ሕወሓት በትግራይ ህዝብ ስም የተቋቋመ፣ ነገር ግን በስሙ እየነገደ ያለ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ በርካታ በደሎችና ግፎችን ሲፈጽም የኖረ ድርጅት ስለመሆኑ የትግራይ ህዝብ ራሱ ምስክር ነው። ይህ ቡድን ግማሽ ምዕተ አመት ለሚሆን ጊዜ አንዴ በነጻ አውጭ ስም፤ ሌላ ጊዜ በመንግስትነት ቆይታው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችን በጅምላ ጨፍጭፏል፤ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለስደት ዳርጓል፤ የትግራይንም ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ለመነጠል ብዙ ተግባራትን ፈጽሟል። በተለይ ቡድኑ የሃሳብ ነፃነትን በመግፈፍ እና ከራሱና ከራሱ ወዳጆች ውጭ ሌሎች ዜጎችን በማፈን ለብዙ ስቃይና መከራ ሲዳርግ ኖሯል።
ሆኖም ይህንን የአፈና ቡድን በመቃወም እስከ ትጥቅ ትግል ድረስ በመሄድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ አልጠፉም። በዚህ መልኩ ሕወሓትን ሲታገሉ ከኖሩና በመታገል ላይ ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ አንዱ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ትህዴን/ ነው።
እኛም በዛሬው የወቅታዊ አምድ ዝግጅታችን በሕወሓት ሃይሎች ለ13 አመታት ታስረው የነበሩና ከለውጡ በኋላ ከእስር የተለቀቁ፣ አሁንም ከትህዴን ጋር በመሆን ሕወሓትን በመፋለም ላይ ከሚገኙት አቶ ብርሃነ ተስፋይ ጋር በወቅታዊ የአገራችን ሁኔታና በተለይ ሕወሓት እየፈፀመ ስላለው ግፍና መከራ ዙሪያ ቃለምልልስ አድርገናል፤ መልካም ቆይታ።
አዲሰ ዘመን፤ እርስዎ ቀደም ባለው ጊዜ ሕወሓትን የተቃወሙበት ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ብርሃነ፤ ከላይ እንደተጠቀሰው ትህዴን የተመሰረተው በ1993 ዓ.ም ነው። ዋናው አላማው ደግሞ የትግራይ ህዝብ ከኢህአዴግ ዘመነ መንግስት ቀድሞ ደርግን ሲዋጋ በኢትዮጵያ ብሎም በትግራይ ሰላም እናመጣለን፤ በኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎች እኩል የሆነ ሰላምና ዲሞክራሲ እናመጣለን ብሎ ነበር የታገለው። ሆኖም ግን ደርግ ተሸንፎ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ጊዜ አንስቶ የሕወሓት አመራሮች አዲስ አበባን ከረገጡ በኋላ የትግራይ ህዝብን አደራ ወደጎን በመተው ራሳቸውን ወደ መጥቀምና ዘመዶቻቸውን ወደ ማደራጀት ነው የገቡት።
ለትግራይ ህዝብ የተገባለትን አደራ ወደጎን ትተው የራሳቸውን ጥቅም ወደ ማሳደድ ስለገቡ በኢትዮጵያ ብሎም በትግራይ ፍትህ እጦት፤ መከራ፤ እስራት፤ መፈናቀል፤ ረሃብ የተለያዩ ችግሮች መምጣት ጀመሩ። እነዚህን ችግሮች ቁጭ ብሎ መመልከት ስለከበደኝ በአፍላው የወጣትነት እድሜ በአስራ ሰባት አመት እድሜዬ ትህዴንን በመቀላቀል ለትግል ወደ በረሀ ወጥቻለሁ።
አዲስ ዘመን፤ ይህ ትህዴን የተባለው ድርጅት ምን ያህል አባላት ይዞ ይንቀሳቀሳል?
አቶ ብርሃነ፤ አንድ ትግል በስንት አባላት ነው የሚከወነው ተብሎ አይጠየቅም፤ ቅድሚያ መነሳት የሚገባው ጉዳይ የትግሉ አላማ ነው። ዋናው የምትታገይበት አላማ ምን ይመስላል? ህዝቡ ይከተለዋል ወይ? ያለው አመለካከት ምን ይመስላል? ነው እንጂ ቁጥሩ አይታሰብም። ትግል ደግሞ በቁጥር ሳይሆን በአላማ ፅናት ድል የሚነሳበት ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን፤ ለአስራ ሶስት አመታት እስር ቤት ነበርኩኝ ብለውኛልና እስር ላይ ከነበሩ ትግሉን በምን መልኩ ያካሂዱት ነበር?
አቶ ብርሃነ፤ ትግል ስትታገይ በእስርም፤ በበረሃም በሁሉም መልኩ ነው። አሁን ለምሳሌ እኔ እስር ላይ በነበረኩበት ወቅት ትግሌን አላቋረጠኩም ነበር። ይህም ማለት በእስር ቤት የሚወጡ ወጣቶችን በመመልመል ወደ ትህዴን ሄደው እንዲቀላቀሉ በማድረግ፤ በዛ አካባቢ ያሉ መረጃዎች ለድርጅቱ እንዲደርስ በማድረግ በእስር ቤት ሆኜ ትግሌን አላቋረጥኩም ነበር። ከወጣሁ በኋላ ደግሞ ከትህዴን ጋር ግንኙነቴ ስላልተቋረጠ ወደ ድርጅቱ ልቀላቀል ችያለሁ።
አዲስ ዘመን፤ መንግስት የጦርነት ፍላጎት ባይኖረም ሕወሓት ደግሞ ወደ ጦርነት እየገባ ይገኛል፤ ለዚህም የትግራይ ህዝብና የዓለም ማህበረስብ አቋም ምን ሊሆን ይገባል ይላሉ?
አቶ ብርሃነ፤ ሕወሓት እስካለ ድረስ ጦርነት አይቆምም፤ ምክንያቱም ይህ የሽብር ቡድን ያለጦርነት መኖር ስለማይችል ነው። ከጦርነት ወጥቶ አያውቅም። ራሱ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት እንኳን ጦርነትን አቁሞ አያውቅም። መጋጨት ጠብ መፍጠር መዋጋት በዚህ አይነት አካሄድ ነው መኖር የሚፈልገው። ከዚህ ከወጣ ወይም ወደ ዴሞከራሲያዊ መንገድ ከመጣ ጥያቄዎች ይመጣበታል። ይህ ቡድን ከበረሃ አንስቶ እስካሁን የትግራይ ህዝብ የሚጠይቀውን ጥያቄ አልመለሰም።
ከትግራይ ህዝብ ብዙ ጥያቄዎች ይቀርቡለታል። ከጥያቄዎቹም መካከል በደርግ ጊዜ በበረሀ የተሰው ታጋዮች እነማን እንደሆኑ? የት ቦታ እንደተሰው ተገልፆ ለትግራይ ህዝብ አልተነገረም። ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን ካልመጡ እንደሞቱ ቁጠሯቸው ከማለት በስተቀር
ለቤተሰብ መርዶ የነገረ አንድም አካል የለም። ሌላው ደግሞ ሕወሓት በትጥቅ ትግል በነበረበት ጊዜ የትግራይ መሳፍንት የሚባሉ ብዙ የትግራይ ባለሃብቶችን እያፈነ በሌሊት ይወስድ ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ይሙቱ ይኑሩ የሚያውቅ ሰው የለም፤ ቢጠየቅም መልስ የሚሰጥ አካል አልተገኘም። ይህ ዋና የትግራይ ህዝብ ጥያቄ ነው። ለዚህ ጥያቄ ደግሞ ሕወሓት ስልጣን ላይ በነበረ ጊዜ መልስ አልሰጠም። ቤተሰቦቻቸውም እስካሁን በጥበቃ ላይ ናቸው። ስለዚህም ነው የህዝብ ጥያቄዎችን ላለመመለሰ ሲል እርስ በእርስ እያባላ የሚኖረው።
አዲስ ዘመን፤ የትግራይ ህዝብ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የሚኖር ከሆነ መቃወም አልነበረበትም ወይ? አሁንስ ይሄን ስርአት ከላዩ ላይ ለማንሳት ምን ማድረግ አለበት?
አቶ ብርሃነ፤ የትግራይ ህዝብ ለውጥም በይው፤ ተቃውሞም በይው፤ አንድ ጉዞ ለመጀመር የሚያስችል ቦታ ሊኖረው ይገባል። ትንሽ መፈናፈኛ ሜዳ ከሌለ ወዴትም መንቀሳቀሰ አይቻልም። ከፊትም ከኋላም ዙሪያው ገደል ከሆነ እስከምትወድቅ ወይም ገደል ውስጥ እስከምትገባ ድረስ ዝም ብለህ ትቆማለህ። አሁን የትግራይ ህዝብ ዙሪያው ሕወሓት በተባለ ገደል የተከበበበት ሁኔታ ነው ያለው። መንቀሳቀሻ ሜዳ የለውም።
ይህ የሽብር ቡድን እስካልጠፋ ድረስ የትግራይ ህዝብ መንቀሳቀስም፤ መቃወምም፤ መነቃነቅም አይችልም። ይህን ያደረገው ደግሞ ወዶ አይደለም፣ ሳይወድ ነው። አንድ የታሰረ እስረኛ ከታሰረ መቃወም አይችልም። ከተቃወመ ምን እንደሚደርስበት
ስለሚያውቅ እሱም አይሞከረውም። በትግራይ ውስጥ ሕወሓትን መቃወም ማለት ራስን በፍቃደኝነት ወደ ጉድጓድ መጣል ማለት ነው።
አሁን የትግራይ ህዝብ አጋዥ የሚፈልገበት ጊዜ ላይ ነው። ረዳት ያስፈልገዋል። የሚያግዘው ካገኘ ወደ ሰላማዊው መንገድ ሊመጣ ይችላል እንጂ፤ አሁን በታጠረበት፤ በረሃብ በችግር በጦርነት እየተጎሳቆለ ባለበት፤ ትንሽ ውልፍት ካለ እየታሰረ እየተገደለ ባለበት መቃወም አይችልም። አሁን የትግራይ ህዝብ እየተዳደረ ያለው በፌደራል መንግስቱ ሳይሆን በሽፍታ ቡድን በመሆኑ አንድ የታገተ ሰው ምን አፍ ኖሮት ይቃወማል፤ እንኳን መቃወም መናገርም ከባድ ሆኖበታል።
አዲስ ዘመን፤ ሕወሓት በዚህ ወቅት ሶስተኛው ዙር ጦርነት ጀምሯል እየተባለ ይገኛል፤ የኢትዮጵያ መንግስትም የአፀፋ ምላሽ እንሰጣለን እያለ ነው እዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድነው?
አቶ ብርሃነ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላሙን አግኝቶ እስከመጨረሻው ፊቱን ወደ ልማት እንዲመልስ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይህን የሽብር ቡድን ማጥፋት ይኖርበታል። ዝም ብሎ ነካክቶ አባሮ መመለስ አይደለም። ይህ ቡድን ቀበሮ ወይም ጅበ አይደለም። መንደር ገብቶ ሲተናኮል ወደ ጫካ የምትመልሰው፤ ይህ የኢትዮጵያ ጠላት ነውና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግዶ ለትግራይ ህዝብ የሚሆን ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ተስማምቶ የሚኖር ከጎረቤት ጋር ተስማምቶ የሚኖር ክልላዊ መስተዳድር ማስቀመጥ ነው።
እንደዛ ካልሆነ ግን ቡድኑ ትግራይን እንገነጥላለን የሚል አስተሳሰብ ያነሳሉ፤ ፍላጎታቸው ይህ ከነበረ በስልጣን በነበሩ ጊዜ ለምን አላደረጉትም ነበር። ከአዲስ አበባ ተባረው ሲሄዱ ነው መገነጠል የሚታያቸው? የትግራይ ህዝብ አቅም አግኝቶ በቃኝ ያላቸው ጊዜ አንዲት ወረዳ ይዘው ሊነጠሉ ነው ወይስ ሌላ አላማ አላቸው? የፌደራል መንግስት ማድረግ ያለበት እነዚህን አስወጥቶ የትግራይ ህዝብ ሰላም የሚሆንበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል።
ይህ ህዝብ ሰቆቃና ግፍ በዝቶበት የሚቆረቆርለት ወገን አጥቶ ነገ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም እስኪል ድረስ ዝም ማለት አይገባም። ዛሬ እየተራበ ዛሬ እየሞተ ዝም የሚል የፌደራል መንግስት ካለ ነገ የኢትዮጵያ አካል አይደለንም የሚል ነገር እንዳይመጣ ስጋቴ ነው። ለዚህም ዛሬ ወገኔ ነው የራሴ ዜጋ ነው በማለት ከገባበት ችግር ማስወጣት የግድ ነው የምለው። እርዳታ መላክ ብቻ ሳይሆን ከችግር አውጥተህ የትግራይ ህዝብ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር በሰላም እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፤ የሕወሓት መሪዎች ለመጨረሻው ምእራፍ ጦርነት ተዘጋጅተናል እያሉ በየመገናኛ ብዙሃኖቻቸው ሲናገሩ ይሰማል፤ ይህ ነገር እንዲያበቃ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ብርሃነ፤ እነዚህ እኩይ ሃይሎች መሪ ያላቸው እራሱ አይመስለኝም፤ ማን እንደሚመራ አይታወቅም፤ አንዱ በዚህ መጥቶ እኔ ነኝ መሪ ሌላው ደግሞ እኔ ነኝ ይላል። የመጨረሻ የመጥፊያ ካርዳቸውን ስለቆረጡ አምና ተሸውዶ የነበረው ህዝብ ነቅቷል። አምና ፀሎት አድርገን ያመጣናቸውን ሕወሓቶች ተራግመን ማጥፋት አቃተን በማለት ህዝቡ ምሬት ላይ ነው።
አሁን ላይ አንድም በፍቃዱ ጥይት የሚተኩስ ወጣት የለም። ወጣቱ መች ጦርነቱ ተጀምሮ እጅ እንሰጣለን እያለ ነው። የትግራይ ህዝብ በዚህ ወቅት መቼ ነው ከዚህ ሰቆቃ የምንገላገለው እያለ ይጠብቃል። የተለያዩ መረጃዎችን እናገኛለን። አሁን ጫን ያለ ጦርነት ቢካሄድ ዋናዎቹ እጅ ይሰጣሉ ወይም ራሳቸውን ያጠፋሉ።
አዲስ ዘመን፤ ለህዝቡ የሚላከው የእርዳታ እህል ተረጂዎች ጋር አይደርስም፤ ህዝቡ በዚህም እየተጎዳ ነው የሚባል ነገር ይሰማልና ስለዚሀ ጉዳይስ ምን አስተያየት አልዎት?
አቶ ብርሃነ፤ የእርዳታ እህል ከዚህ ይሄዳል። ልክ እዛ እንደደረሰ በእነሱ መኪና ተገልብጦ ወደ ወፍጮ ቤት ይሄዳል፤ ከዛ በኋላ ለእነሱ ዳቦ መጋገሪያ ቤቶች ይከፋፈላል። ዳቦ ተጋግሮ ማሰልጠኛዎች፤ የወታደር ካምፖች፤ ለካድሬዎቻቸውና ለደጋፌዎቻቸው ደርሶ ካለቀ በኋላ ነው እንግዲህ ከተረፈ ህዝቡ ሊቃመስ የሚችለው።
የትግራይ ህዝብ ሰቆቃ በዚህ መልኩ ነው የሚገለጸው። በስሙ ይነገድበታል እንጂ እንኳን ከችግር የሚያወጣው የሚልስ የሚቀምሰው እርዳታ እጁ ጋር እንዳይደርስ ሆኗል። እንኳን የእርዳታ እህል ሊደርሰው ለነገ ብሎ ያስቀመጠውን እህል እየነጠቁ ይወስዱበታል። ሰው ትርፍ እህል ካለው ሰው ትርፍ ገንዘብ ካለው እየተነጠቀ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ሰው በረሃብ እያለቀ ነው፤ ከህመም ከጦርነትም በላይ በረሃብ የሚፈጀው ህዝብ በጣም በዝቷል። ይህ የእርዳታ እህል በትክክል ህዝቡ ጋር ስለመድረስ ምን ዋስትና አለ።
ህዝቡ እንደማይደርሰው ልናረጋግጥ የቻልነው በተለያዩ የትግራይ ድንበር አቅም ያገኘው ሰው በተለያየ አቅጣጫ እየተመመ ይገኛል። ሰው ሲጠየቅ ረሃቡ እጅግ የከፋ ስለሆነ እየሸሸን ወጣን የሚሉትን ሰምተናል፤ ስለዚህ መንግስት ይሄንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የማያዳግም ሁኔታ ይሄን የሽብር ቡድን በማጥፋት ህዝቡን ካለበት ሰቆቃ ማውጣት የግድ ነው።
አዲስ ዘመን፤ ይህ የሽብር ቡድን የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ነው ያለው፤ ከፌደራል መንግስቱ ጋርም ሆነ ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ትንኮሳ እያካሄደ እንደሆነ ይነገራል፤ ጦርነቱ መጀመሩ ለትግራይ ህዝብም ሆነ ለአገሪቱ ያለው ተፅእኖ ምን ይመስሎታል ?
አቶ ብርሃነ፤ ጦርነቱ ዳግም አልተጀመረም። በፊቱኑም አላለቀም ነበር። እየተጓተተ ነው እስካሁን የቆየው። እየተጎተተ ቀን እየረዘመ በሄደ ቁጥር ኢትዮጵያ እየተጎዳች፣ ኑሮው እየተወደደ ኢኮኖሚ እየቀነሰ አገር ወደ ድህነት እየገባች ነው የምትሄደው። ለዚህ መድሀኒቱ የዚህን የሽብር ቡድን እድሜ ማሳጠር ነው። ለዚህ ቡድን ጊዜ እየተሰጠው በሄደ ቁጥር አገሪቱም ወደ ከፋ ችግር እየገባች ትሄዳለች፤ የትግራይ ህዝብም ከቀን ወደ ቀን እያለቀ ይሄዳል። ዛሬ በትግራይ ውስጥ በበሽታ ፤በረሃብ ፤ በጦርነት ስንት ሰው እያለቀ እንደሆነ አይታወቅም። ይህ በቀን ሰው እንደቅጠል እየረገፈ ያለውን የትግራይ ህዝብና ሰቆቃ ለማሳጠር ይህን ሰላም ጠል የሆነ እኩይ ቡድን ይበቃል ማለት የግድ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፤ ሕወሓት ያለጦርነት መኖር ይከብደዋል፤ ሁሉ ነገሩ ከጦርነት ጋር የተያያዘ ነው የሚሉ አካላት አሉ በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ ሀሳብ ምንድነው?
አቶ ብርሃነ፤ ከላይ እንደገለፅኩልሽ ይህ ቡድን እንዲህ አደርግልሃለሁ ብሎ ቃል ለገባለት የትግራይ ህዝብም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ መመለሰ የሚከብደው ብዙ ጥያቄዎቸ አሉበት። ጥያቄውን ሽሽትም ራሱን በጦርነት ሸፍኖ እየኖረ ይገኛል። በስልጣን በነበረበት ወቅት እንኳን ከጎረቤት አገር ጋር ጦርነት ላይ ነበር፤ ያ ሲያበቃ ደግሞ ህዝቡ በሃይማኖት እርስ በእርሱ እንዲጣላ ሲሞክር ነበር፤ የሃይማኖት ጦርነት አላዋጣ ሲለው በኳሱም ሆነ በሌላ ሰበብ የአካባቢያዊ ግጭቶች እንዲፈጠሩ ሳይታክት ሲሰራ ኖሯል። ሰው በኳስ ምክንያት በድንጋይ ከመወራወር አልፎ ወደ ጥይት መተኳኮስ ሊደርስ ትንሽ ነበር የቀረው። ስለዚህ ይህ ቡድን በፈረቃ ህዝብን ከማፋጀት የበለጠ ስራ የሚባል መልካም ነገር ሳይኖረው ይሄው እስከዛሬ ድረስ አለ።
አዲስ ዘመን፤ የትግራይ ማህበረሰብ የራሱ የሆነ መገለጫ ያለው፤ የከበረ ባህልና እሴት ባለቤት የሆነ ህዝብ ነው፤ የሕወሓት ቡድን በዚህ ልክ ጠምዝዞ የፍላጎቱ ማስፈፀሚያ ሊያደርገው የቻለበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ብርሃነ፤ ሁሉም ነገር ስርአት አለው። እንኳን ሰው እንስሳት እንኳን የሚመሩበት ስርአት አላቸው። ግን ስርአቱ ተጠብቆ እንዲቆይ መሪ ያስፈልገዋል። ሁሉም ነገር የሚበላሸው ደግሞ በመሪ የተነሳ ነው። የትግራይ ህዝብም መጥፎ የሆነ አመራር ስላለው እየተታለለ ወዳልሆነ ሁኔታ ይገባል እንጂ የራሱ እሴት ባህል የተለየ ማንነት ያለው ህዝብ ነው።
ይህ ብልሹ አስተሳሰብ ያለው ቡድን ደግሞ ህዝቡ እንዳይታይ፣ ማንነቱ እንዲደበቅ፤ ከሌሎች ወንድም ብሔሮች ጋር ተስማምቶ እንዳይኖር አድርገውታል። በእነሱ የጠለሸ ስራ የህዝቡ ስም ጠቁሯል።
አዲስ ዘመን፤ ሕወሓት ወጣቶችን በግዳጅ ወደ ጦርነት እያስገባ ያለበት ሁኔታ አለ። ወጣቶች ይህ እንዳይሆን ምን ማድረግ አለባቸው ይላሉ?
አቶ ብርሃነ፤ አሁን ትግራይ ውስጥ ዋና ነቀርሳ ሆነው ያሉ የበታች ካድሬዎች አሉ። የቀበሌ፤ የወረዳና የዞን አስተዳደሮች ከሕወሓት የበላይ አመራሮች በበለጠ የትግራይ ህዝብ ውስጥ ተሰግስገው ህዝቡን እያስጨረሱ ያሉ ናቸው። ወጣቱንም በሃይል አስገደደው ወደ ጦርነት እንዲሄድ የሚያደርጉት ከህዝቡ ጋር በቅርበት ያሉት እነዚህ የበታች ሀላፊዎች ናቸው። የትግራይ ወጣት ወደ ጦርነት እየገባ ያለው በሃይል ነው እንጂ ወዶ አይደለም። ከዚህ አፋኝ ስርአት ማምለጥ የቻሉት በተለያየ አቅጣጫ ወደ እናት አገሩ እየገባ ነው ያለው። በጦርነቱ ታጣቂ የነበረ፤ ሲቪል የነበረ፤ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ሲሰራ የነበረ እና ሌላው ማህበረሰብ ጦርነቱን ጠልቶ አካባቢውን እየጣለ እየመጣ ይገኛል።
ቀደም ሲል ይሄን ያህል የትግራይ ወጣት ተፈናቅሎ አያውቅም ነበር። አሁን ይህን በግዳጅ ወደጦርነት መማገድን በመሸሽ የትግራይ ወጣት ጥሏቸው እየመጣ ነው ያለው። ይህ የሆነበት ምክንያትም የጦርነትን ውጤት በአግባቡ ስላየው ነው። አሁን ላይ በፍቃዱ ወደ ጦርነት የሄደ ወጣት የማይኖር መሆኑን እገምታለሁ።
አዲስ ዘመን፤ በሕወሓት ቡድን ከአርባ አመት በላይ ህዝብን ከህዝብ የመከፋፈል ስራ ሲሰራ ቆይቷል። የትግራይ ህዝብም ቢሆን ከጎረቤቶቹ ከአፋር ከአማራ ጋር ጠበኛ እንዲሆንም አድርገውታል፣ ይህ አስተሳሰብ መነሻው ከየት ነው ይላሉ?
አቶ ብርሃነ፤ የዚህ አስተሳብ መነሻ ከአመጣጣቸው ላይ ነው። ይሄን ስልሽ መጀመሪያ ወያኔ ሲመሰረት በአንድ አካባቢ በትንሹ በጠባብ ሁኔታ ነበር። ይህ አስተሳሰባቸው አድጎ ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ እርስ በእርስ መሳሳብ፤ የየት አካባቢ ተወላጅ ነው ብለው በመጠያየቅ በአነስተኛ ቡድን ውስጥ ራስን ማስቀመጥ እንጂ ሰፋ ያለ አመለካከት አልበራቸውም። ስለዚህ ከጅምራቸው የተለማመዱት አንደአገር አድጎ ብሔርን ከብሔር ሊከፋፈል በቅቷል።
አዲስ ዘመን፤ ሕወሓት በአሁኑ ወቅት በትግራይ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና መከራ በምን መልኩ ይገለፃል?
አቶ ብርሃነ፤ አሁን በትግራይ ውስጥ ያለው መከራ የሚታወቅና የሚታይ ነው። ምንም ምግብ የለም፤ መድሃኒት የለም፤ ሰው ወደ ልማት ወደ ስራ ሊገባ አልቻለም። ትምህርት ከተቋረጠ ሶስት አመታት ሊሆኑት ነው። ብዙ ወጣቶች ዳግም ወደመሀይምነት እየተጓዙ ነው። አዳዲሰ ትምህርት ቤት መግባት የነበረባቸው ህፃናት ቤት ውለዋል። ህዝብ እንደልቡ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ መንገድ መስራት አልቻለም። በተለያየ የአለማችን ክፍል የነበሩ የትግራይ ልጆች ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት አልቻሉም። በአጋጣሚ ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ሄደው እዛው የቀሩ፤ ከዛም ወደዚህ መጥተው የተለያዩ ቤተሰቦችም በርካታ ናቸው።
የትግራይ ህዝብ በሕወሓት ምክንያት ተቆጥሮ የማያልቅ ግፍና መከራ እያደረሰ ስለሆነ የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የዓለም ማህበረሰብ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶት ይህ መከራ በአጭሩ እንዲያልቅ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል።
አዲስ ዘመን፤ ሕወሓት የተንኳሽነት ባህሪውም በአገር ውስጥም ሆነ ከጎረቤቶች ጋር ያሳያል፣ ፍላጎቱ ምንድነው ይላሉ?
አቶ ብርሃነ፤ የሕወሓት ፍላጎት ሁሉም የትግራይ ህዝብ እንዲቆስል እንዲደማ ነው። በየቤቱ ሰው እንዲሞት ሀዘን ሁሉንም እንዲያዳረሰ ነው። ይህንንም የሚያደርጉት እነሱ እንዳበቃላቸው ያውቃሉ። የነሱ ልጆች ግን ውጭ ነው ያሉት። ውጭ ሆነው እየተማሩ የዓለምን አስተሳሰብ ለመቀየርና የነሱን እድሜ ለማራዘም እየሰሩ ይገኛሉ። እነዚህኞቹ ከወደቁ ዳግም ለማንሰራራት እንዲመቻቸው ትናንት ተመችቷችኋል ቆስላችኋል በማለት ለማነሳሳት እንዲመቻቸው መደላድል ለመስራት ነው።
አዲሰ ዘመን፤ ማስተላለፍ የሚፈለጉት መልእክት ካለ እድሉን ልስጥዎት?
አቶ ብርሃነ፤ ትግራይ ውስጥ ላገጠመው ችግር በአቅሙ መፍትሄ ለመስጠት ድርጅታችን ትህዴን ትግል ላይ ይገኛል። በዚህ ትግልም የትግራይ ህዝብ ከጎናችን እንዲሰለፍ ጥሪ እናቀርባለን። የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ መነጠል እንደማይፈልግ የኢትዮጵያ ህዝብ ተረድቶ ሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች ለመነጠል የተዘጋጀውን ቡድን ለማጥፋት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናችን ቢቆም መልካም ነው። የትግራይ ህዝብም ከሞተው ሕወሓት ጋር አብሮ መሞት ሳይሆን ይህን የሞተ ቡድን በማጥፋት ከተቀረው ወንድም ህዝብ ጋር አብሮ እንዲኖር ማድረግ አለበት። ትህዴን በትግራይ ዙሪያ የድንበር ከተሞች ስላሉ መምጣትና ትግሉን መቀላቀል የፈለገ ወደትግሉ መቀላቀል ይችላል።
አዲስ ዘመን፤ ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን።
አቶ ብርሃነ፤ እኔም አመሰግናለሁ።
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2014