በዓለም የስፖርት ታሪክ እጅግ ውድ ከሆኑ ዋንጫዎች መካከል የዓለም ዋንጫን የሚስተካከለው የለም። የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋ በባለቤትነት በሚያካሂደው በዚህ ውድድር አሸናፊ ለሚሆነው ብሔራዊ ቡድን የሚበረከተው ይህ ታላቅ ዋንጫ፤ 20 ሚሊዮን ዶላር ያወጣል። እአአ በ1974 የተዋወቀው ዋንጫው 36ነጥብ 8ሳንቲ ሜትር ርዝማኔ ሲኖረው 6ነጥብ 1 ኪሎ ግራም ይመዝናል። ከ18 ካራት ወርቅ የተሰራውን ዋንጫ ማንሳትም የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሁልጊዜም ህልም ብቻም ሳይሆን የበርካታ ሃገራት ምኞት ነው።
ይህን ዋንጫ ለማንሳትም ይሁን ለመሳም የታደሉት ግን እንደ አገርም ጥቂቶች ናቸው። ይሁን እንጂ የዓለም ዋንጫ በአራት ዓመት አንዴ በመጣ ቁጥር ዋንጫው በመላው ዓለም በተመረጡ ሃገራት እየተዘዋወረ ለእይታ ይበቃል። ተወዳጅ በሆነው የእግር ኳስ ስፖርት የዓለም ዋንጫን ያህል ትልቅ ክብር ያለው ውድድር የለም። ለዚህም ሩሲያ ያዘጋጀችው እአአ የ2018ቱ የዓለም ዋንጫ ከዓለም ግማሽ የሚሆነው ሕዝብ (3ነጥብ5 ቢሊየን) እንደተመለከተው መረጃዎች ምስክር ናቸው። ይህ ቁጥር የሚያሳየው እአአ በ2014 ብራዚል ካስተናገደችው የዓለም ዋንጫ በ9 ከመቶ የበለጠ እንደሆነ ነው። 22ኛው የዓለም ዋንጫ ደግሞ በዓረብ ሃገራት ታሪክ በኳታር ምድር ሊካሄድ የወራት እድሜ ብቻ ይቀረዋል። በመሆኑም ስፖርት ወዳዱ ሕዝብ በጉጉት እየጠበቀው ከሚገኘው ውድድር አስቀድሞ ዋንጫው በየሃገራቱ በመዘዋወር ለደጋፊዎች እይታ ይበቃል።
ዓለም ዋንጫው በ51 ሃገራት የሚዘዋወር ሲሆን፤ በአፍሪካ ዘጠኝ ሃገራት መዳረሻውን ያደርጋል። ከእነዚህ ሃገራት መካከል አምስቱ በኳታሩ ዓለም ዋንጫ ተሳታፊ የሆኑት (ሴኔጋል፣ ሞሮኮ፣ ጋና፣ ካሜሮን እና ቱኒዚያ) ናቸው። ኢትዮጵያን ጨምሮ አራቱ ሃገራት ደግሞ በውድድሩ ተካፋይ የማይሆኑ ነገር ግን ለዋንጫው መዳረሻ የተመረጡ ሃገራት ናቸው። በዚህም ኢትዮጵያ በአህጉሩ ለዋንጫው በቀዳሚነት አቀባበል ያደረገች ሃገር ሆናለች። የዓለም ዋንጫው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን፤ የሁለት ቀናት ቆይታውም ትናንት በመስቀል አደባባይ ለሕዝብ እይታ ይፋ ሲደረግ ጀምሯል። በዚህ መርሐ ግብር ላይም ከትናንት በስቲያ በቅድሚያ በብሔራዊ ቤተመንግሥት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አቀባበል አድርገውለታል።
ፕሬዚዳንቷ ይህንን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር “እግር ኳስ ሰዎችን በአንድ ላይ በማምጣት፣ አንድ በማድረግ፣ ለአንድ ዓላማ በማሠራት፣ የጨዋታውን ሕግ በማስከበር፣ እርስ በርስ በማከባበር፣ በአንድ ሜዳ ላይ በመጫወት እጅግ ጠንካራ ፋይዳ ያለው መሣሪያ ነው” ሲሉ ገልፀዋል። በተጨማሪም ‹‹ይህንን ዋንጫ በእጄ ለመያዝ ያገኘሁት እድል ለመላው ኢትዮጵያውያን የተሰጠ እድል ነው›› ብለዋል።
በትናንትናው ዕለት በመስቀል አደባባይ የእግር ኳስ ቤተሰቡ ከዋንጫው ጋር ፎቶ የመነሳት ዕድል አግኝቷል። ዋንጫውን በአምባሳደርነት ይዘውት የሚመጡት በውድድሩ ስኬታማ ታሪክ መጻፍ የቻሉ ተጫዋቾች ሲሆኑ፤ ብራዚላዊው የቀድሞ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ጁሊያኖ ቤሌቲ ከዋንጫው ጋር አዲስ አበባ ተገኝቷል። ተጫዋቹ ለአምስት ጊዜያት የዓለም ዋንጫን በማንሳት ቀዳሚ የሆነችው የእግር ኳስ ሃገር ብራዚል የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን አባል ሲሆን፤ ከቡድኑ ጋርም እአአ በ2002 ዋንጫ ማንሳት ችሏል። የቀድሞ የቪላሪያል፣ ባርሴሎና እና ቼልሲ ተጫዋች የሆነው ቤሌቲ፤ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ደቡብ ኮሪያና ጃፓን በጋራ ያዘጋጁትን የዓለም ዋንጫ ማሳካት ችሏል።
ተጫዋቹ አዲስ አበባ ተገኝቶ ከትናንት በስቲያ በሸራተን አዲስ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅትም፤ የዓለም ዋንጫን ያነሳበት ወቅት ህልሙ እውን የሆነበት እንደነበር አስታውሷል። ዋንጫውን ለመውሰድ ጠንክሮ መሥራት፣ ለሙያው ታማኝ መሆንና ስነምግባርን መላበስ፣ ህልምን መከተል፣ በየዕለቱ አዲስ ነገርን ለመማር መዘጋጀትና ጥረት ማድረግ እንዲሁም ውጤት ቢገኝም ሆነ ቢጠፋ በአግባቡ መቀበል መቻል አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁሟል።
የዓለምን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው ፊፋ ውድድሩን ሲያዘጋጅ ለረጅም ዓመታት በስፖንሰርነት አጋር የሆነው ኮካ ኮላ የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካ ደግሞ ዋንጫው በመላው ዓለም የሚኖረውን የጉብኝት መርሐ ግብር ያሳልጣል። ኮካ ኮላ እአአ ከ1976 ጀምሮ ከፊፋ ጋር በአጋርነት እየሠራ ያለ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ60 ዓመታት በላይ ቆይታ አለው። ዘንድሮም ዓለም ዋንጫ የሚካሄድበት ዓመት መሆኑን ተከትሎ ‹‹ማመን የተዓምር መሠረት ነው›› በሚል መሪ ሃሳብ የዋንጫውን ጉብኝት ያካሂዳል። ዓላማውም በመላው ዓለም የሚገኙ ደጋፊዎች ህልም የሆነውን ዋንጫው በቅርበት እንዲመለከቱት ከማድረግ ባለፈ፤ በእግር ኳስ ስፖርት ውስጥ ያሉ ወጣቶችን ማነሳሳት ነው። የዓለም ዋንጫ ጉብኝትም መጨረሻውን የውድድሩ አስተናጋጅ በሆነችው ኳታር ያደርጋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2014