ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብቷ ትታወቃለች። ለኢንዱስትሪዎች ግብዓቶች የሆኑ ማዕድናትና እሴት የተጨመረባቸው የማዕድን ውጤቶችን በስፋት ጥቅም ላይ እያዋለች የምትገኘው ግን ከውጭ በማስገባት ነው። ለእዚህም በየዓመቱ በቢሊዮን ዶላር ወጭ እንደምታደርግ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የሚስተዋለው የምርትና አገልግሎቶች ዋጋ መናር ደግሞ የኢኮኖሚ አቅሟን እየተፈታተነው ይገኛል። በቂ የውጭ ምንዛሪ አቅም ባለመኖሩ ግብዓቶቹን በሚፈለገው መጠንም ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት የማይቻልበት ሁኔታም እየታየ ነው። ይህ ደግሞ በግንባታው ዘርፍ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚገኙ ፕሮጀክቶች በሲሚንቶ፣በብረት፣ለግንባታ ማጠናቀቂያዎችና ሌሎችም አስፈላጊ የሆኑ የማዕድን ውጤት ግብዓቶች ዋጋ መናር ሥራዎች እንዲጎተቱ ምክንያት እየሆነ ነው።
የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዋልታ ለሆነው የግብርናው ዘርፍ የሚውለው የማዕድን ውጤት የሆነው ማዳበሪያም አቅርቦት ችግር ይስተዋልበታል። ለማዳበሪያ ግብዓት የሚሆን የማዕድን ሀብት ሃገር ውስጥ በበቂ መጠን እያለ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ግዥው ከውጭ ይፈጸማል። ዓለም ላይ ያለው የማዳበሪያ ዋጋ ደግሞ እየናረ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ሃገሪቱ በእዚህ ሁሉ ቁጭት ውስጥ ሆና እንደ ማዳበሪያ ፋብሪካ ያሉትን ለመገንባት ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት መድባ ጥረት ብታደርግም ሊሳካላት አልቻለም። በእዚህና በመሳሰሉት ችግሮች ሳቢያ የማዕድን ዘርፉ የሚፈለገው ደረጃ ሊደርስ አልቻለም።
ሃገሪቱ ከራስዋ አልፎ ለውጭ ገበያ በማዋል የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ መጠቀም የሚያስችላት የምድር ውስጥ ፀጋ ቢኖራትም፣ ባለመልማቱ የተነሳ የውጭ ናፋቂ ሆና ቀጥላለች። የሚገርመው ደግሞ በውጭ ምንዛሪ ወደ ሃገር የምታስገባው ለግብዓትነት የሚውል የማዕድን ውጤት በከፍተኛ የጥራት ደረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ሆኖ በሃገር ውስጥ ግብዓት መጠቀም ውስጥ አለመገባቱ ነው፤ ይህም የማዕድን ዘርፉን የሚመራውን አካል ጭምር ቁጭት ውስጥ ከትቶታል።
ይህን ቁጭት ወደ ተግባር ለመለወጥ ማዕድን ሚኒስቴር ማዕድናትን የማስጠናት ፣አዋጭነታቸውን የማስገመገም ጥናት እንቅስቃሴውን አጠናክሯል። ዘርፉን ወደፊት ሊያራምደው የሚችል ፖሊሲ ከመቅረጽ አንስቶ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የ2014 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የእቅድ አፈጻጸም እና ወደፊት መከናወን ስላለባቸው ተግባራት ባለፈው ማክሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል፣የሃገር ኢኮኖሚንም የሚያሳድግ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ምድር ውስጥ እምቅ የማዕድን ሀብት ይገኛል ሲሉ ገልጸው፣ ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ የተጓዘችበት መንገድ የእሳቤ ችግሮችና ሳንካዎች ነበሩበት ሲሉ አስታውቀዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የተፈጥሮ ሀብትን እንደ ፀጋ ሳይሆን፣እንደ ግጭት መንስኤ አድርጎ በመውሰድ፣ የጠራ እይታ ባለመኖሩና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሀብቱ እያለ ግን እንደሌለ ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል። የማዕድን ዘርፉን የሚመጥን ፖሊሲ ተቀርጾ ሥራ ላይ አለመዋሉ፣ተቋማዊ አደረጃጀቱም ችግር ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለአጠቃላይ ሃገራዊ ምርት ያለው አበርክቶ በዚያው ልክ ዝቅተኛ እንዲሆን እንዳደረገው ካለፉ የዕቅድ አፈጻጸሞች ሚኒስቴሩ ተገንዝቧል።
እንደ ሃገር የኢኮኖሚና የፖለቲካ መዋቅራዊ ለውጥ ከተደረገባቸው ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ግን የማዕድን ዘርፉ ከኢኮኖሚ ምሶሶዎች አንዱ ሆኖ ትኩረት አግኝቷል ያሉት ኢንጂነር ታከለ፣ በአስር ዓመቱ የሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መሪ እቅድ ላይም ከአምስቱ ምሶሶዎች መካከል አንዱ የማዕድን ዘርፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ተቋሙን በአዲስ መልክ ሲያደራጅ፣የማሻሻያ ሥራዎችን ሲሠራ ሃገራዊ ዕቅዱንና የማዕድን ዘርፉ የሃገር ኢኮኖሚን መሸከም የሚችል መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን አመልክተው፣ በዚሁ መሠረትም ሚኒስቴሩ በ2014 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት፤ ወጪ ንግድን ማሳደግ፣የገቢ ምርቶችን በሃገር ውስጥ መተካትና ለዜጎች የሥራ ዕድልን መፍጠር በሚሉ ሥራዎችን ከፋፍሎ ማከናወኑን ያብራራሉ።
ኢንጂነር ታከለ እንዳብራሩት፤ ሚኒስቴሩ በዘጠኝ ወር አፈጻጸሙ ለውጭ ገበያ ከቀረቡ የወርቅ፣ጌጣጌጥና የኢንዱስትሪ ማዕድናት 458 ነጥብ 07 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል። ለወጪ ገበያ ከሚቀርቡት ማዕድናት በተጨማሪ ለሃገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችና ለግንባታ ዘርፍ የሚቀርቡ የተለያዩ ማዕድናት የሚገኙ ሲሆን፣አራት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ቶን የኢንዱስትሪ ማዕድናት ምርት ለኢንዱስትሪዎች ቀርቧል።
የማዕድን ዘርፉ በብዛት፣በጥራትና በዓይነት በሃገር ኢኮኖሚ ላይ አበርክቶ እንዲኖረው ሲሠራ የአካባቢው ማኅበረሰብ የዘርፉ ተጠቃሚነትም አልተዘነጋም። በዘጠኝ ወር የሥራ እንቅስቃሴ ለ126ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ተግባር ማከናወን ችሏል። ሚኒስቴሩ ጎን ለጎንም ከፍተኛ ልፋትና ጉልበት የሚጠይቀውን የማዕድን ዘርፍ ሥራ በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን የፈጠራ ውጤቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ እያደረገ ይገኛል።
ባለፉት ዓመታት በማዕድን ዘርፉ የሃገር ውስጥም ሆነ የውጭ የግል ኢንቨስትመንቶች ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑንም አስታውቀዋል። ከተለያዩ ሃገሮች የሚቀርቡ በዘርፉ እንሰማራ ጥያቄዎች እያደጉ መምጣቸውን ገልጸው፣ ይህም ለማዕድን ዘርፉ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ተናግረዋል።
ከኢንዱስትሪ ግብአቶች አንዱ የሆነውና ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች የኃይል ግብዓት የሚውለውን የድንጋይ ከሰል በሃገር ውስጥ ለመተካት ጥቂት ወራት ብቻ መታገስ እንደሚገባ ያስገነዘቡት ሚኒስትሩ፣ በሚቀጥለው በጀት ዓመት የድንጋይ ከሰል ከውጭ በግዥ ማስገባት እንደሚቆም ለምክር ቤቱ አረጋግጠዋል።
በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የድንጋይ ከሰል ለማምረት በፋብሪካ ግንባታ ላይ በሚገኙ ኩባንያዎች ላይ ተስፋ ተጥሏል ሲሉ ገልጸው፣ ኩባንያዎቹ ሥራቸው ሰምሮ እቅዱ እንዲሳካ የባለድርሻ አካላት ያላሰለሰ ትብብር እንደሚያስፈልግ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይ ለብረት ማዕድንም ትኩረት መሰጠቱን ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል። እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ በሃገር ውስጥ ብረት አምራች ፋብሪካዎች ቢኖሩም፣ ፋብሪካዎች በግብዓት በኩል ከውጭ ሃገር ከሚገባ ግብዓት የተላቀቁ አይደሉም። በሃገር ውስጥ የሚገኝ ጥሬ ዕቃን አይጠቀሙም። ክፍተቱን በመለየት በሃገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪ ወጭን ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ ችግሩንም በአጭር ጊዜና በረጅም ጊዜ ለመፍታት እየተሞከረ ነው።
የብረት ግብዓት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ሚኒስቴሩ በጊዜያዊነት የወሰደው የመፍትሔ እርምጃ በግንባታው ዘርፍ ላይም ሆነ በሥራ ላይ የሚገኙ ፋብሪካዎች በግብዓት እጥረት ሥራቸው እንዳይስተጓጎል፣ ከመከላከያ ሚኒስቴርና ከሌሎች መንግሥታዊ ተቋማት 386ሺ ቶን ስብርባሪ ብረቶች በመጠነኛ ዋጋ በግዥ እንዲያገኙ ተመቻችቷል። የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ችግርም በመጠኑም ቢሆን እንዲፈታላቸው ተደርጓል።
ሚኒስቴሩ ዘላቂ መፍትሔ ብሎ ያስቀመጠው የሃገር ሀብትን መጠቀም መሆኑንም ኢንጂነር ታከለ ጠቁመዋል። የብረት ምርት አቅርቦትን ሙሉ ለሙሉ በሃገር ውስጥ ለመተካት ሚኒስቴሩ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ የብረት ማዕድን ጥሬ ሀብት ክምችት መኖሩን የሚያሳይ የጥናት ሰነድ በማዘጋጀት የቅድመ አዋጭነት ግምገማ ጥናት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በጥናት የተገኙ የክምችት ናሙናዎችን በቤተሙከራ ውስጥ(ላቦራቶሪ)የማረጋገጥ ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፣ ብረት ለማምረት የሚያስፈልጉ ጥሬ ማዕድናት ማለትም ብረት አዘል አለት፣ኖራ ድንጋይ፣የድንጋይ ከሰልና የመሳሰሉ መጠናቸውና የጥራት ደረጃቸው በቤተሙከራ መረጋገጡን ይገልጻሉ። በቀጣይ ማከናወን የሚጠበቀው የአዋጭነት ጥናት በማድረግ የዲዛይን፣የቴክኖሎጂና የፋብሪካዎች የቦታ መረጣ ሥራ ማከናወን መሆኑን ያብራራሉ።
በሚኒስቴሩ እየተሠራ ያለው ሥራም ሆነ ሃገር ውስጥ ያለው ሀብት የብረት ኢንዱስትሪዎችን የሚመግብ፣ የግንባታው ዘርፍ የሚያጋጥመውን የግብዓት አቅርቦት ችግር የሚፈታ መሆኑንና ይህም ተስፋ እንደተጣለበት ነው ያመለከቱት።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዋልታ የሆነው የግብርናው ዘርፍም በማዕድን ሀብት የግብዓት ውጤት የሚታገዝ በመሆኑ በዚህ ረገድም ሚኒስቴሩ ትኩረት መስጠቱን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት። ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስፈልጉ እንደ ካልሽየምና ፎስፌት ያሉ ጥሬ ግብአቶች በምዕራብ ኢትዮጵያ የሰልፈርና ፖታሽ ክምችት ደግሞ በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ እንደሚገኝ ተረጋግጧል ሲሉ ጠቁመዋል።
አሞኒያን ለማምረት የሚያስፈልገው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት የማጥናትና የማረጋገጥ፣ተስማሚ ቴክኖሎጂ የመለየትና የኢንቨስትመንት አዋጭነት ጥናት ሥራም እየተሠራ መሆኑን ነው የተናገሩት። የክምችት መጠን ግመታና ኢኮኖሚያዊ አዋጭነት ግምገማ እንዲካሄድም ዓለም አቀፍ የአማካሪ ጨረታ በማውጣት ከዓለም አቀፍ ኩባንያ ጋር የስምምነት ውል መፈጸሙንና ኩባንያው ይህን ሥራውን በአራት ወር አጠናቅቆ እንደሚያስረክብም ጠቁመዋል።
የማዕድን ሀብት በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል የሚገኝ በመሆኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መሥራት ካልተቻለ የሚኒስቴሩ ጥረት ብቻውን ከዳር እንደማያደርስ ይታወቃል። ሚኒስቴሩም ይህን ታሳቢ በማድረግ ከክልሎች በተለይም የማዕድን ሀብት በስፋት ከሚገኝባቸው የክልል ፕሬዚዳንቶችና የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት። ግንኙነቱ መጠናከሩ ለኮንትሮባንድ ንግድ ለተጋለጠው የማዕድን ዘርፉ፣ በዘርፉ ለሚሠማራው ባለሀብት የፀጥታ ሥጋት እንዳይኖር ለማድረግ፣በአጠቃላይ የተደራጀ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ ለመሥራት ያግዛል ብለዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በእስካሁኑ የጋራ እንቅስቃሴም የወርቅ ምርት ኮንትሮባንድን ለመከላከል፣እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ምርት ያቆሙ የማዕድን ኩባንያዎች ወደ ሥራ የማስገባት ተግባርም ከክልሎችና ከፀጥታ ተቋማት ጋር በትብብር መሥራት በመቻሉ መሻሻል ታይቷል።
ሚኒስቴሩ የማዕድን ዘርፉ ከሚገኝበት ውስብስብ ችግር ውስጥ ወጥቶ ለሃገር ኢኮኖሚ አበርክቶ እንዲኖረው ጥረት ሲደረግ ነገሮች አልጋ ባልጋ እንዳልሆኑም ይታወቃል። የማዕድን ዘርፉ በስፋት በሚገኝባቸው አካባቢዎች የፀጥታ ችግር መኖሩ፣ ሥራዎች የተከናወኑት በዘርፉ የሰለጠነ በቂ ባለሙያ አለመኖርና የመሳሰሉትን ተግዳሮቶች በመቋቋም ጭምር እንደሆነ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አቅርበዋል። ክፍተቶቹን ለመሙላትም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሥራት ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ሚኒስቴሩ በነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ፣በወርቅ ምርትና ፍለጋ ሥራ ላይ ተሠማርተው በእቅዳቸው ባልተጓዙት ላይም እርምጃ በመውሰድ ሥራውን የማስተካከል ተልዕኮውን መወጣቱን አስታውቀዋል። ከነዚህ ውስጥም የተፈጥሮ ጋዝ ልማት ላይ የተሰማራው ፖሊ ጂሲኤል የተባለ ኩባንያ፣የወርቅ ምርት ፈቃድ የወሰደው ኬፊ ሜኔራልስ(ቱሉ ካፒ)፣የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አመልክተዋል።
ፓሊ ጂሲኤል አራት የፍለጋ አንድ የልማትና ምርት ፈቃድ እንዳለው ጠቅሰው፣ ኩባንያው ፈቃድ ወስዶ በሠራባቸው 9 ዓመታት የሚጠበቅበትን ሥራ አለማከናወኑ በግምገማ መረጋገጡን አስታውቀዋል። በዚህም ሕዝብና መንግሥት ከፍተኛ ተስፋ የጣለበትን የተፈጥሮ ጋዝ ልማት በተያዘለት ጊዜ እውን እንዳይሆን እንቅፋት መፍጠሩን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፣ ኩባንያው ያለበትን የፋይናንስና የቴክኒክ አቅም ውስንነት እስከ በጀት ዓመቱ ማጠናቀቂያ ድረስ ካላሟላ ስምምነቱ የሚቋረጥ ስለመሆኑ የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጠው ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ በአፋር ክልል ዳሎል የፖታሽ ማዕድን ለማልማት ሚራክል ያራ ዳሎል እና ሰርከም ሚኒራልስ የተባሉ ሶስት ኩባንያዎች የሥራ ፈቃድ ቢወስዱም፣ በመሠረተ ልማት አለመሟላት ሥራቸውን እያከናወኑ አለመሆናቸውንም ለምክር ቤቱ ገልጸዋል። እንደ መንገድና መብራት ያሉ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ከሚኒስቴሩ አቅም በላይ መሆኑን ጠቅሰው የምክር ቤቱን እገዛ ጠይቀዋል።
የሚኒስቴሩን ሪፖርት ያደመጡት የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አንስተዋል። ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከልም በግንባታው ዘርፍ በተለይም የግንባታ ግብዓቶችን መጠንና ሥርጭትን ለመጨመር ስለተሠሩ ሥራዎች፣ብዙ ኢንቨስትመንትና የገንዘብ አቅም የማይጠይቁ በቀላሉ ማምረት በሚቻልባቸው እንደ አሸዋ ያሉ የማዕድን ግብአቶች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ንረት ከምን የመነጨ ነው ሲሉ ጠይቀዋል።
የሃገር ውስጥ የብረታብረት ኢንዱስትሪ ልማት በጣም ደካማና ኢኮኖሚውን የማይደግፍ ሆኖ ስለመቆየቱና ያለውን የብረት ማዕድን ሀብት በተደራጀና በተቀናጀ ለመጠቀም እየተሠራ ስላለው ሥራ፣የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም ከ58 በመቶ በላይ ያለመብለጡና የዋጋ ንረትን የሚያስከትሉ ሰው ሠራሽ ችግሮች የመኖራቸው ጉዳይ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዴት እየታዩ መሆናቸውን የተመለከቱ ጥያቄዎችም ቀርበዋል፡፣ማዕድን ፍለጋ ላይ ለሚሠማሩ ኩባንያዎች ፍቃድ ከመሰጡ በፊት የመሥራት አቅማቸውን ለመለካት የተቀመጠው መስፈርት ምን ያህል የተጠና ነው የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
ሚኒስትሩም ጥያቄዎቹንና አስተያየቶቹን ተገቢነት ያላቸው ሲሉ ገልጸው፣ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። አብዛኞቹን አስተያየቶችንም ሚኒስቴሩ በግብዓትነት ወስዶ እንደሚሠራባቸው አስታውቀው፣ የምክር ቤቱንም ድጋፍ የሚጠይቁ፣በፖሊሲና በአዋጅ የሚፈቱ ጥያቄዎም እንዳሉ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ምክር ቤቱ ቢገነዘበው ባሏቸው ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ሃገር ውስጥ ያለው የድንጋይ ከሰል ጥራት የለውም በሚል ከውጭ እንዲገባ ግፊት ይደረግ ነበር። በተግባር ሲረጋገጥ ግን የሃገር ውስጥ የከሰል ድንጋይ ከውጭ ከሚገባው የድንጋይ ከሰል የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ ሆኖ አልተገኘም። በሚሊዮን በሚቆጠር ዶላር ወጭ እየወጣ ወደ ሃገር ውስጥ እንዲገባ ሲደረግ የነበረው አላግባብ ነው። ይሄን መስመር የማስያዝ ሥራ እየተሠራ ነው።
ብረትን በተመለከተም እንደተናገሩት፤ በሃገር ውስጥ 18 የብረት ፋብሪካዎች ይገኛሉ። ፋበሪካዎቹ የኢትዮጵያን ማዕድን ፈልገውና አምርተው እንዲያቀርቡ በሚል አይደለም የተገነቡት። ከውጭ የሚገቡ ብረቶች ላይ አነስተኛ ነገሮች በመጨመር ነው ለገበያ ሲያቀርቡ የቆዩት። ‹‹ሁሉም ነገር ከውጭ ይገባል። የሃገራችንን ሀብት እንዳንጠቀም ነበር ሲደረግ የቆየው።
ትርክቶቻችን በተቀየሩ ቁጥር ሃገራዊ ሀብቶቻችንን የምናይበት አይናችን ሲከፈት ችግሮች ይወገዳሉ›› ሲሉም ተናግረዋል። በአጠቃላይ ዘርፉ ሃገራዊ ምርት ላይ ባለመድረሱ ብዙ ብዥታዎች እንደሚኖሩም ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ እስካሁን የደረሰባቸውን የማዕድን ሀብቶች ብቻ አዲስ ባቋቋመው የማዕድን ጋለሪ ለማስተዋወቅ ዝግጁ መሆኑንም አስታውቀዋል። ጊዜ የሚወስዱ የማዕድን ፍለጋና ልማት ሥራዎች እንዳሉም ጠቅሰው፣ ፀጋዎች መኖራቸውን ግን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2014