አምዳችን “አገርኛ” እንደ መሆኑ መጠን ትኩረታችንም አገር በቀል ጉዳዮች ላይ አድርገናል። ለዚህም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (መያዶች)ን መቃኘት የዛሬው ርእሰ ጉዳያችን ይሆናል። በተለይም፣ ችግሮቻችንን በራሳችን አቅምና ነባር እውቀት ከመፍታት አኳያ ለማብራራት ጥረት ይደረጋል።
በሀገራችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አሉ። በተለይም፣ መሰረታቸው አውሮፓና አሜሪካ የሆኑ መያዶች ቁጥር ቀላል አይደለም። በተለይ ወደ ደቡብ የአገራችን ክፍል ሲኬድ የሚታየው የመያዶች ቁጥር የጉድ የሚያሰኝ ነው። ይሁን እንጂ፣ የተሰራው ስራ ሲታይ ደግሞ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ወይም ካገኘነው ያጣነው ይበልጣል ያሰኛል።
እነዚህን መሰል ችግሮች ስንመለከት መሰረታቸው አገር ውስጥ የሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቢበዙ፤ መብዛት ብቻም ሳይሆን ቢጠናከሩና በየዘርፉ ቢሰማሩ በከፍተኛ ደረጃ ለችግሮቻችን መፍትሄዎችን ያመጣሉ ተብሎ ይታሰባል። ይታሰባል ብቻም ሳይሆን ይጠበቃልና አዋጭነታቸው ከዚህ በመለስ የሚባል አይደለም።
ይህን፣ የአገር በቀል ተቋማት (መያዶቻችንን) አገራዊ ፋይዳ በተመለከተ ከዚህ በፊት በዚሁ አምድ ላይ እያንዳንዳቸውን በተናጠል በመውሰድ አላማ፣ ተግባርና ኃላፊነታቸውን፤ እንዲሁም እስከ ዛሬ ያከናወኗቸውን ሰብአዊ ተግባራት ለመፈተሽ ችለናል። የተሻለ አገልግሎት ያስመዘገቡትን የበለጠ እንዲሰሩ፤ ደከም ያሉትም እንዲጠናክሩ፤ አዳዲሶችም ወደ “መድረኩ” እንዲመጡ የሚቻለውን ጥረት ሁሉ ስናደርግ ቆይተናል። ዛሬም እንደ አጠቃላይ በመውሰድ የአገር በቀል መያዶችን አደረጃጀት፣ አላማ አፈፃፀማቸውን እያነሳን የምንነጋገር ሲሆን፤ ይህም ካሉት ጋር ከመተዋወቅም ባለፈ ወደፊት ሊፈጠሩ፤ ሊመጡ የሚገባቸውንም ከወዲሁ በመቀስቀስ ስሜት ሰጪ መልእክት ለማስተላለፍ ነው።
እዚህ ላይ አንድ አብይ ጉዳይ አስታውሶ ማለፍ ተገቢ ይሆናል። ይህ ተገቢ ጉዳይ አገር በ“አገር በቀል መያድ” እና “አገር በቀል ያልሆነ መያድ” መካከል ምን ልዩነት አለ፣ ለምንስ ሁለትን ከፍሎ ማየት አስፈለገ? የሚለው ሊሆን ቢችል፤ መልሱ ብዙም አስቸጋሪ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የመጀመሪያው መልስ የሚሆነው “ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ” እንዲሉ፤ ወይም፣ በተደጋጋሚ ሲነገር እንደሚሰማው፤ በአህጉሪቱ መሪዎችም ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ የሚታየው “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለው ሲሆን፤ ሌላውና ዋናው መልስ ግን በውጭ የእርዳታ ድርጅት ስቃይን ከማየት፣ ጓዳ ጎድጓዳውን ለእነሱ አስረክቦ እግር ከወርች ከመታሰር፣ ባልታሰበና ባልተፈለገ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ገብቶ ከመተላለቅ (በተለይ እነሱ “ሶስተኛው አለም” በሚሉት በአፍሪካ) … ያመለጠ አገር አለመኖሩና በጠባቂነት ስነልቦና ተቀፍድዶ መያዙ ነው። አሁን፣ ወደ ተነሳንበት፣ ወደ አገር ውስጥ መያዶች እንመለስ።
በለጋ ወጣቶች ፒያሳ አካባቢ የተቋቋመውና በእውነት ለተቸገሩ ፈጥኖ ደራሽ የሆነው “ደግ ፒያሳ” ኑሮዋ በዩናይትድ ኪንግደም፣ ኤደንብራ ከተማ ያደረገችው፤
‹‹ፀሐይ ጎልጎታ የህብረተሰብ ድርጅት›› የሚል በጎ አድራጎት ተቋም ለማቋቋም ያሰበችው፣ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት የሆነችው የአርባ ምንጯ ፀሐይ አካሉ፣ በተለይ ለአረጋውያን፣ እናቶች፣ ሴቶች፣ ህፃናትና ለማረሚያ ቤት ታራሚዎች እያደረገች ያለችው ድጋፍ የሚበረታታና ሌሎችም ሊከተሉት የሚገባ አርአያነት ያለው ተግባር ሲሆን፤ በየጎዳናው የወደቁ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማንን በማንሳትና በመንከባከብ በገንዘብ ሊተመን የማይችል ትልቅ ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኙትን፤ እነ ሜቄዶንያ፣ ሙዳይ፣ ጌርጌሲኖንና ሌሎች የበጎ አድራጎት ድርጅቶችንም ከዚሁ ጋር አያይዞ በአርአያነት መጥቀስ ይገባል።
ይህ አርአያነት ያለው የሀገር በቀል መያዶች ተግባር፣ በተለይም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ አገራችን መግባትን ተከትሎ በጉልህ ታይቷልና እንዳይዳከም፤ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ተደራሽነቱንም እንዲያሰፋ አጠቃላይ የህዝብና መንግሥት ድጋፍ ያስፈልገዋል። ያነጋገርናቸው የ“ደጉ ፒያሳ” ወጣት አመራሮችም ያሉት ይህንኑ ነው፤ “የበለጠ እንድንሰራ፤ ተጠናክረን እንድንቀጥል የመንግሥት ድጋፍ ያስፈልገናል።”
ማህበራዊ “ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ፣ በዚህ በጎ ተግባር ላይ ተሳትፈው የአካባቢያቸውን አቅመ ደካማና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን እየረዱ ካሉ፤ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ፣ መሰረታቸው ኢትዮጵያዊ (አገር በቀል) የሆነ በጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል አንዱ ‹‹የላምበረት ልጆች ለላምበረት ነዋሪዎች›› በሚል መርህ የተመሰረተው “የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ የበጎ አድራጎት ድርጅት” ነው።
አቶ ደጉ መኮንን ‹‹የላምበረት ልጆች ለላምበረት ነዋሪዎች›› የሚለውን መርህ የሚያራምደው የ“የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ በጎ አድራጎት ድርጅት” ዋና ስራ አስኪያጅ ነው። አቶ ደጉ እንደገለጸው፤ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ከመመስረቱ በፊት የላምበረትና አካባቢው ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት አቅመ ደካማና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን አረጋውያን ይረዱ ነበር።
ይሁንና በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ በተከሰተ ወቅት የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ በጎ አድራጎት ድርጅት በሚል ህጋዊ ሰውነት ይዞ በሰባ አባላት ተመስርቷል። ድርጅቱ የተቋቋመበት ዋነኛ አላማም በተለያዩ ምክንያቶች ታመው አልጋ ላይ የቀሩ፣ አቅመ ደካሞችንና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የላምበረትና አካባቢውን ሰዎች ለመርዳት ነበር።
ድርጅቱ እንደተመሰረተም በላምበረትና አካባቢው የሚኖሩና በውጭ ኑሯቸውን ያደረጉ የላምበረት ተወላጆች ጋር በመተባበር በአካባቢው ላይ ረጅም ጊዜ የኖሩ፣ ሰው ተጠግተው የሚኖሩና አቅመ ደካማ የሆኑ ሰዎችን በገንዘብና በቁሳቁስ መርዳት ጀመረ። በተለይ ደግሞ ወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ የተከሰተበት ጊዜ እንደ መሆኑ ድርጅቱ አባላቱ ገንዘብ እንዲያዋጡ በማድረግና በውጭ ሀገራት ያሉትም የአካባቢው ተወላጆች ገንዘብ እንዲልኩ በማድረግ አቅመ ደካማ ለሆኑና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ አድርጓል ። የበጎ አድራጎት ተግባራቸው ዝርዝሩ ብዙ ነው።
የዚህ ፅሁፍ ዋና አላማ አገር በቀል መያዶችን በብዛት ማፍራት የሚቻልበትና ከውጭ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች መላቀቅ ወይም ነፃ መውጣት የሚገባ መሆኑን ማሳሰብ እንደ መሆኑ መጠን የ“የላምበረትና አካባቢው ለወገን ደራሽ በጎ አድራጎት ድርጅት”ን ልምድ ይካፈሉታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ወደ ሌላው አገር በቀል ማህበረ-ባህላዊ (በተለይም ሃይማኖታዊ) ወደ ሆነውና ወደ ተቋምነት ሊቀየር ስለሚገባው አገራዊ እሴት እንሸጋገር።
በኢትዮጵያ ቂምና በቀልን አራግፎ እርቅና ሰላም የሚወርድበት ቱባ ባህላዊ እሴት አለ፤ ሀገር በቀል እውቀት አለ። ሁሉም ብሄሮች እርስ በእርሳቸውና ከሌላው ማህበረሰብ ጋር በሚፈጥሯቸው ጊዜያዊ ግጭቶች ባህላዊ የእርቅና የሽምግልና ሥርዓቶችን እያከናወኑ አብሮነታቸውን ሲያስቀጥሉ ኖረዋል። ይህንን ደግሞ የትም ቢሄዱ ያገኙታል፣ የኦሮሚያውን ገዳ፣ የሃላባ ቁሊቶውን ሴራ … ጨምሮ ማለት ነው። ሌሎችንም እንደዛው።
ኢትዮጵያ ስለዲሞክራሲ፣ ስለመልካም አስተዳደር፣ ስለእርቅና ሰላም ከየትኛውም ሀገር ሳትበደር ጥቅም ላይ ልታውላቸው የሚገቡ ጥሩ ጥሩ ተሞክሮዎችን ማግኘት የምትችልባቸው ባህላዊ እሴቶች ያሏት የመሆኑን ያህል፤ እነዚህን ሁሉ በተደራጀ መልኩ ስትጠቀምባቸው አትታይም። ከእነዚህና ሌሎች ቱባ ባህላዊ እሴቶች መካከል ደግሞ አንዱ የጋሞ አባቶች የሽምግልና ሥርዓት /ዱቡሻ/ እንደ ሆነ ይታውቃል። ይህ በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ ሊቀጥል ይገባዋል።
”በጋሞ ምድር ጠብና አለማግባባት፤ ቂምና ቁርሾ የሚወገዱባቸው ጠንካራ ባህላዊ እሴቶች አሉ። የጋሞ ብሄረሰቦች ችግሮችን በባህላዊ መንገድ የመፍታት የቆየ ልምዳቸውን ጥቅም ላይ እያዋሉ ማህበራዊ መስተጋብራቸውን አጠናክረው የሚኖሩ ህዝቦች ናቸው። ልጆቻቸው ከማህበረሰቡ እሴቶች እንዳያፈነግጡ በአባቶች ምክርና ተግሳጽ ተኮትኩተው ስለሚያድጉ ለባህላዊ እሴቶች ተገዢዎች ናቸው፤ ታላላቆቻቸውንና አባቶቻቸውን ያከብራሉ፤ የሽማግሌዎችን ቃል ያደምጣሉ። ” የሚለውንም የተረጋገጠና በዛ በቀውጢ ወቅት (የጋሞ አባቶች እሳት ለብሶ፣ እሳት ጎርሶ ህንፃዎችን ለማጋየት የመጣውን የተቃውሞ ሀይል ቄጤማ ይዘው በመንበርከክ እንዴት እንደመለሱት) በአይናችን የተመለከትነው እውነት እዚህ ሊጠቀስ ይገባዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ በወቅቱ በጋሞ የሰላምና ሽምግልና አባቶች ስም አንድ የሰላም ተቋም ይገነባል ማለታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም፣ ከተደረገ ማለት ነው፣ እዚህ በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ … እያልን ያለነውን ሃሳብ የሚያጠናክር ነው።
በቅርቡ በሀገራችን ተከስቶ የነበረውን አስቸጋሪና መደገም የሌለበትን አፍራሽና በርካታ ቤተ-እምነቶችን ዶጋ አመድ ያደረገ፤ የበርካታ ንፁሀንን ሕይወት የቀጠፈ ተግባር አስመልክተው፤ “ለመሆኑ ሃይማኖተኛ ሆኖ በሌላ ሃይማኖት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን መፈጸም ምን ያህል ከሃይማኖቶች አስተምህሮ ጋር አብሮ ይሄዳል?” በሚል ማእከላዊ ጥያቄ (ጭብጥ) ዙሪያ ሃሳባቸውን ያካፈሉ የሁለት ሃይማኖቶች (ክርስትና (ኦርቶዶክስ ተዋህዶ) እና እስልምና) አባቶች (መጋቤ ካህናት አባ ሀብተጊዮርጊስ አሥራት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የገዳማት መምሪያ ዋና ኃላፊ፤ እንዲሁም፣ ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ፣ አራዳ ክፍለ ከታማ፣ ወረዳ ሁለት የሆነው ሼህ ሙሐመድ አሊ ሙሳ እንዳሉት፤ ድርጊቱ በማንኛውም መስፈርት የሚደገፍ አይደለም።
እዚህ ላይ ድርጊቱ በሃይማኖት በኩል የማይደገፍ መሆኑን ከመግለፃቸው ባለፈ ሁለቱም አባቶች (ሁለቱም ባልተገናኙበትና ምንም በማይተዋወቁበት ሁኔታ) የሰጡት ማብራሪያ በአንድ ምሳሌ (ልዩነታቸውንና አንድነታቸውን የገለጹበት መንገድ) የተደገፈ መሆኑ ሲሆን፤ ይህም ሙስሊምና ክርስቲያን በዋና ሃይማታዊ ጉዳዮቻቸው ቢለያዩም በብዙ ነገሮች ይመሳሰላሉ። በአንድ ወቅት ሁለቱም የየራሳቸውን ከብት ባርከው ካረዱ በኋላ በተለያየ ክር እያሠሩ በአንድ እቃ ይቀቅሉታል። ከዚያም ሲበስል አውጥተው የየራሳቸውን ይመገባሉ። እንግዲህ ስጋው አንድ ላይ ሲቀቀል በመረቁ መነካካቱ አይቀርም፤ የሁለቱም ሃይማኖት ተከታዮች በማህበራዊ ህይወታቸው ብዙ የሚጋሯቸው፤ የጋራ የሆኑ እሴቶች አሏቸው። በበርካታ ጉዳዮች የተሳሰሩ ስለ መሆናቸው ጥሩና ወቅታዊ ማሳያ ሲሆን፤ ልዩነትንም አንድነትንም አክብሮ አብሮ መኖር እንደሚቻል በምሳሌ ያረጋገጡበት ቃለ መጠይቅ ነበር።
ከዚህ ምሳሌ በተጨማሪ፣ አሁን ያለውም ሆነ ወደ ፊት የሚመጣው ትውልድ የቀደሙት አባቶቹ እንዴት ተስማምተውና ተከባብረው እንደኖሩና እንደሚኖሩ በሚገባ መረዳት እና እሱም ያንኑ የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል ያለበት መሆኑንም ነው የሃይማኖት አባቶቹ በመልእክታቸው የተናገሩት። “የሃይማኖት አባቶች ወጣቶችን እየሰበሰቡ ማስተማርና መምክር እንደ ቀዳሚው ዘመን ተከባብረንና ተመካክረን እንድናድር ማድረግ አለባቸው። መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት (ተቋማት) ችግር ከመድረሱ በፊት ፈጥኖ በመድረስ አጥፊዎችን እየተከታተሉ እርምጃ መውሰድ (ለህግ ማቅረብ) ይኖርባቸዋል። ” የሚለውም መልእክታቸው ነበር።
በአጠቃላይ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማለት ይቻላል። ዋናውና መሰረታዊው ጉዳይ ግን እጅ እየዘረጉ፣ አላማቸው ምን እንደሆነ እንኳን በውል ሳይታወቅ፣ የውጭ እርዳታ ድርጅቶችን መቀበል መብቃት አለበት። እንደነ ቻይና ራሳችንን ችለን ለሌሎችም የምንተርፍበት መንገድ ከወዲሁ ሊመቻች ይገባል። የበርካታ አገር በቀል እውቀቶች፣ እሴቶች፣ ትውፊቶች … (ለዛውም “የሚዳሰሱ” እና “የማይዳሰሱ” የሚሉትን ሳናካትት) ባለቤቶች ነንና እነሱን ወደ ተቋማት በመቀየር ከራሳችን ሀብት ራሳችን ተጠቃሚ እንሁን፤ ለዚህ ደግሞ የጋራ ግንዛቤ፣ የጋራ ራእይ፣ የጋራ ግብ … ያስፈልጋል የሚለው ነውና በዚሁ እንሰናበታለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2014