የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከግንቦት 21 እስከ ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም በሐዋሳ ከተማ ይካሄዳል። የኦሊምፒክ ስፖርት በሆኑና ባልሆኑ በርካታ የውድድር አይነቶች ስድስት ሺህ ወጣቶች ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ የመጀመሪያው የወጣቶች ኦሊምፒክ ላይ ለመሳተፍ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የውስጥ ውድድሮቻቸውን በማካሄድ የሚወክሏቸውን ስፖርተኞች መርጠዋል፤ እየመረጡም ይገኛሉ።
የኦሮሚያ ክልል በሐዋሳው የወጣቶች ኦሊምፒክ ውጤታማ ሆኖ ለማጠናቀቅ ከወዲሁ ዝግጅቱን የጀመረ ሲሆን፤ የሚወክሉትን ስፖርተኞችም ባለፉት አስር ቀናት በሻሸመኔ ከተማ አካሂዶ ከትናንት በስቲያ ባጠናቀቀው የኦሮሚያ ወጣቶች ኦሊምፒክ መርጧል። ክልሉ፣ በሐዋሳው የወጣቶች ኦሊምፒክ ትልቅ ውጤት ለማስመዝገብ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳደረገ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ለዚህም ሰሞኑን በሻሸመኔ ከተማ ሰፊ ውድድር በማካሄድ ክልሉን በተለያዩ ስፖርቶች የሚወክሉትን ወጣቶች በብዛት መምረጡን አሳውቋል።
የኦሮሚያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሳሚያ አብደላ፣ በተለይ ለአዲስ ዘመን በሰጡት አስተያየት፤ ክልሉ በሻሸመኔ ከተማ ለአስር ቀናት የዘለቀ ሰፊ ውድድር በማካሄድ በተለያዩ ስፖርቶች ተስፋ ያላቸው ተተኪ ወጣቶችን እንዳገኘ ተናግረዋል። በሻሸመኔው ውድድር ከሶስት ሺህ በላይ ስፖርተኞች መሳተፋቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ሳሚያ፤ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ከሶስት መቶ በላይ የተሻለ ብቃት ያሳዩ ስፖርተኞች ተመርጠው በቀሪዎቹ ጥቂት ቀናት ክልሉን ለመወከል እንደሚዘጋጁ አስረድተዋል።
እነዚህ ወጣቶች በሻሸመኔው ውድድር በተለያዩ ስፖርቶች ተስፋ ሰጪ እምቅ አቅም እንዳላቸው ያሳዩ ሲሆን፤ ለክልሉም ይሁን አጠቃላይ እንደ አገር ተተኪ ሆነው እንደሚወጡ ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል። በቀጣይ አስር ቀናትም ዝግጅታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ኃላፊዋ አክለዋል።
ባለፉት ጥቂት አመታት በተለያዩ አገር አቀፍ ውድድሮች የኦሮሚያ ክልል ስፖርት መቀዛቀዝ ያሳየ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊዋ፤ ዘንድሮ ጥሩ የመነቃቃት ጅምር እንዳለ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ክልሉ እንዳለው እምቅ የስፖርት አቅም አሁን ያለበት ደረጃ በቂ ነው ተብሎ ስለማይታመን አበረታች ጅምሮች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ቢሮው ጥረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
እንደ አገር ብዙ ጊዜ በወጣቶች መካከል በሚካሄዱ ውድድሮች ከእድሜ ማጭበርበር ጋር የተያያዙ ችግሮች ጎልተው ይታያሉ። ይህም ክልሎችን ውጤት ከማሳጣት ባሻገር የማይገባቸውን ውጤት ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ሲያጎናጽፋቸው ይስተዋላል። የኦሮሚያ ክልል ይህ የተለመደ ችግር እንዳይገጥመው ወጣቶቹን በተገቢው እድሜ ለመመልመል የተለያዩ ጥንቃቄዎችን እንዳደረገ ተገልጿል። “እድሜን በተመለከተ ጥብቅ ቁጥጥር ያደረግነው
በአገር አቀፍ ደረጃ ስንወዳደር ውጤት ላይ ብቻ ትኩረት ስለማናደርግ ነው፣ ዛሬ ውጤት አምጥተን ነገ ተተኪዎችን ማጣት አንፈልግም፣ ከተገቢው የእድሜ ክልል ውጭ ስፖርተኞችን አሳትፈን የክልላችንን አንገት ማስደፋት አንፈልግም፣ ለነገ ተስፋ የሚሆኑ ጠንካራ ወጣቶችን አሰልፈን ዛሬ ውጤት ብናጣ ከሁለትና ሶስት አመታት በኋላ እነዚህ ወጣቶች በአዋቂዎች ውድድር ጠንካራ ተፎካካሪና ውጤታማ ሆነው ይክሱናል” በማለት ከእድሜ ጋር የተያያዘውን ጉዳይ የቢሮው ኃላፊዋ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ይካሄዳል ተብሎ ከታሰበበት ወቅት ዘግይቶ ከፊታችን ግንቦት 21/2014 ጀምሮ እንደሚካሄድ ሲገለጽ፤ በርካታ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የዝግጅት ጊዜ ማጠሩን ቅሬታ ያነሳሉ። በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ክልል ከዝግጅት ጊዜ ማጠር በተጨማሪ የውድድሮች መደራረብ ጫና ሊኖረው እንደሚችል ቢገምትም ይህን ጫና ተቋቁሞ ውጤታማ ለመሆን ጥረት ማድረግ እንጂ እንቅፋት አድርጎ መቁጠር እንደማይፈልግ ኃላፊዋ ተናግረዋል።
በሻሸመኔው ውድድር ከሰላሳ በላይ ዞኖች፣ ከተሞችና የተለያዩ የወጣቶች ስፖርት ማሰልጠኛ ማእከላት የተውጣጡ ከሶስት ሺ በላይ ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። አዘጋጁ ሻሸመኔ ከተማ አስራ ሁለት ወርቅና አስር ብር በመሰብሰብ አጠቃላይ የዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። በተመሳሳይ አስራ ሁለት የወርቅና ስድስት የብር ሜዳሊያ በመሰብሰብ የቅርብ ተፎካካሪ የሆነው የአርሲ ዞን ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ቢሾፍቱ ከተማ የሰበሰባቸው አስራ አንድ የወርቅ ሜዳሊያዎች ሶስተኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ አስችለውታል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 13/2014