የኢኮኖሚያችን የጀርባ አጥንት ሆኖ ዘመናትን የተሻገረው ግብርናችን ዛሬም ድረስ በሁለት እግሩ መቆም አቅቶት እየተንፏቀቀ እኛም በምግብ እህል ራሳችንን መቻል አቅቶን የባዕዳንን እጅ ጠባቂ ሆነን ለመቆየት ተገደናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ለዘርፉ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ምክንያት በተለይም በጋን በስንዴ ምርት ለማሳለፍ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተው ውጤትም እየታየባቸው ስለመሆኑ እየተነገረ ነው። ከዚህም ባሻገር ግብርናው ትራንስፎርም አድርጎ ሰዎች የግብርና ምርትን ሲያመርቱ ከቤተሰባቸው የቀለብ ፍጆታነት ባለፈ ለገበያም እንዲያመርቱ የማገዝ ሥራም እየተሠራ ስለመሆኑ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ይናገራሉ። እኛም በዚህና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግረናቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ ለመነሻ ይሆነን ዘንድ ግብርናን ትራንስፎርም ማድረግ ማለት ምን ማለት ነው?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ማለት ምርት አምርቶ በራስ ከመጠቀም ባለፈ ለገበያ ማቅረብ ወይም ደግሞ ለገበያ ማምረት ማለት ነው። እዚህ ላይ ትልቁ ሃሳብ ሰዎች የግብርና ምርቶችን ሲያመርቱ ለቤተሰባቸው ፍጆታ ብቻ የሚያመርቱ ከሆነ ብዙ ርቀው አይሄዱም። ብዙ ለውጥም አያመጡም። ነገር ግን ለንግድ ብለው የሚያመርቱ ከሆነ ምርቱ በስፋት በጥራት እንዲሁም በተወዳዳሪነት ለማምረት የሚያስችል ሥርዓት ውስጥ ይገባሉ ማለት ነው።
ይህንን ለማድረግ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። በነገራችን ላይ አብዛኞቹ ያደጉ አገራት የመሬት ስሪታቸው ሰፋፊ ግብርናን (እርሻን ) መያዝ የሚችል ነው። በተለይም ለንግድ የሚሠሩ ተቋማት አልያም ኩባንያዎች ሰፋፊ መሬቶችን በመያዝና ግብርናውን በሜካናይዜሽን በመደገፍ ይሠራሉ። እኛ አገር ባለሀብት ሆነው በዚህ አካሄድ የሚሆኑ ጥቂቶች ብቻ ሲሆኑ አብዛኛው አርሶ አደር ግን አነስተኛ ወይንም በትንሽ መሬት ላይ የሚሠሩ ሥራዎች ናቸው።
አሁን ባለንበት ሁኔታ መሬት የመንግሥትና የሕዝብ ነው፤ ያለንን የመሬት ስሪት ይዘን የግብርና ትራንስፎርሜሽንን እውን ለማድረግ ምን ማድረግ አለብን? ተብሎ ውይይት ተካሂዶበት በዚህም ስምምነት ላይ ደርሰን የቀጠልንበት አርሶ አደሮቹን ወደ ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ማምጣት ፤ ኩታ ገጠም በሆነ መልኩ እንዲያመርቱ ማድረግ ነው።
