ሰሞኑን ማህበራዊ ሚዲያው በአማራ ክልል በሚካሄደው ዘመቻ ዙሪያ ባለ ክርክር ተወጥሮ ከርሟል። መንግስት ዘመቻው ህግን የማስከበር ነው ሲል ይህን የሚቃወሙ ሀይሎች ደግሞ መንግስት የያዘው ፋኖን ማሳደድ እና ትጥቅ ማስፈታት ነው የሚል ክርክር ያነሳሉ። በመንግስት በኩል የክልሉ አስተዳደር ይህን ይቃወማል።
የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ እንደሚሉት ከሆነ ዘመቻው እየተካሄደ ያለው ፋኖ ላይ ሳይሆን በፋኖ ስም በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ነው። “ሥርዓትና ሕግ የሚያከብሩ፣ የተጋደሉ፣ የተዋጉ ፋኖዎች አሉ፣ በእነዚህ ስም መነገድ አይቻልም፣ ማህበረሰቡ ለጀግና ፋኖዎች የሚሰጠው ክብር ይታወቃል፣ ፋኖነትን ከደሙ ጋር ያዋሀደ ጀግና ሕዝብ ነው፣ እስር ቤት ጥሶ ወንጀለኛን ያስለቀቀ ቡድን ላይ እርምጃ ስትወስድ ፋኖን ትጥቅ ሊያስፈታ ነው ይልሃል፣ ይሄ የፋኖ መገለጫ አይደለም፤ ይሄ ትልቁን ክብራችን የማዋረድና የመናቅ ነው” ብለዋል አቶ ግዛቸው።
ከዚህ የኃላፊው ንግግር በመነሳት የምናነሳው አንድ ጥያቄ አለ። ፋኖ ማን ነው? ይህ ጥያቄ ቀጥሎ ለሚኖሩ ውይይቶች ወሳኝ ነው። ፋኖ ለምንለው ሀይል የምንሰጠው መገለጫ (characteristics) ከዚያ ሀይል ጋር ለሚኖር መስተጋብር ያለው ፋይዳ ወሳኝነቱ የጎላ ነው። ይህ ግን ለፋኖ ብቻ ሳይሆን ለቄሮም ፤ ለዘርማም፤ ለሌላውም የሚሰራ ነው። እነዚህ ቡድኖች ማናቸው? ምንድን ነው መገለጫቸው? የሚለውን ከለየን በኋላ ነው የልማት ወይም የጥፋት ሀይሎች ናቸው የሚለውን የምንበይነው። በዚህ መልኩም ነው ሕወሓት እና ኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድን ተብለው የተሰየሙት እና እርምጃ እየተወሰደባቸው ያለው።
አሁን ላይ ፋኖ ነኝ ፤ ቄሮ ነኝ ፤ እገሌ ነኝ የሚል ሰው ብዙ ነው። በዚህም የተነሳ እነዚህ ስሞች የብዙ የተለያየ አጀንዳ ያላቸው ሀይሎች መሰባሰቢያ ሆነዋል።ይህ ብዙ ችግር እያስከተለ ነው። ሁሉም የልቡን ከፈጸመ በኋላ ሲያዝ ፋኖ ስለሆንኩ ተያዝኩ ፤ ቄሮ ስለሆንኩ ተጎዳሁ እያለ ህዝብ ማወናበዱን ተያይዞታል። ስለዚህም ፋኖ ማለት ይህ ነው ፤ እንዲህ አይነት ባህሪ ያለው ፤ ይህን የሚያደርግ ይህን ደግሞ ፈጽሞ የማያደርግ ፤ በዚህ ቦታ የሚገኝ በዚያ ቦታ ደግሞ የማይገኝ ፤ እንዲህ የሆነ እና እንደዚያ ያልሆነ ነው ተብሎ የማንነት መገለጫ ሊሰጠው ይገባል። በዚህ መልኩ ፋኖን ከተራ ወንበዴ መለየት ይቻላል።በተመሳሳይም ለቄሮም እንዲሁ።ለዘርማም እንዲሁ።ለሌላውም እንዲሁ።
ከላይ እንዳልኩት መገለጫዎችን ማውጣት መቻል ከአላስፈላጊ ትርምስ ለመዳን ያግዛል። ለምሳሌ ያህል በአንድ ወቅት ላይ ልማታዊ ባለሀብት የሚል ብያኔ ተፈጥሮ ነበር።ይህ ስያሜ ስራቸውን በአግባቡ ለሚሰሩ፤ ጉቦ ለማይሰጡ ፤ ግብር በሰአቱ ለሚከፍሉ ፤ ህገወጥ የገበያ ውድድር ለማይፈጥሩ፤ ኢኮኖሚያዊ ሳቦታጅ ላይ ላልተሰማሩ ባለሀብቶች የሚሰጥ ስም ነበር። እነዚህ ባለሀብቶች የመንግስት ጥበቃ የማይለያቸው እና የልማት ቅድሚያ የሚሰጣቸውም ናቸው። ይህ ማለት ከነዚህ በተቃራኒ የሆኑ ባለሀብቶች አሉ ማለት ነው። ልማታዊ ባለሀብት የሚለው መጠሪያ እና መገለጫዎቹ በእርግጥም ጠቀሜታ አላቸው። አንደኛ ሁሉም ባለሀብት ሌባ ነው ወይም ሁሉም ባለሀብት ሀብቱን በልፋት ነው ያገኘው ከሚል ስህተት ለመዳን እና ባለሀብትን ሁሉ በአንድ አይን ላለማየት ያግዛል። ሁለተኛ ከመልካሞቹ ባለሀብቶች ጋር የሚደረገውን ውይይት በበጎ ለመቃኘት ከአስቸጋሪዎቹ ባለሀብቶች ጋር የሚደረገውን ውይይትም ቆምጠጥ ለማድረግ ያስችላል። ሶስተኛው እና ዋነኛው ግን መንግስት ማንን እንደ አይኑ ብሌን ማየት እንዳለበት ማንን ደግሞ በአይነ ቁራኛ መከታተል እንዳለበት ለመወሰን ያስችላል።
ወደ ፋኖ ጉዳይም ሲመጣ በተመሳሳይ መታየት ያለበት ጉዳይ አለ። ትክክለኛው ፋኖ ማን ነው? በፋኖ ስም የሚነግደው ወንበዴስ ማነው? የሚለውን መለየት ያስፈልጋል። ትክክለኛው ፋኖ ቅድሚያ ለህዝብ የሚሰጥ ፤ በጦርነት ወቅት በጀግንነት የሚዋጋ ፤ በሰላም ቀን ተግቶ የሚያርስ የሚነግድ ፤ ትዳር እና መኖሪያ ያለው ፤ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ ግዴታውን በቅጡ የሚወጣ ፤ ህግን የሚያከብር ፤ የጎበዝ አለቃነት ስሜት ያልተጠናወተው ፤ ለአላማው እንጂ ለስልጣን እና ለጥቅም የማይሞት ወዘተ…መሆን ያለበት ነው። በተቃራኒው ህጻናትን አግቶ ገንዘብ የሚጠይቅ ፤ ሴቶችን የሚደፍር ፤ ወንዶችን የሚገድል ፤ ቤት አልባ አውደልዳይ ፤ ህግ የማያከበር ፤ ስራ መስራት የማይወድ ፤ መሳሪያው ከትከሻው የማይወርድ ፤ ህገወጥ መሳሪያ እና ገንዘብ የሚያዘዋውር ፤ ባለሀብቶችን እንዳይሰሩ የሚያደናቅፍ፤ የጎበዝ አለቃ የመሆን አላማ የያዘ ፤ በጎጥ የታጠረ ፤ ከጠላቶች ጋር ለጊዜያዊ ጥቅም የሚያብር እሱ ደግሞ ፋኖ ሳይሆን በፋኖ ስም የሚመጣ ወንበዴ ነው። ስለዚህም በዚህ መሰረት የመጀመሪያው ፋኖ የልማት እና የሰላም ሀይል ነውና ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባ ሲሆን ሁለተኛው በአንጻሩ በፋኖ ስም የሚንቀሳቀስ ወንበዴ ነውና እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል።
በእርግጥ እስካሁን እንዳየነው ከሆነ የአማራ ክልልም በዚህ መሰረት እየተጓዘ ይመስላል። ትክክለኛ የሰላም ሀይል ናቸው እውነተኛ ፋኖ ናቸው ያላቸውን ሸልሟል። ከሽልማቱ በኋላ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን “ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ የአይበገሬነት እና የአትንኩኝ ባይነት ተምሳሌቶች ናቸው! በማለት የፋኖ መገለጫ አይበገሬነት እና አትንኩኝ ባይነት እንደሆነ ተናግረዋል። ስለዚህም ክልሉ ሰላማዊ የሚላቸውን ፋኖዎች ለይቷል፤ መገለጫቸውንም በይኗል ማለት ነው። ይህ ከሆነ ዘንድ ክልሉ ቀጣይ ተግባሩ መሆን ያለበት ይህን የትክክለኛ ፋኖ መገለጫ ለህዝቡ ማሳወቅ ሲሆን፤ በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሰውን ወንበዴም የማጋለጥ ተግባር በአግባቡ ሊሰራ ይገባል። ይህ ስራ ከተሰራ ህዝቡ ፋኖ ስለሆንኩ ታሰርኩ በሚል ማወናበጃ አይሳሳትም ማለት ነው። ትክከለኛው ፋኖ መገለጫው ከታወቀ ያ ሰው እኔ ፋኖ ነኝ ባይል እንኳ ህዝቡ ስራውን አይቶ ያውቀዋል፤ ይደግፈዋል። በተቃራኒው ፋኖ ሳይሆን ፋኖ ነኝ የሚለውንም ወግድ አንተ ወንበዴ ነህ ማለት ይችላል።
ስንጠቀልለው ክልሉ ፋኖ ለሚለው መጠሪያ መገለጫውን ሊያበጅለት እና ህብረተሰቡን ቀድሞ ሊያሳውቅ ይገባል። ያኔ ህዝብ ከመንግስት ጎን በመሆን የሰላም አጋር መሆን ይችላል።
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2014