እጩ ዶክተር ፍሬዘር እጅጉ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጆርናሊዝም ኤንድ ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ። ከእጩ ዶክተር ፍሬዘር አንድ ሀገር መገናኛ ብዙሃኖቿን እንዴት ትጠቀም፤ የማህበራዊ ሚዲያዎች በአንዲት ሀገር ላይ ያላቸው ተፅዕኖ የሚለውንና ሌሎች ጉዳዮችን አንስተናል፤ መልካም ቆይታ።
አዲስ ዘመን፡- መገናኛ ብዙኃሃን ለአንድ ሀገር ያለውን ጠቀሜታ እንዴት ይገልጹታል?
እጩ ዶክተር ፍሬዘር፡- መገናኛ ብዙሃን ለአንድ ሀገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ይሰጣሉ። መገናኛ ብዙሃን ለአንዲት ሀገር ዜጎች መረጃዎችን በመስጠት፤ ለመዝናናት፤ የእለት ከእለት የህይወት ውጣ ውረድን ለማምለጫነት ይጠቀሙበታል። ከዚህ ባለፈ ከማህበራዊና ባህላዊ እሴቶች አንፃር መገናኛ ብዙሃን ኢ መደበኛ ትምህርት ቤቶች በመሆን ያገለግላሉ። የአንድን ሀገር እሴቶችን ባህሎችን አስጠብቆ ለማቆየትም የመገናኛ ብዙሃን ሚና የላቀ ነው።
መገናኛ ብዙሃን የሀገር ግንባታ የተሳካ ይሆን ዘንድ የሚያደረጉት አስተዋፅኦም ቀላል አይደለም። የሀገረ መንግሰትን፤ ሀገረ ብሄርን ለማፅናት የጋራ አመለካከቶችን ለመፍጠር ሀገራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ ግልጋሎቱ ከፍተኛ ነው። በተለይም የአፍሪካ ሀገራት ነፃ በወጡ ጊዜ መገናኛ ብዙሃን ከፍተኛ ሀላፊነትን ወስደው ሀገር ግንባታ ላይ ሲሰሩ እንደነበር ይታወቃል። ስለዚህም መገናኛ ብዙሃን ሀገር በመገንባት ተግባር ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው ማለት ነው።
ከቴክኖሎጂና ልማት አንፃር ሲታይም በአንድ ሀገር ላይ የተለያዩ አዲስ ቴክኖሎጂዎቸ ሲመጡ እነዛን ቴክኖሎጂዎችና አዳዲስ ሀሳቦች ህዝቡ ዘንድ እንዲደርስ ለማድረግ ከቴክኖሎጂው ጋር እንዲግባባና በአጠቃላይ በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ልማት ለማምጣት መገናኛ ብዙሃን ታላቅ ሚና አላቸው። በአንድ ሀገር ህዝብ ውስጥም የጋራ ትውስታንና አስተሳሰብ በመፍጠር ሂደት ሚዲያ ሀይል አለው።
በችግርና በቀውስ ጊዜ ዜጎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ስለ ጉዳዩ አውቀው እንዲጠነቀቁ ለማድረግም ይጠቀማል። ይህ ሲባል በኮቪድ 19 ወቅት ቶሎ ቶሎ መረጃዎች ለህዝቡ ሲደርስ እንደነበረው አይነት ማለት ነው። በአንድ ሀገር አደጋ ሲከሰት፤ የተለያዩ ቀውሶች ሲፈጠሩ ተገቢውን መረጃ በማድረስ ለማህበረሰቡ ግልጋሎትን ይሰጣሉ።
አዲስ ዘመን፡- የመገናኛ ብዙሃን ሚና በተለይም ሀገር በተለያዩ ቀውሶች ውስጥ ስትሆን ምን መምሰል አለበት?
