የደንቢዶሎ፣ የአሶሳ፣ የሻኪሶ ወርቅ፤ የወረኢሉ ማዕድን፤ የዳሎል ልዩ ሰልፈር፤ ለአንገት ሀብል፣ ለእግር አልቦና ለጣት ቀለበት መዋቢያና ለተለያየ ጌጣጌጥ የሚያገለግሉ እንደ ኦፓል ያሉ እንዲሁም የብረት ማእድንና የተፈጥሮ ጋዝ ኢትዮጵያን በማእድናት የበለጸገች አሰኝተዋታል::
ለጌጣጌጥ፣ ለግንባታው፣ ለኢንዱስትሪው ዘርፎች የሚውሉት ግብአቶችና ሌሎችም የከበሩ የድንጋይ ማእድናት ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ፣ እነዚህን እምቅ የማዕድን ሀብቶቿን በተመለከተ ከግሪክ ቀደምት ፀሐፍት እስከ ቅዱስ መጽሐፍት ዓለም የመሰከረላት መሆኑን ከታሪክ ድርሳናት መረዳት ይቻላል::
ይሁንና ከእነዚህ ማእድናት በትንሹም ቢሆን እየለማ ያለውና አገርን በሚገባ ተጠቃሚ እያረገ የሚገኘው የወርቅ ማእድን ነው፤ ሌሎቹ በቅጡ ያልለሙና ጨርሶ ያለሙም ናቸው:: ይህም በማእድን ሀብቱ ላይ ገና ብዙ መሰራት እንዳለበት ያስገነዝባል::
የማዕድን ሀብቷ አይነት፣ የሀብቱ መገኛ ሥፍራዎች፣ አጠቃላይ የሆነ መረጃ አገሬውም ሆነ የዓለም ማህበረሰብ የሚያውቅበትና አይቶም አድናቆቱን ሊገልጽ የሚችልበት አልፎም ተርፎም አልምቶ ሊጠቀምበት የሚያስችል ጋለሪ (የማሳያ መዘክር) ሳይኖራት ዘመናት ተቆጥረዋል:: የሥነምድር ትምህርት ክፍል ያላቸው አንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) መጠነኛ የሆነ ጋለሪ ቢኖራቸውም አጠቃላይ አገራዊ ሀብቱን በሚዳስስ መልኩ በተደራጀ ሁኔታ ስፋት ያላቸው አለመሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ::
አሁን ግን ማዕድን ሚኒስቴር ኢትዮጵያ የማዕድን ጋለሪ እንዲኖራት መሠረት በመጣል ክፍተቱን በመሙላት አስተዋጽኦ ማድረግ ችሏል:: ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ የማዕድን ጋለሪ ይፋ አድርጓል:: አንዳንዶችም የማዕድን ጋለሪውን ለአገር ትልቅ አበርክቶ ያለው ሲሉ አስተያየታቸውን በጽሁፍ በማህበራዊ ድረጋጾች (ፌስቡክ) ጭምር ገልጸውለታል::
‹‹በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ››እንዲሉ፣የጋለሪው መደራጀት የማእድን ሀብቱ በተለያየ መንገድ እንዲገለጽና ገቢም እንዲያስገኝ ዕድል የሚሰጥ መሆኑ ተስፋ አሳድሯል:: የአገር ውስጥም የውጭ ኢንቨስትመንት ለመሳብም የጎላ ፋይዳ አለው:: ባለሀብቱ በጋለሪው ውስጥ በሚያገኘው መረጃ መሠረት ማእድን ለማልማትና ተጠቃሚ ለመሆን መሰማራት የሚፈልግበትን አካባቢና የማዕድን አይነት ለመለየት ሂደቱን ቀላል ያደርግለታል::
በሌላ በኩል ደግሞ የቱሪስት መስህብ ሆኖ ገቢ በማሰገኘት በአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ ያበረክታል:: የአገር ገጽታን በመገንባትም ሚናው የጎላ ይሆናል:: ለቱሪስቱና ለኢንቨስተሩ በጽሁፍ ማስረጃና በቃላት ከሚነገረው በላይ ማዕድናቱን በአይኑ ማየት እንዲችል መመቻቸቱ የበለጠ ትኩረትን ይስባል::
ለዘርፉ ተመራማሪዎችም መረጃ የማግኘት ድካማቸውን ከመቀነሱ በተጨማሪ የጥናት ሥራቸውን ለመለየትም ቀላል መንገድ ይሆንላቸዋል:: በዘርፉ ሙህራንን የሚያፈሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸው በቅርብ ርቀት ላይ በተግባር የተደገፈ ዕውቀት አደንዲያገኙ ያግዛቸዋል::
የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት፣ የኢኮኖሚው አውታር እንደሆነ ከሚነገርለት የግብርናው ዘርፍ በመቀጠል የማዕድን ሀብቱ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ እንዲሆን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የማዕድን ዘርፉን እንደ አንድ ትልቅ አጀንዳ ይዞ በለውጥ ጎዳና ላይ መገኘቱ እያስመሰገነው ነው:: ምስጋናውም ተቋሙን ለሚመሩት ሆኗል:: ሚኒስቴሩ ይፋ ያደረገውን የማዕድን ጋለሪ ለተለያዩ የተቋማት መሪዎችና ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች በማስጎብኘት ላይ ይገኛል::
