በተደራጀና በተቀናጀ አሰራር የታገዘ ባይሆንም የጓሮ አትክልት ልማት(የከተማ ግብርና) ለከተሞች አዲስ አይደለም። ለምግብነት የሚውል የአትክልት ልማት በስፋት ባይስተዋልም፣ ለባህላዊ ህክምና የሚያገለግሉ እንደ ጤናአዳም፣ ዳማከሴ፣ ለመአዛነት የሚያገለግሉ እንደ ጠጅ ሳር፣ አርቲ እንዲሁም ለምግብ ማዘጋጃ የሚያገለግሉ እንደ ኮሰረት፣ የጥብስ ቅጠልና የመሳሰሉትን ተክሎች ከደጃፍና ከጓሮ አይጠፉም።
እነዚህን እጽዋት ለልማት የሚውል በቂ መሬት ባይኖርም እንኳ በእቃ እና ባሉት ክፍት ቦታዎች ማልማት የተለመደ ነው። ሰፊ የግብርና ሥራ በሚከናወንበት በገጠርም ሳይቀር ከፍ ብሎ ከተጠቀሱት አትክልቶች በተጨማሪ ጎመን፣ ቃሪያ፣ ቲማቲም፣ ድንች የመሳሰሉት አትክልቶች በጓሮ እንዲለሙ ይደረጋል።
የቦታ ጥበትን ምክንያት እያደረጉ ብዙዎች ይህን ልማት እያካሄዱ ባይሆንም፣ ልማቱን የቦታ ጥበት ባለበትም ቦታ ጭምር ማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ ስለመኖሩ ተሞክሮዎች እያመለከቱ ይገኛሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በቤተመንግስት አትክልቶችን በማልማት አርአያ ሆነዋል፤ ያለሙትን አትክልትም ሰዎች እንዲጎበኙ በማድረግ፣ ከለማውም በማቋደስ ልማቱ ይበልጥ እንዲሰፋ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል።
የከተማ ግብርና አሁን በመንግስት በኩል የከተማ ግብርና ትኩረት ተሰጥቶታል። ይህን ተከትሎም የተቀዛቀዘው የጓሮ አትክልት ልማት አሁን ሰፋ ባለ መልኩ የከተማ ግብርና በሚል መንግሥትም አቅጣጫ አስቀምጦለት እየተሰራበት ነው። በአዲስ አበባ የከተማ ግብርና በቢሮ ደረጃ እየተመራም ነው። በአዲስ መልክ እየተካሄደ ያለው ይህ የከተማ ግብርና ብዙዎችንም እያነቃቃ ይገኛል።
ለከተማ ግብርና የግድ ሰፊና የተንጣለለ ቦታ አያስፈልግም። በጠባብ ቦታም ልማቱን ማካሄድ ይቻላል። በቂ የልማት ቦታ የሌለው እንኳን ግድግዳንም እንደ መሬት በመጠቀም፣ በየበረንዳውና አጥሩ ጥግ በእቃዎች ጭምር የአትክልት ችግኞችን መትከል ጀምሯል።
የከተማ ግብርና በተለይ የምግብ ዋጋ በናረበት በዚህ ወቅት አስፈላጊነቱ የጎላ ነው። በከተማ ግብርና የሚለሙ አትክልቶች ለምግብነትም ለአይን ማረፊያም በመሆን ያገለግላሉ። ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ የዕለት ፍጆቻዎች የሆኑ አትክልትና ፍራፍሬዎች በቀላሉ አልምተው መጠቀም የሚያስችላቸው በመሆኑ አማራጭ የኑሮ ውድነት መፍቻ እርምጃዎች በመሆን የራሳቸው አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፤የአይን ማረፊያ በመሆንም ያገለግላሉ። ለአካባቢ ውበትን ያጎናጽፋሉ፤ ለአልሚዎቻቸውም ትርፍ ጊዜያቸውን ስራ ላይ በማዋል እንዲጠቀሙበት በማድረግ ያገለግላሉ።
የከተማ ግብርና ልማት ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ እንደሆነም የዘርፉ ባለሙያዎች ምክራቸውን ሲለግሱ ይሰማሉ። ሰዎች በጓሮአቸው እያለሙ መጠቀምን ባህል እያደረጉ ቢቀጥሉ ተጓጉዞና በተለያየ ሂደት ውስጥ አልፎ ለገበያ ከቀረበው አትክልት ይልቅ ከእርሻ ላይ ትኩስ ማግኘት መቻላቸው ለጤናቸው፣ወጪ በመቆጠብና ድካም በመቀነስ ተጠቃሚ ይሆናሉ።
