በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች መካከል ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት ኢትዮጵያን በ2020 ቶኪዮ ኦሊምፒክ ዋጋ አስከፍሏታል። በዚያ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ እየለመደች ከመጣችው ውጤት በተቃራኒ ዝቅተኛ የሜዳሊያ ቁጥር አስመዝግባለች። ሕዝብም በዚህ ዝቅተኛ ውጤት ቅር ከመሰኘት አልፎ ቁጣውን በተለያየ መልኩ ሲገልጽ እንደነበር አይዘነጋም። የሁለቱ ተቋማት አመራሮች ውዝግብ ለተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት የአንበሳውን ድርሻ ቢይዝም ከኦሊምፒኩ በኋላ ግንኙነታቸው ይበልጥ እየሻከረ መሄዱ አሳሳቢ ነበር።
ሁለቱ አካላት ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው የአገርን ስፖርት ከማሳደግ ይልቅ ይባስ ብለው ከኦሊምፒኩ በኋላ በይፋ ግንኙነት ማቆማቸው ጉዳዩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎት ነበር። መንግሥት በዚህ ረገድ ጣልቃ ገብቶ ሁለቱን አካላት ለመሸምገል ውዝግቡ በጦፈበት ወቅት አለሁ ቢልም ይህ ነው የሚባል ትርጉም የሚሰጥ ሥራ ሳይሠራ ቆይቷል። ይህም የፓሪሱ 2024 ኦሊምፒክ በተቃረበበት በዚህ ወቅት በቶኪዮ ኦሊምፒክ የነበረው ውዝግብ እንዳይቀጥል የብዙዎች ስጋት ነበር።
የአገሪቱን ስፖርት በበላይነት የሚመራው የመንግሥት አካል እንደአዲስ አመራሮቹ ተቀይረው ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከሆነ ወዲህ በኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል የነበረውን አለመግባባት ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በተለይም ካለፈው ሳምንት ወዲህ የሁለቱን ስፖርት ተቋማት አመራሮች ለማወያየትና የነበሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት መድረኮችን በማመቻቸት ያደረገው ጥረት ፍሬ ያፈራለት ይመስላል። ሁለቱ የስፖርት ተቋማት ባለፈው ዓርብ በልዩነቶቻቸው ላይ መምከራቸው የሚታወስ ሲሆን ከትናንት በስቲያም ችግሮቻቸውን ፈተው በጋራ ለመሥራት እንደተስማሙ አሳውቀዋል።
ከትናንት በስቲያ ምሽት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋባዥነት በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች ‹‹ካለፈው ስህተታችን ተምረን ሕዝባችንን ለመካስ ተባብረን መሥራት ይጠበቅብናል›› በማለት የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በመድረኩ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ለየብቻ እና በተናጠል መድረኮችን በማመቻቸት ችግሮቻቸውን በራሳቸው እንዲመለከቱትና የመ ፍ ት ሔ ባለቤት እንዲሆኑ ያደረጉበት የአመራር ብስለታቸውን በማድነቅ አመስግነዋል።
ሚኒስትሩ በበኩላቸው ‹‹ችግ ሮች ወዲያው ካልተፈቱ መዘዛቸው ዋጋ ያስከፍላል›› በማለት ከቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ውጤት መቀነስ ጋር ተያይዞ ከዝግጅት እስከ ፍጻሜ የነበረውን ሁኔታ አስመልክቶ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና ከኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌደሬሽን ጋር የተናጠል እና የጋራ መድረኮችን በማዘጋጀት በተፈጠሩ ችግሮች ላይ መግባባት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።
ሚኒስትሩ ችግሮቹ ቀላል እንደነበሩ እና ቶሎ ባለመፈታታቸው እንዲደራረቡ እና እንዲባባሱ በመደረጋቸው ዋጋ ወደ ማስከፈል ተሸጋግረው ለመንግሥትም ትልቅ የቤት ሥራ ሆነው እንደነበር በማስታወስ ‹‹ችግሮች እንዳይከሰቱ በመከላከል እና ከተከሰቱም ቶሎ ለመፍታት መሥራት ያስፈልጋል›› ብለዋል።
የተከሰቱት ችግሮች መነሻቸው ከየት እንደሆነ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በጥልቀት የገመገመ ሲሆን በዋናነት ሁለቱ አካላት ከተሰጣቸው ኃላፊነት አኳያ ሕግና አሠራርን ተከትለው ሳይናበቡ በመሥራት የተፈጠሩ እንደነበሩ አቶ ቀጄላ ተናግረዋል። በዚህ መሠረት ሁለቱ አካላት የተሠጣቸውን ኃላፊነት ተናበው እና ተስማምተው የሚሠሩ ከሆነ ችግሮች እንደማይፈጠሩ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል። ችግሮች ከዚህ በኋላ ከተፈጠሩም በአስቸኳይ መፍትሔ እየተሰጣቸው በመሄድ ጤናማ የሥራ ግንኙነት እንዲኖር ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የሁለቱ ስፖርት ተቋማት አመራሮች ከዚህ ቀደም ከአንዴም ሁለቴ በተለያዩ ጉዳዮች አለመግባባት እየፈጠሩ ሲወዛገቡ የነበረ ሲሆን ታርቀናል ወይም ልዩነቶቻችንን ተነጋግረን ፈተናል ካሉ በኋላ ዳግም ሲቃቃሩ እንደነበር ይታወሳል። በተለይም ኦሊምፒክን የመሳሰሉ ታላላቅ የውድድር መድረኮች በተቃረቡ ወቅት በአትሌቶች ምርጫ እንዲሁም ከዝግጅት ጋር በተያያዘ በጉዳዩ ላይ ‹‹እኔ ነኝ አዛዥ›› በሚል ሲካረሩ ማየት የተለመደ ነው።
አሁንም ሁለቱ አካላት ‹‹ከስህተታችን ተምረን በጋራ እንሠራለን›› ብለው ቃል ቢገቡም ከአትሌቶች ምርጫና ዝግጅት ጋር በተያያዘ ነገም ተመሳሳይ አለመግባባት ውስጥ እንዳይገቡ በርካቶች ስጋት አላቸው። አሁን በምን ጉዳይ ላይ እንደተግባቡ የተገለፀ ነገር አለመኖሩም ነገ በተመሳሳይ ውዝግብ እንዳይጠመዱ ስጋት ነው። ለዚህም ከዚህ ቀደም አወዛጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ለሁሉም ግልፅ የሆነ ሕግና ሥርዓት ማበጀትና በዚያም መሠረት መመራት እንደሚያስፈልግ የስፖርት ቤተሰቡ እምነት ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2014