በጋለሪው ውስጥ የተደራጁትን የማዕድን የሀብት አይነቶችና መገኛቸውን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ሚኒስቴሩ በሥራ ላይ ለውጥ ለማምጣት ከተቋማዊ አደረጃጀት ጀምሮ የወሰዳቸው እርምጃዎች መልካም ተሞክሮ በመሆን ጭምር በተለያየ ዘርፍ ላይ የሚገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማነቃቃት ለተሻለ ሥራ ለማነሳሳትም ጥሩ ተሞክሮ ሆኗል::
መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ የማዕድን ዘርፍ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆኑ የጥቅም ግጭት ሊፈጠር የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል:: የፖለቲካ አጀንዳ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም ስለማይጠፉ ጥንቃቄ ይፈልጋል:: የማዕድን ልማቱ የሚከናወንባቸው ሥፍራዎች የተሟላ መሠረተ ልማት የሌለባቸው በመሆናቸው፣ በዘርፉ ለመሰማራት ቁርጠኝነትን ይጠይቃል::
ልማቱን ለማካሄድ ቴክኖሎጂና የገንዘብ ሀብት ዋናው ለዘርፉ አስፈላጊ ከሚባሉት መካከል ይጠቀሳል:: በተለይም እሴት የተጨመረበት የማዕድን ልማት ለማከናወንና ከባህላዊ የማዕድን ቁፋሮ ሥራ ለመውጣት ተሞክሮውና አቅሙ ያላቸው ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ይመረጣል:: ይህም ወደ ውጭ ኩባንያዎች ለማማተር አንዱ ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል::
የአገር ውስጥ ባለሀብቱ ከማዕድን ልማቱ ይልቅ ጥሬ ሀብቱንና እሴት የተጨመረበትን ለገበያ በማቅረብ ላይ ነው በስፋት ተሰማርቶ የሚስተዋለው:: ይህም ቢሆን አመርቂ እንዳልሆነ፣ በባህላዊ መንገድ በማዕድን ቁፋሮ ሥራ ላይ ለሚገኘውም ሆነ ለአገር የሚፈለገውን ጥቅም እያስገኘ እንዳልሆንም ይታወቃል:: በዚህ ሁሉ ተግዳሮት ውስጥ ነው የማዕድን ልማቱ የሚከናወነው::
ስራው አድካሚ ቢሆንም የሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ግን ድካሙን የሚያስረሳ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያስገነዝባሉ:: በማዕድን ሚኒስቴር የተደራጀው አዲሱ የማዕድን ጋለሪ በዘርፉ የነበሩትን ክፍተቶች በመሙላት ዘርፉንም ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገርና በማነቃቃት ረገድ የላቀ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል::
ጋለሪው ለመጎብኘት ዕድሉን ካገኙት የአገራችን ባለሀብቶች መካከል በምግብ ኢንደስትሪው በተለይም ዘይት አምርቶ በማቅረብ የሚታወቁት አቶ በላይነህ ክንዴ አንዱ ናቸው:: ስለጉብኝታቸውና አጠቃላይ በማዕድን ልማቱ ላይ ስላላቸው ግንዛቤ ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉን ጠየቅናቸው:: እሳቸው ከጉብኝቱ በሁለት መንገድ ግንዛቤ አግኝተዋል:: አንዱ ከመዋቅራዊ ለውጥ ጀምሮ ሚኒስቴሩ የወሰደው እርምጃ ለተሻለ አፈጻጸም የሚያበቃ መሆኑን ተሞክሮ አግኝተውበታል:: እንደ ተቋምም ብዙ እርምጃዎችን በመጓዝ ለለውጥ ያሳየውን ትጋት ለመረዳት ችለዋል::
ኢትዮጵያ የበርካታ ማዕድናት ሀብት ባለቤት ስለመሆኗ ግንዛቤው ቢኖራቸወም ጋለሪው ከጠበቁት በላይ ስለዘርፉ እውቀት እንዲኖራቸው አስችሏቸዋል:: አቶ በላይነህ አንዳንዶቹን የማዕድን አይነቶች ያውቋቸዋል፤ ይሁንና ግን የሚገኙበትን አካባቢ ባለማወቃቸው የተሟላ መረጃ አልነበራቸውም:: በመሆኑም ሚኒስቴሩ በጋለሪው ውስጥ ያደራጃቸው የማዕድን አይነቶች ናሙናዎች የተለያዩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ የሚገኙባቸውን አካባቢዎችንም ጭምር ለማወቅ ችለዋል::
በተለይም እንደርሳቸው ያሉ ባለሀብቶች በዘርፉ ለመሰማራት አይናቸውን እንዲከፍቱና በዘርፉ ላይ ቢሰማሩ ለራሳቸውም ሆነ ለአገር የኢኮኖሚ ዕድገት ጠቀሜታ ያለው አበርክቶ እንደሚኖራቸው አስገንዝቦአቸዋል:: በግላቸውም ያልተሰማሩበት ዘርፍ በመሆኑ እንዲሰማሩ አነሳስቷቸዋል::
የማዕድን ዘርፉ ብዙ መዋዕለነዋይና ቴክኖሎጂ ይፈልጋል፣ በሚል ከአገር ውስጥ ባለሀብት ይልቅ የውጭው ኩባንያ ላይ የማተኮር ሁኔታ አብዝቶ ስለሚታይ እንዲሁም ያለው ነባራዊ ሁኔታ የአገር ውስጥ ባለሀብትን የሚጋብዝ ስለመሆኑ አቶ በላይነህ የቀረበላቸውን ጥያቄ በተለያየ መንገድ ቃኝተውታል:: እርሳቸው እንዳሉት፤ አቅም ያለው በራሱ መንቀሳቀስ የሚችልበት ዕድል የተሟጠጠ አይደለም:: ሁለተኛ አማራጭም አለው::
ከውጭ አገር የዘርፉ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና (ሼር ሆልደር) ሆነው መስራትም ይቻላል:: በዘርፉ ላይ መሠማራት ባይቻል እንኳን ሁሉም የአገር ውስጥ ባለሀብት ሊያደርገው የሚችለው እንዳለም ጠቁመዋል:: ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የማእድን ሀብቱን በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንት በመሳብ የየራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል ይላሉ::
እሳቸው ከጉብኝታቸው የማእድን ሀብቱን ለማስተዋወቅ የሚያስችል ግንዛቤ አግኝተዋል:: ከጋለሪው ባገኙት መረጃ ስለማዕድን አይነቶቹና የሚገኙበትን አካባቢ በማስተዋወቅ ዘርፉ በኢኮኖሚያው ውስጥ የላቀ ሚና እንዲኖረው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ናቸው::
አቶ በላይነህ ማዕድን አዋጭ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደሆነና ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገትም ወሳኝ ከሆኑ መካከል አንዱ እንደሆነ ቢገነዘቡም ግብርናን ያስቀድማሉ:: ‹‹የግብርናው ሥራው ግንባር ቀደም ሚና ይጫወታል የሚል እምነት አለኝ›› ይላሉ:: ግብርናው በአመት ሶስቴ ምርት የሚገኝበትና የኢኮኖሚውም ዋልታ ነው ሲሉ ይገልጻሉ::
ይሄ ሳይዘነጋ የማዕድን ልማቱ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ነው የሚሉት:: ነገር ግን በዘርፉ ባለመሰራቱ የሚፈለገውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳላስገኘ መረዳታቸውን ያመለክታሉ:: የማዕድን ልማት ሥራው ተጠናክሮ አገራዊ የኢኮኖሚ ዕደገት ላይ የላቀ ለውጥ አስመዝግቦ ለማየትም ተስፋ አድርገዋል::
ጋለሪው የመጎብኘት ዕድሉን ባያገኙም የተደራጀ የማዕድን ጋለሪ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲኖር ይመኙ እንደነበር የገለጹልን ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የምድር ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ይርጉ ናቸው:: እንደ ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ገለጻ፤ በእስከ አሁኑ ተሞክሮ በኢትዮጵያ የማዕድን ሀብት የሚገኝባቸው አካባቢዎች ከካርታ (በምስል) ላይ ነበር ሰው መረጃ እንዲኖረው ወይንም እንዲያውቅ የሚደረገው:: አሁን ላይ የሚታይ፣ የሚዳሰስና የሚጨበጥ ነገር በጋለሪ ለእይታ መዘጋጀቱ ለዘርፉ ትልቅ እመርታና የሚያስደስት ሆኖ ነው ያገኙት::