በአካባቢያቸው ተደራጅተውና ተቀናጅተው በስፋት ቢያለሙ ደግሞ የገቢ ምንጭ ይሆናቸዋል።ዜጎች ተደራጅተው ሰርተው ገቢ ሲያገኙ መንግሥት ለዜጎች ሥራ ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት በማገዝ እንዲሁም እንደሀገር በግብርና ሥራ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማጠናከር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ግልጽና አስተማማኝ የሆነ የከተማ ግብርና ኤክስቴንሽን ሥርአት ቢኖር፣የማህበረሰቡ ትኩረትና ግንዛቤ ከፍ ቢል፣ከታችኛው እርከን እስከ ላይኛው ቅንጅታዊ አሰራር ቢኖር የከተማ ግብርናው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል የከተማ ግብርናን አስፈላጊነት አስመልክቶ በተለያየ ጊዜ በተካሄዱ መድረኮች ምክረሀሳቦች ተሰጥተዋል።
እየተነቃቃ ያለው የከተማ ግብርና በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን፣በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችም ተሞክሮዎች በመስፋት በመተግበር ላይ ይገኛል። ተቋማት ያሏቸውን ክፍት ቦታዎች ለልማት እንዲውል በመፍቀድ ጭምር እያገዙ የሚገኙበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።
በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ቡኖ በደሌ ዞን በደሌ ከተማ ለሥራ በተገኘንበት ወቅት ተሞክሮውን ለማየት ዕድሉን አግኝተናል። በበደሌ ከተማ ግብርና ጽህፈትቤት ግቢ ውስጥ ተገኝተናል። ለተወገዱ ቁሳቁስ ማጠራቀሚያነት ሲያገለግል የቆየ ቦታ ልማቱ እንዲከናወንበት ተቋሙ ይፈቅዳል። በቦታው ላይ አልምተው ገቢ እንዲያገኙ የተፈቀደላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ደግሞ አነስተኛ ገቢ ያላቸው በሴፍቲኔት የታቀፉ ናቸው። ተጠቃሚዎቹም የዳንዲጉዲና ሴፍቲኔት ማህበር አባላት ናቸው።
ማኅበሩ በከተማ ግብርና ልማት ላይ ያለውን ተሳትፎ በተመለከተ የማህበሩ አባል አቶ ተስፋዬ ደምሴ እንደገለጹልን፤ የዳንዲጉዲና ሴፍቲኔት ማህበር 20 ቀጣና ያለው ሲሆን፣እያንዳንዱ ቀጣናም የተደራጁ አባላት አሉት። ከነዚህ ውስጥ አንዱ እርሳቸውን ጨምሮ 32 አባላት የሚገኙበት ቡድን ነው።እርሳቸውም የቡድኑ መሪ(አባ ሶዶሚ) ናቸው።
አባላቱ በከተማ ጽዳት በመንግሥት ተቀጥረው የሚሰሩ ሲሆኑ፣ባላቸው ትርፍ ጊዜ ደግሞ በከተማ ግብርና በመሳተፍ አትክልት አልምተው በመሸጥ በሚያገኙት ኑሮ ገቢያቸውን ይደጉማሉ። የበደሌ ከተማ አስተዳደር በየተቋማቱ ባሉ ክፍት ቦታዎች ሁሉ አልምተው እንዲጠቀሙ ፈቅዶላቸው ነው ወደ ልማት የገቡት።
እኛም በልማቱ ስፍራ ተገኝተን እንዳረጋገጥነው ካሮት፣ ቀይስር፣ ቆስጣና ሌሎች የአትክልት ችግኞችን በአንደኛው መደብ ላይ በማፍላት፣በሌላኛው ወገን ቀድመው ዘር በመበተን ያፀደቋቸውን የተለያዩ የአትክልት አይነቶች ሲንከባከቡ ነበር።
አባላቱ የልማቱን ሥራ ሲያከናውኑ የግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ እገዛ ስለሚያደርጉላቸው የሥራ ክፍተት አልተፈጠረባቸውም። አብዛኞቹ አባላት በከተማ ውስጥ የኖሩ በመሆናቸውም እንዲህ ላለው የግብርና ልማት ሥራ ቅርብ አልነበሩም። የግብርና ሥራ የግድ በገጠር ብቻ መከናወን እንዳለበትና ሰፋፊ የሆነ መስኖ ያስፈልጋል የሚል ነበር እምነታቸው።
እያካሄዱ ባሉት ልማት በአነስተኛ ቦታ የተለያየ የአትክልት አይነት ልማት ማከናወን እንደሚቻልም ግንዛቤ አግኝተውበታል። በተግባርም አረጋግጠዋል።ቀድመው ልማቱ ውስጥ አለመግባታቸው ቁጭት ውስጥ ከቷቸዋል። ከልማቱ ገና ጥቅም ባያገኙም ተስፋ አድርገዋል። የልማት ቦታም ሆነ የባለሙያ ድጋፍ እያገኙ ስለሆነ እነርሱም ምርቶቹን ለገበያ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቀሚ ለመሆን አቅደዋል። የጀመሩት የከተማ ግብርና ከራሳቸው አልፎ ለሀገርም አቅም ይፈጥራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው አቶ ተስፋዬ ነግረውናል።
በበደሌ ከተማ እየተከናወነ ስላለው የከተማ ግብርና እና ጽህፈት ቤቱ እያደረገ ስላለው ሙያዊ ድጋፍና ክትትል በተመለከተ የበደሌ ከተማ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ ብዙአየሁ ነገሰ እንዳሉት፤ በከተማው የግብርና ሥራ የተጀመረው በ2011ዓም ሲሆን፣ የከተማውን ደረጃ በሚያስጠብቅ መልኩ ነው እየተከናወነ የሚገኘው። የግብርና ሥራውም የሚከናወነው በከተማዋ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ጭምር ነው። ለተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ማዘጋጃ በጽህፈትቤቱ ስር የሚገኝ የችግኝ ጣቢያ በመኖሩ የግብአት አቅርቦት ችግር አያጋጥምም። በሰኔ ወር የሚተከል አቮካዶና ሌሎች ችግኞችንም በማዘጋጀት ለአልሚው ይመቻቻል።
በከተማዋ ለከተማ ግብርና 13 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን አቶ ብዙአየሁ ይገልጸሉ። ከዚህ ውስጥ ወደ 11 ሄክታር የሚሆነው አትክልትና ፍራፍሬ እንደሚለማበት ይገልጻሉ። በቀሪው ሁለቱ ሄክታር ላይ የበቆሎ ልማት ነው የሚከናወነው ይላሉ።
በልማቱ ላይ እንዲሳተፉ ዕድሉ የተመቻቸው ሥራ ለሌላቸው ሲሆን፣እነሱም በማህበር ተደራጅተው እንዲሳተፉ ነው የተደረገው። በዚሁ መሠረትም 42 መሠረታዊ ማህበራት ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ሲሉ ያብራራሉ።
ግለሰቦችም በመኖሪያ ቤታቸውና በአካባቢያቸው እንዲያለሙ ይበረታታሉ። አስፈላጊው ድጋፍም በጽህፈትቤቱ ይደረግላቸዋል። ከእርሻ ሥራው ጎን ለጎን ከብት ማድለብ፣ የወተት ልማት፣ዶሮ ማርባት፣ንብ ማነብ በአጠቃላይ ሁለገብ የእንስሳት ልማት በማከናወን በዘርፉ የሥራ እድል እንዲፈጠር ማድረግ ተችሏል።
ሸማቹም ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ የኑሮ ውድነትን ለማርገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ነው አቶ ብዙአየሁ የሚናገሩት። በአካባቢው የከተማ ግብርናን ሰዎች በፍላጎታቸው የሚያከናውኑት እንጂ በተደራጀ መልኩ መንግሥታዊ ድጋፍ እየተደረገለት እንዳልነበር ያስታወሱት ባለሙያው፣ በጽህፈት ቤቱ ክትትልና ድጋፍ በተደራጀ መልኩ መሰራት ከጀመረ ወዲህ የማህበረሰቡም የማልማት ፍላጎት እያደገና ጥቅሙም እየታወቀ መምጣቱን አመልክተዋል። ይህንንም አጠናክሮ በመቀጠል የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በጽህፈትቤቱ በኩል እየተደረገ ስላለው ሙያዊ ድጋፍና ክትትል አቶ ብዙአየሁ እንዳስረዱት፤ጽህፈት ቤቱ በእንስሳት ልማቱ ላይ የከብቶች አያያዝ፣ጤንነታቸውን እንዴት መከታተል እንዳለባቸው፣አመጋገባቸውን፣በአጠቃላይ ሳይንሱን ተከትለው እርባታውን እንዲያከናውኑ ምክረሀሳብ ይሰጣል፤ አስፈላጊ የሆነ ሙያዊ ድጋፍም ያደርጋል።
አትክልትና ፍራፍሬ ልማቱ ላይም በተመሳሳይ ስለችግኝ ማፍላት፣ችግኞችን በመበተንና ለማጽደቅ መከተል ያለባቸውን ዘዴ በተግባር በማሳየት ጭምር እገዛ ይደረጋል። ግብአትም እንዲያገኙ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ይሰራል። ለአብነትም በዶሮ እርባታ ላይ ለተሰማሩ በአካባቢው ከሚገኘው ኤልፎራ ከተባለ ድርጅት የሁለት ቀን ጫጩት እንዲያገኙ ጽህፈት ቤቱ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። ተሞክሮዎችን ለማስፋትና የልማቱን ተሳታፊዎች ለማበረታታት ሞዴል አልሚዎችን በመለየት እወቅና በመስጠት የማነቃቃት ሥራ ይሰራል።
