ታላቁን የስፖርት መድረክ ኦሊምፒክ ከሌሎች ታላላቅ የስፖርት መድረኮች ለየት የሚያደርገው ነገር የመክፈቻና የመዝጊያ ሥነሥርዓቱ ነው። ኢትዮጵያ በተለያዩ ዓመታት በኦሊምፒክ ጽንሰ ሃሳብ መሠረት በርካታ አገር አቀፍ ውድድሮችን ለማከናወን ጥረት አድርጋለች። ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ በሐዋሳ የተጀመረውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክን የመሰለ የመክፈቻ ሥነሥርዓቱ በኦሊምፒክ ለዛና ጣዕም የተዋጀ ውድድር ግን ማስታወስ አስቸጋሪ ነው። ድንገት የጣለው ዝናብ ሳይረብሻቸው የመክፈቻው ሥነሥርዓት ድምቀት ከሆኑት ከኢትዮጵያ አየር ኃይል ሄሊኮፕተሮች አጀብ አንስቶ እስከ ሲዳማ ፈረሰኞችና በአጭር ዝግጅት የተለያዩ ትርኢቶችን በማራኪ ሁኔታ እስካቀረቡት ወጣቶች የመክፈቻ ሥነሥርዓቱ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም የተዋጣ ሆኗል።
ይህ የመክፈቻ ሥነሥርዓት ኦሊምፒክ ኦሊምፒክ በሚሸቱ ትርኢቶች ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ እንግዶችም የታጀበ ነበር። የታላቁ የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ጀግና አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ታሪካዊ ተፎካካሪ የኬንያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አትሌት ፖል ቴርጋት እስከ አፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አሕመድ ሃሺምና ሌሎችም ዓለም አቀፍ እንግዶች እንዲሁም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በሥነ ሥርዓቱ ታድመዋል።
የውድድሩን መጀመር በስፍራው ተገኝተው ያበሰሩት የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘው ተሻገር፣ ጽንሰ ሃሳቡ በዓለም ላይ ከሰረጸ መቶ ዓመታትን የተሻገረው ኦሊምፒክ ሰላም የሰፈነባት የተሻለች ዓለምን ለመፍጠር፣ በፍትሐዊ ውድድር መግባባትን፣ከመሸናነፍ በላይ ተሳትፎን የሚያስቀድም መሆኑን በማስታወስ ሁሉን በአንድ ላይ በሚያሰባስበው መድረክ ወጣቶችን በስፖርት ማሰባሰብ ጥቅሙ ከስፖርትም የበለጠ መሆኑን ተናግረዋል። “ኦሊምፒክ ለኢትዮጵያ የአልሸነፍ ባይነት ምልክት ነው” ያሉት አፈ ጉባኤው የአበበ ቢቂላ የሮም ኦሊምፒክ ድል ለዚህ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል። ኦሊምፒክና ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን ከአበበ ቢቂላ በኋላ በታላቁ መድረክ ድል የተቀዳጁ በርካታ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ማሳየታቸውን ያስታወሱት አፈ ጉባኤው በትውልድ ቅብብሎሽ የደመቀውን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቀጣይነት ለማረጋገጥ የወጣቶች ኦሊምፒክ መካሄዱ ያለውን ፋይዳ አብራርተዋል። በዚህ መድረክ ወጣቶችን በተገቢው ዕድሜ በማወዳደርም በዋናው ኦሊምፒክ ሀገርን የሚወክሉ አትሌቶች የሚፈሩበት መሆን እንደሚገባው አስገንዝበዋል። በውድድሩ የሁለት ሳምንት ቆይታ የኦሊምፒክን ጽንሰ ሃሳቦች ተግባራዊ በማድረግ ተወዳዳሪዎች በመተሳሰብና በሰላም እንዲያጠናቅቁ አሳስበዋል።
የውድድሩ አስተናጋጅ ሲዳማ ክልል ፕሬዚዳንት ደስታ ሌዳሞ ባደረጉት ንግግር፣ የኦሊምፒክ ጽንሰ ሃሳብ ካለ አንዳች ልዩነት በአንድነትና በመተሳሰብ አብሮ የመኖር ጥበብ መሆኑን በማስታወስ የኦሊምፒክ ዓላማና ግብ ለአሁኗ ኢትዮጵያ ትልቅ መልዕክት እንዳለው ገልጸዋል። “ወንድማማችነትና ኅብረትን ከኦሊምፒክ መማር አለብን” ያሉት ፕሬዚዳንቱ ኦሊምፒክ ወጣቶች ከራስ ይልቅ ለሀገር ቅድሚያ መስጠትን የሚማሩበት መድረክ መሆኑን በመገንዘብ በዚህ መድረክ የሚሳተፉ ወጣቶች ሊኮሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በክብር እንግድነት የተገኙት የአኖካ ዋና ጸሐፊ አሕመድ ሐሺም በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ትልቅ የኦሊምፒክ አቅም እንዳላቸው በመግለጽ ያላቸውን እምቅ አቅም በእንዲህ አይነት መድረኮች አውጥተው መጠቀም እንዳለባቸው ጠቁመዋል። ከዚህም ባሻገር በዚህ የወጣቶች ኦሊምፒክ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ለዓለም ሕዝብ ማሳየት እንዳለባቸው በማስገንዘብ አፍሪካውያን ምሳሌ አድርገው እንዲመለከቷቸው ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ባደረጉት ንግግርም፣ እየቀነሰ የመጣውን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ውጤት ለማሻሻል ትምህርት ቤቶችን የተተኪ ስፖርተኞች መፍለቂያ በማድረግ በወጣቶች ኦሊምፒክ መድረክ እንዲያልፉ ጥረት መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል። ይህ የወጣቶች ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ መልካም ገጽታዋን የምታስተዋውቅበትና የሚወራባት አሉባልታ እውነት እንዳልሆነ ለዓለም የምታሳይበት አጋጣሚ እንደሚፈጥርም አክለዋል። አንድነትና መተባበር ምን ያህል እንደሚያጠናክርም ወጣቶች ከዚህ መድረክ እንደሚማሩ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
እስከ ሰኔ 04/2014 በሚቆየው በዚህ የወጣቶች ኦሊምፒክ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ስድስት ሺ ያህል ወጣቶች በኦሊምፒክና የኦሊምፒክ ባልሆኑ ስፖርቶች ተሳታፊ ናቸው። ከኦሊምፒክ ስፖርቶች አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣መረብ ኳስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ እጅ ኳስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ጅምናስቲክና ወርልድ ቴኳንዶ ፉክክር የሚደረግባቸው የስፖርት አይነቶች ሲሆኑ የኦሊምፒክ ባልሆኑ ስፖርቶች ቼዝ፣ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶና ውሹ መካተታቸው ታውቋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2014