ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም የማዕድን ሀብት ልማት ፖሊሲ ረቂቅ ማዘጋጀቷ ይታወሳል።ረቂቅ ፖሊሲው መነሻ ያደረገው የሀገሪቱን የማዕድን አለኝታና በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ላይ እንደሆነ ይጠቁማል። በረቂቁ ላይ እንደሰፈረው እስከ 21ኛው ክፍለ ዘመን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ድረስ ስኬቶችና ሀገራዊ አቅሞች እውን መሆን የቻሉት የጥሬ ማዕድን ሀብትን ለተለያዩ ዘርፎች በግብዓትነት በመጠቀም ነው። ወደ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሲመጣ ደግሞ በሀገሪቱ ትርጉም ባለው ደረጃ ዘመናዊ የማዕድን ሀብት ልማት የሚታየው በወርቅ ደረጃ ነው።
ይሁን እንጂ ይህን ልማት ወደ ሌሎች የከበሩ ማዕድናት የማስፋፋት ውስኑነቶች ይስተዋላሉ። የወርቅ ማዕድን ማውጣት ሥራም ቢሆን የረጅም ጊዜ ታሪክ ይኑረው እንጂ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ከማሳደግ፣ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር፣በገንዘብ ተቋማት ዋስትና ከመቆጠር፣በሀገር ደረጃ እንደ አንድ ኢንደስትሪ ተወዳዳሪ ሆኖ ጎልቶ ከመውጣት አንጻር ብዙ ርቀት መጓዝ አለመቻሉ በሰነዱ ሰፍሯል። ኢትዮጵያ ለወጠነችው መዋቅራዊ ሽግግር እቅድና የመካከለኛ ገቢ ትልም መሳካት ወሳኝ እንደሆኑ የታመነባቸውን የአምራች ኢንደስትሪና የግብርና ቴክኖሎጂን ከማፋጠን አንጻር ከማዕድን ልማት ገና ብዙ ሥራ ይጠበቃል።ዘርፉ በሌሎች ተቋማት ላይ እንደሚስተዋለው ሁሉ የአፈጻጸም ሥልትና የተቋማት ዝቅተኛ ብቃት እንዲሁም ተቀናጅቶ አለመሥራት ክፍተቶች እንዳሉበትም በሰነዱ ተወስቷል። የሥርዓት መለዋወጥም ልማቱ ቀጣይነት እንዳይኖረውና ትኩረትም እንዲያጣ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ በመዋቅራዊ ሽግግር ሂደት በኢንዱስትሪ ልማት መበልጸግ ግብ አድርጋ ስትንቀሳቀስ ጥሬ ማዕድናትን ወይንም በከፊል የተሰናዱ የማዕድን ውጤቶችን በግብአትነት መጠቀሟ የግድ መሆኑም ተመልክቷል። በሀገር ውስጥ የሚገኙ ማዕድናትን ለግብአትነት መጠቀም አዋጭ ብቻ ሳይሆን፣የመዋቅራዊ ሽግግር የማይታለፍ እርከን መሆኑም በሰነዱ ተመልክቷል። ለቀጣዮቹ 20 አመታትም የማዕድን ዘርፍ ልማት ርዕይ ተቀምጧል። በእነዚህ አመታት ውስጥ የኢንዱስትሪ ልማት መሠረት የሚሆን ፍትሐዊና ዘላቂ ማህበራዊ ተጠቃሚነትን እንዲሁም ዘላቂ ልማትን የሚያረጋግጥ እንደዘርፍም ተወዳዳሪ የሆነ የማዕድን ኢንዱስትሪ አቅም መፍጠር አንዱ ሲሆን፣በሌላ በኩል ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው መካከል አንዷ እንድትሆንና ለዚህም የሚመጥኑ አቅሞች ባለቤት ለመሆን እንድትበቃ ከተተለመው ርዕይ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ማስቻል እንደሆነም ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ያላትን ሀብት የመለየትና በዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ዘዴ የማጠናቀር የትኩረት አቅጣጫ የሆነውን የልማት ስትራቴጂዎችን ካላት ሀብት ጋር ማጣጣም መቻልን ፣ ለአምራች ኢንደስትሪ ልማትና ግብርናው እንዲዘምን የግብአት አቅሞችን ቀድሞ መለየት በማዕድን ዘርፍ ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪ ለመገንባት፣አዋጭ መስኮች ለመለየትና በማዕድን ዘርፍ ልማት በሚደረግ ኢንቨስትመንት ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት ቀልጣፋና ወጪ ቆጣቢ ሥርዓት መዘርጋትን የመሳሰሉ ጉልህ ፋይዳዎች ታሳቢ ያደርጋል። ዝርዝር ሀሳቦችን ያካተተው ይህ ረቂቅ የማዕድን ሀብት ፖሊሲ ለመጽደቅ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ይገኛል።ማዕድን ሚኒስቴር የማዕድን ዘርፉን በአግባቡ ለመምራትና ለማስተዳደር የሚያስችል ፖሊሲ እንዲረቅ ከማድረግ ጀምሮ በውስጣዊ አደረጃጀቱም አቅም ለመፍጠር የሰው ኃይልን ጨምሮ በተለያዩ አደረጃጀቶች መዋቅራዊ ለውጥ(ሪፎርም) በማድረግ፣የተቋሙንም ገጽታ በመለወጥ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ የማዕድን ዘርፉ በሀገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ አስተዋጽኦው ከፍ እንዲል እየሰራ መሆኑን የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሪት ፌቨን ተሾመ ገልጸውልናል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ለመጽደቅ መጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው የማዕድን ሀብት ልማት ረቂቅ ፖሊሲ፣አንዱ የማዕድን ዘርፉን የሚመለከት ሲሆን፣ሌላው ደግሞ የነዳጅ ሀብትን የሚመለከት ነው። በተለይም ማዕድንን የሚመለከተው ፖሊሲ ዘርፉ ወደፊት ሊደርስ የሚችልበትን የእድገት ደረጃ ጭምር የሚያመላክትና ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ሲሆን፣ፖሊሲው ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርቧል።
ሚኒስቴሩ የማዕድን ልማት ፖሊሲ እንዲወጣ ከማድረግ ጀምሮ እየወሰዳቸው ስላለው የለውጥ እርምጃዎች ፣ እስካሁንም ባከናወናቸው ተግባራት ያስመዘገባቸውን ውጤቶችና በቅርቡ ደግሞ በደቡብ አፍሪካ ኢንቨስቲንግ ኢን አፍሪካ ማይኒንግ(investing in Africa Mining) በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው ጉባኤ እንዲሁም የዚሁ መርሃ ግብር ቀጣይ በሆነው የካናዳ ጉባኤን በተመለከተና በአጠቃላይ በዘርፉ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን እንቅስቃሴ እንደገለጹልን፤ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ያላቸውን የማዕድን ልማት ሥራዎች ለይቶ እየሰራ ይገኛል። ከትኩረት አቅጣጫዎቹ አንዱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በግዥ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የማዕድን ግብአት በሀገር ውስጥ መተካት ሲሆን ፣ ሥራዎችም ተጀምረዋል።
ለአብነትም ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ለኃይል ግብአትነት የሚውለውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለመቀነስ የተወሰደው እርምጃ ይጠቀሳል። በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎትና የገንዘብ አቅም ያላቸው ስምንት የውጭ ኩባንያዎች ሀብቱ በሚገኝባቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተመቻችቶላቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል። ኩባንያዎቹ ግዙፍና ከስድስት ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው ናቸው። ግብአቱን በማምረት በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር እገዛ ያደርጋሉ።ኩባንያዎቹ በዘርፉ መሰማራታቸው የውጭ ንግድ አቅም ለመፍጠርና ለማሻሻልም ሚና ይኖረዋል። ኢትዮጵያ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በየአመቱ ወደ 300 ሚሊየን ዶላር ታወጣለች።ይህን ወጪ ለማስቀረት ወይንም ለማዳን ብቻ ሳይሆን፣ግብአቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብም የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማግኘት ታሳቢ ያደረገ ነው።በመሆኑ በሁለተኛው የትኩረት አቅጣጫ የወጪ ንግድን ማሳደግ ነው።
የማዕድን ዘርፍ የተረጋጋና ከፀጥታ ስጋት ነጻ የሆነ አካባቢን ይፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ በገጠማት የጦርነትና የተለያዩ ችግሮች ምክንያት በውጥረት ውስጥ ብትሆንም በማዕድን ዘርፉ አበረታች የሆኑ ውጤቶች እንደተመዘገቡ፣በተለይም በወርቅ ማዕድን በ2013 በጀት አመት ጥሩ የሚባል ገቢ ለሀገር ማስገኘት መቻሉን ጠቅሰዋል። በተያዘው በጀት አመትም ጥሩ ውጤት እንደሚመዘገብ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ያሳያል። በበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወር አፈጻጸም ከአምና ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር የ12 በመቶ ብልጫ ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በትኩረት እየሰራ ያለው የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሰራር ሥርአት መዘርጋት ነው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የጀመራቸውን የለውጥ እንቅስቃሴዎች ዘለቄታ እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር ያለው የቁርጠኝነት ማሳያዎችን በተመለከተ ዳይሬክተሯ ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹የተለያዩ መሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ በሀገሪቱ የማዕድን ሀብቶች በስፋት የሚገኙት የፀጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ነው። ሆኖም ግን ሥራው አልተስተጓጎለም። የበለጠ ውጤታማ ለመሆን ሚኒስቴሩ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ስምምነት በማድረግ የማዕድን ፖሊስ ክፍል እንዲዋቀርና ትላልቅ በሚባሉ የማዕድን መገኛ ስፍራ የፀጥታ ኃይል ተመድቦ እንዲሰራ በማድረግ የፀጥታ ስጋት ለመቀነስ የሚያስችል እርምጃ ተወስዷል። ይህ በመሆኑም ቀደም ሲል በፀጥታ ሥጋት ሥራ አቋርጠው የነበሩ ኩባንያዎች ወደ ሥራ ተመልሰዋል።አዳዲስ ኢንቨስተሮችንም መሳብ ተችሏል። ሥራውን በማጠናከር በበለጠ መንቀሳቀስ እንደሚገባ በሚኒስቴሩ ግንዛቤ ተይዟል›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። የፀጥታ መዋቅሩ መኖር የሀገር ሀብትን አላግባብ የሚያባክኑ ህገወጦችን ለመከላከልም አጋዥ እንደሚሆን አመልክተዋል።
እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ ፤ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ብሎ ለይቶ በአስር አመት ውስጥ ለመተግበር በዕቅድ ከያዛቸው አምስት ምሶሶዎች የማዕድን ዘርፍ አንዱ በመሆኑ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውም ይህንኑ መሠረት አድርጎ በትኩረት ነው ተግባሩን እየተወጣ የሚገኘው። በትኩረት ካከናወናቸው ተግባራት የሰው ኃይል የአቅም ግንባታ አንዱ ሲሆን፣አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለይም የማዕድን ሀብቱ በስፋት በሚገኝባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) ጋር አብሮ ለመሥራት እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። የትምህርት ተቋማቱ በማዕድን ዘርፍ ላይ ያተኮሩ የትምህርት ክፍሎችን (ዲፓርትመንቶች) በመክፈት ሙያተኞችን እንዲያፈሩ ማስቻል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በጥናትና ምርምር አበርክቶ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።
በዚሁ መሠረት የትምህርት ተቋማቱ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር የሚሰሩበት ሥርዓት ተዘርግቷል። በአሁኑ ጊዜም ቁጥራቸው ወደ 45 የሚሆኑ ተማሪዎች በትምህርት ላይ ይገኛሉ። ለግንባታ የሚውለው ማርብል የተባለው ግብአት ላይ ስልጠና ለመስጠት በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ማዕከል ለማቋቋም የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ተደርሷል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የውስጥ አቅሙን በማጠናከር፣የሌሎችንም ባለድርሻ አካላት ትብብር በመጠየቅና በማሳተፍ በሀገር ውስጥ እያከናወነ ካለው እንቅስቃሴ በተጨማሪ በተለያዩ ሀገራት በሚካሄዱ ጉባኤዎች ላይ በመሳተፍ ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ያላትን እምቅ ሀብት ለማስተዋወቅና በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸውን ባለሀብቶችንም ለመሳብ ጎን ለጎን ጥረት እያደረገ ይገኛል። በቅርቡ በደቡብ አፍሪካና በካናዳ በተከታታይ የሚካሄድ ጉባኤ ይጠቀሳል።
እዚህ ላይ ዳይሬክተሯ በሰጡት ማብራሪያ፤በማዕድን ዘርፍ ላይ በደቡብ አፍሪካና በካናዳ በሚካሄዱ ጉባኤዎች ላይ በዓለም ላይ ስመጥር የሆኑ የማዕድን ኩባንያዎችና እምቅ ሀብቱ ያላቸው ሀገሮች የሚሳተፉበት፣ አንዱ ለሌላው ያለውን ተሞክሮ የሚያካፍልበት እና የገበያ ትስስርም የሚፈጠርበት መድረክ ነው። ኢትዮጵያም ሀብቷን ለማስተዋወቅና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ይህን አጋጣሚ ትጠቀምበታለች። ባላቸው የማዕድን ሀብት ልማት ፖሊሲ፣ሀብቱን በማልማትና ከዘርፉ ገቢ በማግኘት ከኢትዮጵያ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ሀገራትና ኩባንያዎች ጋር በመገናኘት ልምድ ትቀስማለች። ይህም በደቡብ አፍሪካ እና ከአንድ ወር በኃላ ደግሞ በካናዳ በተመሳሳይ ጉባኤ ይካሄዳል።ከሁለቱ ሀገራት ቀጥሎ ወደፊት የሚካሄደው የዓለም የማዕድን ጉባኤ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲካሄድ ከወዲሁ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር ተጀምሯል።ጉባኤው በየአመቱ የሚካሄድ በመሆኑ ኢትዮጵያ ሦስተኛውን ዕድል አግኝታ እንድታዘጋጅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
በዚህ ወቅት ባለሀብቱ ቢሰማራባቸው ተብሎ ቅድሚያ የተሰጣቸው የትኞቹ የማዕድን ዘርፎች ናቸው ተብለው ለተነሳው ጥያቄም ዳይሬክተሯ በሰጡት ምላሽ፤ እንደሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ሆነ ግብርናውን ለማዘመን ማዳበሪያ ትልቁን ድርሻ የሚይዝ በመሆኑ ቅድሚያ ከተሰጣቸው መካከል ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ እንዲመረት ነው። ለማዳበሪያ ግብአት የሚውል ፖታሽ የተባለው ማዕድን በተለይ በአፋር ክልል ውስጥ በስፋት የሚገኝ በመሆኑ ባለሀብቱ በዚህ ዘርፍ ላይ ቢሰማራ ይመረጣል። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ የማዳበሪያ ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ ከሀገር የመግዛት አቅም በላይ እየሆነ ነው። ስለሆነም በሀገር ውስጥ እንዲመረት መደረጉ ተገቢ ነው።
ይሄ ትኩረት ይሰጠዋል። ሌላው ትኩረት የተሰጣቸው ዘርፎች ለግንባታ ግብዓት የሚውሉ ማርብልና ሴራሚክስ ናቸው፡፡ የትኩረት አቅጣጫዎቹ በቅደም ተከል ቢጠቀሱም በአጠቃላይ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ተደርጎባቸው ወደሀገር የሚገቡ ግብአቶች በሀገር ውስጥ ምርት እንዲተኩና ለውጭ ገበያም ቀርበው የውጭ ምንዛሪ ግኝትን እንዲያሳድጉ ነው የሚፈለገው። የማዕድን ዘርፉ ተነቃቅቶ በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ሚና እንዲኖረው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ከቀጠለ የላቀ ውጤት እንደሚመዘገብና እንደሀገር የተያዘው የልማት ግብም እንደሚሳካ ተስፋ እናደርጋለን።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5/2014