በዚህም እስካሁን በተከናወነው ሥራ በከብት እርባታና በወተት ልማት ላይ ተሰማርተው ይሰሩ ከነበሩ ማህበራት ሁለት ማህበራትን ወደ ኢንቨስትመንት ደረጃ ማሳደግ ተችሏል። በተለይ በእንስሳት ልማት ለመሰማራት ፍላጎት እያላቸው ነገር ግን በካፒታል(ገንዘብ)እጥረት ችግር ይገጥማቸው ለነበሩ አሁን ላይ ለከተማ ግብርና በተሰጠው ትኩረትና በማህበር ተደራጅተው ለመንቀሳቀስ ፍላጎት ላላቸው ጥሩ መደላድል ተፈጥሮላቸዋል። በእንስሳት ልማቱ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች ቢሟሉ የበለጠ መስራት ይቻላል ያሉት አቶ ብዙአየሁ፣ በተለይ ለእንስሳት ማዳቀያ የሚሆን ግብአት እጥረት መኖሩን ተናግረዋል።
ለከተማ ግብርና ተግዳሮት ከሚሆኑት አንዱ የውሃ አቅርቦት እንደሆነ ይታወቃልና ከዚህ አኳያ የገጠማቸው ችግር ይኖር እንደሆነ አቶ ብዙአየሁ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ በከተማዋ ዙሪያ በሶስት አቅጣጫዎች ከሚፈሱ ወንዞች ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት ዕድል በመኖሩ በዚህ በኩል ስጋቱን ማቃለል ይቻላል።
በደሌ ከተማ አባቦኩና ሹረሙ የተባሉ ቀበሌዎች ያሉት ሲሆን፤አንዱ ቀበሌ 9፣ሌላኛው ደግሞ 8 ቀጣና አለው። በከተማው ወደ አንድ መቶሺ ህዝብ እንደሚኖር ይገመታል።
አጠቃላይ በዞኑ ከተሞች ስላለው የከተማ ግብርና ሥራ የቡኖ በደሌ ዞን ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ጅፋር እንዳሉት፤ ዞኑ በግብርና ውጤቶች የከተማውን ነዋሪ ፍላጎት የማሟላት ሥራ በቂ እንዳልሆነ በዞን ደረጃ በግምገማ ተለይቶ አቅጣጫ በማስቀመጥ የከተማ ግብርናን የማዘመን ተግባር ለማከናወን ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው። ግብርናውን የሚያግዙ ባለሙያዎችን በስልጠና ከማብቃት ጀምሮ ነው እርምጃ የተወሰደው።
የልማት የትኩረት አቅጣጫውም የአትክልትና ፍራፍሬ፣እንዲሁም የእንስሳት ልማት መሆናቸውን አቶ ዳዊት ጠቅሰው፣ በነዚህ የልማት ሥራዎች የከተማው ነዋሪ ቢያንስ ራሱን መመገብ እንዳለበት እምነት ተይዞ እየተሰራ ይገኛል ይላሉ። በተለይ በእንስሳት ልማት በኩል በማዳቀል ዘዴ ሰፊ ሥራ መሥራት የሚቻልበት ዕድል በመኖሩ የእንስሳት ተዋጽኦን በበቂ ሁኔታ ለተጠቃሚው ማቅረብ የሚቻልበት እድል እንደሚኖር ኃላፊው አመልክተዋል።
ቢሮው አልተሰራም ብሎ ከገመገመው አንዱ የወተት ማዕከል መቋቋም ላይ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ዳዊት፣ የወተት ልማቱ ከተከናወነ በኃላ በማእከል የሚቀርብበት ሁኔታ መመቻቸት እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሶ ይህንንም ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በከተሞች በተለያየ ምክንያት ስራ ላይ ያልዋሉ ቦታዎች ሞልተዋል፤ ይህ ብቻ ሳይሆን የተባለው ቦታ ባይኖር እንኳ በእቃ ልማቱን ማካሄድ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ስለመኖራቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ የአትክልት ልማቶች ጥሩ ማሳያዎች ናቸው።
የከተማ ግብርና ልማትን ለማካሄድ በቂ ቦታ የለም የሚል አመለካከት በብዛት ባለበት ሁኔታ በበደሌ ከተማ በከተማ ግብርና በኩል እየተከናወነ ያለው ተግባር እንደ ሀገር ከተያዘው አቅጣጫ ጋር የሚሄድና ለሌሎችም በተሞክሮነት የሚጠቅስ ነው። በተለይ ተቋማት ስራ ላይ ያላዋሏቸውን ቦታዎች ለእዚህ አገልግሎት እንዲያውሉ በበደሌ እየተከናወነ ያለው ተግባር በአርአያነት ሊወሰድ ይገባዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2014