ፖለቲካ ማለት በቡድን ያሉ ግለሰቦች የጋራ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሚያስችላቸው ሂደት ነው። በዚህ ምክንያት ምንም እንኳ ፖለቲካ የሚለው ቃል ብዙ ጊዜ ከአገርና ከመንግሥት ጋር የተገናኘ ቢሆንም በሌላ አንጻር የሰው ልጆች በቡድን ሆነው በሚገኙበት ማናቸውም ስብስብ ይገኛል፣ ለምሳሌ በኩባንያዎች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሃይማኖት መዋቅሮች፣ በቤተሰቦች ውስጥ ሳይቀር ፖለቲካ አለ። የኃይል አመዳደብ፣ የቁጥጥር፣ የውሳኔ ላይ መድረስ፣ የምጣኔ ሃብት ክፍፍል ጥያቄዎች በሁለትና ከዚያ በላይ ባሉ ሰዎች መካከል ሲነሱ ያንን ጥያቄ ለመፍታት በሚደረግ ሂደት፣ በዚያ ፖለቲካ አለ። ከዚህ አንጻር በአንዳንዶች አስተሳሰብ አብዮት፣ ጦርነት፣ ማህበረሰባዊ ግጭት ፖለቲካ ሳይሆኑ የፖለቲካ ሂደቱ ክሽፈት ናቸው። በሌሎች አስተያየት እኒህም የአጠቃላይ ሂደቱ አካል ስለሆኑ እንደ ፖለቲካ ይወሰዳሉ ሲል ዊኪፒዲያ ስለ ፖለቲካ ምንነት ይተነትናል፡።
ፖለቲካ ይህ ከሆነ ዘንዳ አንዳንድ ምሁራን ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዲህ ሲሉ ይገልፁታል። ፖለቲካችን ከሽኩቻ፣ ከጥሎ ማለፍ እና ሴራ አልተላቀቀም። ቅንነት የሌለበት የሕይወት እንቅስቃሴ ሁሉ ጨው የሌለው ወጥ እንደማለት ነው። ነገራችንን ሁለ አያጣፍጠውም።
ኢትዮጵያውያን በባህሪያችን በሌሎች ላይ መፍረድ ልማዳችን ነው። አትፍረድ ይፈረድብሃል፤ ባልንጀራህን ከራስህ አስበልጠህ ውደድ፤ ሁለት ካለህ አንዱን አካፍል ወዘተ…. የሚሉት የአምላክ መመሪያዎች ብዙም ትኩረት የሰጠናቸው አይደሉም፤ እናም ሁልጊዜ ነገሮችን የምንረዳበት መነጽር ሁሉ ከነባራዊ ሁኔታዎች (ለምሳሌ ከጊዜ፣ ከቦታ፣ ከሁኔታ) አንጻር ሳይሆን ከራሳችን ፍላጎት አንጻር ነው።
ነገራችንን ስንመዝን ከራሳችን ድክመት ወይም ጥንካሬ አንጻር ሳይሆን በቅርባችን ካለ፣ ከምናውቃቸው ሰዎች ነው። ኑሯችን ሁሉ ከራሳችን ጋር ሳይሆን በሌሎች ሕይወት ውስጥ ነው። በዚህም ነው በነገራችን ሁሉ መሻሻሉን ለማምጣት እንድንችል መሠረታዊ የሆነው የራስን ድክመትና ጥንካሬ ማወቅ ፍላጎቱንም አቅሙንም ያጣነነው። የዚህ ውጤት ወይም ነጸብራቅ ደግሞ ዘወትር በማያልቅና አላአስፈሊጊ ፉክክር ወይም ሽኩቻ ውስጥ መሆናችን ነው። እኔስ ከማን አንሼ የሕይወት መመሪያችን ነው። የአንዳችን ማሸነፍ የሌላችን መሸነፍ፤ የአንዱ መሻል የሌላው መቆርቆር፤ የአንዱ ማግኘት የሌላው ማጣት፤ የአንዳችን ማግኘት የሌላው ማጣት ይመስለኛል ሲሉ አሁናዊ ፖለቲካው ይተነትኑታል።
የዛሬ የአዲስ ዘመን እንግዳ በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑት አቶ ትዕዛዙ ናቸው። እርሳቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ዳራ፣ የፖለቲካ ምንነትና የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ብሎም የዓለም የፖለቲካ ጉዞ እና ኢትዮጵያ አካሄድን አስመልክቶ ሙያዊ ሃሳቦችን ሰንዝረዋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- ወቅታዊ የኢትዮጵያን እና ዓለም አቀፉ ፖለቲካ ግንኙነት እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ትዕዛዙ፡- በብዙ መንገድ ማየት ይቻላል። እንደሚታወቀው የውጭው ፖለቲካ ውስጣዊ ፖለቲካ ላይ የራሱ አስተዋፅኦ አለው። ውስጣዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴው ከውጭው ዓለም ጋር ለሚደረገው ግንኙነት የራሱ የሆነ አዎንታዊና አሉታዊ ትርጉም አለው። በአሁኑ ወቅ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚታወቅ ነው። እስካሁን ድረስ ያልተቋጨና ከአሸባሪ ሕወሓት ጋር ያለው ጦርነት አልተቋጨም። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ከራሳቸው ብሔራዊ ጥቅምጋር በተያያዘ አቋም ይዘዋል። ተደጋግሞ ሲነገር እንደነበረው በአሁኑ ወቅት የአሜሪካ እና የምዕራባውያን አቋም ከኢትዮጵያ ጋር በተቃርኖ የቆመ ነው። ይህ የሚያሳየን ውስጣዊ የፖለቲካ ትኩሳታችንና ያለን ወቅታዊ ሁኔታ ከውጭው ዓለም ፖለቲካ ጋር በቀጥታ እንደሚገናኝ እንደማሳያ የሚወሰድ ነው።
ብዙውን ጊዜ የውጭ ግንኙነት የሚመሠረተው በአገራት ብሔራዊ ጥቅም ላይ ነው። መንግሥታትም የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያቸውን ሲያረቁ ከብሔራዊ ጥቅማቸው ጋር በተሳሰሰረ መንገድ ነው። የሕወሓትን አካሄድ ብንመለከት ምዕራበውያን የወገኑለት ቡድን ነው። ይህ ማለት ከምዕራባውያን ስትራቴጂክ ጥቅምና ፖሊሲ አኳያ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የእነርሱን ብሔራዊ ጥቅምና ስትራቴጂክ አጋርነት አያሳካም ብለው ስለሚያስቡ ይህን መሰል እና ድጋፍ ለሕወሓት እያደረጉ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። አሁን ያለንበት ሁኔታ የሚያሳየውና የሚያሳየው ፖለቲካዊ ምስልም ይህንኑ የሚያስረግጥ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ሁኔታ ዓለም ለሁለት ጎራ የተከፈለ ነበር። በሌላ በኩል የዩክሬን ጉዳይ የዓለም ፖለቲካ ሽኩቻ ይታወቃል። የእነዚህ ድምር ውጤትስ?
አቶ ትዕዛዙ፡- እንደአጠቃላይ ልዕለ ኃያላን የምንላቸው አገራትና መንግሥታት እርስ በእርስ የሚያደርጉት ሽኩቻ እኛ ዘንድ የሚያመጣው ጉዳትና ጥቅም አለ። የዩክሬን እና ራሺያ ጉዳይ ብንመለከት የልዕለ ኃያላን አገራት በጥቅም ላይ የሚያደርጉት ሽኩቻ ነው።
ይህ ለኢትዮጵያ ይዞ የመጣው ጥቅም ቢኖር ምዕራባውያን ለጊዜውም ቢሆን ዓይናቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ነቅለው ወደ ዩክሬንና ራሺያ ትኩረት አድርገዋል። እኛ ግን ይህን ክፍተት መጠቀም አለብን። በርካታ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁራንም የሚመክሩት ይህንኑ ነው። መንግሥትም በፍጥነት መሥራት የሚገባውን ሥራ መሥራት አለበት የሚል አቋም አለ።
በንፅፅር ምዕራባውያንና አሜሪካ ከእኛ ጋር ስትራቴጂክ ጥቅም የላቸውም ማለት አይደለም። ነገር ግን የዩክሬን ጉዳይ ጊዜ የማይሰጣቸውና እጅግ እንቅልፍ የነሳቸው በመሆኑ ትኩረታቸውን በሙሉ ወደዚያ አድርገዋል። በዚህ አጋጣሚ አቅማቸውን ለማሳየትና ራሺያን ለማዳከም የሚጣጣሩበት ወቅት እንደሆነ በግልፅ እየታየ ነው። ምዕራባውያን በመተባበር እና አሜሪካ በበላይነት እየመሩት ባለው በዚህ ፖለቲካዊ ዘመቻ በዓለም ላይ የሚደረገውን እየተመለከትን ነው። በዚህ የጦርነት ወቅት ለዩክሬን ያልተደረገ ድጋፍ የለም። በገፍ የጦር መሳሪያ ወደ ዩክሬን እየጓጓዘ ነው። በቀጥታ በጦርነቱ ላይ እየተሳተፉ ነው ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር ቢከብድም ማዕቀብ በማዕቀብ ላይ እየጣሉ ራሺያን ለማዳከም እየሠሩ ነው። ይህ ሁሉ የሆነው ኃያላን በፈጠሩት ሽኩቻ ሲሆን በድሃ አገራት ላይ ደግሞ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑ ግልጽ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አሁን በሚስተዋለው የዓለም የፖለቲካ ሚዛን ውስጥ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ናት ወይስ ተጎጂ?
አቶ ትዕዛዙ፡- አሁን የሚስተዋለው የዓለም የፖለቲካ ትግልና አካሄድ ዓለምን ያልተማከለ ወደ ሆነ ዓለም እየወሰዳት ስለመሆኑ በርካቶች እየተናገሩ ነው። ለበርካታ ዓመታት በዓለም የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና የጦር ሚና ላይ አሜሪካ በብቸኝነት እየመራች ነበር። በዚህ ውስጥ ወዳጅ ናቸው፤ ለእኔ አካሄድም ይበጁኛል ያለቻቸው ምዕራባውያንን በማስከተል ብዙውን ነገር ስትቆጣጠር፤ በብቸኝነት ፈላጭ ቆራጭ ሆና ቆይታለች። በዚህ ዓለምን እንደአንድ አድርጎ የመቆጣጠርና የመግዛት አዝማሚያዎችና ፍላጎቶች በሰፊው ሲንፀባረቁ ኖረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የአሜሪካን የኃይል ሚዛን የሚገዳደሩና የምዕራባውያንን አለንባይነት የሚፈታተኑ ፖለቲካ ኃይል ሚዛን በእጅጉ እየጎላ ነው። ይህ ደግሞ አሜሪካ ዓለምን በብቸኝነት ለመቆጣጠርና ለመምራት በምታደርገው ጥረት ላይ ትልቅ አደጋ የጣለ አድርጋ የምትወስድ መሆኑ ግልፅ ነው። በየአቅጣጫው በዓለም ላይ ተገዳዳሪ የሆኑ ኃይሎች እየተበራከቱና ለብሔራዊ ጥቅማቸው በሚበጃቸው መንገድ ጎራም እየፈጠሩ ነው። ታዲያ ይህ በዓለም የፖለቲካ አሰላለፍና አወቃቀር ላይም የራሱ የሆነ አሻራ ጥሎ የማለፍ ዕድል እንደሚኖረውም የዘርፉ ምሁራን በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው።
በአሁኑ ወቅት ቻይና ፣ሩሲያ፣ ቱርክ፣ ሕንድ እና ሌሎች አገራት በሁሉም ዘርፍ በመጉላት ወደፊት እየመጡ ነው። በዚህም የአሜሪካን የበላይነት ፈተና ውስጥ እያስገቡት ነው። ይህ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ አገራት እንደ መልካም አጋጣሚ ወይንም ተጠቃሚነት ሊወሰድ ይችላል። ቀደም ሲል አሜሪካ በነበራት የኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ዓለምን እንደፈለገችው ትጠመዝዝ ከነበረበት አካሄድ በተወሰነ መንገድ ለመራመድ ዕድል ይሰጣል የሚል እሳቤ አለ። አሁን አጋር ኃይሎችን ለመጠቀም ዕድል ይሰጣል። ለአብነት በትግራይ ክልል በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ አሜሪካ ፈቃደኛ ባትሆንም የጦር መሳሪያ ከአሜሪካ ውጭ ከሆኑ እንደ ቱርክና የአረብ አገራት ስናገኝ ነበር። ይህ ከጥቅሞቹ እንደ አንዱ መወሰድ ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ዓለም አቀፍ ፖለቲካ ግንኙነትና አካሄድ ጉዳት አያመጣም?
አቶ ትዕዛዙ፡- የለውም ብሎ መደምደም አይቻልም። ዓለም ሲከፋፈል አለመረጋጋት ይዞ ይመጣል። የተከፋፈለ ዓለም ነው ያለው። ስለዚህ ግንኙነቶች በጣም የመስፋፋት እና የግጭት መስፋፋትም በዚያው ልክ ሊኖር ይችላል። ይህም የኢኮኖሚና ሰላም መናጋት ያመጣል። አንዱ የዓለም ክፍል ሲቃወስ ሌላውም በዚያው ልክ ይቃወሳል። ለአብነት በአሁኑ ወቅት በዩክሬን እና ራሺያ መካከል ያለውን ቀውስ ብንመለከት ዓለምን እያናጋው ይገኛል። በዚህ ዘንዳ ካየነው ጉዳቱ የከፋ የመሆን ዕድልም ይኖረዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከዓለም አቀፉ ፖለቲካ ግንኙነትና አካሄድ በመረዳት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙየፖለቲካ ፓርቲዎች በኃላፊነት እየተንቀሳቀሱ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ትዕዛዙ፡- በዓለም ላይ ያለውን የፖለቲካ ጎራ፣ አካሄድ እና ጫና በሚገባ መረዳት፣ መተንተንና መተንበይ ያስፈልጋል። በአጠቃላይ ታሪካዊ ዳራዎችን፣ አሁናዊ ሁኔታዎችንና የነገ ቢሆኖችን መገምገምና መረዳት ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የፖለቲከኞች፣ የመንግሥትና የዘርፉ ባለሙያዎች ኃላፊነት ነው። ነገሮችን በሚገባ መረዳትና ቁርጥ ያለ የፖለቲካ ማዕቀፍ ይዞ መንቀሳቀስ ይገባል። የፖለቲካ ሜዳውን ማወቅና መሠረታዊ ሥራቸውም መሆን አለበት፡ አንድ ፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፍ ሰው በተደራጀ መንገድ ፖለቲካን መሥራት የለበትም። ይህን ካለመረዳት የተነሳ በአገራችን ችግሮች ይስተዋላሉ።
በፖለቲካው ዓለም ከእኛ ጋር ስትራቴጂክ አጋር የምንላቸው እነማን ናቸው የሚለውን ማወቅ ይገባል። በዓለም ፖለቲካ ተጠቃሚ የሚያደርገን አካሄድ የቱ ነው የሚለውን ማወቅ ብሎም ሕዝብን በዚያው ልክ ማንቀሳቀስ ተገቢ ነው። ይህን እያደረጉ ነው ወይ የሚለውን ካነሳን በአንድም ይሁን በሌላው መልኩ እዚህ አገር በተለይም ስለ ፓርቲ ፖለቲካ ማውራት ከጀመርን ወዲህ በተለይም ከ1960ዎቹ የጀመረ ነው።
አብዛኞቹ ችግሮቻችን የሚመነጩት ከፖለቲከኞቻችን ነው ብንል ማጋነን አይመስለኝም። ፖለቲከኞቻችን የችግሩ መንሰኤ ከሆኑ ዋንኛው ነገር የዓለምን እና አገራዊ ሁኔታ ተረድተውት የፖለቲካ ፕሮግራም ቀርፀው እየተንቀሳቀሱ አይደለም ማለት ነው። ዘመናዊ ፖለቲካ ተጀመረበት ብለን የምናስበው 1960ዎቹ እንኳን ብናይ ከጅምሩ የፖለቲካ አካሄዳቸውን ብናይ የፖለቲካ ዕይታቸው፣ ፍልስፍናቸው የተወሰደው ከውጭ ነው። በወቅቱ ከዓለም ፖለቲካ ላይ ነግሶ የነበረውን ሌኒንዝም፣ ሶሻሊዝም በቀጥታ በመውሰድ ለመተግበር የሚደረግ ሙከራ ነበር።
ስለዚህ የዓለምና አገር ውስጥ ፖለቲካን በደንብ ባጣጣመ መንገድ መረዳትና ያንን ማስኬድ ላይ ችግር ነበር ማለት ነው። ያኔ አብዛኛው የሚስተዋለው መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ችግር ፈጣሪ ነበር። አይደለም ለአገሪቱ መጥቀም ቀርቶ እርስ በእርስ የሚጠፋፉ ሆነው ነው የተገኙት። ህልውናቸው እንዳይኖርም ያደረገ ነው። በመሆኑም የሕዝብና አገርን አጠቃላይ ሁኔታ ልትረዳ ከሆነ መሰል አዙሪት ውስጥ መልሶ የሚጥለን ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶች አሉ። ይሄን አስመልክቶ በየክልሉና በየከተማው የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መግለጫዎችን ያወጣሉ። ሕዝባዊና አገራዊ አንድነት የሚያስጠብቁና ችግሮችን የሚቃልሉ ናቸው ብለው ያስባሉ?
አቶ ትዕዛዙ፡– የዚህ አገር ችግር መሠረታዊ ምንጩ የፖለቲካ ልሂቃን ናቸው። የችግሩ ፈጣሪ ፖለቲከኞች ናቸው። ይህ ደግሞ የሚመነጨው ከሚከተሉት ፖለቲካ ፕሮግራም ነው። እዚህ አገር ዋነኛ የፖለቲካ መሰባሰቢያ መድረክ ዘውግ ወይንም ብሔርተኝነት ነው። ይህ ደግሞ የተመሠረተው ደግሞ የብሔርን ፖለቲካ ገዢ ሃሳብ አድርጎ ያስቀመጠው ሕገመንግሥቱ ነው። አብዛኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስልጣን ላይ ያለው ጭምር የብሔር ፖለቲካ ላይ ያተኮረ ነው። አንዱ ፓርቲ ለሆነ ብሔር ብቻ የቆመ ነው። አንዱ ከሌላው በተቃርኖ የቆመበት ፖለቲካና ሃሳብ ነው። ሁላቸውንም ብናይ ታሪክ የሚረዱበት፤ አንዱ አንዱ ፓርቲ ከሌላው ጋር ሲታይ ያላቸው የፓርቲ ራዕይ ሙሉ ለሙሉ የሚጋጭ፤ አንዱ ከሌላቸው በሐሳብም የማይስማማ ነው። አይደለም አብሮ ለመስራት ቀርቶ ሌላው አንደኛው አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ ሌላውን ለማጥፋት የሚሠራ ነው የሚመስለው። በመሆኑም የፖለቲካው ችግር ምንጭ የፖለቲካው ልሂቃን ናቸው። ስለዚህ ይህ መቅረት አለበት። ሕገመንግሥቱን ጨምሮ በዚህ መንገድ በፖለቲካ መደራጀትን በሕግ ማዕቀፍ መልክ ማስያዝ ይገባል። የአገሪቱን የረጅም ጉዞ የሚያመላክትና በጋራ ለመኖር የሚያስችል እንጂ እርስ በእርስ የሚጠፋፋ መልክ ይዞ መኬድ የለበትም። ይህ በጊዜ ካልተስተካከለ ለአገሪቱም አይጠቀምም። አገሪቱ ውስጥ የሚገኘውን የፖለቲካ አደጃጀትና ቀጣይ ዘመናትን ዕጣ ፈንታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ሥርዓትና የፖለቲካ ስሪት መፍጠር ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር በሰነድ የተደገፈ ፖለቲካዊ ሥርዓትን የመተግበር ችግር ወይስ ያልተከሰተን የፖለቲካ ሰነድ መፍጠር?
አቶ ትዕዛዙ፡- ሁለቱም ናቸው ብዬ አስባለሁ። በአንድ መልኩ ተግባር ዝም ብሎ አይመጣም። መነሻው ሃሳብ ነው። ሃሳብ የፖለቲካ ፓርቲ መነሻ ይሆንና ወደ ተግባር ይገባል። የእኛ አገር የብሔር ጽንፈኝነት መሠረታዊ ችግሩ ነው። ከዚህ በፊት የነበረው ሕወሓትና መሰሎቹ ይዘውት የመጡት ትርክት ነው። በሌላ በኩል የትግበራ ችግር ነው። ሌላው ቀርቶ ራሳቸው አልተገዙበትም። ሕጉ በራሱ ችግር የለበትም የአፈፃፀም እንጂ ይባላል።
መጀመሪያ መቅደም ያለበት ብሔራዊ ጥቅም ነው። እያንዳንዱ ጥያቄዎች የሚስተናገዱበትን ማበጀት የሚቻለው በዚህ ነው። ነገር ግን እዚህ አገር የሚደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች መጀመሪያ የሚያተኩሩት የወጡበት ብሔር እና ቋንቋ እንጂ አገር ላይ አይደለም።
ኢትዮጵያ የሚለውን በሁለተኛ ደረጃ የሚይዙ ናቸው። ሕወሓትና መሰሎቹ በዚህ ደረጃ አውርደውታል። ከኢትዮጵያ ህልውና በተቃራኒና በግብታዊነት የቆሙ ናቸው። አገራዊ የፖለቲካ ስትራቴጂ የላቸውም። ኢትዮጵያ እኛን ካልጠቀመች እንደፈለገች ትሁን የሚል ነው። ይህ ደግሞ በግልጽ ሕገመንግሥታዊ ድጋፍ ስላላቸው አይፈረድባቸውም። በመሆኑም ይህን ማስተካከል ያስፈልጋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የትግበራ ብቻ ሳይሆን የሕግ አለመሻሻል እና ጥሩ አለመሆን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችንና ፓርቲያቸውን ስብስብ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ትዕዛዙ፡- መሠረታዊ ነገሩ ይህ ነው። የዘመናዊ ፖለቲካ፤ ዴሞክራሲና መሰል ነገሮች የቅርብ ጊዜ ናቸው። ለዚህ ልምድና ባህሉ የለንም። በአፍሪካ አገራት አኳያም ገና ብዙ ይቀረናል። ገና የ50 ዓመት ልምድ ነው። ፖለቲከኞች ወደ ፖለቲካ እና ፓርቲ የሚገቡት መጀመሪያ ዓላማው ሕዝብን ማገልገል ነው፤ ምንም እንኳን ፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ መታገያ ስልት ቢሆንም። አስቀድሞ የሚታሰበው ግን አገርን መጥቀምና ሕዝብ ማገልገል ነው። ነገር ግን እዚህ አገር በተጨባጭ የሚታየው ብዙዎች ፓርቲዎች ሆኑ በግለሰብ የሚሳተፉት የግልና የተወሰነ ቡድን ብቻ ለመጠቅም ሲሠሩ፤ ሲያሴሩ፤ እርስ በእርስም ሲጠፋፉ እናያለን።
ተመሳሳይ ፖለቲካ አይዶሎጂ ኖሯቸው እንኳን አንዱ ሌላውን ያጠፋል። መኤሶን እና ኢህአፓን ብንመለከት በብዙ ነገር ተመሳሳይ ነበሩ። ፖለቲካችን ከሽኩቻ፣ ከጥሎ ማለፍ እና ሴራ ያልተላቀቀው በምንም ሳይሆን በልሂቃኖቻችን ባህሪያዊ ምክንያቶች ነው። የዚህ ሁሉ መሠረቱ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አጥፊ የፖለቲካ ባህላችን የራሱ አስተዋጽኦ አለው። ይህም ልዩነቶችን በንግግር ሳይሆን ከሆነ በጠብ፣ በሴራ፣ ካልሆነ በኩርፊያ መፍታት ባህላችን መሆኑ ነው።
ነገር ግን በተወሰነ የግል ጥቅም እና የተሻልኩ ነኝ በሚል እርስ በእርስ በመጠፋፋትና ለአሁኑ ፖለቲካ መጥፎ ጠባሳ ጥለው አልፈዋል። በሕግ አለመመራት፤ አገር አለማስቀደም፤ ቁርጠኛ አለመሆን ችግሮች አሉ። እነዚህ ከተስተካከሉ ወደፊት የተሻለ ነገሮችን ማየት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- ሸኔ እና መሰሎቹ የወጡበትን ብሔር ጭምር እየጎዱት ነው። ከዚህ አኳያስ የዘውጌ ፖለቲካ የራሱን ወገን በትክክል ይጠቅማል ማለት እንችላለን?
አቶ ትዕዛዙ፡- እውነታውን ያለመረዳት ችግር ነው። እነርሱ እንደሚያስቡት አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ አመጣጥና አኗኗር ይታወቃል። የሕዝቡን ትስስር የተረዱ አይመስልም። አሁንም ከዱሮ እሳቤ አልወጡም። ሕወሓትን ማየት በቂ ነው። የትግራይ ሕዝብ ያለበትን የተመለከተ ሌላ ምሳሌ አይፈልግም። ሸኔም ከዚህ የተለየ ዕድል የለውም። አሁን የሚስተዋለውን አለመረጋጋት ከመፍጠር የዘለለ ምንም ለውጥ አያመጡም። የተወሰነ ቡድን ችግር ነው ብለው የወሰዱትን የኢትዮጵያ ችግር ነው ብለው ወስደዋል። ግን እነርሱ እንደ ትልቅ አጀንዳ ያነሱት ትንሽ ችግር ነው።
እዚህ አገር የበርካቶች ፍላጎት ተመሳሳይ ነው። በሁሉም ሕዝብ ዘንድ ልማት፤ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ይፈልጋል። ነገር ግን እነዚህ ዘውጌ ፖለቲከኞች ብሔርን ወሰዱት እንደ ትልቁ የማታገያ ስልት አድርገው ነው። ይህ ማለት ደግሞ የኢትዮጵያን መሠረታዊ ችግሮችን የመተንተን የማወቅና ማስተካከል አቅማቸው አነስተኛ መሆኑን ያሳያል።
አዲስ ዘመን፡- ሸኔን የመሳሰሉ አካላት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እርስ በእርስ መከፋፈል መጀመራቸውም በሚዲያ ሰምተናል። ይህ ለምን የሆነ ይመስሎታል?
አቶ ትዕዛዙ፡-በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ መሰላቸት አለ። በሕዝቡ ላይ የሚያደርሱት እንግልትና በደል በጣም ጫፍ እየነካ ነው። የሚያመጡት ለውጥም እንደሌለ የተረዱ ይመስለኛል። ከአገር ውስጥና ከውጭ ሆነው አገር ለማፍረስ ከሚሠሩት ጋር ተናበው ቢሠሩም ምንም ሊያመጡ አልቻሉም። በመሆኑም በራሳቸው ሥራ የተሰላቹና ተስፋ የቆረጡ ይመስለኛል። ከዚህ በኋላ ያለውን ሕዝባዊ ጫና መቋቋም የሚቻላቸው አለመሆኑንም ይገነዘቡታል።
በዚህ ወቅት ግን በርካታ ሥራዎች መሠራት አለባቸው። በእነዚህ ቡድኖች መካከል የተፈጠረውን ሁኔታ ማጤን ያስፈልጋል። መንግሥት ክፍተቶችን በመጠቀም የተጠናከረ ሥራ መሥራት አለበት። በአሁኑ ወቅት እንደ አገር ሰፊ ችግር ውስጥ በመሆናችን ለመፍትሄ መሥራት አለብን። የሚወሰደው እርምጃም አስተማሪ እንዲሆን በተደጋጋሚ ሊታሰብበት ግድ ይላል። ሕዝብና መንግሥት የሚገኙትን ዕድል መጠቀም አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ ሆነው ሙያዊ ሐሳብዎትን ስላካፈሉን እናመሰግናለን።
አቶ ትዕዛዙ፡– እኔም ሐሳቤን እንዳካፍል ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ!
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ግንቦት 11/2014