሆነውበታል:: እኔም ብሆን ለደርግ እውቅና የምሰጠውም ፊውዳላዊ ስርዓትን ማጥፋቱ ነው:: ፊውዳሎቹ ከተማ ቁጭ ብሎ በጭሰኛ ማሳረስ ብቻቸውን ነበር የሚጠቀሙት:: በወቅቱ ብዙዎቻችን አንድና ሁለት ሄክታር መሬት ያለው አርሶ አደር በማህበር ተደራጅቶ ትራክተርና ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያ አግኝቶ እንዲጠቀም፣ የእህል ማስቀመጫ መጋዘን በማህበር እንዲኖረው፣ ማህበር አቋቁመው ቀጥታ ለገበያ እንዲያቀርቡ እንወተውት ነበር:: ሃሳቡም ተቀባይነት አግኝቶ ስራዎች ተጀምረውም ነበር:: ይሄ ሥራ በጅምር ላይ እያለ ወያኔ መጣና ጠቅላላ መሬት የመንግስት ነው ተባለ:: አሁንም ድረስ አርሶአደሩ የሚያርሰው መሬት ባለቤት አልሆነም፤ መሬቱንም አስይዞ ከባንክ መበደር አይችልም::
ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ ታሪክ ልንገርሽ:: አንድ የሃብታም ልጅ ሰራተኞች ያፀዱለታል፤ ልጁ ግን ተመልሶ ጭቃ ውስጥ ገብቶ ቦክቶ ይመጣል:: አንድ ቀን ግን አባትየው አየውና ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ጭቃ ውስጥ ከገባ ራስህ አፅዳ›› ብሎ አዘዘው:: ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያ ልጅ ሃላፊነቱ የራሱ መሆኑን ስለተረዳ ንፁህ ሆኖ ቤቱ ይመለስ ጀመር:: ያንን ያያ አባትም ለምን ጭቃ ውስጥ እንዳልገባ ቢጠይቀው ‹‹እንዴ አባባ እኔ ነኝ እኮ የማፀዳው›› ብሎ መለሰለት:: የመሬት ባለቤት ጉዳይም እንዲሁ ነው:: መሬት የግል ሆኖ ለወለድሽው ልጅ ካልሰጠሸና ‹‹መሬቱ የእኔ ነው›› እስካላልሽ ድረስ ምርትና ምርታማነት ብዙ ይቀንሳል:: ነገ ይወሰድ አይወሰድ አታውቂም፣ ዋስትና ስለማይኖርሽ ብዙ አቅደሽ አትሰሪም:: የእኔ የሚለው የትም አለም ውስጥ ትልቅ ነገር ነው:: ጫማዬንም ለማፅዳት የእኔ ነው ማለት አለብኝ:: ያን ጊዜ እኮራለሁ::
በነገራችን ላይ እንደ ኢትዮጵያ ያለ ህግ የትም የለም፤ የወያኔ መንግስት የመሬት ባለቤትነትን ከህዝብ ሲቀማ ምርታማነቱ የዚያኑ ያህል እንደሚቀንስ አላሰበውም ነበር:: እነ ኬንያ፣ ታንዛኒያ ምርታማ ሲሆኑ ለምን ብሎ ቢጠይቅ ሚስጥሩ ይህ መሆኑ በተገነዘበው ነበር:: ስለዚህ አሁንም ቢሆን ገበሬው እንደልቡ እንዲያለማ ከተፈለገ መሬቱ የእርሱ መሆን አለበት:: በኢትዮጵያ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የመሬት ባለቤትነት ጉዳይ እልባት ሊያገኝ ይገባዋል:: መንግስት መሬት ላራሹ ተብሎ የተከፈለውን የዚያን ሁሉ ወጣት ህይወት ከግምት ውስጥ ማስገባት ይጠበቅበታል:: በመሆኑም አሁን በመሬት ላይ ያለው ፖሊሲ መሻሻልና በዋናነትም መሬት የገበሬው መሆን አለበት:: ያንን ማድረግ ሲቻልም ነው ምርታማ የሆነ አርሶአደር መፍጠር የምንችለው::
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ ከኢትዮጵያዊነትና ከሃገር ፍቅር ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍቶች ላይ ያሎትን አመለካከት ይንገሩንና ውይይታችንን እናብቃ?
ዶክተር ጌታቸው፡- እኔ በአሁኑ ጊዜ የተወለዱ ወጣቶች የታደሉ አይደሉም ባይ ነኝ:: ምክንያትም እንደኛ ከልጅነታቸው ጀምሮ ስለሃገር ፍቅርና ኢትዮጵያዊነት አስተምሮ ያሳደጋቸው ባለመኖሩ ነው:: ከሁሉም ህዝብ ጋር እንዴት ተቻችሎ መኖር እንዳለበት ተነግሮት አላደገም:: አልተዳለም የምለው፤ የኢትዮጵያዊነት ስሜቱን ከትውልዱ በመቀማቱ ምክንያት ነው:: አንድ ቀን የስምት ዓመት ልጄ ኳስ እየተጫወተ ሳለ ሮጦ መጣና ‹‹ብሔሬ ምንድን ነው›› ብሎ ጠየቀኝ፤ ኢትዮጵያ ብዬ ነገርኩት:: ተመልሶ ሲሄድም ከኢትዮጵያዊነት ሌላ ብሔር የሚባል ነገር እንዳለ ነገሩትና መጣ:: አሁንም ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት በስተቀር ብሔር የሚባል ነገር እንደሌለ አስረድቼ ዳግመኛ ቢመለስም አማራ ወይም ኦሮሞ የሚል ብሔር ስያሜ ይዞ ካልመጣ ኳሱ ቡድን ውስጥ አናስገባም ብለው መለሱት:: እንግዲህ የስምንት ዓመት ህፃናት አንደበት ይህ ሊነገር የቻለው ቤተሰቦቻው ቀርፀው ያሳደጓቸው በዚህ መልኩ መሆኑን ነው የሚሳየው::
ድሮ የትም ክልል ብንሄድ ጠያቂና ከልካይ አልነበረም፤ ምክንያቱም ሁሉም ቦታ ሀገራችን ነው ተብሎ ይታሰብ ስለነበረ ነው:: አሁን ግን ያ ሁሉ ተቀይሯል ፤ ማንም ሰው እንደፈለገ ከክልል ክልል መንቀሳቀስ አይችልም:: ሌላው ይቅርና ሲዊዲን በሰው ሃገር ስራ ተሰጥቶኝ በነፃነት ስኖር ቆይቼ እዚህ ስመጣ ግን ያ ሁሉ ተቀይሮ ነው የጠበቀኝ::
ስለዚህ በእኔ እምነት ጎሳ ላይ መሰረት ያደረገው ስርዓት መቀየር አለበት:: በመሰረቱ ክልላዊ አደረጃጀቱ በራሱ በአንድ ሃገር ውስጥ መፈጠር የሌለበት ነው:: አማራ እንዴት ከኦሮሞ ክልል ይኖረዋል?:: ክፍለ ሀገር እንጂ ክልል የሚባል ነገር በአንድ ሃገር ውስጥ ሊኖር አይገባም:: ይሄ ወያኔ እንድንለያይ ያደረገው ሴራ ነው:: አንድን ሃገር በክልል ከከፈልሽው በኋላ እኔና አንቺ መነጋገር አንችልም:: ከ17 ዓመት የትዳር ዘመን ቆይታ በኋላ ነው ባለቤቴን ከየትኛው ጎሳ እንደመጣች የጠየኳት:: ምክንያቱም ለእኔ ሰው መሆንዋ እንጂ ጎሳዋ ወይም የዘር ምንጯ ጉዳዬ ስላልሆነ ነው:: ልጆቼም ሆኑ ጋደኞቼ ፈረንጅ ነው ያገቡት፤ ከየት ጎሳ እንደመጡ ልጠይቃቸው ነው:: ኦሮሞ ጓደኞች አሉኝ፤ ጉራጌ ጓደኞች አሉኝ ለእኛ ጓደኝነታችን እንጂ የምናስቀድመው ጎሳችንን አይደለም:: እኔ ወደ ሀገሬ ከተመለስኩ በኋላ እስካሁን ሊዋጥልኝና ልቀበለው ያልቻልኩት ነገር ነው::
በመሆኑም አሁን ላይ ይህ ከፋፋይ አስተሳሰብ ያመጣብንን ጣጣ ስላየን እንደቀድሞ አንድ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊነት የሚል አስተሳሰብ መመለስ አለብን:: ከዚህ ሌላ ምርጫ የለንም:: ሁሉም ሰው በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ መኖር አለበት:: አሁን ያለው ትውልድ ከስህተቱ መመለስ አለበት:: መንግስት ይህ ሃገራዊ ስሜት እንዲመጣ ከልቡ መታገል አለበት:: ግብረ-ገብ ትምህርት በየትምህርት ቤቱ በቋሚነት ሊሰጥ ይገባል:: በተጨማሪ መንግስት በተለወጠ ቁጥር ባንዲራ የሚለወጥበት ነገር ላለመግባባታችን አንዱ ምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ:: ሌላው አገር እንዲህ አይነት ነገር የለም:: ለምሳሌ አሜሪካ እንኳን 300 ሌሎቹም ከ400 እስከ 900 ዓመታት ባንዲራቸውን አስቀጥለው ነው የዘለቁት:: ሌሎች ነገሮች ይለዋወጣሉ፣ ፓርቲ ይለዋወጣል፣ አገር ይለዋወጣል፣ መሪዎች ይለዋወጣሉ፣ ይሞታሉ፣ ባንዲራ ግን ይቀጥላል:: እኛ ጋር ግን ሰው በተለዋወጠ ቁጥር ባንዲራ ስንቀይር ነው የኖርነው:: ይህ ክፉ ልምድ መሻሻል አለበት ብዬ ነው የማምነው:: ከሁሉ በላይ አባቶቻችን በጦር ሜዳ ታግለው ነጮችን ያንበረከኩበት አረንጓዴ፤ ቢጫ ና ቀይ ባንዲራችንን ቢቀጥል ብዙዎቻችንን የሚያስማማ ይመስለኛል::
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ::
ዶክተር ጌታቸው፡- እኔም አመሰግናለሁ
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ሰኔ 4 /2014