በግብርናው ዘርፍ በተያዘው በጀት አመት ዘጠኝ ወራቶች ከወጪ ንግድ የተገኘው 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አበረታች መሆኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወድሷል። ለግብርና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት ከሆኑት አንዱ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሰሞኑን ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ነው ዘርፉ በቋሚ ኮሚቴው ምስጋና ያገኘው። የቋሚ ኮሚቴው አባላት ያደረጉትን የመስክ ምልከታና ባለሥልጣኑ ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረበውን የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ሪፖረት መሠረት በማድረግ ባለሥልጣኑ ወደፊት ሊያስተካክለው በሚገባ ክፍተቶቹ ላይ ምክረ ሀሳብ ሰጥቷል። የባለሥልጣኑን የዘጠኝ ወር አፈጻጸምና በቋሚ ኮሚቴው የተሰጠውን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበናል።
በግብርናው ዘርፍ አንዱ በሆነው የቡና ልማት በዘጠኝ ወር የተከናወነውንና አፈጻጸሙን እንዲሁም የተገኘውን አበረታች ለውጥ ለማስቀጠልና የበለጠ ለመንቀሳቀስ የባለሥልጣኑን ዝግጁነት እንዲሁም ያለፉ ተሞክሮዎችን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ለቋሚ ኮሚቴው እንዳስረዱት፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ዝርያ ያላቸው በሌላው ዓለም ተፈላጊ የሆኑ የቡና እና የቅመማቅመም ምርቶች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ በዘርፉ ከልማቱ እስከ ግብይት ባለው ሰንሰለት ውስጥ የተለያዩ ተግዳሮቶችና ክፍተቶች ይስተዋላሉ። ክፍተቶቹ ደግሞ ለገበያ ብቁ የሆነ ቡና እንዳይመረት አድርጓል። ይህም ገበያ ላይ ያለው ድርሻ ከሦስት በመቶ እንዳይበልጥ ምክንያት ሆኗል። ሌላው ምክንያት አመታዊ ምርቱ ከ600ሺ እስከ 700ሺ ቶን የበለጠ አለመሆኑ ነው። ከሚመረተው አጠቃላይ ምርት ውስጥም 50 በመቶ የሚሆነው ለአገር ውስጥ ፍጆታ ነው የሚውለው። የግብይት ሰንሰለቱ ረጅም ሂደትን የሚያልፍ መሆኑም የራሱ ተጽዕኖ በመፍጠሩ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ከ30 በመቶ ወይንም ከ200ሺ ቶን በላይ እንዳይሆን አድርጓል። በጥራትና በብዛት አምርቶ በዓለም ገበያ ላይም ተወዳዳሪ ሆኖ ከፍተኛ ስኬት አለመመዝገቡ ብቻ ሳይሆን፣ ዘርፉ አምራች አርሶአደሩንም ተጠቃሚ አለማድረጉ ሌላው ተግዳሮት ነው። አርሶአደሩ ኪስ ገብቶ ኑሮውን የሚለውጥ ነገር እያስገኘለት አይደለም። በዚህ የተነሳም የቡና ተክሉን በሌላ የገቢ ማስገኛ ለመለወጥ የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ቡና አምራች ከሆኑ አገራት አንዷ የሆነችው ቬትናም ቡና አምራች አርሶአደሯ ከሚያመርተው ምርት 95 በመቶ ኪሱ ይገባል። የኢትዮጵያ ቡና አምራች አርሶአደር ኪሱ የሚገባው ከ45 ከመቶ አይበልጥም ነበር። በወቅቱ የቡና ጉንደላ አለመካሄድና የተሻለ ዝርያ አለመጠቀም በምርትና ምርታማነት መቀነስ ላይ የራሱ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በቅመማ ቅመም ዘርፉም እንዲሁ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። በአጠቃላይ በዘርፉ እሴት የማይጨምሩ ተዋናዮች የበዙበት ነው። እነዚህ ያለፉ የዘርፉ ክፍተቶችን አስተካክሎ ወደ ለውጥ ውስጥ በማስገባትና በማነቃቃት የበለጠ ተጠቃሚ ለመሆን ተስፋዎች አልተሟጠጡም ይላሉ ዶክተር አዱኛ።
