“ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ከመባሉ አስቀድሞ ብሂላችን “ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ” በማለት ለራስ ችግር መፍትሄ ከራስ መሆን እንዳለበት፤ ሊሆንም እንደሚገባ አምነንበት ስንጠቀምበት ኖረናል። ሌላው ቀርቶ በተረቶቻችን ከአፋችን ወርዶ አያውቅም። ከዛሬው እንግዳችን የምንረዳውም ይህንኑ ሲሆን ሌሎችም ሲያደርጉት፤ ለችግሮቻችን መፍትሄ አመንጭዎቹ ራሳችን ልንሆን እንደሚገባ ሲጥሩ ኖረዋል። በተለይ በቀደመው ዓለም፣ በጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ለራሳችን ችግር መፍትሄው ራሳችን ከመሆን አልፈን ለሌላው ሁሉ ስንተርፍ ስለ መኖራችን ማስረጃዎቹ ብዙ ናቸው።
ከባህላዊ አልባሳት አልፈን፤ ከባህላዊ አመጋገብ ዘልለን እስከ ባህላዊ ህክምናና ግጭት አወጋገድ ድረስ የዘለቅን ስለመሆናችን አይደለም ያኔ ዛሬም የሚመሰክረው ብዙ ነው። ባጭሩ፣ ያኔ ለሚያስፈልጉን ጉዳዮች ሁሉ መፍትሄዎቹ እራሳችን ነበር እያልን ነው። ጥገኞች አልነበርንም እያልን ነው። ለእውቀት፣ ለጥበብ፣ መፍትሄዎችን ለማፍለቅ ወዘተ ጉጉ ነበርን እያልን ነው። “ዛሬስ?” የዛሬው ዝግጅታችን ይህንን ጥያቄ መመለስ ባለመሆኑ ጉዳዩን ለሌላ ጊዜ አሳድረን ወደ ዛሬው እንግዳችን እንመለስ። የዛሬው እንግዳችን አቶ ጌቱ በቀለ ይባላሉ። ነዋሪነታቸው ኦሮሚያ ክልል፣ ዓለም ገና ከተማ ነው።
አቶ ጌቱ በባህሪያቸው ፈጣን ናቸው። ለነገሮች ጊዜ የሚሰጥ አይነት ተፈጥሮ የላቸውም። ሁሉም ነገር ከኛ ማለፍ የለበትም። የሁሉም አይነት ችግር መፍትሄው ከእኛው ጋር አለ። ከእኛው ሊመነጭም ይገባል ባይነት የሚታይባቸው ደፋር ሰው ናቸው። አገራዊ ስሜታቸው ከአስተሳሰባቸው ከመታወቁም ባለፈ በየአጋጣሚው ኢትዮጵያዊነትን ሲያጎሉ ነው የሚሰሙት። ሲናገሩ ኢትዮጵያ አለች፤ ሲሰሩም ኢትዮጵያ ውስጣቸው ነች። ከማንምና ከምንም በላይ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ከፍ እንዲል ነው የሚፈልጉት።
ባለ ትዳርና የልጆች አባት የሆኑት አቶ ጌቱ በሚያልፍ ሕይወታቸው የማያልፍ ስራ ሰርቶ ማለፍን ከሚመርጡት ሰዎች ነው ምድባቸው። ይህ ደግሞ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ ሙሉ ለሙሉ ሲንፀባረቅ የነበረና ባከናወኗቸው ተግባራትም ውስጥ በሚገባ የሚታይ ነው።
አቶ ጌቱ የሚሰሩትና እንዲሰራም የሚፈልጉት የሰው ልጅ ጭንቅላት ላይ ነው። በተለይም እውቀት ላይ። የእውቀት ዋና መገኛ ምንጩ ደግሞ ማንበብ መሆኑን የተረዱ ናቸው። በመሆኑም የሁሉም ስራዎቻቸው ድምር አቅጣጫው የሚያመለክተው ወደዚያው፤ ወደ ንባብ ነው።
አቶ ጌቱ በቀለ በማህበረሰብ፣ በተለይም በትውልድ ወደኋላ መቅረት ደስተኛ አይደሉም፤ ብቻ ሳይሆን የሚፀፀቱ ሰውም ናቸው። ሰው ወደኋላ መቅረት የለበትም የሚል ሙሉ እምነት አላቸው። እሳቸው ራሳቸው ከንባብ ብዙ ያተረፉ፤ ምናልባትም በንባብ አማካኝነት ከ18 በላይ የሙያ አይነቶችን የቀሰሙ፤ የሙያዎች ባለቤት የሆኑ ሰው ናቸው። ንባብ “ከሁሉም በላይ በʻእችላለሁ’ ስሜት እንድንቀሳቀስ አድርጎኛል” ነው የሚሉት። በመሆኑም በእነ “ፈለገ ብርሃን”፣ “ያልታየው ብርሃን የሥነፅሁፍ ምሽት ክበብ” አማካኝነት ወጣቱን ወደ ንባብ ሕይወት ለማምጣትና የአገራችንን የንባብ ባህል ለማሳደግ ሁሌም እንደ ተጉ ነው እዚህ የደረሱት።
አቶ ጌቱ የንባብ ውጤት ናቸው። በአሁኑ ሰዓት በፈርኒቸር ስራ ሙያ ላይ የተሰማሩ ይሁኑ እንጂ፤ ስፖርተኛ ናቸው፤ የእግር ኳስ አሰልጣኝ ናቸው። መድረክ መሪ ብቻም ሳይሆኑ መድረክ አስተባባሪና አስተዋዋቂም ናቸው። ግንበኛ ብቻም ሳይሆኑ ቀለም ቀቢም ናቸው። “ብዙ ብዙ ነገሮችን መስራት እችላለሁ። ይህ ሁሉ ታዲያ በማንበቤ ምክንያት የመጣ ነው” ሲሉ በኩራት ይናገራሉ። ከእሳቸው አንጻር ሲገመግሙት ደግሞ የአሁኑ አብዛኛው ትውልድ ያለበት ሁኔታ ይጸጸታቸዋል። ስለዚህም ይሄን መጥፎ ባህል መቀየር አለብን ብለው ያስባሉ። ‹‹በአሁኑ ሰዓት ወጣቱ ጥገኛ ሆኗል፤ ስራ ጠባቂ ሆኗል፤ ከእውቀት ተገልሏል፤ አቋራጭ መንገድ ፈላጊ ሆኗል፤ እራሱን ችሎ እንዳይቆም ሁሉ እየተደረገ ነው። ከዚህ ሁሉ ውስብስብ ችግር መውጣት የሚችለው ደግሞ በእውቀት እና በንባብ ነው።›› ይላሉ። እርሳቸው ህብረተሰቡን እያሳተፉ የሚገኙት በንባብ ብቻ አይደለም፤ “ሁለንተናዊ” በሚባል ደረጃ ነው። በመሆኑም ስፖርተኞችን አፍርተዋል። በጋዜጠኝነቱም አሉበት፤ (በተለይ በኤፍ ኤም ሬዲዮኖች) በርካታ ጋዜጠኞችን አፍርተዋል። የፊልም ስክሪፕት ፀሐፍትን ሳይቀር አብቀለዋል። ክበባቸው በድርሰቱ ዓለምም ይሳተፋል/ያሳትፋልና በርካታ ገጣሚያንንና ፀሐፍትን ማስከተል ችለዋል። የፈርኒቸር ባለሙያዎችን በተመሳሳይ አውጥተዋል። ሌሎች በርካቶችንም በልዩ ልዩ ዘርፎች አፍርተዋል (ሁሉንም በስማቸው እየጠሩ ነው የነገሩን። የአቶ ጌቱ ማህበራዊና ሙያዊ አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የዜግነት ግዴታን ከመወጣት አኳያም ሲታይ ጉዳዩ ከፍ ያለ ነው።
ይህን ሁሉ ፍሬ እንጥቀስላቸው እንጂ አቶ ጌቱ ስራቸውን ሲያከናውኑ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አይደለም። በርካታ እንቅፋቶች እያደነቃቀፏቸው ነው እዚህ የደረሱት። ከ”ይሄ እብድ (መራታ) . . .፣ እብዱ መጣ . . .፣ እብዱ ጀመረ . . .” ከሚሉ ቅስም ሰባሪ አስተያየቶች ጀምሮ፣ እስከ የስራ ቦታቸውን ማፍረስ፣ የክበብ አባላቱ የሚሰበሰቡበትን ቤት መብራት ማጥፋት፤ በጀነሬተር ለመጠቀም ሲሞክሩም መከልከል፤ በግልፅ “ወጣቱን ታነሳሳለህ” በሚል መወቀስ ወዘተ ሁሉ ካጋጠሟቸው ችግሮች በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።
ይሁን እንጂ አቶ ጌቱ በተፈጥሯቸው ተስፋ የሚቆርጡ አይደሉምና ተስፋ ሳይቆርጡ፤ ለማንምና ለምንም ሳይንበረከኩ ስራቸውን በመቀጠል ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ የደረሱ ሰው ናቸው፤ ይህ አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የሚናገሩት።
‹‹በ1997 አካባቢ የነበረን እንቅስቃሴ ከ97 ምርጫ ጋር በተያያዘ ታገደ፤ ክበባችንም ተዘጋ። የተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮችን ስናደርግ የነበርን ቢሆንም ሁሉም እንዲቋረጡብን ተደረገ፤ ሰው ፋብሪካ ሲያቃጥል እኛ ስፖርታዊ ውድድር በማድረጋችን ተቃውሞ ገጠመን። ሁሉንም እያለፍን ነው እዚህ የደረስነው›› የሚሉት አቶ ጌቱ፤ ኢትዮጵያ . . . ኢትዮጵያ . . . በማለታቸው ብቻ እንደ ፖለቲካ አመለካከት ተቆጥሮባቸው ከፍተኛ ወከባ ውስጥ ሲገቡ እንደ ቆዩ፤ ኢትዮጵያዊነትን የማይወዱ የሚሰሯቸውን ስራዎች እንደማይወዱላቸው ነው የሚናገሩት። በአገር ፍቅር ላይ የሚሰሩትንም ስራ እማይደግፉላቸው ብዙዎች ናቸው። የንባብ ባህልን በየትምህርት ቤቶች ለማስፋፋት የምናደርገው ጥረት ሁሌም እንቅፋት እንደ ገጠመው ነው በማለት የነበረውን ውጣውረድ ያስታውሳሉ።
“በቀለ የንባብ፣ ሥነ ሥዕልና ግብረ ገብ ክህሎት ሙከራ ትምህርት ቤት” በሚል ስያሜ ማሰልጠኛ ከፍተው መንቀሳቀስ ሁሉ ጀምረው ነበር፤ መቀጠል አልቻሉም። የንባብ ስልጠና ይሰጡ ነበር፤ ኮሮኮንቹ በዛባቸው። ከ180 በላይ አባላት ቢኖሯቸውም ወደ ንባብ የሚመጡት በጣት ከሚቆጠሩ ሊበልጡ አልቻሉም።
የንባብ ክበቡ አባላት ያሉት ሲሆን አባላቱ ሁለት አይነት ክፍያን ይፈፅማሉ፤ 40 እና 60 ብር። ባለ 40ዎቹ በአንድ ጊዜ አንድ መፅሀፍ መዋስ ሲችሉ፤ ባለ 60ዎቹ በአንድ ጊዜ ሁለት መፃህፍትን መዋስ እንደሚችሉ የሚናገሩት አቶ ጌቱ በተለያዩ ጊዜያት (ለምሳሌ በ10ኛው ዙር) በርካታ ቁጥር ያላቸው መፃህፍትን (ከ900 በላይ) ለተቋማት ለግሰዋል።
አባላት መዋስና ዝም ብሎ “አንብቤያለሁ” ብሎ መመለስ ብቻ ሳይሆን፤ በርካታ ተግባራት ይጠበቁባቸዋል። ስላነበቡት መፅሀፍ ምንነት ይናገራሉ፤ ለአባላት ጭብጡን በተመለከተ የዳሰሳ ፅሁፍ (ቡክ ሪቪው) ያቀርባሉ። በየወሩ እሁድ የመፃህፍት ቀን ይከበራል፤ እዛ ላይ የሚያቀርቧቸው ስራዎች ሁሉ አሉ። ኢትዮጵያ “የንባብ ቀን” እንዲኖራት የሚሰሩት ስራ አለ።
ይህ ብቻም አይደለም፣ ይህንን ቃለ መጠይቅ ሊያደርግ በሄደው ጋዜጠኛ አማካኝነትም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (እያከናወነ ላለው የመፃህፍት ማሰባሰብና ለአብርኆት ቤተ መፃህፍት የማስገባት ተግባር እገዛ የሚሆን) 93 መፃህፍትንም ለግሰዋል።
ከማንም በፊት “ኢትዮጵያ የንባብ ቀን ያስፈልጋታል” የሚል ሀሳብን በማቀንቀንና ለመንግስት ተደጋጋሚ ጥያቄን በማቅረብ እዚህ የደረሰው የአቶ ጌቱ በቀለና አባሎቻቸው እንቅስቃሴ “የንባብ ባህል በኢትዮጵያ” በሚል ርእስ መጽሐፍ የማሳተም እቅድ እንዳለውም አቶ ጌቱ ይናገራሉ።
ይህንን ሁሉ ስናደርግ ያለ ድጋፍ አይደለም የሚሉት አቶ ጌቱ በዶክተር እንዳለጌታ ከበደ የሚመራው “ዛጎል ቤተ መፃህፍት” ከፍተኛ የመፃህፍት እገዛ ሲያደርግላቸው እንደ ነበረ፤ 200 መፃህፍትንም እንደ ሰጣቸው የገለፁ ሲሆን ይህም ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር በከፍተኛ ሁኔታ እንዳበረታታቸውም ይናገራሉ።
በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን አካሂደዋል። እነ አቶ ጌቱን ከሌሎች ስፖርታዊ ውድድር አድራጊዎች ለየት የሚያደርጋቸው አንድ ነገር ያለ ሲሆን፤ እሱም ከውድደሩ በኋላ የእነሱ ሽልማት ዋንጫ ሳይሆን መፃህፍት መሆኑ ነው።
ይህ የመፃህፍት መሸለም ተግባራቸው በብዙዎ እንዲደነቁ፤ እንዲመሰገኑ ከማድረጉም በላይ በ12ኛው ዙር ውድድር አቶ ጌቱ በቀለ የበጎ ሰው ሽልማትን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
አቶ ጌቱ በቀለ የመሰረቱትና የሚመሩት ይህ ማህበራዊ ተሳትፎን የሚያከናውን ክበብ በብዙ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰራ ሲሆን፤ በጤና ላይ ይሰራል። “የእናቶች ቀን”ን ያከብራል። በተለያዩ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመገኘት ስለ ግጭት አፈታት ያስተምራል። በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የሰጠው ስልጠናም አንዱና ተጠቃሹ ነው።
አቶ ጌቱ እንደሚናገሩት ይህንን የሚያክል ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን በሚወጡበት ወቅት ከአካባቢው የስራ ሀላፊዎች እያገኙ ያሉት ድጋፍ የሚያበረታታ አይደለም። እንደውም እንደ አንድ የፖለቲካ ክንፍ እሚታዩበትና አላስፈላጊ ጫና የሚፈጠርባቸው ጊዜ አለ። ይፈሯቸዋል። ወጣቱን ያነሳሳብናል፣ … የሚል ስጋት ሁሉ ያድርባቸዋል። ባህልና ቱሪዝምን የሚመለከቱ መስሪያ ቤቶች አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ ሲገባቸው አያደርጉም፤ እንዲያውቁት ሁሉ ሲደረጉ ምንም አይነት ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ አይደሉም። በመሆኑም በሚፈለገው መሰረት ለወጣቱ የንባብ ልምድንም ሆነ ሌላውን ለማካፈል አልተቻለም። ባጭሩ፣ ወጣቱን በሚፈለገው መጠን ወደ ንባብ ባህል ማምጣት አልተቻለም።
በአሁኑ ሰዓት ወጣቱ ብዙም ባለ ማስተዋል ወደ አልተፈለገ ግጭት ውስጥ ሲገባ የመታየቱን፣ አልፎ አልፎም በሌሎች አጀንዳ የመጠለፉን ወዘተ ጉዳይ በተመለከተም፤
ይህ ወጣቱ የተሰራበት ስሪት ውጤት ነው። እንዲህ እንዲሆን ነው የተሰራው፤ እየተሰራም ያለው። ጥገኛ እንዲሆን ተፈልጎ ነው የተሰራው። የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲህ እንዲሆን ነው እያደረጉት ያሉት። ጥገኛ ትውልድ እየፈጠሩ ነው። በራሱ የሚተማመንና በሌላውም የሚያምን እንዳይሆን ነው እያደረጉት። ወደ ውጭ የሚያይ ትውልድ መፍጠር ላይ ነው እየተሰራ ያለው። መስራትን ሳይሆን የውርስ ሀብትን የሚጠብቅ ትውልድ እየፈጠሩ ነው ያሉት። ህልም የሌለው ትውልድ እየፈጠሩ ነው ያሉት። የቴክኖሎጂ ተገዥ ነው። አያነብም፤ ከስክሪን ውጭ ሀርድ ኮፒ (መፃህፍት) ጋር ትውውቁ እምብዛም ነው። ትልቁ ችግር ይህ ነው። ይህ ደግሞ የሚወገደው በእውቀት ነው፤ ቀደም ሲል እንደገለፅኩት፣ በንባብ እንጂ በሌላ አይደለም። ስለዚህ የንባብ ባህልን ማሳደግና ወጣቱን ወደ እዚህ ውስጥ ማስገባት የግድ ይሆናል በማለት ያብራራሉ።
ግርማ መንግሥቴ እና አብዱረዛቅ መሐመድ
አዲስ ዘመን ግንቦት 12 ቀን 2014 ዓ.ም