እዚህ ላይ ኩታ ገጠም ግብርና ዋናው ጥቅሙ አንድና ሁለት ሄክታር ያላቸው አርሶ አደሮች በተናጠል ቢያመርቱ አንደኛ አንድ ዓይነት ምርት አያመርቱም፤ ሁለተኛ ሜካናይዜሽን ለመጠቀም ያስቸግራል፤ በሦስተኛ ደረጃ ያመረቱት ምርት ትልቅ ሆኖ ለገበያ ለማቅረብም አይመችም። በመሆኑም የኮሜርሻላይዝድ ክላስተር አካሄድ እንዲለመድ በሚል ተስማምተን እየሠራን ነው።
በዚህ መሠረት ስንሄድ ደግሞ ሦስት ደረጃዎች አሉት፤ አንደኛው የአካባቢ የግብርና ሥነምህዳር ምንድን ነው? ሊመረትበት የሚችለው ምን ዓይነት ሰብል ነው? የበቆሎ አካባቢ ከሆነ በቆሎን እንደዚሁ በአካባቢው ስንዴ በብዛት ለማግኘት የሚያመች ከሆነ እንደዚያው ስንዴ በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አርሶ አደሮችን በዚያ መልክ አደራጅቶ ይዞ መሄድ ነው። ይህንን ዘዴ ተጠቅሞ በሚመረትበት ጊዜ ደግሞ የኮሜርሻላይዝድ ወረዳውን የክላስተር ወረዳ እንለዋለን። የዚህ ጥቅሙ ሊመረት የሚችለውን ሰብል በስፋት ማምረት ነው።
በዚህ ይለማመዱና ወደ እውነተኛ ኩታገጠም ወደሚባለው የአመራረት ሥርዓት ይገባሉ ማት ነው። ይህም ሁለተኛው ደረጃ ነው። ይህ በራሱ አርሶ አደሮቹ መሬታቸውን አንድ ላይ እንዲያዋህዱ ዕድል የሚሰጥ ሲሆን ይህም የሚሆንበት አካሄድ ደግሞ ከግማሽ እስከ አስር ሄክታር ያለው ይኖራል፤ እነዚህን መሬቶች በማዋሃድ ድንበር የሚባለውን ነገር ትተን የመሬቱን ስፋት ብቻ በመያዝ አንድ ላይ በማሽነሪ ይታረሳል አንድ ላይ ይዘራበታል በተመሳሳይ አንድ ላይ ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ይጨመሩበታል። ምርቱም በሚደርስ ጊዜ አንድ ላይ ተሰብስቦ በአንድ ቦታ ላይ እንዲቀመጥ ይሆናል። ከዚያም ለገበያ ይቀርባል። ይህ አካሄድ ደግሞ ምንን ይፈጥራል መሰለሽ፤ ሽርክና እንዲኖር ያደርጋል።
በመሆኑም ይህ መሬት የኔነው በዚህ ጋር ድንበሩ ነው የሚለው ነገር ይጠፋና ወደ ኢንተርፕራይዝነት ይተላለፋሉ። በዚህ ጊዜ ደግሞ ኩባንያ ይሆናሉ። በዚህ ደግሞ ምናልባት አርሶ አደሩ በኩባንያው ሊሠራ አልያም ደግሞ የሼሩ ተካፋይ ብቻ ሆኖ ሊኖር ይችላል። በመሆኑም በዚህ መልኩ ከፋፍለን እየሄድንበት ያለነው የአመራረት ለውጥ ነው እንግዲህ ግብርና ትራንስፎርሜሽን የሚባለው።
አዲስ ዘመን፦ የኩታ ገጠም አካሄድ ግብርናውን በማዘመን ወይም ትራንስፎርም በማድረግ በኩል ጥሩ ነው፤ ነገር ግን በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ብዙ ርቀት ተሂዶበታል? ለመሄድስ ያስችላል? የአርሶ አደሩ አረዳድስ ምን ይመስላል?
ዶክተር ማንደፍሮ ፦ ውጤታማ የሆኑ እንዳሉ ሁሉ መሻሻል ያለባቸው አካባቢዎችም አሉ። ለምሳሌ ድሮም ቢሆን የግብርና ቴክኖሎጂን ይዘን ገጠር ስንገባ ቶሎ የሚቀበል አርሶ አደር አለ፤ ቶሎ የማይቀበል ወይም የሚጠራጠርም አለ፤ በአንጻሩ ደግሞ ምንም ለውጥ የማይፈልግ አርሶ አደርም አለ። እነዚህ ሦሰት ምድቦች ደግሞ የትም ቦታ ያሉ በመሆኑ ስንጀምር የምንጀምረው የምንገባበት መስፈርትም ፍላጎት አላቸው ወይ? የሚለው በመሆኑ ወደዚህ ሥራ የሚገባው አርሶ አደር ፍላጎቱ ይታያል። በመቀጠል ደግሞ ምን ያህል መሬት አላቸው የሚለውም ይታያል፤ እናም እነዚህን መስፈርት ማሟላት የኩታ ገጠም እርሻ ውሰጥ ለመግባት ወሳኝ ነው።
አሁን ባለንበት ሁኔታ በተለይም የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተር ውስጥ ሦስት መቶ ወረዳዎች አሉ። ይህ ደግሞ ከአገሪቱ የቆዳ ስፋት አንጻር ሲታይ በጣም ሰፊ ነው። በአርሶ አደር ደረጃ ስናየው ደግሞ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶ አደሮች በመጀመሪያው ዙር ውስጥ አሉ። ከዚህ ወደ ግብርና ክላስተር የገቡት 1 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ናቸው። እዚህ ላይ ሁሉም አርሶ አደሮች እንዲገቡ ያልሆነው በተለይም ወደኢንተርፕራይዝ በሚገቡበት ጊዜ በመካከላቸው ችግር ቢፈጠር የሚዳኙበት የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ነው። በመሆኑም ይህንን እየሠራን የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፉን ማሻሻል ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ትልቁ ችግር የመሠረተ ልማት ውስንነት ነው። ለምሳሌ መንገድ፣ ምርቱ ገዢው ጋር እስከሚደርስ ድረስ የሚጠራቀምበት ቦታም አለመኖር ችግር ነው። እነዚህ ነገሮች ደግሞ በሥራው ላይ ፈተና ሆነው ቆይተዋል።
ከዚህ ውጪ ግን ጥቃቅን ችግሮች በተደራጀ መልኩ ከማዕከል ወደገጠር በመሄድ ዘር፣ ማዳበሪያ እና ሌሎችም ምርቶች እጥረት ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ የገለጿቸውን ችግሮች ለማለፍስ ምን እየተሠራ ነው?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ አዎ፤ ይህንን ችግር ለማለፍ ቢያንስ በወረዳዎቹ ውስጥ እነዚህ አርሶ አደሮች ዘር አምራች ቡድን እንዲኖራቸው፤ ከዚያ ደግሞ የሚደራጁት አርሶ አደሮች ውስጥ ፈጣን የሆኑትን ለብቻ በማደራጀት የዘር አምራች እንዲሆኑ ይደረጋል። ሌላው ደግሞ በዚህ መልኩ የሚደራጁ አርሶ አደሮች የሚያገኙት ጥቅም ለግብርና ግብዓት ቅድሚያ እንዲያገኙ ይደረጋል። ይህም ደግሞ በግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ውስጥ የተካተተ ነው።
በተጨማሪም እንደ ማሳያ አርሶ አደሮችን በዘር በማደራጀት ማከማቻ እንዲኖራቸው የማድረግ ሥራ ሠርተናል። ከዚህ ሌላም የግለሰብ ማዳበሪያም ይሁን ሌላ የግብርና ግብዓቶችን የሚያስመጡ አካላትን አርሶ አደሮቹ መካከል በመግባት በወረዳ ከዚያም አልፎ በትንንሽ ከተሞች እንዲያዳርሱ ለማድረግ የአንድ መስኮት ገበያ እንዲኖር በማድረግ በአሁኑ ወቅት ወደ 183 ሱቆች ተከፍተዋል። በመሆኑም ዘር አምራች ካለ ሌሎቹን የግብርና ግብዓቶች በአንድ መስኮት ገበያ ማግኘት ከተቻለ የተመረተው ምርት ደግሞ ወደ ገበያ እስከሚወጣ ድረስ ማቆያ ቦታ ከተገኘ ትልቁ ችግር ተፈታ ማለት ነው።
ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚገባው በአሁኑ ወቅት አግሮ ኢንዱስትሪ ተብለው በኦሮሚያ በአማራ በደቡብ እንዲሁም በሌሎች ክልሎች ካሉት ጋር ማስተሳሰር ነው፤ እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ ቡልቡላ ላይ ላለው የፍራፍሬ መጭመቂያ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች በሙሉ ወደፍራፍሬ ማምረት ቢገቡ። ቡሬ ያለው ደግሞ አኩሪ አተር እንዲያመርትና ይህ ምርት ደግሞ በአካባቢው ላሉት የዘይት መጭመቂያ ኢንዱስትሪ ባለቤቶች እንዲያቀርቡ ትስስር መፍጠር ይፈልጋል።
በዚህ መልኩ ከሄድን ደግሞ አርሶ አደሮቹ ምርታቸውን ለኢንዱስትሪም ይሁን ለአገር ውስጥ ገበያ በቀጥታ ያቀርባሉ ማለት ነው። ይህ ሁኔታ ሲፈጠር ደግሞ ወደ ትክክለኛና የገበያ አማራጭ ወደተፈጠረለት የአመራረት ሥርዓት ውስጥ ይገባሉ።
እዚህ ላይ ግን እንደ ትልቅ ችግር የሚታየው በአገራችን ውስጥ ያሉ ማሽነሪዎች ማለትም ትራክተር ኮምባይነር እንዲሁም ሌሎች መጠናቸው አነስተኛ መሆን ነው። በመሆኑም ከቻልን ማምረት፤ ካልቻልን ደግሞ ከውጭ አገር በስፋት ማስገባት የሚኖርብን ወቅት ላይ እንገኛለን። በነገራችን ላይ በዚህ ዙሪያ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥም ያስፈልጋል ተብሎ በአሁኑ ወቅት ማሽነሪዎች ከታክስ ነፃ ሆነው እንዲገቡ ተደርጓል። ይህ ለሚያስገቡትም ሆነ ለሚጠቀሙት ትልቅ ማነቃቂያም ነው።
አዲስ ዘመን፦ የግብርና ዘርፉን ለማዘመን እንግዲህ እርስዎም እንዳሉኝ ሜካናይዜሽን ትልቁን ቦታ የሚይዝ ነው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም አበረታች ሥራዎች በመንግሥት በኩል እየተሠሩም እንደሆነ ነግረውኛል ፤የተሰጠውን ዕድል ተጠቅሞ ግብርናችንን በሜካናይዜሽን ከማዘመን አንጻር ያለንበት ደረጃ ምን ይመስላል?
ዶክተር ማንደፍሮ ፦ እንግዲህ እስከ አሁን ድረስ ሜካናይዜሽንን እየተጠቀምን ነው፤ ለምሳሌ እኔ ገንዘብ ይኖረኝና ትራክተር፣ መዘሪያ፣ ኮምባይነርና ሌሎቹንም ላስመጣ እችላለሁ፤ ነገር ግን ከመጡ በኋላ እንዴት እንደምጠቀም ሲበላሽ ጥገናው ምን መምሰል እንዳለበት እንዴትም አገልግሎት እንደምንሰጥ እውቀቱ ላይኖረን ይችላል፤ ከላይ ካልኩት የትራንስፎርሜሽን ክላስተር ውስጥ አንዱና እያቋቋምን ያለነው ሜካናይዜሽን ሰርቪስ ሴንተር ነው። ይህ ሰርቪስ ሴንተሮች ሦስት ነገሮችን ይሠራል፤ አንደኛው የጥገና ጋራዝ ሲሆን የግብርና ማሽነሪዎች ሲበላሹ ተጠግነው ወደ ሥራ እንዲወጡ ያደርጋሉ። ሁለተኛ እንደ ትራክተርና ሌሎች ማሽነሪዎችን በመግዛት የኪራይ አገልግሎት መስጠት ነው። ሦስተኛ ልክ እንደ ተሽከርካሪ ማሰልጠኛ ሁሉ ባለሀብቶቹን በማሰልጠን የማሽከርከር ፍቃድ ይሰጣል።
በሌላ በኩል ከእነዚሁ ማሽነሪዎች ጋር በተያያዘም ቀደም ሲል በነበሩ ብልሹ አሠራሮች ምክንያት፤ ለምሳሌ አዳማ ላይ የቆሙ በሺዎች የሚቆጠሩ ትራክተሮች አሉ። በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገብተው ጥቅም ላይ ሳይውሉ ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው ያለ መንግሥትም ለውሳኔ የተቸገረባቸው፤ አሁን እንኳን ባሉበት ሁኔታ ለአርሶ አደሩ ተሰጥተው አገልግሎት ቢሰጡ ለምርታማነት የምንደርገውን ጉዞ እንደሚያግዙን ይሰማኛል።
ለግብርና ትራንስፎርሜሽን ሜካናይዜሽን ከላይ የጠቀስኳቸው የግብርና ግብዓቶች የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ከፍተኛ ሚና ያላቸው በመሆኑ አዋህዶ መሄድ ከተቻለ አቅራቢውንና ተጠቃሚውን በቀላሉ አገናኝቶ የሚፈለገውን ለውጥም ለማምጣት ቀላል ይሆናል። ነገር ግን እነዚህ በሙሉ ካልተሳሰሩ የግብርና ትራንስፎርሜሽን እውን ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ ምርጥ ዘር ማዳበሪያና መሰል ግብዓቶች ግብርናውን ትራንስፎርም ለማድረግ እንደ ቁልፍ መንገድ ናቸው፤ አሁን ደግሞ የእነዚህ ግብዓቶች ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ እየናረ መምጣት በግብርና ሥራው ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ የዓለም አቀፉ ገበያ አገራችን ላይ ትልቅ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። በተለይም የማዳበሪያ ዋጋ በዚህን ያህል መጨመር ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው ። የሚገርመው ነገር ደግሞ ማዳበሪያ ዋጋ መጨመሩ ብቻ ሳይሆን ችግሩ አቅርቦቱም በጣም መቀነሱ ነው። አሁን የደረሰበትን የዋጋ ደረጃ እርግጠኛ ባልሆንም በእጥፍ ስለመጨመሩ አውቃለሁ። ይህ ደግሞ በሁለት መንገድ ተጽዕኖ አለው። አንደኛ ቀድሞ ስናስገባ ከነበረው በእጥፍ የውጭ ምንዛሪን ይወስዳል፤ አገር ውስጥ ከደረሰም በኋላ ደግሞ አርሶ አደሮቹ በጨመረው ዋጋ የመግዛት አቅም ላይኖራቸው ይችላሉ።
በመሆኑም ይህ ሁኔታ የተለየ አካሄድና የፋይናንስ ሥርዓት ይፈልጋል። ምናልባት አርሶ አደሮች ይህንን ገንዝብ በብድር መልክ የሚያገኙበትን አልያም ደግሞ የተጎዱና አቅም የሌላቸው ከሆኑ ደግሞ በነፃ እስከመስጠት ድረስ የደረሰ ሥርዓት መዘርጋት ካልቻልን ከችግሩ ለመውጣት ይከብደናል።
አዲስ ዘመን ፦ ምናልባት ከላይ የተቀመጡት መፍትሔዎች እንዳሉ ሆነው አሁን ካለንበት ችግር እንዴት እየወጣን ነው? ለምሳሌ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያዎች እንዲለመዱ የማድረግ ሥራው ምን ይመስላል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ችግሩን እየተወጣን ያለነው በተለያየ መልኩ ነው። አንደኛ መገዛት የሚቻለው ያህል ማዳበሪያ ተገዝቷል። አገር ውስጥና በየክልሉ የደረሰ የማዳበሪያ መጠን አለ። ወደብ ላይ ያለም እንዲሁም እየተጓጓዘ ያለ ማዳበሪያ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ሲገጥሙን በዚህ ሙያ ላይ ያሉ አንጋፋ ባለሙያዎች አሰባሰብን ምንድን ነው ማድረግ የሚቻለው? ብለን መክረናል፤ ያገኘነው አንዱ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጀት ነው፤ ይህ እንግዲህ የተፈጥሮ ከሰብል ወይም ከእንስሳት የሚገኝ ግብዓትን ይጠይቃል። ነገር ግን ይህ በማይገኝባቸው አካባቢዎች ላይስ? የሚለውን አይተናል። አሁን በተለይም እነዚህ ግብዓቶች በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ ኮምፖስት እየሠራን መሄድ ነው፤ ለዚህ ትልቅ አስተዋጽዖ ያላቸው ከተማ አካባቢ ያሉ ሰዎች ናቸው። እነሱ ላይ እንሥራ ብለናል። ክልሎችም በሰፊው እየሄዱበት ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ማዳበሪያ የማያስፈልጋቸው ወይንም ደግሞ ጥቂት ብቻ የሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ለምሳሌ ወንዝ የሚፈስባቸው በክረምት ጎርፍ ያለባቸው አካባቢዎች መሬቱ ለም በመሆኑ እነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ እንዳይጠቀሙ የግብርና ባለሙያዎች ምክር ሃሳብ እየሰጡ ነው።
በሦስተኛ ደረጃ በግል ባለሀብቶች የሚተዳደሩ እርሻዎች ለአነስተኛው አርሶ አደሩ ከመጣው ማዳበሪያ ላይ እንዳይሻሙ መሬታቸው ላይ መጀመሪያ ናይትሮጂንን የሚይዙ ሰብሎችን ዘርተው እሱን ገልብጠው ጥራጥሬ እንዲዘሩ በማድረግ ማዳበሪያው እንዲቆጥቡ እየሆነ ነው። በዚህ መልክ ስትራቴጂክ ለሆኑ ምርቶች ብቻ ማዳበሪያን በመጠቀም ይህንን የችግር ወቅት እንድናልፍ ምክረ ሃሳብ ተሰጥቶ በዚያ እየተሄደበት ነው ።
ይህም ቢሆን ግን ገዝተን የምንጠቀመውን ማዳበሪያ በአንድ ጊዜ እንተካዋለን ማለት አይደለም፤ ምክንያቱም ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት ራሱ አንድና ሁለት አመት ይፈልጋል። ዘንድሮ እያዘጋጀን ያለነው ምናልባትም ለቀጣይ እና ከዚያ በኋላ ለሚመጣው ዓመት ይጠቅመን ይሆናል እንጂ ለዚህ አመት አይደርስም። በሌላ በኩልም በመስኖ የሚጠቀሙ አካባቢዎች እርካሽ የሆኑ የጥራጥሬ ሰብሎችን ዘርቶ እነሱን በመገልበጥ ሌሎች ምርቶችን መዝራት ልክ እንደ ማዳበሪያ ስለሚያገለግል እሱንም እየመከርን ነው።
አዲስ ዘመን ፦ እዚህ ላይ ግን ይህ አካሄድ በግብርና ባለሙያው እንዲሁም በአርሶ አደሩ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ምን ያህል ነው? በሚፈለገው ልክ ተረድተውታል ማለት ይቻላል?
