እንደምን አላችሁ ልጆች፣ ሰላም ናችሁ? ሳምንቱ እንዴት ነበር፣ ጥሩ ነበር አይደል? ወይስ ሥራ፣ ጥናትና ቤተሰብን ማገዝ በዝቶባችሁ ቆየ? መቼም ይህንን ተግባራችሁን እንደማትጠሉት አስባለሁ። ምክንያቱም እነዚህን ተግባራት መከወን ለጉልበታችሁ ብርታት፤ ለአዕምሯችሁ መጎልበትን ያላብሳልና። ስለሆነም ሁሉም ጥሩ ሥራ ስለሠራችሁ ቢበዛባችሁም አትበሳጩ፤ አትቆጩበትም።
ሥራ በጣም ጥሩ ነው። በተለይ ለጤናና ሰውነት መጎልበት ትልቅ ጥቅም ይሰጣል። ስለዚህም መሥራትን ልምዳችሁ ልታደርጉት ይገባል። በእርግጥ የእኛ ሥራ መሆን ያለበት ጥናት ብቻ ነው ልትሉ ትችላላችሁ። አንዳንድ ጊዜ ግን ቤተሰብን ማገዝ ሲጨመርበት መልካም ነው። በደንብ አጥንቶ፣ ከፍተኛ ውጤት አምጥቶ፣ 1ኛ መውጣት እንዳለ ሆኖ በሥራም ቤተሰብን ማስደሰት ያስፈልጋል። ብቻቸውን ለፍተው የእናንተን ጉሮሮ ከመድፈን ታድኗቸዋላችሁ። ስለሆነም በርትታችሁ አግዟቸው?
ልጆች ለዛሬው ጽሑፋችን መነሻ ያደረግነው ልክ እንደባለፈው ሳምንት በፈጠራ ሥራ አገሯን ለማገዝ፣ ሕዝብን ለማገልገልና ራሷንም ለማብቃት የምትጣጣረውን ልጅ ታሪክ ነው። እንግዳችን ለየት ያለ ተሰጥኦ አላት። አርክቴክት መሆን ትፈልጋለች። ለዚህ ደግሞ ሁልጊዜ ትተጋለች። በትምህርቷ በጣም ጎበዝ መሆኗ ደግሞ አግዟታል። ተማሪ በጸሎት በፍቃዱ ትባላለች። የዳግማዊ ምኒልክ አጸደ ሕጻናትና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ስትሆን፤ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ክበብ አባል ነች።
በጸሎት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፤ የንድፈ ሀሳብ ንድፎችን መሥራት የጀመረችው ገና የአንደኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነው። በጣም ጎበዝ ሰዓሊ ነች። በአካባቢዋ ያለውን ሁሉ በማየት በቀላሉ ማስፈር ትችላለች። ከዚያም አልፋ ችግር ነው የምትለውን የማህበረሰብ ጉዳይ በማንሳት የመፍትሄ ሀሳብ በንድፎቿ ለማሳየት ትጠራለች። ስለዚህም ለስዕል ያላት ፍቅር ለየት ያለ ነው።
ይገርማችኋል ልጆች የዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት የሳይንስ ክበብ አባላት የማይሰሩት የፈጠራ ሥራ የለም። ከቀለም ትምህርታቸው በተጨማሪ ለአገር ይጠቅማል የሚሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። በጸሎትም በሥዕል ሥራዋ ብዙዎች ያውቋታል። አጠቃላይ የሕንጻ ዲዛይን ሥራ ሳይቀራት የመሥራት ብቃት አላት። በተለይም በሳይንስ ክበብ ውስጥ ብዙ የሰራቻቸውና እውቅናን ያገኙ ሥራዎች አሏት። አንዱ የአዲስ አበባ ሕንጻ አሰራሮችን ይመለከታል። ለአካል ጉዳተኞች እንዴት ምቹ መሆን ይችላሉ በማለት ዲዛይኗን አስቀምጣ ለውድድር ጭምር ቀርቦላት እንደነበር ታስታውሳለች።
በጸሎት ከአካል ጉዳተኞች ጋር ተያይዞ የሰራችው ፈጠራ እንደሌሎቹ በዊልቸር የሚሄዱትን ብቻ ያቀፈ አይደለም። አይነ ስውራን የሆኑ በድምጽ፤ መስማት የተሳናቸው ደግሞ በምልክት ቋንቋ እንዴት መገልገል አለባቸው የሚለውንም ያካትታል። በየጥጋጥጉ (በኮሪደሮች) ይህ ነገር መኖር አለበትም የሚል ነው። በቃ ዘመናዊ የሚባለው ሕንጻ ዲዛይን ነው።
ረጅም ጊዜ ድረስ በአብዛኛው በሥዕል ወይም በንድፍ ደረጃ ሰርታ በተግባር ቢቀየር ውጤት ያመጣል ብላ የምታስበውን የፈጠራ ሥራ ነበር የምትሰራው። ነገር ግን ይህ ብቻ በቂ እንዳልሆነ በማመኗ ሌላውኛ የፈጠራ ሥራዋን ይፋ እንድታደርግ ሆናለች። ይህም ጫጩት ማስፈልፈያ (ኢንኩቤተር)ን ሠርቶ ማሳየት ሲሆን፤ ብዙ የለፋችበት እንደሆነ ታስታውሳለች። ይሁን እንጂ በንድፍ ያስቀመጠችውን በተግባር ለመተርጎም መቸገሯን ታነሳለች። ለዚህ ደግሞ ፈተና የሆነባት የግብዓት እጥረት እንደሆነም አጫውታናለች።
ቤተሰቦቿ የተማሩ በመሆናቸው በፈለገችው ነገር ሁሉ ያግዟታል። በተለይ ወንድሟ በጥበቡ ዙሪያ ብዙ ነገር ስለሚሰራ ብርታት ይሰጣታል። ነገሮችን አማክራው የተሻለ እንድታደርገው ያግዛታል። ይህ ደግሞ ሁልጊዜ አዲስ ነገር ለመፍጠርና አዲስ ሀሳብ ለማመንጨት እድል እንደሚሰጣትም ነግራናለች።
በፈጠራ ሥራ ውስጥ ተስፋ መቁረጥ በምንም መልኩ አያስፈልግም። ይህ አይነት ልምድ ካለን ያሰብነው ላይ ልንደርስ አንችልም። በዚያው ልክ ይህንን ከጨረስኩ በቃኝ መባል የለበትም። ምክንያቱም ፈጠራ ሁልጊዜ አዲስ ነው። እናም ልጆች የፈጠራ ባለቤት እንዲሆኑ ከፈለጉ ከዛሬ ነገ የተሻለ ሥራ ለመከወን መትጋት አለባቸውም ብላለች። ሁልጊዜ ‹‹እችላለሁና እኔ ጎበዝ ነኝ›› የሚለውን ሀሳብ ለራሳቸው መንገርና ውስጣቸው ላይ መቆየት እንዳለባቸው ትመክራለች።
ተማሪዎች ተሰጥኦዋቸውን በቀላሉ ለማወቅ የሚወዱትን ነገር መለየት አለባቸው። ከዚያ በትምህርት መጎበዝና ምርጫቸውን ሊያጎለብቱ የሚችሉ ትምህርቶችን በይበልጥ ማወቅና ማጥናት ይጠበቅባቸዋል። እኔ ፊዚክስና ሒሳብን በይበልጥ እወዳቸዋለሁ። ምክንያቴ ደግሞ ለዲዛይን ሥራ አስፈላጊ ናቸው። እናም ሌሎች ልጆችም አጥብቀው የሚወዱት ነገር ሊኖራቸው ይገባል። ከመደበኛ ትምህርቱ ባሻገር ለተሰጥኦዋቸው ማበልጸጊያ የሚሆናቸውን መረጃም አፈላላጊ መሆን ያስፈልጋቸዋል ስትል ምክሯን ትለግሳለች።
በሉ እንግዲህ ልጆች፣ የዛሬ ልዩ እንግዳዬን ተዋወቃችሁልኝ አይደል? ብዙ ተሞክሮ እንዳካፈለቻችሁም አምናለሁ። በሚቀጥለው ሌላ እንግዳ ይዘንላችሁ የምንቀርብ ሲሆን፤ በሌላ ፕሮግራም እስከምንገናኝ ድረስ መልካም ሳምንት።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2014