እንደርሳቸው ገለጻ ባለሥልጣኑ ክፍተቶችን በመለየት የተለያዩ የእርምጃ ሥራዎች በመሥራት በለውጥ ሂደት ላይ ይገኛል። ባለሥልጣኑ የቡና ጉንደላ እንዲካሄድ አገራዊ ንቅናቄ በመፍጠር ያረጀውን በአዲስ የመተካት ሥራ በመሥራት ለውጥ ለማምጣት ባደረገው እንቅስቃሴ መሻሻሎችን ማምጣት ችሏል። ባለሥልጣኑ በዘርፉ ከልማት እስከ ግብይት ያለውን ክፍተትና ተግዳሮት መሠረት በማድረግ በተለይም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር የማሳ ሽፋንን ማሳደግ፣ አገራዊ ገቢ ወይንም የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲጨምር፣ አርሶአደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን፣ እነዚህን ጨምሮ ስድስት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን በመለየት የ15 አመት እቅድ ነድፎ ለውጥ ለማስመዝገብ እየሠራ ይገኛል። በዚሁ መሠረት መሻሻሎች ታይተዋል። ለአብነትም 45 ከመቶ ይገኝ የነበረው የአርሶአደሩ ገቢ ወደ 91 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል። በገበያ ትስስሩም ከአቅራቢ ወደ ላኪና እና ቀጥታ ንግድ እንዲካሄድ በተደረገው መሠረት በአሁኑ ጊዜ አንድ ሺ 500 አርሶ አደሮች የወጪ ንግድ ፈቃድ አውጥተው ምርታቸውን በቀጥታ መላክና ከአቅራቢዎች ጋርም መገናኘት ችለዋል። የቡና አቅርቦቱ በቀጥታ መከናወኑንም የመቆጣጠሪያና መከታተያ ሥልት ተዘርግቶ በአግባቡ እየተሠራ ነው። በዚያው ልክ የገበያ ተወዳዳሪነትን ለመጨመር በቡና ጥራት ላይም በተሠራው ሥራ የጥራት ደረጃውን ከ34 ወደ 54 በመቶ ማድረስ ተችሏል። ጥራቱ ሲጨምር የመሸጫ ዋጋውም ጨምሯል።
ሌላው ባለሥልጣኑ ካከናወናቸው ተግባራት አንዱ በሄክታር ላይ የሚገኝ የቡና መጠንን ከፍ ለማድረግ የማሳ ሽፋንን ከመጨመር ጀምሮ ምርታማነትን የሚጨምሩ የተሻሻሉ ዝርያዎች መጠቀምና የአተካከል ዘዴውንም ማዘመንና ጉደላ በማካሄድ አሮጌውን በአዲስ መተካት የሚሉት ይጠቀሳሉ። በሕገወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩ የንግድ ግብይቱ ወደኋላ እንዳይቀለበስ ቀድሞ የተጀመረውን የገበያ ደህንነት ሥራ ማጠናከር ነው። ለዚህም በአግባቡ መረጃ መለዋወጥና የገበያ መዳረሻዎችን መለየት ናቸው። ዕቅዶችን ለማሳካት የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ማሟላትም ሌላው ተግባር ነው። ግብአት ማሟላቱ የብድር አገልግሎት ለሚያስፈልጋቸው ማሟላትንም ያካትታል። ቡናን በክላስተር (ኩታገጠም )ዘዴ ማምረት ጠቃሚ በመሆኑ በኦሮሚያ ክልል በደሌ፣ ኢሉባቦርና ጅማ ዞኖች ላይ የተጀመረውን በክላስተር የማልማት ዘዴ ይጠናከራል።
ባለሥልጣኑ በምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ የሚጠበቅበትን ድጋፍ በማድረግ ያግዛል። ሥራዎች በዚህ መልኩ ተጠናክረው ከቀጠሉ ምርትና ምርታማነቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጨምራል። ባለሥልጣኑ ያጋጥመው የነበረውን የባለቤትነት ጉዳይም ለመፍታት ሥራ መሥራቱን ያወሱት ዶክተር አዱኛ፤ የኢትዮጵያ ቡና ከጅቡቲ ካለፈ በኋላ ከሌላ አገር ምርት ጋር ተቀላቅሎ ለገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ቡና መለያ (ብራንድ) በማዘጋጀት ችግሩን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል። መለያ መኖሩ የተወዳዳሪነት አቅምን ለማሳደግ ሚናው የጎላ ይሆናል። በዋጋ የመወዳደር አቅምንም ፈጥሮልናል። ከዚህ ቀደም የነበረውን የተዘበራረቀ የመሸጫ ዋጋ ማስቀረትም ተችሏል።
ሻይና ቅመማቅመም ላይ ያለውንም ነባራዊ ሁኔታ ዶክተር አዱኛ እንዳስረዱት፤ የሻይ ለቀማ ወቅቶች ሁለት ጊዜ በመሆኑ ምርቱና ገቢው ላይ አመታዊ ሪፖርት የሚቀርብ ቢሆንም፣ምርታማነቱ ከፍተኛ ነው። ቅመማ ቅመም እንዲሁ ከእቅድ በላይ ነው የተመረተው። ሻይ ለቀማ ላይ ወደፊት መስተካከል አለበት ብሎ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ ያየው ነገር ከሰው ጉልበት አሠራር መውጣት የሚችልበት ሁኔታ መስተካከል እንዳለበት ነው። በለቀማ ወቅት ሰፊ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። የሰው ኃይሉን ከቦታ ወደ ቦታ በማዘዋወር ለማሠራት ደግሞ አገራዊ የፀጥታ ሁኔታ ምቹ አላደረገውም። ባለሥልጣኑ በልማት ሥራውና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያከናወናቸው ተግባራት በተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ ያስቻለው ቢሆንም፣የበለጠ በመሥራት በአገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ሚናውን መወጣት እንደሚጠበቅበት ግንዛቤ ይዞ እየሠራ ይገኛል።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት ያደረጉትን የመስክ ምልከታና ተቋማቱ ያቀረቡትን ሪፖርት መሠረት አድርገው በሰጡት አስተያየት የቡናና ሻይ ባለሥልጣን አርሶአደሩ እንደ አንድ ታሪክ አድርጎ የሚወስደውንና በስስት በማየት ጭምር ለ40 እና 50 አመታት ሳይከናወን የቆየውን የቡና ጉደላ ማከናወኑ፣ ቡና በኩታገጠም (ክላስተር) እንዲለማ ሥራ መጀመሩና ግብይት ላይም ያሳያቸው መሻሻሎች ተጠናክሮ ለበለጠ ውጤት መሠራት ይኖርበታል። በቀጣይ መሠራት ያለበትንም ሥራ አመላክተዋል። በአሁኑ ጊዜ አርሶአደሩን ለስጋት የዳረገውን የቡና አድርቅ በሽታ በመከላከልና ተያያዥ ክፍተቶችን ለይቶ በመተግበር ላይ ትኩረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ባለሥልጣኑ እንደ ብዝሃ ሕይወት ካሉ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት መፍትሄ መስጠት እንዳለበትም አመላክተዋል። በሻይ ልማት ላይ ግን ትኩረት አልተሰጠም የሚል ሀሳብ አንስተዋል። ሻይ ከተመረተ ትርፋማ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ ልማቱ አርሶአደሩንም ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እየተከናወነ አይደለም። በከፋ ዞን የመስክ ምልከታ ላይ ያስተዋሉትን ለአብነት እንደጠቀሱት፤ ከአርሶአደሩ ምርት በማቀነባበር ሥራ ላይ የተሰማራው አንድ ድርጅት ብቻ በመሆኑ አማራጭ የገበያ ዕድል ለማግኘት አላስቻላቸውም። ይህ ደግሞ የልፋታቸውን ዋጋ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። በማቀነባበር ሥራ ውስጥ የአርሶአደሩ ተሳትፎ እንዲኖር በማድረግ ችግሩን መፍታትም አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል። በቅመማቅመም ላይ በሰጡት አስተያየት ምርቱ ከፍተኛ እንደሆነና አርሶአደሩም ለማምረት ዝግጁ እንደሆነ በመስክ ምልከታ አረጋግጠዋል። ምርቱና የወጪ ንግዱ ግን የተመጣጠነ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ከሕገወጥ ጋር ተያይዞም አባላቱ እንዳነሱት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በነበራቸው የመስክ ምልከታ የክልሉ የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በሕገወጥ መንገድ ለገበያ ሊውል የነበረውን አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲገባ ያደረጉበት መንገድ ያስመሰግናቸዋል። አንዳንዴ ሕገወጡ ተመልሶ ለሕገወጥ የሚውልበት አጋጣሚም በመኖሩ ሕጋዊነትን የመከላከሉ ተግባር የአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን፣ አገራዊ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
እነዚህንና ሌሎችም ለተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊ በተሰጠ ማብራሪያ ባለሥልጣኑ በዘርፉ የሚስተዋለውን ክፍተት በሦስት መንገዶች ለመፍታት ጥረት አድርጓል። አንዱ የሚያስፈጽምበት አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ አልነበረውም። ይህን አዘጋጅቷል። ሁለተኛ አዋጅ፣ መመሪያና ደንቦችን የሚደግፍ ሪፎርም ያዘጋጀ ሲሆን፣ ሪፎርሙ በተለይም የቡና ልማቱን ምርትና ምርታማነት ሊያሳድግ የሚያስችልና ከዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ግኝት እንዲያድግ የሚያስችል ነው። ሦስተኛው ደረጃ በስትራቴጂ በሚከናወን የዕቅድ ሥራ ላይ ያተኮረ ነው። በቅመማቅመም የወጪ ንግድ ማነስ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በቋሚ ኮሚቴ አባላት ለቀረበው ጥያቄም፣ ለውጭ ንግድ የሚውሉት ውስን በመሆናቸው እንደሆነና ወደፊት ገበያ በማፈላለግ አቅርቦቱን የማሳደግ ሥራ እንደሚሠራ ምላሽ ተሰጥቷል። በተጨማሪም እሴት የተጨመረባቸው የቅመማቅም የወጪ ንግድ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል የሚቀርብ መሆኑንም አስታውሰዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሶሎሞን ላሌ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የግብርና ምርቶች በዚህ ደረጃ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት መቻላቸው የተጠሪ ተቋማቱ ጥረትና ድምር ውጤት መሆኑን ውጤቱ ያረጋግጣል። ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የተገኘው ውጤት ይበል የሚያስብል ነው። ከዚህ አንጻር ግብርና ሚኒስቴርም ሆነ ተጠሪ ተቋሙ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የውጭ ምንዛሬ ለአገሪቱ በማስገኘት ረገድ ላቅ ያለ ሥራ ሠርተዋል። በዘጠኝ ወራት ውስጥ በቡና ምርት ብቻ ዓምና ከነበረው 72 ነጥብ 7 በመቶ የውጭ ምንዛሬ ማሳደጉ እጅግ በጣም ውጤታማ ሥራ ነው ተብሎለታል። በቡና የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ብቻ 894 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ችግር ለመቅረፍ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል። በቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም በጋራ ሲታይ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 525 ነጥብ 13 ሚሊዮን ዶላር ወደ 907 ነጥብ 15 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱም ትልቅ እምርታ መሆኑም ተገልጿል። በአጠቃላይ የግብርና ዘርፉ እንደ አገር ሲገመገም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ትልቁን ድርሻ እንደተወጣ ነው የጠቀሰው።
በተጨማሪም ባለሥልጣኑ ጥቂት የነበረውን የኢትዮጵያ ቡና ኤክስፖርት መዳረሻ ወደ 33 አገራት ማሳደጉ በጥንካሬ ተነስቷል። የቋሚ ኮሚቴ አባላት የግብርና ሥራው በሚከናወንበት ሥፍራ ድረስ በመሄድ ባደረጉት የመስክ ጉብኝት ማረጋገጥ እንደቻሉት የቡና ልማቱ በአማካይ ከሚገመተው በላይ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተከናወነ ይገኛል። መልካም የሆኑ ተሞክሮዎችን በጥናት ለይቶ ማስፋፋት እንደሚጠበቅ ምክረሀሳብ ተሰጥቷል። የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳጣት የአገርን ሀብት ለብክነት የሚዳርገውን ሕገወጥነትን በመከላከል ረገድም መሠራት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው በመስክ ጉብኝቱ የታዘበውን መነሻ በማድረግ አስገንዝቧል። በምግብ እህል ራስን መቻል እና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶችን ማምረት ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠ ኃላፊነት እንደሆነና የኢኮኖሚ ሽግግር በአገሪቱ ማምጣት እና የሥራ ዕድልም በግብርና ዘርፉ ይፈጠራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም በቋሚ ኮሚቴው ተገልጿል። ደላላን በመከላከል እየገባ የዋጋ ንረት መፍጠሩን ለማስቆም በትብብር አመርቂ ሥራ ሊሠራ እንደሚገባም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም