አፍሪካ በእግር ኳስ ትልቅ አቅም ያላት አህጉር ብትሆንም እንደ ሌሎቹ አህጉራት ትልቅ ደረጃ መድረስ አልቻለችም። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ይቀመጣሉ። ለአፍሪካ እግር ኳስ እንቅፋት ብለው ባለሙያዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሚያስቀምጡት ምክንያት አንዱ በትክክለኛው እድሜ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊና ወጣት ተጫዋቾች በበቂ ሁኔታ አለማፍራት ነው። በተለይም የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ በአፍሪካ የተለያዩ ውድድሮች የተለመደና መፍትሔ ያልተገኘለት መሆኑ የአህጉሪቱን እግር ኳስ እድገት እየጎተተው እንደሚገኝ ብዙዎች ያምናሉ። ካፍ በታዳጊና ወጣቶች በሚያካሂዳቸው ውድድሮች ይህን የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ ለመቆጣጠር የተለያዩ የእድሜ መመርመሪያ ቴክኖሎጂዎችን ሲጠቀም ቢስተዋልም ችግሩን ማስቀረት አልቻለም። በዚህም አስደናቂ ተሰጥኦ ይዘው ወደ ፊት ትልቅ ደረጃ የመድረስ ተስፋ ያላቸው ታዳጊዎች በእድሜ የበላዮቻቸው ተውጠው ሕልማቸው ሲጨልም ማየት የተለመደ ሆኗል። ይህ ችግር እግር ኳሳቸው ዳዴ እያለ በሚገኝ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ብቻም ሳይሆን የተሻለ ደረጃ ላይ በሚገኙ የአፍሪካ አገራት ጭምር በስፋት መስተዋሉ የአህጉሪቱ እግር ኳስ ላይ ተስፋ እንዳይጣል ያደርጋል።
የደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳኒ ጆርዳን፣ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ የአፍሪካን እግር ኳስ ወደ ኋላ እየጎተተው እንደሚገኝ ተናግረዋል። የአህጉሪቱን እግር ኳስ ከሌሎች አህጉራት ጋር ተፎካካሪ ሆኖ እንዲወጣ ከተፈለገም አሰልጣኞች የእድሜ ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
እንደ ዶክተር ዳኒ ገለጻ፣ አፍሪካ ፊፋ በታዳጊና ወጣቶች መካከል የሚያካሂዳቸውን ሁሉንም ውድድሮች ማለት ይቻላል አሸንፋለች። አፍሪካ ኦሊምፒክን ጨምሮ፣ከ17ና20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ውድድሮችን አሸንፋ አሳይታለች፣ ይሁን እንጂ በዋናውና በአዋቂዎቹ የዓለም ዋንጫ ከግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚነት የዘለለ ታሪክ የላትም። ይህም የሆነው አፍሪካ በታዳጊና ወጣቶች ውድድር ላይ ከእድሜ በላይ ተጫዋቾችን በማሰለፏ ነው። በታዳጊ ውድድሮች አዋቂዎች ይጫወቱና ስኬታማ ይሆናሉ። ከዚያ ወደ አዋቂዎች ውድድር ሲሸጋገሩ አቅምና ጉልበታቸውን ጨርሰው በትክክለኛ እድሜ የብቃታቸው ጥግ ላይ ከሚገኙ የሌሎች አህጉራት ተጫዋቾች ጋር መፎካከር ይሳናቸዋል።
ይህን የእድሜ ችግር በቅርቡ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ኪንሻሳ ላይ በተካሄደው የፓን አፍሪካ የትምህርት ቤቶች ውድድር ላይም እንዳስተዋሉ የሚናገሩት ዶክተር ዳኒ፣ ለዚህም በታዳጊ ወጣቶች ላይ የሚሠሩ አሰልጣኞችን ዋነኛ ተጠያቂ ያደርጋሉ።
የአንድ ሃገር የወደፊት እግር ኳስ ስኬት ያለው በትምህርት ቤቶች በሚገኙ ታዳጊዎች ላይ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ዳኒ፣ ከእድሜ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ፊት ለፊት አውጥቶ በመነጋገር መፍትሔ ማበጀት እንደሚያስፈልግ ያምናሉ። ለዚህም አሰልጣኞች ችግሩን በቅርበት ተከታትለው እንዲቀርፉ የአሰለጣጠን መንገዶችን ማስተካከል አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ። እግር ኳሳቸው ባደገ እንደ አውሮፓ ባሉ ሃገራት አንድ የታዳጊ አሰልጣኝ ለሃያ ተጫዋቾች ነው የሚመደበው፣ እንደ አፍሪካ ባሉ አገራት ግን ብዙ ጊዜ አንድ አሰልጣኝ ሁለት መቶ ታዳጊዎችን ሊያሰለጥን የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ ችግሩን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንዳደረገው ዶክተር ዳኒ ያብራራሉ።
እግር ኳስ ትልቅ የገቢ ምንጭ እየሆነ በመጣበት በዚህ ወቅት በአፍሪካ ከአሰልጣኞች በተጨማሪ የተጫዋች ወኪሎች በአቋራጭ ጥቅም ለማግኘት በታዳጊ ውድድሮች አዋቂዎችን ማበረታታቸው ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገው ሚስጥር አይደለም። ለዚህም ተጫዋቾች የተለያየ ሁለት እድሜ ይለጠፍባቸዋል። በርካቶቹ የአውሮፓ ክለቦችም ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎችን ለመመልመል በዚህ እንደሚቸገሩ ይታወቃል።
“እድሜ ማጭበርበር የአፍሪካን እግር ኳስ መግደል ነው” የሚሉት የግብጽ እግር ኳስ ማኅበር የሚዲያ ኦፊሰር ሜድሃት ሻላቢ እድሜ ማጭበርበርን በአፍሪካ እግር ኳስ እንደ ካንሰር አድርገው ይገልጹታል። ይህ መጥፎ ልማድ የአፍሪካን እግር ኳስ እያጠፋው ነው የሚሉት ባለሙያ እድሜ የሚጭበረበር ከሆነ በተለያዩ ደረጃዎች የሚካሄዱ የታዳጊና ወጣት ውድድሮች ፋይዳ ምኑ ላይ ነው? ብለው ይጠይቃሉ።
የእድሜ ማጭበርበር ችግሮችን ለመቅረፍ ፊፋ እኤአ በ2009 ከ17 አመት በታች የዓለም ዋንጫ ጀምሮ ማግኔቲክ ሪሶናንስ ኢሜጂንግ(ኤም አር አይ) የተባለውን ቴክኖሎጂ በተለያዩ የወጣት ውድድሮች ላይ ለመጠቀም መወሰኑ ይታወቃል። ይህ ቴክኖሎጂ እስከ 17 ዓመት ድረስ ያሉ ታዳጊዎችን ትክክለኛ እድሜ ለመለየት 99 በመቶ ስኬታማ ነው ቢባልም ከተጠቀሰው እድሜ በኋላ ለመለየት ሲቸገር ተስተውሏል። በኢትዮጵያም ታላቅን ታናሽ፣ ታናሽን ታላቅ አድርጎ የለየበት አጋጣሚ እንደነበር አይዘነጋም። ያም ሆኖ ቴክኖሎጂው አፍሪካ ውስጥ የእድሜ ጉዳይ አሳሳቢነቱን በተለያዩ ውድድሮች የተጭበረበሩ እድሜዎችን በማጋለጥ ማሳየቱ አይካድም።
የቅርቡን ለማስታወስ ያህል በ2020 የካፍ የወጣቶች ውድድር ኮሚቴ የዚምባቡዌ፣ኮሞሮስ፣ቦትስዋናና ሌሎች አገራት ብሔራዊ ቡድኖችን ከደቡብ አፍሪካ አገራት የ17 ዓመት በታች ዋንጫ ተሳትፎ በእድሜ ማጭበርበር ምክንያት ማገዱ ይታወቃል። በበርካታ አጋጣሚዎችና የታዳጊ እንዲሁም ወጣት የአፍሪካ ውድድሮች አገራት ሙሉ በሙሉ ባይታገዱ እንኳን በእድሜ ማጭበርበር ተጫዋቾቻቸው ከውድድሮች ያልተሰናበቱበት አጋጣሚ አይታወስም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2014