የዓለምን እግር ኳስ የሚመራው ፊፋ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከጀመራቸው ውድድሮች መካከል አንዱ ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ተጠቃሽ ነው፡፡ እአአ ከ2005 ወዲህ የተወለዱ ታዳጊዎች ብቻ የሚሳተፉበት ይህ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው እአአ በ2008 በኒውዝላንድ አዘጋጅነት ነበር፡፡
በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው (ዘንድሮ ከአራት ዓመት በኋላ ይደረጋል) በዚህ ውድድር ሰሜን ኮሪያ የሁለት ጊዜ አሸናፊ በመሆን የበላይነቱን ይዛለች፡፡ በአንጻሩ ከአፍሪካዊያን አገራት ትልቅ የሚባለው ውጤት የተመዘገበው እአአ 2012 ሲሆን ጋና ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችበት ነው፡፡ ተተኪ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሚካፈሉበት ውድድሩ የአፍሪካዊያን ተፎካካሪነት እምብዛም አይደለም፡፡
ህንድ የምታዘጋጀው 7ኛው የዓለም ከ17 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ ከስድስት አህጉር አቀፍ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽኖች የተወጣጡ 16 ቡድኖች ተሳታፊ የሚሆኑበት ውድድሩ፤ በአንድ አገር ከምትወከለው ኦሺንያ በቀር ሁሉም አህጉራት ሶስት ሶስት አገራትን ያሳትፋሉ፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በአህጉሪቱ በሚገኙ ሶስት ብሄራዊ ቡድኖች የሚወከል ሲሆን፤ ለዚህም አራት ዙር ያለውን የማጣሪያ ውድድር በመምራት ወደማጠቃለያው እያመራ ይገኛል፡፡ ለመጨረሻው ዙር ያለፉ ስድስት አገራትም ዛሬ እና ከነገ በስቲያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
ወደ መጨረሻው ዙር ያለፉት ስድስት አገራት ኢትዮጵያን ጨምሮ ናይጄሪያ፣ ካሜሮን፣ ታንዛኒያ፣ ጋና እና ሞሮኮ ናቸው፡፡ ካሜሮን እና ታንዛኒያ ዛሬ የሚጫወቱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም የናይጄሪያ አቻዋን በሜዳዋ የምትገጥም ይሆናል፡፡ በዚህ ዙር ላይ በደርሶ መልስ አሸናፊ የሚሆኑት ሶስት አገራትም አህጉራቸውን ወክለው በህንዱ የዓለም ዋንጫ ላይ ለመካፈል ትኬታቸውን የሚቆርጡ ይሆናል፡፡ ‹‹ፍላሚንጎ›› በሚል መጠሪያ ስም የሚታወቀው የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫው በተከታታይ ለአምስት ጊዜያት ተሳታፊ መሆን ችሏል፡፡ በተሳትፎዎቹም በሶስቱ ሩብ ፍጻሜ መድረስ ችሏል፡፡ በአንጻሩ ኢትዮጵያ በዚህ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን በሚደረገው ማጣሪያ ለፍጻሜ ስትደርስ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ዛሬ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ለሚደረገው ጨዋታም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ የሚመራው ቡድኑ ትናንት በጥሩ መነቃቃት የመጨረሻ ልምምዱን በካፍ የህልቀት ማዕከል ሰርቷል። በቦታውም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በመገኘት ቡድኑን ማበረታታቸውን ፌዴሬሽኑ በድረገጹ አስነብቧል።
ፕሬዚዳንቱ ለተጫዋቾቹ ባስተላለፉት መልዕክትም እዚህ ደረጃ በመድረሳቸው ፌዴሬሽኑ ደስተኛ መሆኑን ገልጸው፤ እዚህ መድረሳቸውን ብቻ የመጨረሻ ግብ ማድረግ ሳይሆን ለህንዱ የዓለም ዋንጫ ማለፍ ብሎም በውድድሩ ስኬታማ ለመሆን ማሰብ እንደሚገባ ተናግረዋል። ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ክፍተቶች ትምህርት በመውሰድ እና የሜዳ የበላይነትን በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም የጫና ስሜት ሳይሰማቸው በመጫወት ውጤት አስመዝግበው በሴቶች እግር ኳስ በር ከፋች መሆን እንደሚችሉም ፕሬዚዳንቱ በማበረታቻቸው ጠቁመዋል። ለዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስፈላጊውን ማበረታቻ እንደሚያደርግም አክለዋል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ ለመጨረሻው ዙር የደረሰው ጠንካራዋን እና እአአ በ2010 እና 2018 በዓለም ዋንጫው ተሳታፊ የነበረችውን ደቡብ አፍሪካን 3 ለ1 በሆነ ድምር ውጤት በመርታት ነው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2014