የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ተሳትፎና የተመዘገበው ውጤት እንዲሁም በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና የስፖርት ማህበራት መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሚረዳ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ውይይት ተደረገ። የውይይቱ ዓላማ የስፖርት ማህበራቱ መፍትሄ ለማምጣትና በቀጣዩ የ2024 ፓሪስ ኦሊምፒክ በጋራ እንደሚሰሩ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ነው።
በኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር አዘጋጅነት በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይም ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ፣ የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲሁም በኦሊምፒኩ ተሳታፊ የነበሩ የስፖርት ማህበራት ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል። አስቀድሞም በሚኒስትሩ የተዘጋጀው ሰነድ የቀረበ ሲሆን፤ ባለድርሻ አካላቱን በተናጠል በማወያየት ሂደቱ ምን ይመስል ነበር የሚለውን ዳሷል። በዚህም ኢትዮጵያ ከሲድኒ እአአ 2000 ኦሊምፒክ እስከ ቶኪዮ 2020 ድረስ ከተካፈለችባቸው ኦሊምፒኮች አነስተኛ የሜዳሊያ ቁጥር (1የወርቅ፣ 2የብር እና 1 የነሃስ በጥቅሉ 4ሜዳሊያዎች)የተመዘገበበት መሆኑ ተነስቷል።
ይሁንና ኦሊምፒኩ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ ትኩረት የተሰጠውና በመንግስትም 156 ሚሊዮን ብር የተመደበበት ነው። ወራትን አስቀድሞ እቅድ በማውጣት ወደ ዝግጅት መግባቱም ጠንካራ ጎኑ ቢሆንም የስፖርት ማህበራቱ በአግባቡ ኃላፊነታቸውን አለመወጣታቸው እንዲሁም ስፖርቱን የሚመራው መንግስታዊው አካል ህግን ማስከበር አለመቻሉ ደካማው ጎን መሆኑን ሰነዱ አመላክቷል። እንደ መፍትሄ ሃሳብም መንግስት ህግን ማስከበርና ቁርጠኛ እርምጃ መውሰድ፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጤናማና ቅንጅታዊ ግንኙነት እንዲፈጥር፣ የስፖርት ማህበራት በኦሊምፒክ የሚኖራቸውን ሚና እና ዓለም አቀፍ አሰራሮችን እንዲያገናዝብ እንዲሁም ለአገር ክብር ቅድሚያ በመስጠት መስራት ተገቢ መሆኑ ተመላክቷል።
በኦሊምፒኩ ተሳታፊ የነበሩት የስፖርት ማህበራት እንዲሁም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በሰጡት አስተያየትም ኦሊምፒኩን ተከትሎ ያስተናገዱትን ቅሬታ አንጸባርቀዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ ግን ሁሉም በወቅቱ ስፖርቱን ይመራ የነበረው ኮሚሽን በአግባቡ ስራውን ባለማከናወኑና በቁርጠኛ አመራር አቅጣጫ ባለመስጠቱ ችግሩ እዚህ መድረሱን ነው የጠቆሙት።
መድረኩን የመሩት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ፤ የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክን ተከትሎ የተከሰተው ችግር እስካሁንም አለመፈታታቸው እአአ በ2024 ለሚዘጋጀው የፓሪስ ኦሊምፒክ መደናቀፍ እንዳይፈጠር መድረኩ ውይይቱ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ነገር ግን ክፍተቶቹ በቅርቡ ወደ ስራ በገባው የማህበራት አሰራር ሊሞሉ የሚችሉ ስለመሆኑ እምነት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 15/2014