እንደ ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ገለጻ፤ ከዩኒቨርሲቲ በየአመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በዘርፉ ይመረቃሉ:: ነገር ግን አብዛኞቹ በተማሩት ሙያ እየሰሩ አይደለም:: ዘርፉ እንዲህ ትኩረት አግኝቶ ከተሰራበት ባለሙያዎቹ ወደ ሙያ ዘርፋቸው ለመመለስና ለመሰማራት ዕድል ይሰጣቸዋል:: በግላቸውም የሚጠብቁት በመሆኑ ደስተኛ ናቸው::
ተጨባጭ የሆነ ነገር ባለሀብቱ እንዲሰራ ያነቃቃል:: ዜጋውም የአገሩን ሀብትና ከዘርፉ ስለሚገኘው ገቢ ግንዛቤ እንዲኖረው ያስችለዋል:: ስለጥቅሙ ሲረዳ ደግሞ በባለቤትነት ስሜት ሀብቱን ይጠብቃል:: ይንከባከባል:: ተቆርቋሪነቱ ሲጠናከር ወደ ግጭት የሚያመራው ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ያስችላል:: የፖለቲካ አጀንዳ መሆኑም ይቀንሳል:: ኢንቨስትመንትን ለመሳብም ሆነ ለተለያየ ነገር መረጃ ወሳኝ በመሆኑ መረጃ የሚገኝበት ነገር መደራጀቱ በመልካም ጎን ይወሰዳል::
መንግሥት ለዘርፉ ስለሰጠው ትኩረት ፕሮፌሰር ገዛኸኝ እንደተናገሩት፤ በአንድ ጊዜ ሁሉንም መሥራትም ሆነ ትኩረት መስጠት የሚቻል ባለመሆኑ መንግሥት ውስጣዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ አዋጭ በሚላቸው አገራዊ ጠቀሜታ ባላቸው የማእድን ሀብቶች ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ መንቀሳቀስና መሥራት፣ ፖሊሲም መቅረጽ ዋና ተግባሩ በመሆኑ ኃላፊነቱን በዚህ መንገድ መወጣቱን መገንዘብ ይቻላል::
እስከ አሁን በግብርና እና የግብርና ውጤቶች፣ በኢንዱስትሪው ላይ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል:: አሁን ደግሞ የማዕድን ልማቱን ተጨማሪ አድርጎታል:: በማዕድን ዘርፉ የሚደረገው እንቅስቃሴ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ደግሞ ቀዝቀዝ እያለ እንጂ ትኩረት የተነፈገው እንዳልበርም አስታውሰው፣ አሁን ላይ ይበልጥ ትኩረት ማግኘቱን ተናግረዋል::
እንደ ፕሮፌሰር ገዛኸኝ ማብራሪያ የማዕድን ዘርፍ በጥናትና ምርምር መደገፍ አለበት:: ኢትዮጵያ እምቅ የሆነ የማዕድን ሀብት አላት ሲባል በመረጃ የተደገፈ መሆን ይኖርበታል:: የሀብት አይነቱ፣ መጠኑና አዋጭነቱ የሚታወቀው በጥናትና ምርምር የታገዘ ሥራ ሲሰራ ነው:: በጥናትና ምርምር አሁን አገሪቱ አላት ከሚባለው በላይ ሀብቱ ሊኖራት ይችላል:: አመላካች የሆኑ ነገሮችም አሉ::
የወርቅ ወይንም የሌላ ማዕድን ዋጋ ገበያ አንዴ ወደ ላይ ይወጣል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ወደታች ይወርዳል:: ፍላጎት በሚኖርበት ወቅት የወርቅ ማዕድን አውጭዎች ለፍለጋ በስፋት ይሰማራሉ:: አጋጣሚውን ለመጠቀምና ገበያውን ለመያዝ ቀድሞ በጥናትና ምርምር ለይቶ መዘጋጀት ያስፈልጋል:: በተለይም እንዲህ ያለው ዝግጅት በአገር አቅም በማይቻል ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በሚፈልጉት ላይ ነው መሆን ያለበት::
ኢትዮጵያ ሰፋ ባለ ሁኔታ የማዕድን ሀብቷን ለማስተዋወቅና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የጀመረችው እንቅስቃሴ በማዕድን ሀብታቸው ታዋቂ የሆኑት እንደ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያ ያሉ አገሮች ተሞክሮው እንዳላቸውና ይህ ደግሞ ዜጋው ሳይቀር ስለሀብቱ እንዲያውቅ ያስቻለ መሆኑን ፕሮፌሰር ገዛኸኝ አስታውሰዋል::
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12/2014