ዶክተር ማንደፍሮ ፦ ይህ ችግር ከመምጣቱ በፊትም የተፈጥሮ ማዳበሪያን የሚጠቀሙ አካባቢዎች ነበሩ። ብዙም ባይሆኑ። ከላይ እንዳልነው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለመሥራት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችም እንደልብ አይገኙም፤ እንዲሁም የሚገዛው ማዳበሪያ እንደልብ ስለነበረና ለአጠቃቀምም ቀላል ስለሆነ ሁሉም ወደእሱ የማተኮር ሁኔታ ነበር። ይህ የአሁኑ ሁኔታ ግን በተለይ ለእኛ አገር የማንቂያ ደወል ሆኖልናል። የሚገዛ ነገር ላይ ተንጠልጥለን እንዳንሄድ የራሳችን የሆነ ነገር ሊኖረን እንደሚገባም ያመላከተ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በአገር ውስጥ ማዳበሪያን ማምረት ግድ እንደሚለንም ያየንበት ወቅት ነው።
አዲስ ዘመን፦ በአሁኑ ወቅት የበጋ ስንዴ ሰብልን የማምረት እንቅስቃሴው ውጤታማ መሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ገልጸዋል፤ ለመሆኑ በዚህ ዘርፍ ላይ የተገኘው ተጨባጭ ውጤት እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ የበጋ ስንዴ በጣም ውጤታማ ነው። እዚህ ላይ ግን በስንዴ ልማት ራሳችንን እንድንችል አራት ምሰሶዎች ተቀምጠው መሥራት ከተጀመረ ቆየት ብሏል፤ አንዱ አሁን ስንዴ የሚመረትበት 2 ሚሊዮን የሚሆን መሬት ላይ የምርምር ውጤት ምክረ ሃሳብ እንዲሁም በክላስተር እየተሠራ አሁን ላይ ያለውን በአማካይ በሄክታር 31 ሚሊዮን ኩንታል እዚህ ላይ 5 ሚሊዮን ኩንታል ቢጨመር ከሚያስፈልገን ከ 50 በመቶ በላይ ነው ብቻውን፤ ሁለተኛ አሲድ የሚያጠቃቸው በርካታ ቦታዎች ላይ ኖራ ብቻ በመጠቀም ቢሠራ 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በሄክታር ማግኘት ይቻላል፤ ከዚህ ውስጥ እንኳን 2 ሚሊዮን ኩንታሉ ቢሳካ እነዚህን ብቻ በመሥራት ራሳችንን ከበቂ በላይ በሆነ ሁኔታ እንችላለን ማለት ነው። ሦስተኛው ደረጃ ደጋማ ሆኖ ውሃ የሚተኛባቸውን አካባቢዎች ውሃውን በማጠንፈፍና ለዚያ የሚሆን ማሽነሪን በመጠቀም ተጨማሪ ስንዴ ብናመርት፤ አራተኛው ስንዴን እንደተያዘው በመስኖ ብናመርት የሚሉ ምክረ ሃሳቦች ነበሩን።
ነገር ግን ይህ የመስኖ በጣም እየተነገረለት ያለው ዋናው ምክንያት ሰብል በሌለ ጊዜ የሚዘራና ያልተለመደ ስለሆነ ነው። አሁን ደግሞ ትልልቅ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ሥራው ላይ ተሳትፎን እያደረጉ በመሆኑ 405 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ተዘርቷል በምርታማነት 24 ሚሊዮን ኩንታል እናገኛለን ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን ካገኘን ደግሞ ከውጭ የምናስመጣው ስንዴ አይኖርም።
ይህንን ባናደርግ ኖሮ በተለይም በጦርነቱ ምክንያት ሊገጥመን ይችል የነበረው ችግር ከባድ ነበር። በመሆኑም በዚህ መልኩ በምግብ እህል ራስን መቻል ላይ ትኩረት አድርገን መሥራት እንዳለብንም ይሰማኛል። በመሆኑም ቀጣይነት እንዲኖረው ሥርዓት ማበጀት በፕሮግራም እንዲታቀፍ ማድረግም ያስፈልጋል። ይህ ከሆነ ዘላቂ የሆነ የስንዴ አምራች ከመሆናችንም በላይ እኛው ራሳችን ስንዴን ለውጭ ገበያ የምናቀርብ የምንሆንበትም ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
አዲስ ዘመን፦ ለግብርናው ዘርፍ የተለየ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ሥራዎች ይሠራሉ፤ ነገርግን አሁንም ግብርናው የመሪነት ቦታውን መያዝ አልቻለም፤ የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው?
ዶክተር ማንደፍሮ ፦ አዎ ግብርና መሪያችን ነው እንላለን፤ ነገር ግን በሚያስፈልገው ልክ በጀት አልተመደበለትም። ለምሳሌ ስንዴን ባነሳልሽ መጀመሪያ ሦስት ሺ አምስት መቶ ሰራን፤ ከዚያ 20 ሺ ቀጥሎ 80 ሺ አሁን ደግሞ 4መቶ ሺ ብለናል። ገንዘብ ቢኖር ግን ይህንን በሙሉ በአንድ አመት ውስጥ መሥራት እንችል ነበር። በመሆኑም ግብርናው የሚገባውንና እኛም የምንለውን ያህል በጀት አልመደብንም።
በሌላ በኩል ደግሞ 75 በመቶ የሚሆነው ሕዝባችን ግብርና ላይ ጥገኛ ነው እንላለን፤ ይህ ማለት ደግሞ የአገሪቱን 75 በመቶ የሚሆነውን በጀት ዘርፉ ይፈልጋል ማለት ነው። ነገር ግን በአፋችን ግብርና እዚህ እዚያ መድረሱ አገሪቱን ያሳድጋል ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች ማደግና መስፋፋት ሚናው ላቅ ያለ ነው እንላለን ነገር ግን ተግባራዊ ሥራ የለም።
አሁን በእኛ ደረጃ የተፈጥሮ ሀብት በእጃቸን ነው ባለሙያም ምንም ችግር የለብንም ነገር ግን የሌለን ገንዘብ ነው። ይህንን ያመጣው ደግሞ ከላይ ያሉት አመራሮችና የሀብት (በጀት) ክፍፍሉን በሚሠሩት አካላት መካከል ያለ የሰፋ ልዩነት ይመስለኛል። በመሆኑም የግብርናው ዘርፍ በቂ የሆነ ሀብት አልተመደበለትም። ይህንን ማስተካከል ከቻልን ብዙ ርቀት መሄድ እንችላለን።
አዲስ ዘመን ፦ መጪው ጊዜ የክረምት ወቅት ነውና ለቀጣይ የግብርና ሥራ መደረግ ይኖርበታል ብለው የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
ዶክተር ማንደፍሮ፦ ወቅቱ የመኸር ጊዜ በመሆኑ የቢሮ ሥራን ቀነስ አድርጎ አርሶ አደሮቹን ማገዝ ይገባል። በተለይም ደግሞ አሁን ያለንበት የማዳበሪያ እጥረት በምርቶች ላይ ተጽዕኖ እንዳይኖረው አርሶ አደሩን በቅርበት የምንሰጠው ምክረ ሃሳብ ለነገ ምርታችን ወሳኝ በመሆኑ እዚህ ላይ ትኩረት አድርገን መሥራት ይኖርብናል። በሌላ በኩል ደግሞ ነጥለን አውጥተን ትኩረት የምንሰጣቸው ሰብሎች ላይ ሁሉም ክልል ተሳታፊ ቢሆን እላለሁ። ለምሳሌ የበጋ ስንዴ ላይ ተሳትፎ ያደረጉት አብዛኞቹ በኦሮሚያ ክልል ያሉ የግብርና ሴክተሮች ናቸው፤ ይህንን አስፍተነው ሁሉም እንዲሠሩ በማድረግ ላይ ትኩረት እንስጥ። በተጨማሪም አብሮ የመሥራት የኅብረት ስሜታችንን ማሳደግ ያስፈልጋል።
ሌላው የማስተላልፈው መልዕክት በዚህ ዓመት የዲቃላ በቆሎ ዘር እጥረት ሊያጋጥመን ይችላል። ሆኖም አንዳንድ ክልሎች ላይ ይህ ዘር በብዛት አለ በመሆኑም የእኔ ከሚለው ስሜት ወጥተን እኛ ብለን እንደ አገር መሥራትን መካፈል አብሮ ሠርቶ አብሮ ለመለወጥ መነሳት ያስፈልገናል።
አዲስ ዘመን፦ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ማንደፍሮ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም