የዛሬዋ እንግዳችን ከስልሳ ዓመት በፊት አካባቢ በትግራይ ክልል በምትገኝ አንዲት ትንሽ የገጠር ቀበሌ ተወለዱ። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትግራይ ከተከታተሉ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አቀኑ። ከአራት ዓመታት የዩኒቨርሲቲ ቆይታ በኋላ በነበራቸው ከፍተኛ ውጤት በዩኒቨርሲቲው እንዲቀሩ ተደረገ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፋርማሲ ትምህርት ክፍል (እስኩል ኦፍ ፋርማሲ) ውስጥ ለዘጠኝ ዓመታት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ ነፃ የትምህርት ዕድል አግኝተው ወደ አሜሪካ ሃገር ሄዱ።
በአሜሪካን ሃገር ቆይታቸው ፖስት ዶክተሪያል፤ ፋርማስቲካል ኢንዱስትሪ ላይ ለ26 ዓመታት ሲሠሩ ከቆዩ በኋላ ልጆቻቸው የእናታቸውን እርዳታ የሚፈልጉበት ጊዜ ስላበቃ ባለኝ እውቀት ሃገርን ላገልገል ብለው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ ።
በ2012 ዓ.ም ወደ ሃገራቸው የተመለሱት ፕሮፌሰሯ መቀሌ ዩኒቨርስቲ ለአንድ አመት ከሁለት ወር ገደማ አስተማሩ፡፡ ሕወሓት መራሹ ጦርነት ከፍቶም እንኳን ለሁለት ወራት እዛው እንደነበሩ ይናገራሉ። የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ፕሮፈሰር ሐረገወይን አሰፋ ሴት ልጃቸው ሄርሜላ አረጋዊ በይበቃል (NO MORE) እንቅስቃሴ አስጀማሪነት የምትታወቅ ናት።
“…. ልጆቼን ሳሳድግ አንድም ቀን ፖለቲካ አውርቼ አላውቅም፤ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ ስላደጉ ከሁሉም ዓለም ክፍሎች ከመጡ ወጣቶች ጋር የመገናኘት እድሉ ነበራቸው፤ ነገር ግን አሁን ይህ ጦርነት ሲመጣ የሁለቱም አመለካከት በተለያየ ፅንፍ ሄደ ፤ ይህ የአመለካከት ምርጫቸው ግን የራሳቸው ነው”ይላሉ።
ልጃቸው ሄርሜላም ስለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠቷና ከእውነቱ ጋር በመቆሟ የተነሳ ሥራዋን እስከማጣት ደርሳለች። ስለሳቸው ይሄንን ካልን ዘንዳ በቆይታችን ወዳካፈሉን ቁም ነገር እንመለስ።
አዲስ ዘመን፦ በጦርነቱ ወቅት መቀሌ ነበርኩ ብለውናል እና በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ እንዴት ያስታውሱታል?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ ጦርነቱ ሳይጀመር አዲስ አበባ ለፕሮፌሰሮች የተዘጋጀ ውይይት ነበር። ጦርነቱ የተጀመረ ዕለት በረራ ስለነበር ለስብሰባው የሚቀርብ ጽሑፍ በማዘጋጀት አምሽቼ ስለነበር እንቅልፍ ጥሎኝ ምንም ነገር አልሰማሁም። ጠዋት ስነሳ መብራት ጠፍቷል። ስልኬን ስሞክርም አይሠራም። ወጣ ብዬ ጎረቤት ስጠይቅ ጦርነት እንደተጀመረ ሰማሁ።
አዲስ ዘመን፦ ጦርነቱ ጀመረ፤ እርስዎ ደግሞ በወቅቱ ቢሮዎ አይደር ሆስፒታል ውስጥ ነበርና እንደው የነበረው ነገር የሕዝቡ ጉዳት በተለይም በሴት እህቶቻችን ላይ የደረሰውን ነገር ካዩትም ከሰሙትም ተነስተው ምን ይላሉ?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ ጦርነት እንግዲህ ቀይ ምንጣፍ የሚያስነጥፍ ወይም ምቹ ነገሮች ያሉት አይደለም፡፡ ከዛ በተጨማሪም ሰዎችን ሳይመርጥ ሁሉንም ችግር ላይ የሚጥል ነው፡፡ ነገር ግን ይህኛው ጦርነት ሲደረግ የተባለውን ያህል ሴቶች እየተደፈሩ አልነበረም፤ እንደውም ከጦርነቱ በፊት በርካታ ሴቶች ይደፈሩ ነበር፤ በሽሬ አንድ ፖሊስ 50 ሴቶችን ደፍሮ መነጋገሪያም ሆኖ ነበር፤ ነገር ግን ይህን ሲሠራ የቆየውን አፀያፊ ተግባር አንድም ቀን እርምጃ ሳይወሰድ በጦርነት ወቅት እንዲህ ሆነ ብሎ የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ እጅግ በጣም ከባድ ነው። በኢኮኖሚ ደከም ያለ አባወራ ሚስቱ ቆንጆ ከሆነች የአካባቢው ባለስልጣን ሊቀማው ይችላል፤ ማንም ጠያቂ አልነበረውም። ስለዚህ በጦርነቱ ጊዜ እዛ ያሉት ራሳቸው ጥቃቱን ላለማድረሳቸው ምን ማረጋገጫ አለ። እንደዚህ አይነት ነውርን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ ማኅበረሰቡን አለማክበር ነው።
ጦርነት በተፈጥሮው የሚያመጣው ችግር እንዳለ ሆኖ መከላከያ ሠራዊት ወደ ክልሉ ሲገባ እባካችሁ እኛ ወንድሞቻችሁ ነን፤ አንድ ሕዝብ እንሁን የሚል ቅስቀሳ ከማድረግ በቀር የከፋ በደል አላየሁም፡፡ ከዛ በኋላ ግን ክፍተቱን ተጠቅሜ እኔም ወደ አዲስ አበባ ስለመጣሁ ስላለው ነገር ከወሬ በዘለለ ሰምቼ አላውቅም ።
አዲስ ዘመን፦ አሁን በምን ሥራ ላይ ነው የሚገኙት?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን ፦ አሁን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የውጭ ግንኙነት ፓርትነር ሺፕና ሪሰርች ግራንት አማካሪ ነኝ። ለረጅም ጊዜ ባካበትኩት ልምድ የሃገሬን ዩኒቨርሲቲ እያገለገልኩ እገኛለሁ።
አዲስ ዘመን፦ የሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በእርሶ እይታ እንዴት ይገልጹታል?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ በሃገራችን ያለው ተግዳሮት ቀላል አይደለም። ግን ተስፋ ደግሞ ይታያል። ለምሳሌ በርካታ ፓርኮች ተሠርተዋል። ይህ ማለት ሰው ለመዝናናት ቡና ቤት ከመሄድ እንደዚህ አይነት ቦታዎች እየሄደ ግዜ ያሳልፋል። የአኗኗርና የሥራ ባህል እየተቀየረ ይሄዳል የሚል ተስፋ አለኝ። አሁን የምንመለከታቸው ችግሮች ሃገር ይሄን ሁሉ ጦርነት እያደረገች ስለሆነ የመጣ ነው። ይህ ጦርነት እያለ ቀርቶ አሜሪካን ሃገር እኮ ነዳጅ በመጨመሩ ምክንያት ብቻ ኢኮኖሚው ላይ ጫና ሲፈጥር ይታያል። ይህ ጦርነት ሲያልቅ ግን ለለውጥ የተዘጋጀ ሁኔታ ስላለ ነገ ተስፋ ያለው ወቅታዊ ችግር ይታየኛል።
አዲስ ዘመን፦ ለእርስዎ የሃገር ፍቅር ስሜት እንዴት ይገለጻል፤ በተለይ ልጆች የሃገር ፍቅር ስሜት ይዘው እንዲያድጉ ከማድረግ አንጻር እርስዎ የነበረዎት ሚና ምን ይመስል ነበር?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ የአገር ፍቅር ስሜት ከሰብዓዊነት የሚመነጭ ነው። ሃገር ሃገር ብትሆንም፤ ምንም ቢሆን የሌላን ሃገር ሃገሬ ማለት ባይቻልም ከሃገር ፍቅር ስሜት በፊት ሰብዓዊነት ይቀድማል። እናት አንድ ጥሩ ነገር ስታይ ይሄን ለልጄ ብላ እንደምታስበው ሁሉ ሁሌም የተሻሉ ሀሳቦችን የተሻሉ ነገሮችን ስመለከት ለሃገሬ ማለት ልምዴ ነው። መጀመሪያ አሜሪካን አገር ስሄድ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሚሲሲፒ የሚባል አነስ ያለ የዩኒቨርሲቲ ከተማ ነበር። ያኔ ከየት ነሽ ሲሉኝ ከኢትዮጵያ የሚል መልስ ስሰጥ ለመሆኑ የሚበላ አላችሁ ይላሉ። በዚህ ግዜም ሃገር ተነስቶ አይመጣ ነገር እያልኩ እቆጫለሁ። ነገር ግን ሃገርን መውደድ ሰውን ከመውደድ ይጀምራል። ሄርሜላ ግን ለሃገሯ መቆም የጀመረችው ሁኔታዎችን ከመመልከት ነው።
በውጭ ሃገራት ያሉ ጋዜጠኞች ለአፍሪካ የተለየ ትርክት እንዳላቸው ትመለከታለች። መጀመሪያ በሲኤን ኤን በተመለከተችው ሐሰተኛ ዘገባ ተታላ የነበረች ሲሆን በስተመጨረሻ ግን ሁኔታዎችን ተገንዝባ ለሃገሯ ዋስ ጠበቃ ለመሆን ተነሳች።
ሄርሜላ ከባድ የሆነ የጋዜጠኝነት ሙያ ፍቅር ያላት፤ ለእውነት የመቆም ዝንባሌም ነበራት፤ በችሎታዋም ብቁ የተባለች ልጅ ናት፤ ያደገችው ምሁራን ባሉበት አካባቢ ነበር ፤ እኔ ባደኩበት ትግራይ ሴቶች ላይ የሚደርሰው የባህል ተፅእኖ ከባድ ስለነበር እኔ ባለፍኩት መንገድ ልጆቼ እንዳያልፉ ጥረት አድርጌያለሁ ። ልጆቼ በነፃነት እንዲያድጉ አገራቸውን ሕዝባቸውን እንዲወዱ ከምንም በላይ ደግሞ በዚህ ሁኔታ አገር አጣብቂኝ ውስጥ ስትገባ መፍትሔም ሆነው ብቅ እንዲሉ የተቻለኝን ሁሉ አድርጌያለሁ። በዚህም ተሳክቶልኛል ማለት እችላለሁ፡፡ ሔርሜላ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆና ነበር ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ ለመሆን ታልም የነበረው፤ ለጋዜጠኝነት ትምህርትም ዩኒቨርሲቲዎችን መምረጥ የጀመረችው ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ሳታጠናቅቅ ነበር።
በ2002 ዓ.ም በጋዜጠኝነት ከተመረቀች በኋላ አልጀዚራ አሜሪካ ውስጥ ሠርታለች፤ ሲቢሲ ውስጥ ፕሮዲውሰር ሆና አገልግላለች ፤ በተለያዩ ቦታዎች በተለያዩ ደረጃዎች ሠርታ ነበር። ሄርሜላ በጥልቀት ጉዳዩን ተመልክታ ባላት አቅም ድምፅ ለመሆን ስትነሳ ወንድሟ ብሩክ ደግሞ በዛኛው ፅንፍ ቆሞ ሆይ ሆይ እያለ ይገኛል። ሄርሜላ በዚህ አቋሟ ሥራዋን እስከማጣት ደርሳለች። ምን ፈተና ቢመጣ ግን ከሐቅ ፍንክች እንዳትል እመክራታለሁ፤ እሷም በሐቅ ስለተነሳች ይህን ሁሉ ንቅናቄ ለማስነሳት አልከበዳትም ።
ወንድሟ ብሩክም በጣም ጠንካራ ወጣትና በሕይወቱም ስኬታማ ነው። የኮምፒውተር ሳይንስ ምሩቅም ነው። ከላይ እንደነገርኩሽ ምንም አይነት የሃገራችንን ፖለቲካ ወሬ ሰምተው አያውቁም፤ አሜሪካ ያሉ የሕወሓት ደጋፊዎች ግን እንደሚፈልጉት ሊጠመዝዙት ችለዋል። እጅግ በጣም እየተጠቀሙበት ነው። ይህ ሲሆን ግን ምናለ ቀድሜ በደንብ ባስተማርኩት እያልኩ አስባለሁ። ፈጣሪ ግን ከሐቅ ጎን ስለሆነ መጨረሻው ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፦ የበቃ (NO MORE) እንቅስቃሴ በዓለም ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩ ይታወቃል፤ የዚህ ሃሳብ መነሻ ደግሞ ሄርሜላ ናትና በዚህ ላይ እርስዎ ያለዎት አስተያየት ምንድነው ?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ ሄርሜላ ሐቅን ይዛ ነው የምትሄደው። ፈጣሪ ሐቅን ስለሚደግፍ እነሱ ግፊታቸውን እስከመጨረሻው ሲያደርጉ እሷም ሐቅንና እውቀትን ይዛ ወደፊት እንድትቀድም ሆኗል። በተለያየ መንገድ ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርስባታል። ሴቶች ስለሆናችሁ መተንፈስ አትችሉም እስከማለት ተደርሷል፤ ሳንተነፍስ መቆየት ደግሞ በሕይወት እንዳንቆይ ያደርገናል። እኔ ዋሽቼ ልተኛ አልችልም፤ ልጄም ውሸት ዋሽታ መተኛት አትችልም፤ በዚህም እኮራባታለሁ።
አዲስ ዘመን፦ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን የውጭ ጫና ለመቀልበስ ምን መደረግ አለበት ይላሉ፤ ከዚህ አንጻር በተለይ የዲያስፖራው ሚና ምን መሆን አለበት?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ ዲያስፖራው ማኅበረሰብ ሁሉም ነገር ስለማይናገር ነው እንጂ በጣም እየሠሩ ነው ያሉት። ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በጋራ በመሆን የተለያዩ ውሳኔዎች እንዳይወስኑ እንቅስቃሴዎች እያደረጉ ነው። በአደባባይ ከሚታዩት በላይም ውስጥ ለውስጥ ሥራዎች ተጠናክረው እየተሠሩ ይገኛሉ። የአሜሪካ ምርጫም እየደረሰ ስለሆነ ውሳኔው የሚዘገይ ይመስለኛል። ይህ የኔ ግምት ነው። ሃገር እንዳትፈርስ ግን የሁላችንም የጋራ ትብብር በማድረግ ያሉ ችግሮችን ከሕዝቡ ጫንቃው ላይ ማንሳት ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ ሕወሓት በተደጋጋሚ የትግራይን ሕዝብን ከሕጻናት ጀምሮ እስከ አረጋውያን ድረስ በጦርነት በመማገድ ከፍተኛ ጥፋት እየፈፀመ ነው፤ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው ይላሉ፤ እውን ይህ ቡድን እንዲህ የሚያደርገው ለትግራይ ሕዝብ አስቦ ነው?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ ሕወሓት ሲባል ዛሬ የምንመለከታቸው ልጆች በ13 በ14 ዓመታቸው ተገፍተው ጥላቻን ተሞልተው የወጡ ናቸው። ሕወሓት ከ 40 ዓመታት በፊት የጀመረውን በጥላቻ የተሞላ የጦርነት ታሪክ ዛሬም እየቀጠለ ይገኛል። የሽብር ቡድኑ ይህን መጥፎ ታሪኩን እንደ እምነትና አምልኮ በመቁጠር የጥላቻ ትርክቱን በማስቀጠል ሕፃናትን በ 13 ዓመት እድሜያቸው መሣሪያ አሸክሞ ወደ ግንባር በመላክ ጦርነት እየቀሰቀሰ ነው። ይህ የሽብር ቡድኑን በጦርነት የማምለክ ባህልን የሚያሳይ ነው።
ጦርነት ሲደረግ የሚጨፈርበት ቦታ ትግራይ ብቻ ነው፤ ክልሉ በእናቶች ስም ጦርነት የሚሰየምበት፤ አንድ እናት ጀግና ለመባል አምስት ልጆቿን ገፍታ እንድትልክ የምትገደድበት በክልሉ ውስጥ ቡድኑ እንዳሻው የሚያደርግበት በመሆኑ ሴቶች መጠቀሚያ እንጂ እናትነታቸው እንኳን በተግባር የተገለጠበት አይደለም ።
በተለይ ክልሉ ከድሮም ጀምሮ በጦርነት ውስጥ ያለፈ በመሆኑ ጦርነትን እንደ ትልቅ ነገር ከዚያም ባለፈ እንደ አምልኮ የመቁጠር ሁኔታ አለ። ለልጅ ጥላቻን ማስተማር ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ከመሆኑም በላይ ሕፃናት ላይ ጥላቻን መዝራት በሂደት የትግራይን ሕዝብ የሚጎዳ በመሆኑ ከጦርነት ታሪክና ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር ማስተማር ያስፈልጋል ። ልጆችን ጥላቻ ሞልቶ ማሳደግ ትውልድ ላይ መፍረድ ነው።
ለትግራይ ጦርነት ባህል እንደሆነ፤ ጦርነት ሁሉንም ነገር እንደሚፈታ ማሰብ ጀግንነት በመሞት እንደሆነ የሚያስብ ኃይል ነው ያለው። ትግራይን ወደ ኋላ ያስቀረው እገሌ ነው በማለት ሌሎችን ተጠያቂ የማድረግ እሳቤ ጥላቻን ማብዛት ላይ ነው ያለው። በኅብረተሰብ ደረጃ ይህ ተመሳሳይነት ያለው አስተሳሰብ ተፈጥሯል።
አዲስ ዘመን፦ ይህ ጦርነት በትግራይ ጎረቤቶች ሁሉ ላይ እንደሚስፋፋ ይነገራልና ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሉት ሀሳብ ካለ ቢያካፍሉን?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ ጎረቤት ሃገራትንና ጎረቤት ክልሎችን መተንኮስ ከሕወሓት ባህሪ አንፃር የሚጠበቅ ነው። ከዚህ ቀደም አብሮ ከኖረው ሕዝብ ጋር የማይታረቅ ጉዳት ውስጥ አስገብተውን ነበር። በደንብ ጉዳት ሲያደርሱ ብዙ ደጋፊ የሚያገኙ ስለሚመስላቸው አይጎዱም ማለት አይቻልም። የኢትዮጵያ መንግሥትም እነሱን ለመመከት አያንስም። እነሱ በባህሪያቸው ጉሬላ ፋይተርስ የሚባሉ ዓይነት በመሆናቸው፤ በሽምቅ ውጊያ እየገቡ አይረብሹም ማለት ስለማይቻል በተቻለ መጠን ሁሉም በጋራ መከላከል ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ የትግራይ ሕዝብ ከዚህ የሽብር ቡድን ራሱን ለመከላከል ያልቻለው ለምንድነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ ከሃምሳ ዓመት በላይ የሚያውቃቸው እነሱን ነው፤ ሕወሓት የትግራይ ሕዝብ አካል እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። እምነታቸውን የሚወዱትን ያህል ቡድኑንም ይቀበሉታል። ያምኑታል፡፡ ማኅበረሰቡ ሕወሓት ትክክል ነው ብሎ የሚያምነውን ያህል የቡድኑ እርስ በእርሳቸው እንኳን የሚተማመኑ አይመስለኝም። ስህተታቸውን ስለሚያውቁት ሕዝቡ የሚያምናቸውን ያህል በራሳቸው አይተማመኑም ። ቀደም ሲል ከሕወሓት አመራሮች ጋር በቅርበት ስንነጋገርም የተገነዘብኩት ይሄንን ነው። የሕወሓት አባላት ለራሳቸው ከሚሰጡት ግምት በላይ ሕዝቡ ተቀብሏቸዋል።
ሕወሓትን ከትግራይ ሕዝብ ለመለየት ጊዜ የሚወስድ ይመስለኛል። አንዳንድ ጉዳዩ በጊዜ የገባቸው ያፈነገጡ ሰዎች ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጥለው ማየት የሚከብዳቸው አካላት ያሉ ሲሆን ይህ በስፋት ቢመጣ ለውጥ ሊመጣ ይችላል የሚል አመለካከት አለኝ።
አዲስ ዘመን፦ ሕወሓት አሁንም ቢሆን ለሌላ ሶስተኛ ዙር ጦርነት እየተዘጋጀ እንደሆነ እየተገለፀ ነው፤ ለመሆኑ የዚህ አካሄድ ዓላማው ምንድነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ ቀድሞ ነገር እነዚህ ሰዎች ምን እንደሚያደርጉ አያውቁትም። ገና ሲጀመርም ጦርነት መታሰብ አልነበረበትም ፤ አንድ ዓመት ከምናምን በትግራይ ኖሪያለሁ፤ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከግቢያቸው ውጪ አይታዩም ነበር። መከላከያ ሠራዊት ሄዶ ከገበሬው ጋር ሲያጭድ፤ ገንዘብ አዋጥቶ ዓመት በዓል ከአረጋውያን ጋር ሲያሳልፍ፤ ነበር የሚታወቀው። 80 በመቶው የሃገር መከላከያ ሠራዊት በክልሉ ስለነበረ የኃይል ሚዛኑ ወደእኛ ያመዝናል ብለው ስላሰቡ ይሆናል ይህንን ያደረጉት።
ይሄ ሁሉ ሰው ይሄ ሁሉ ድሃ አለቀ፤ ትግራይ ነፃ ሆና ታላቋ ትግራይን እንመሥርት በሚል የማይረባ ወሬ ያልተገባ መስዋዕትነት ተከፈለ። ትግራዋይ ኢትዮጵያዊ ካልሆነ ማንስ ኢትዮጵያዊ ሊሆን ይችላል። ጭራሽ የማይታሰብ ነገር ነው። አሁንም ካፈርኩ አይመልሰኝ ዓይነት መወራጨት እንጂ ምንም እንደማያደርጉ ያውቁታል፡፡ ግን ግራ ገብቷቸዋል፡፡ ትግራይን ነፃ እናወጣለን ማለት ምን ማለት ነው? ትግራይንማ ከሌሎቹ ክልሎች ነጥለው ይዘውት ተቀምጠዋል። ስለዚህ ማነው ነፃ የሚወጣው ይህ ጥያቄዬ ነው።
በሚያሳዝን ሁኔታ አብዛኛው ሰው እየተዋጋ ያለው የሚመስለኝ ሕወሓት እስካለ ድረስ መሬታችን አይሰጥም ብለው ስለሚያስቡ ይመሰለኛል፤ ዓላማ የሌለው ባዶ መወራጨት ብቻ ይመስለኛል። ጦርነቱ ሕዝብ ይጨርሳል እንጂ ምንም ጥቅም የለውም። ፈጣሪ ልቦናቸውን ይመለስላቸው፤ ፈጣሪ ከተጎጂው ወገን ይቁምና መፍትሔ ይስጥ ከማለት በስተቀር ምን ይባላል።
አዲስ ዘመን፦ በውጭ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በምቹ ሁኔታ ውስጥ ሆነውና ልጆቻቸውም በጥሩ ትምህርት ቤት እያስተማሩ የትግራይን ሕዝብ ግፋ በለው የሚሉበት እና የደሃውን ልጆች ለጦርነት የሚማግዱበት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል ፤ ለእነዚህ አካላት የሚያስተላፉት መልዕክት ካለ ፤
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ ጭፍን ደጋፊዎች ስለሆኑ ልትነግራቸው የምትፈለገውን ነገር አይሰሙም። ምንም እንኳን በሞያቸው ትልቅ ደረጃ የደረሱ ቢሆኑም እንኳን በትግራይ ፖለቲካ አንድ አይነት አመለካከት ያላችው የማኅበረሰብ ክፍሎች በመሆናቸው ከስሜታቸው በላይ የሰውን ቁሰል አይረዱም። ለብዙ ጊዜ የዘር ማጥፋት ተፈፀመብን እያሉ ስለኖሩ ካፈርኩ አይመልሰኝ አይነት አካሄድ ነው የሚከተሉት። እኔ ለሕዝቡ ማስተላለፍ የምፈለገው ፀቡም ፍቅሩም ሃገር ስትኖር ነውና መጀመሪያ ሃገርን በአንድነት ለማቆም መሥራት በተረፈ በሰላሙ ጊዜ ክርክር ማድረግ ለሁሉም ይጠቅማል ።
አዲስ ዘመን፦ ይህ የጥፋት ኃይል የትግራይ ሕዝብ ላይ ያደረሰውን ጉዳት እንዴት ይገልፁታል?
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ ይህ ቡድን መጀመሪያ ራሱን ባልሆነ መልኩ ተመልክቶ ያልተገባ አቅም ለራሱ ሰጥቶ የፌደራል መንግሥቱን ሲወጋ የትግራይን ሕዝብ ከእናት ሃገሩ ነጥሎታል። የሕዝቡ ሕይወት ማለቁ፤ ሌላው የኢትዮጵያ ተማሪ እየተማረ የትግራይ ሕፃናት ትምህርት ቤት አይሄዱም። ልጆቹ ከትምህርት ይልቅ ለጦርነት እየተማገዱ ነው። የእርዳታ እህል እየተላከ ሕዝቡ ጋር ሳይደርስ በረሃብ እንዲያልቅ እየተደረገ ነው። በዚህ ክረምትም ድሃው ገበሬ እያረሰ አይደለም ፤ ረሃቡ፤ ሕመሙ፣ ችግሩ ሁሉ ለሕዝቡ ጉዳት ነው። እንዴት ግን ሰው ከራሱ ሊድን ይችላል። ጠላቱን እራሱ ካልጣለና በቃን ብሎ ካልተነሳ ጥፋቱ እየበዛ የሚሄድ ይመስለኛል።
የሕወሓት ሰዎች በመሞት የሚያምኑ የመኖር ጉጉት የሌላቸው በመሆኑ መከራ አያስተምራቸውም፣ ሕዝቡ ግን በቃን ብሎ ይሄንን አስከፊ ቀንበር ከላዩ ላይ አውልቆ መጣል ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፡፡
ፕሮፌሰር ሐረገ ወይን፦ እኔም በጣም አመሰግናለሁ
አሥመረት ብሥራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2014 ዓ.ም