ባለፈው እሁድ በአዲስ አበባ ሁለት አንጋፋ ሰፈሮች የተዘጋጁ የወጣቶች የእግር ኳስ ውድድሮች የፍጻሜ ፍልሚያዎች ተካሂዷል። በሁለቱም ቦታዎች በብዙ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ ተገኝቶ የታደመ ሲሆን ብዙ ዝነኛ ሰዎች፤ የመንግሥት ኃላፊዎች፤ አርቲስቶች እና ሌሎችም በክብር እንግድነት ተሳትፈዋል።
በመጀመሪያ ወደ ፈረንሳይ ለጋሲዮኑ ውድድር እንጓዝ። ውድድሩ ዘንድሮ ሲካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። አዘጋጆቹ እንደሚሉት ከሆነ ለመጨረሻ ጊዜ ተመሳሳይ ውድድር በአካባቢው የተካሄደው ከ24 ዓመት በፊት ሲሆን ከዚያ በኋላ ካቻምና የተካሄደው ውድድር የመጀመሪያው የዘንድሮው ደግሞ ሁለተኛው ነው። ውድድሩ የተካሄደበት የጨፌ ዞናል ስቴድየም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የፈረንሳይ አካባቢ ወጣቶች የተጫወቱበት እና ባለፈው አመት በአዲስ መልክ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተገንብቶ ሥራ ላይ የዋለ ነው። እሁድ እለት በተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ ላይ ሜዳው በሕዝብ ከአፍ እስከ ገደፉ ሞልቶ ሲታይ የአካባቢው ነዋሪ ይህን ጊዜ ምን ያህል ናፍቆት እንደነበር ምልክት ነው።
የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆነውን ወጣት ሀብታሙ ጌታቸውን ‹‹የዚህ ውድድር አላማ የፈረንሳይ ለጋሲዮን ወጣት መልሶ ወደ ስፖርት እንዲመጣ ማድረግ ነው። በአሁኑ ወቅት ወጣቱ በመዋያ እጦት ወደ ሱስ እና ሌሎች አላስፈላጊ ነገሮች ውስጥ እየገባ ነው። ስለዚህም ይህን ለመመከት በታዳጊዎች ላይ የተመሠረተ ውድድር ማዘጋጀት አለብን። በዚህ ውድደር 12 ቡድኖች፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች እና በብዙ ሺ የሚቆጠር ታዳሚ ተሳትፎበታል። በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር ያሉ የፈረንሳይ ለጋሲዮን ልጆች ወጣቶቹን በብዙ ደግፈዋል። በዚህም የተነሳ ውድድሩ ደማቅ ሆኖልናል። ትልቅ መነቃቃትም ፈጥሯል›› በማለት ለአዲስ ዘመን አስተያየቱን ሰጥቷል።
በቀጣይ አካባቢውን የሚወክል እና በሊግ የሚወዳደር የእግር ኳስ ክለብ ለመመስረት ጥረት ላይ እንደሆኑ የሚናገረው ወጣት ሀብታሙ የሜዳውን አስተዳደር እና አጠቃቀም ሕዝባዊ ለማድረግም ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን ገልጿል። በእለቱ በውድድሩ ላይ ታዳሚ የነበረችው አርቲስት ፋንትሽ በቀለ እና እህቶቿ ለፍጻሜ ለደረሱት ቡድኖች የትጥቅ መግዣ የ100ሺ ብር ስጦታ አበርክተዋል።
በኮልፌ የተካሄደው ውድድር ደግሞ ኢምር በኮልፌ ቶርናመንት የተሰኘ ሲሆን የፍጻሜ ጨዋታውም በተለምዶ መላጣ ሜዳ በሚባለው አካባቢ ተካሂዷል። የፍጻሜውን ጨዋታም በሺ የሚቆጠር የኮልፌ እና አካባቢው ነዋሪ ታድሞበታል። ኮልፌዎች የውድድሩን ፍጻሜ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብር ለመግለጽ እንዲሁም ጀግኖቻቸውን ለማክበር ተጠቅመውበታል። ምስጋናው ከተቸራቸው መካከል አንጋፋው ደራሲ ሀይለመለኮት መዋእል፤ ‹‹የወታደር ልጅ ነኝ›› በሚል የግጥም መድብል የምናውቃት ሻለቃ ወይንሀረግ፣ የቀድሞ ቦክስ አሰልጣኝ ኢንስፔክተር ሰለሞን፣ የኦሜድላ ስፖርት ክለብ መስራች አቶ አስረስ ተጠቃሽ ናቸው። ውድድሩ በቆየበት ጊዜ ሁሉ የአካባቢውን ሕዝብ ትኩረት ይዞ የከረመ ሲሆን ብዙ ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች እና ታዳጊዎች መታየታቸው ተነግሯል።
አዲስ አበባ ከተማ በኢትዮጵያ የስፖርት ታሪክ በተለይም በእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ የሆኑ ስፖርተኞችን በማፍራት የምትታወቅ ሲሆን ነገር ግን ባለፉት ሁለት አስርት አመታት እነዚህን ስፖርተኞች ያፈሩ ሜዳዎች በተለያየ ምክንያት ለሌላ አገልግሎት ውለው ወጣቱ በመዋያ እጦት ሲንገላታ እንደኖረ ይታወቃል። ተተኪ ስፖርተኞች የማፍራት እድሉም እየተመናመነ ሲሄድ እንደቆየ የሚታወቅ ሀቅ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የሜዳዎቹ መጥፋት እንደዚህ ዓይነት ውድድሮችም አብረው እንዲጠፉ በማድረግ ወጣቱ በጋራ የሚገናኝበትን እድል እንዲያጣም አድርገውታል። በቅርብ ጊዜያት ግን ሁኔታዎች የመለወጥ እና አካባቢያዊ ውድድሮች የመመለስ አዝማሚያ እየታየባቸው ሲሆን ለዚህም ከላይ የጠቀስናቸው የፈረንሳይ ለጋሲዮን እና የኮልፌ ውድድሮች ማሳያ ናቸው።
መንግሥት በቅርቡ ከጀመረው የማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት ውድድሮች ባሻገር እንዲህ ዓይነት ውድድሮችን መደገፍ እና ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር ማገዝ እንዳለበት ይታመናል። ባለሀብቶች በጥቂት ክለቦች ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከመገፍገፍ እንዲህ ዓይነት ውድድሮችን በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም የስፖርት ቤተሰቡ እምነት ነው። አሰልጣኞች እና ክለቦችም ውሏቸውን እንዲህ ባሉ ቦታዎች በማድረግ አዳዲስ ተስፈኛ ወጣቶችን ከየሰፈሩ መመልመል እንደሚገባቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። ይህን ማድረግ ከተቻለ አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ እግር ኳስም ሆነ ለመላው ስፖርት የሚጠቅሙ ምርጥ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደምትችል እርግጥ ነው።
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2014