እጩ ዶክተር ፍሬዘር፡- መገናኛ ብዙሃን በመደበኛውም ጊዜ ቢሆን መሰረታዊ የጋዜጠኝነት መርሆችን፤ የሙያ ስነ ምግባርን ተከትለው ስራቸውን መስራት ይጠበቅባቸዋል። በቀውስ ወቅትም የተለያዩ ሀላፊነቶችን ይወጣሉ። ዜጎች በሀገራቸው ውስጥ ስላለው ቀውስ እንዲረዱ ቶሎ ቶሎ መረጃዎች ያደርሳሉ። ከዚህም በተጨማሪ ለሁሉም አካላት እኩል መድረክ የመሆን ሀላፊነት አለባቸው።
በቀውስ ወቅት ሲሆን መገናኛ ብዙሃኖች ተግዳሮቶች ውስጥ ይወድቃሉ። ቀውስ በራሱ በጥንቃቄ መዘገብ ያለበት ጉዳይ በመሆኑ ከፍተኛ የሆነ የሙያዊ ስነ ምግባርን ተከትለው መስራት ይጠበቅባቸዋል። በቀውስ ጊዜ ግጭቶችና ጉዳቶች ይኖራሉ። በጋዜጠኝነት ውስጥ አሉ ከሚባሉ አራቱ መሰረታዊ መርሆች አንዱ ጉዳትን መቀነሰ ነው። ይህንን የስነ ምግባር መርህ በመከተል ማንኛውንም አይነት ዘገባ በሚዘግቡበት ጊዜ ግጭቱ ካደረሰው ጉዳት በተጨማሪ አካላዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ጉዳት እንዳይፈጠር የሚሰሩትን ሰራ በጥንቃቄ መስራት ተገቢ ነው። ጉዳቶችን ላለማባባስ ጥረት ማድረግ የሙያ ስነ ምግባሩ ከሚጠይቃቸው ጉዳዮች አንዱ ነው።
ሌላኛው የስነ ምግባር መርህ ገለልተኛ ሆነው ስራዎችን መከወን፤ ይህም ገለልተኛ በመሆን ግጭቶች የሚቀንሱበት ዜጎች ወደ ሰላም የሚመጡበትን መንገድ መፈለግ ነው። ጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ታማኝነቱ ለህዝብ መሆን ይኖርበታል። ሁሌም ማንኛውም አይነት የመገናኛ ብዙሃን ስራዎችን ለዜጎች በሚጠቀም መልኩ በመቃኘት መሰራት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የማህበራዊ ሚዲያው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ መሆኑ ይታወቃል፤ ይህ ሚዲያ በሀገራችን የፖለቲካና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ያለውን አንድምታ እንዴት ይመለከቱታል?
እጩ ዶክተር ፍሬዘር፡- መገናኛ ብዙሃን በታሪካቸው ውስጥ በርካታ ሂደቶችን አልፈዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎም አሁን የዲጅታል ቴክኖሎጂ ዘመን ላይ ደረሰናል። ስለ ማህበራዊ ሚዲያ ሲወራ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል። አንደኛው መደበኛ መገናኛ ብዙሃን የምንለው እንደ ሬድዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ጋዜጣና መፅሄት የመሳሰሉት ሲሆን፣ ሌላው አማራጭ ሚዲያ ነው። ይህ አማራጭ ሚዲያ ደግሞ በሁለት ይከፈላል። ይህም ዲጂታል ሚዲያና ሶሻል ሚዲያ በመባል ይታወቃል። በዲጅታል ሚዲያ ድረ-ገጾችና ሌሎች ሲካተቱበት፤ ማህበራዊ ሚድያ የምንለው ደግሞ በሌላ አማራጭ መረጃዎችን በፍጠነትና በቀላሉ ለመድረስ እንዲያስችል ሆኗል።
በሀገራችን ያለው የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴን ከበጎው ጎን ስንነሳ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑበት ነው። የጤና መረጃን በፍጥነት እያደረሰ ከመሆኑም በላይ፤ ሀገራዊ አጀንዳዎችም በፍጥነት ማህበረሰቡ ዘንድ በመድረስ በጎ ተፅእኖ እየፈጠረ ይገኛል። በአብዛኛው ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ቢኖርም በርካታ ችግሮችም እየተከሰቱ ነው። በተለይ ሀሰተኛ መረጃዎችን በቀላሉ ማሰራጨት መቻሉ ጉዳዩን አደገኛ እንዲሆን ያደርጋል። ነገር ግን ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች በአመዛኙ በጎው ጎን ስለሚጎላ እሱ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል። በቅርቡ በተደረገ አንድ ጥናት በመደበኛው መገናኛ ብዙሃን የሌሉ የፕሮግራም ይዘቶችን፤ ወይም አሰራሮችን ማህበረሰቡ ከማህበራዊ ሚድያ ስለሚያገኝ ወደዛ እያዘነበለ እንደሚገኝ ያመላክታል።
የማህበራዊ ሚዲያ መምጣትም በርካታ ነገሮችን ለውጧል። በፊት ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ለመግባት የግድ የሙያው ወረቀት ሊኖር ያስፈለጋል፤ በተጨማሪ ዋና ዋና መደበኛ ሚዲያዎች ላይ ይሰራል። አሁን ግን ማንኛውም ሰው ያገኘውን መረጃ ማሰራጨት እንዲችል እድል ፈጥሯል። ይህ የማህበራዊ መገናኛ ተፈጥሯዊ ባህሪ
ያመጣው ነው። ይህ ደግሞ የተሳሳቱ መረጃዎች እንዲሄዱ ከማድረግም ባሻገር ዜጎች የራሳቸውን አመለካከት ብቻ መርጠው የሚያዳምጡበት ከእነርሱ አመለካከትና እሳቤ ውጪ ያለውን የማያዩበት የማያዳምጡበት ነገር ፈጥሯል። ይህም ሌሎች አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን አይቶ ከመቀበል ይልቅ የራስን ሀሳብ ብቻ የሚያጠናክር መሆኑ አንድ ችግር ነው።
ሌላው ተመልካች/አድማጭ (ኦዴንስ) መበጣጠስን ፈጠሯል። ይህ ሲባል የተወሰኑ የተወሰኑ ቡድኖች በመሆን የተከፋፈሉ ተመልካች/አድማጭ መብዛታቸው አንድ አይነት አመለካከት የጋራ ራእይ ህዝቡ ውስጥ እንዳይፈጠር አድርጎታል፤ በዚህም በርካታ ተቃርኖዎች እንዲበዙበት ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- የማህበራዊ ሚዲያዎቹ መብዛት ለሀገራችን እድል ነው ወይስ እርግማን ?
እጩ ዶክተር ፍሬዘር፡- እያንዳንዱ ቴክኖሎጂ ሁለቱንም ነገር ይዘው ይመጣሉ። የማህበራዊ ሚዲያም ለዜጎች መረጃዎችን የሚያቀርብ ብዙ ዜጎች በቀላሉ መድረስ የሚችል በመሆኑ ጥሩ እድል ልንለው እንችላለን፤ ግን በሀገራችን ባለው ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ውስጥ ደግሞ ስጋት ሊሆን ይችላል። ሀሰተኛ መረጃዎች፤ ፅንፍ የወጡ አስተሳሰቦች የሚሰራጩበት በመሆኑ የተለያዩ ስጋቶች ሊፈጥር ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ማህበራዊ ሚድያዎች ለምን በዚህ ልክ ፅንፍ ወጡ? ዜጎችስ ለምን በፍጥነት ሊቀበሏቸው ቻሉ?
እጩ ዶክተር ፍሬዘር፡- የሀገራችን መደበኛ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሌለ ማለትም የህዝብን አመለካከት ለመቃኘት የሚረዱ ፕሮግራሞች፤ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚገልፁበት መድረክ የላቸውም። ዜጎች ለምን ማህበራዊ ሚዲያን እንደሚመርጡ ሲጠየቁም አዳዲስና ወቅታዊ መረጃ እናገኝበታለን ብለዋል። ማህበራዊ ሚዲያዎች የተለያዩ ሀሳቦች የሚንፀባረቁበት መደረክ ነው፤ ነፃ የሆኑ ድምፆችን የምንሰማበት ነው ይላሉ። በዚህም መደበኛው ሚድያ ሀላፊነቱን በአግባቡ ያለመወጣቱን ልንመለከት እንችላለን።
አዲስ ዘመን፡- መገናኛ ብዙሃን የየራሳቸው ውግንና አላቸው፤ ለምሳሌ አልጀዚራ የአረቡን አለም መብት ሲያስጠብቅ፤ ቢቢሲ ለእንግሊዞቹ የሚሰራ ነው ማለት እንችላለን፤ የኛ ሀገር ሚዲያዎች ውግንናቸው ለማን ነው?
እጩ ዶክተር ፍሬዘር፡- ይህ ጥያቄ ከባድ ጥያቄ ነው፤ የሀገራችን መገናኛ በዙሃን ውግንናን ከማየታችን በፊት ማንኛውም ሀገር የራሱ ብሄራዊ ጥቅም እንዳለው እናስታውስ። በእርግጥ ብሄራዊ ጥቅም ምንድን ነው የሚል ግልፅ ትርጓሜ ባይኖርም በማንኛውም ሀገር የሚኖሩ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃን ብሄራዊ ጥቅማቸውን አሳልፈው ሊሰጡ አይገባም።
ማንኛውም የምዕራባውያን ሚዲያ፤ በተለያዩ ስርአቶች ውስጥ ያሉ የመገናኛ በዙሃን ጋዜጠኞች ብሄራዊ ጥቅማቸውን አሳልፈው አለመስጠታቸው ህዝብ ላይ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ መስራት ሙያዊ ግዴታቸው ስለሚሆን ነው። እነዚህ የውጭ ሚዲያዎች በሀገራቸው ውስጥ ያሉ ሁነኛ እሴቶችን አስጠብቀውም ማስቀጠል ዋና ተልዕኳቸው ነው።
እኛ ሀገር ያሉ መገናኛ ብዙሃን ለማን ነው መወገን ያለባቸው ሲባል ለህዝቡ ነው መሆን ያለበት። አሁን የኛ መገናኛ ብዙሃን ለማን ነው የሚወግኑት ተብሎ ሲታሰብ በቅድሚያ ማእቀፋቸው ምን ይመስላል ብሎ መመልከት ይገባል። አሁን ባለው ሁኔታ ምንም እንኳን የግሎቹ መገናኛ ብዙሃኖቸ ቢበዙም ባላቸው አስተዳደር ስርአተ፤ የገንዘብ አቅምና ሀይል ብዛትና ሌሎች መስፈርቶች የመንግስቶቹ ጠንካራ ማእቀፍ አላቸው። የግሎችም የንግድ የሚባሉትም አሉ። እንደ አጠቃላይ ግን መገናኛ ብዙሃኑ ፋይናንስ ለሚያደርጋቸው የሚወግኑ ይመስላል።
የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ብዙውን ጊዜ በትክክል የሚተረጎመው በሀገራዊ ለውጦች መካከል ነው። ወርቃማው የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ወቅት የሚባለው የንጉሱን መውደቅ ተከትሎ ታይቶ የነበረ በመቀጠልም በደርግና በኢህአዴግ ሽግግር ዘመን፤ ቀጥሎ ደግሞ በአሁኑ ለውጥ ታይተው የነበሩ ሁሉም አመለካከቶችን በመገናኛ ብዙሃን መመልከት ጀምረን ነበር። የሀሳብ ብዘሃነትን የሚያስተናግዱ ሚዲያዎችም በርክተው ነበር።
እንደ ሀገር የመገናኛ ብዙሃን በቁጥር መሻሻልም ቢኖርም ህዝብን ብቻ ያማከለ የህዝብ አይንና ጆሮ ብቻ ለመሆን ረጅም መንገድ ይጠይቃል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ግን የሀገሪቱ ሚደያዎች ወግንና ያው የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርጋቸው አካል ብንል ይቀላል።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የውጭ ጠላቶች ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት እያሳዩ እንደሆነ ይታወቃል፤ በዚህ ሂደት ደግሞ የውጭ ሚዲያዎች ጣልቃ ገብነት ከፍተኛ ነው፤ ለመሆኑ የእነዚህ ሚዲያዎች አፍራሽ እንቅስቃሴ ከምን የመነጨ ነው?
እጩ ዶክተር ፍሬዘር፡- በሀገራችን በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በርካታ ዘገባዎች ተሰርተዋል። በዘገባዎቻቸውም የምዕራባውያኑ መገናኛ ብዙሃን በተገቢው መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ የገጠመውን ችግር አልዘገቡትም ለማለት ይቻላል።
በጦርነት ጊዜ ያለ ዘገባ በተለያየ መንገድ ይዘገባል። በሀገራችን የተሰሩ የዘገባ አይነቶችን ስንመለከት ሌሎች ሀገሮችስ በምን መልኩ ነው በተለይ ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት ብሎ መመልከት ያስፈልጋል። ለምሳሌ በቬትናም በተደረገ ጦርነት ላይ የተሰሩ ዘገባዎች፤ በባህረ ሰላጤው ጦርነት የተደረጉና ሌሎች በግጭቶች ወቅት የተደረጉ ዘገባዎቸ ላይ የተሰሩ ጥናቶች ላይ የተገኘው ግኝት የየሀገሮቻቸው ልሂቃን በጦርነት ላይ ተመሳሳይ አቅም ያላቸው ከሆኑና የልሂቃኑ መከፋፈል ካለ መገናኛ ብዙሃኑ የዘገባ ሁኔታ የተለያየ ይሆናል።
በጦርነት የመጀመሪያ ወቅት አካባቢ በአንፃራዊነት ሚዛናዊነት ያለው ዘገባ ይዘግባሉ፤ ይህም የልሂቃን ስምምነት በማይኖርበት ወቅት ነው። የልሂቃኑ መግባበት በጉዳዩ ላይ ካለ ግን የሊሃቃኑ ሀሳብ በዘጋቢዎቹ ላይ ሲንፀባረቅ ይተያል። ወደ ሀገራችን ስንመጣ በለውጡ ማግስት የነበረ በጎ ዘገባ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ መቀየሩን እንመለከታለን። የምዕራባውያን ልሂቃን ስምምነት በመኖሩ የእነርሱን የልብ ትርታ ተከትለው ከመዘገብ ውጭ የተለየ ሚዛኑን የጠበቀ፤ የሁሉንም ወገኖች ጉዳይ የተመለከተ ስራ ሲሰሩ አልታየም።
ይህ የሆነው በተለያየ ምክንያት ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግስት የምዕራባውያን ሚዲያ በቅርበት አስጠግቶ መልካም ግንኙነት ይፈጥራል ወይ? ከእነዚህ የውጭ ሚዲያዎች ላይ የጋራ ጥቅም ላይ መግባባት ላይ አልደረሰም። በእነዚህ ሚዲያዎችም የሚሰራጩ ዘገባዎች ውሸት መሆናቸውን ሊያጋልጥ የሚችል ስራ መስራት፤ እራሳቸውን አስጠግቶ በተቻለ መጠን በተለየ መልኩ እንዲዘግቡ ማድረግም መፍትሄ ነው።
አሁን ላይ ምዕራባውያን ሚዲያ ያሉባቸውን ችግሮች ብቻ የሚያነሳ ሲሆን በመፍትሄ ደረጃ ያሉ ስራዎችን መስራት ግን መንግስት ይጠበቅበታል። ከአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ግንኙነት አንፃር መልካም ግንኙነት ቢኖር ያሉ ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በምዕራባውያን የሚዲያ አስተምህሮ ሚዲያ እውነት ብቻ መዘገብ አለበት ብለው ያስተምራሉ፤ በአንጻሩ የራሳቸው ሚዲያ ግን የውሸት ዘገባ ጭምር ይሰራል፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው?
እጩ ዶክተር ፍሬዘር፡- የጋዜጠኝነት ትምህርትና የጋዜጠኝነት የእለት ከእለት ትግባራ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ይሄን ነጥለን መመልከት ይገባናል። በአሜሪካ ውስጥ የጋዜጠኝነት ትምህርት ተስፋፍቶ ትግበራው ላይ የነበሩ በርካታ ችግሮችን ለመቆጣጠር ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ አካላት ትግበራውን የሚመራ ሰነድ ሊያዘጋጁ ችለዋል።
ለዜጎች ፍላጎት ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ የትርፍ እሽቅድድም ላይ ማተኮር አይነት ነገሮች በምእራባዊያኑ የጋዜጠኝነት ትግበራ ላይ ታይቶ ነበር። ይህን ማንሳት ያስፈለገው የጋዜጠኝነት ትግበራ በትምህርቱ ባለቤቶች ምዕራባውያንም ችግር ያለበት ሲሆን በእኛ ሀገርም የራሱ የሆኑ ፈተናዎች አያጣም ለማለት ነው።
የምዕራባውያንን አስተምህሮ ስናስብ ችግሩ ከትምህርቱ ሳይሆን ከትግበራው መሆኑን እንመለከታለን። ሚዲያዎች በፖለቲካና በኢኮኖሚ ተፅእኖ ስር ይወድቃል። እራሳቸውን ነፃ ማድረግ ስለሚከብዳቸው እንጂ ትምህርቱ የብዙ ጊዜ ልምድን ቀምሮ የተዘጋጀ በመሆኑ ችግር አለበት ባይባልም ትግበራው ላይ ትኩረት አድርጎ በሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልኩ ሊዘጋጅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በሀገራችን የመገናኛ ብዙሃን ግብ ምን መሆን አለበት? አደረጃጀቱስ ምን ቢመስል ተፅእኖ ፈጣሪ ሚዲያ ማግኘት እንችላለን?
እጩ ዶክተር ፍሬዘር፡- በሀገራችን መሰረታዊ መሻሻል ያለበት ለመገናኛ ብዙሃን የሚሰጠው ግብ ነው። ግቡ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ እንደ አንድ ተሳታፊ አድርጎ የመዘገብ ነው ወይስ ተመልካች ሆኖ የሚሰራውን ነገር አንደ መስታወት ሆኖ ለህዝብ ማቅረብ ነው። ሚናው መፈተሽ አለበት፤ ይሄ ሚና ካልታየና ካልተፈተሸ ሌሎች ላይ የምናመጣቸው ለውጦች በሙሉ እምብዛም የሆነ ውጤት አይኖረውም።
በሀገራችን የጋዜጠኝነት ሞዴል ምን መምሰለ አለበት የሚለውም በውይይትና በጥናት ዳብሮ እስከ ዛሬ የነበሩ በየዘመኑ የታዩ የጋዜጠኝነት ትግበራዎች ክፍተቶች ምን ይመሰላል የሚለውን ፈትሾ እንደ ሀገር የጋዜጠኝነት ሞዴልን ማዘጋጀት ለሀገርና ለፀና መንግሰት ስርአት ጠቃሚ ነው። ከዚህም ባሻገር የዜጎች የኑሮ ደረጃ እንዲያድግ፤ ሰዎች ንቃተ ህሊናቸው አድጎ በሀገራቸው ጉዳይ ወሳኝ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የሚያስችል ሊሆን ይገባል።
በአንድ ሀገር የሚኖር የሚዲያ ስርኣት በአራት መሰረታዊ ነገሮች ይወሰናል። አንደኛው ህግ ወይ መንግስት የሚዘረጋቸው ህጎች ማለትም የሚድያ አዋጅ፣ መረጃ የማግኘት ነፃነት አዋጅ፣ ሚዲያን የሚገዙት ህጎች አንድም ተፅእኖ ያሳድራሉ። ሁለተኛው የመገናኛ ብዙሃን የኢኮኖሚ አቅም መጠናከርና አለመጠናከር፤ የጋዜጠኝነት የሚዲያ ሲሰተሙ ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሙያተኝነት ማደግ እና የፖለቲካና የሚዲያ ግንኙነት ተፅእኖ ያሳድራል።
ሚዲያ ከአደረጃጀቱ አንስቶ መፈተሽ አለበት፤ ምክንያቱም ባለቤቱ አደረጃጀቱን ነው የሚመስለው። የመገናኛ ብዙሃን ባለቤትነት የመንግስትም የህዝብም ሲባል ይሰማል፤ የንግድ ብሎም ልዩ የህዝብና የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን የሚባል ነገር አለ። ሁሉ በየአደረጃጀታቸው ሁኔታ ተጠሪ የሆኑለት አካል አለ።
በፌደራል ደረጃ ያለው የመንግሰት መገናኛ ብዙሃን ተጠሪነቱ ለተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን፣ በክልል ደረጃ ያሉት መገናኛ በዙሃኖች ለክልል ምክር ቤት ተጠሪ እንዲሆኑ ህግ ወጥቷል። ሌላው ወሳኝ ነገር የቦርድ ሹመት ላይ ህጉ የተለያዩ አከላት እንዲስተናገዱ ይናገራል። እሱም መተግበር አለበት። መገናኛ ብዙሃን በአዋጅ ነው የሚቀቋሙት፤ ሲቋቋሙም ነፃ ሆነው መስራት እንዳለባቸው አዋጆች ላይ ተደንግጓል። የተለያዩ የመንግስት ሰልጣን ላይ ያሉ አባላት የቦርድ አባላት እንዳይሆኑ አድርጎታል።
ሌላው ህገ መንግስት አንድ መገናኛ ብዙሃን የተለያዩ ሀሳቦችን ማስተናገድ በሚችልበት አካሄድ መዋቀር አለበት ይላል። ያ ምን ያህል ስራ ላይ አንደሚውል ማወቅ አይቻልም። ከእያንዳንዳቸው ህጎች መገናኛ ብዘሃን የሀሳብ ብዝሃነትን ማንቀሳቀስ በሚችል መልኩ መቋቋም እንደሚገባቸው በወረቀት ደረጃ ተቀምጧል። በአስራር ደረጃ እውነት የተለያዩ ሀሳቦችን ለማንሸራሸር የተመቸ ነው የሚሆን ነው ለማለት አያስደፍርም። የሚዲያ ሀላፊዎችም በገዥው ፓርቲ ስለሚሾም ነፃ፣ ሁሉንም ሀሳብ የሚቀበል የሚዲያ ሀላፊም ማግኘት ይከብዳል።
አደስ ዘመን፡- ካለይ በርካታ ችግሮችን አንስተናል፤ መፍትሄዎቹስ ምንድን ናቸው ይላሉ?
እጩ ዶክተር ፍሬዘር፡- መፍትሄዎች የመንግስት መገናኛ ብዙሃንን ማጠናከር የማህበራዊ ሚዲያዎችን ተፅእኖ ለመቀነስ ዋንኛው ቁልፍ ተግባር ነው። መገናኛ ብዙሃን አድሏዊነታቸውን ለመቀነስ በአንድ ሀገር ያለ ሚዲያ ካለበት የፖለቲካ ተፅእኖ ወጥቶ የሁሉም ሀሳብ የሚስተናግድበት ጠንካራ ሚዲያ የሚሆንበት አካሄድ መፍጠር ያስፈልጋል።
ሁለተኛው መፍትሄ የሚድያ መሰረታዊ እውቀትን ማስፋፋት ያሰፈልጋል። ይህ ሲባል በማሀበራዊ ሚድያም ሆነ በሌሎች መገናኛ ብዙሃኖች የሚቀርቡ ሀሳቦችን ተከላክሎ ማስቀረት አይቻልም፤ ቴክኖሎጂውንም ማቆም አይቻልም። ዜጎች መረጃ የመፈለግ አቅማቸውን እውቀቶችን የመመርመር አቅማቸውን ማሳደግ ይገባል። መረጃ ደግሞ ሲያገኙ ቆም ብለው መረጃዎችን በትኩረት ማየት የሚችሉ መመርመር የሚችሉ እንዲሆኑ ማድረግ ችግሮችን ያቃልላሉ ብዬ አስባለሁ። መረጃዎቸን የመመዘን ከህሎትን ማዳበር ለበርካታ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ ነው እላለሁ።
ይሄንን ለማዳበር እንደ ሀገር የሚድያ ሀሁ (ሊትሬሲ) ከልጅነት ጀምሮ በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች መስጠት ያስፈልጋል። ለእያንዳነዱ ሰው የሚዲያ ከህሎትን ማሳደግ። አሁንም ማህበረሰቡን የሚያነቃ ስራ መስራት ይገባዋል። ያኔ ማንኛውም አይነት የሚዲያ ቴክኖሎጂ ቢመጣ በእውቀት የተቃኘ የሚያመዛዝን ህዝብ ስለሚኖር ከስጋት የፀዳ ማህበረሰብ ይኖረናል ማለት ነው።
አዲስ ዘመነ፡- ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
እጩ ዶክተር ፈሬዘር፡- እኔም አመስግናለሁ።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም