የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ባለፈው እሁድ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም በደማቅ የመክፈቻ ስነስርአት ተጀምሯል። ከትናንት በስቲያ አንስቶም የኦሊምፒክ በሆኑና ባልሆኑ በርካታ የስፖርት አይነቶች የተለያዩ ውድድሮች በፉክክር ታጅበው ቀጥለዋል። በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎች በታዳጊና ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርገው በሚካሄዱ ውድድሮች የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ አሳሳቢ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ የወጣቶች ኦሊምፒክ ሲካሄድ በእድሜ ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ባይቻል እንኳን ችግሮችን በተቻለ መጠን ቀንሶ አገርን በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች የሚወክሉ ተተኪ አትሌቶችን ለማፍራት ታስቦ ነው። በኦሊምፒኩ ባለፉት ሁለት ቀናት ውሎ ከእድሜ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ስፖርቶች ጎልተው የወጡ ችግሮች ባይኖሩም ሊበረታቱ የሚገቡ መልካም ጅምሮች እንደነበሩ መታዘብ ተችሏል። በተለይም እንደ ካራቴ በመሳሰሉ የፍልሚያ ስፖርቶች ተሳታፊዎች ያቀረቧቸው ወጣት ስፖርተኞች “አይን አይቶ ልብ ይፈርዳል” እንደሚባለው የእድሜ ተገቢነት የሚነሳባቸው ሆነው አልተገኙም። ይልቁንም በነዚህ ስፖርቶች እየተወዳደሩ የሚገኙ ወጣቶችም ይሁኑ እንዲሳተፉ መርጠው ወደ ውድድሩ ስፍራ ያመጧቸው ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በእድሜ ጉዳይ ላይ ያደረጉት ጥንቃቄ አስመስግኗቸዋል።
እንዲህ በተገቢው እድሜ ስፖርተኞች ፉክክር ሲያደርጉ ማየት ከዚህ ቀደም በመላ አገሪቱ ምንያህል ታዳጊና ወጣት ስፖርተኞች ሽልማትና ዋንጫን አልመው በሚሰሩ ሰዎች እንደተዋጡና እንደተበደሉ የሚያሳይ ቁጭትን ይፈጥራል። ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው የወጣቶች ኦሊምፒክ መመስገን ካለበት ዋነኛ ጉዳይ በተለይም ትኩረት በማይሰጣቸው እንደ ካራቴ በመሳሰሉ የፍልሚያ ስፖርቶች ኢትዮጵያ ወደ ፊት ተስፋ ያላቸው በርካታ ባለተሰጥኦ ታዳጊዎች እንዳሏት ማሳየት መቻሉ ነው።
የዘወትር የስፖርቱ ነቀርሳ የሆነው የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ ከፍልሚያ ስፖርቶች በተጨማሪ ኢትዮጵያ ውጤታማ በሆነችባቸው ስፖርቶች ክልሎች ትኩረት ሰጥተው ቢሰሩ ትምህርት እንደሚሆንም በውድድሮች ላይ የተገኙ የስፖርት ቤተሰቦች አስተያየት ሲሰነዝሩና ሲወያዩ ቆይተዋል።
በፍልሚያ ስፖርቶች በተለይም ትናንት በርካታ ፉክክሮችን ባስተናገደውና ካለፈው ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ጀምሮ የኦሊምፒክ ስፖርቶች ውስጥ የተካተተው የካራቴ ስፖርት ላይ የታዩ ተወዳዳሪዎች በተገቢው እድሜ ለውድድር የቀረቡ ብቻም ሳይሆን በስፖርቱ ትልቅ አቅም ያላቸው መሆኑን አሳይተዋል። ስፖርቱ በኦሊምፒክ የተካተተ መሆኑም ለእነዚህ ተወዳዳሪዎች ትልቅ የሞራል ስንቅ እንደሰጣቸው በስፍራው ያነጋገርናቸው ወጣት ስፖርተኞችና ባለሙያዎች ተናግረዋል። በዚህ ስፖርት እነዚህን ባለተሰጥኦ ለጋ ወጣቶች ትኩረት ሰጥቶ በቅርበት መከታተል ከተቻለም በቀጣይ በግብጽ በሚካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ቻምፒዮናና በሴኔጋል ዳካር በሚካሄደው የአለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ውድድር ላይ ለአገራቸው አንድ አዲስ ነገር ማበርከት የሚችሉበት እድል እንደሚኖር ተስፋ አሳይተዋል። ባለፈው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በወርልድ ቴኳንዶ ስፖርት በአትሌት ሰለሞን ቱፋ መወከል መቻሏ ከተለመደው የአትሌቲክስ ስፖርት ባሻገር በፍልሚያ ስፖርቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከተቻለ ቢያንስ ተሳትፎ ከባድ እንደማይሆን ማየት ተችሏል። የካራቴ ስፖርትም በኦሊምፒክ መካተት መቻሉ አሁን በኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ብቅ ያሉት ታዳጊና ወጣት ስፖርተኞች ህልማቸው እስከ ኦሊምፒክ እንዲዘልቅ አድርጓቸዋል። እነዚህን ወጣቶች ደግፎና ተንከባክቦ የመያዝና በተለያዩ አለም አቀፍ ውድድሮች ልምድ እያገኙ እንዲዳብሩ የማድረግ የቤት ስራው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑና የኦሊምፒክ ኮሚቴ ይሆናል።
ከፍልሚያ ስፖርቶች አንዱ የሆነው ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ዳዊት አስፋው፣ በዚህ የወጣቶች ኦሊምፒክ የእድሜ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ቀደም ተብሎ ማሳሰቢያ እንደተሰጣቸው ይናገራሉ። ያም ሆኖ በአንዳንድ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ ችግር አይኖርም የሚል እምነት የላቸውም። “እድሜ ማጭበርበር የኢትዮጵያን ስፖርት ይጎዳል እንጂ አይጠቅምም ብለን ተነጋግረን ተማምነናል” ያሉት አቶ ዳዊት ተሳታፊ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም በዚህ ረገድ የተቻላቸውን ጥረት በማድረግ ኮሚቴውን እንደረዱት አብራርተዋል። ይህ የመጀመሪያ ወጣቶች ኦሊምፒክ እንደመሆኑም ከእድሜ ጋር የሚነሱ ችግሮችን በቀጣይ መሰል ውድድሮች ከባለሙያዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር የተሻለ ውጤት የሚታይበት ልምድ እየተገኘ እንደሚገኝም አቶ ዳዊት ገልጸዋል ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24/2014