አንዱ አካባቢ ከሌላው አካባቢ መጠኑና አይነቱ ይለያይ እንደሆን እንጂ ኢትዮጵያ የእምቅ የማዕድን ሀብት ባለቤት ናት። ሀብቱ የሌለበት አካባቢ አይገኝም። ይህን እውነታ ደግሞ ከዘርፉ ተመራማሪዎች ብቻ ሳይሆን፣ በየአካባቢው የሚኖረው ማህበረሰብ ጭምር በልምድ የሚያውቀውና የሚያረጋግጠው ነው። ማዕድን የማውጣቱ ሥራ ባህላዊ ነው መባሉም ማህበረሰቡ አካባቢው ላይ ያለውን ሀብት ጠንቅቆ እንደሚያውቅ አንዱ ማሳያ ነው። በተለያየ የህብረ ቀለማት ቀልብን የሚስቡት ለጣት ቀለበት፣ ለአንገት ሀብልና ለተለያየ ማስዋቢያ የሚውሉ ፈርጦች በባህላዊው የማዕድን አውጭ በቁፋሮ ከመሬት ውስጥ ወጥቶ ገበያ ላይ የዋሉ ናቸው። ባህላዊው የማዕድን ቆፋሪም ቢሆን ሸጦ ከሚያገኘው ገቢ በመጠኑም ቢሆን፣ ኑሮውን እየደጎመበት ነው።
ኢትዮጵያ ወርቅን ጨምሮ ለግንባታና ለኢንደስትሪ ግብአት እንዲሁም ለጌጣጌጥ የሚውል የሁሉም አይነት የከበሩ ማዕድናት ባለቤት ናት። ይልቁንም ተደጋግሞ የሚነሳው ይህን እምቅ ሀብቷን ለይታና በአግባቡ ባለማስተዳደር ጥቅም ላይ በማዋል በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ወደ አገር የሚገባውን የማዕድን ውጤት በአገር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለመተካትም ሆነ ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ ማድረግ አለመቻሏ ነው። ጥረቶች ቢኖሩ እንኳን አጥጋቢ በሚባል ደረጃ የሚገለጽ አይደለም። ጥሬ እቃው በአገር ውስጥ እያለ ለግንባታ ማጠናቀቂያ የሚውሉ እንደሴራሚክ፣ ለቤት ቀለምና ለተለያዩ ፋብሪካዎች ግብአት የሚውሉ በውጭ ምንዛሪ ከውጭ ተገዝተው እንደሚገቡ ተሞክሮዎች ያሳያሉ። ዘርፉ በክትትልና ቁጥጥር ማነስም ለህገ ወጥነት መጋለጡ ይታወቃል። በዚህ የህገ ወጥ ሥራ ውስጥ ተዋናይ የሆኑ የአገርን ጥቅም በማስቀረት የሚፈጥሩት ተጽዕኖም በግልጽ ይታያል።
ዘርፉን ለማልማት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይና ቴክኖሎጂ የሚፈልግ እንደሆነ ከዘርፉ ባለሙያዎች እንሰማለን። ሀብቱ እያለ በአቅም ውስንነት በሚፈለገው ልክ መጠቀም አልተቻለም። ዘርፉ በተለያየ ተግዳሮት ውስጥም ሆኖ እንደአገር ከቀጠናው አገራት ጋር በልማት ለመተሳሰር የተነደፈው የአስር አመት መሪ ዕቅድ ውስጥ አንዱ የኢኮኖሚው ማሳደጊያ የጀርባ አጥንት ተደርጎ በእቅዱ ተካትቷል። የእቅዱ አካል ሆኖ ውጤት እንዲያመጣ ወይንም አስተዋጽኦ እንዲኖረው ካስፈለገ መንግሥት ብቻ ሳይሆን በዘርፉ ላይ በተለያየ መንገድ ድርሻ ያላቸው ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በዚህ ረገድም በምርምርና ጥናት እንዲሁም በሀሳብ ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይጠቀሳሉ። በአሁኑ ጊዜ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ዩኒቨርሲቲዎች ተደራሽ ሆነዋል።
ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በአካባቢው ስላለው የማዕድን ሀብት በአይነት፣ በመጠንና ሊያስገኙ ስለሚችሉት ጥቅም ጭምር በጥናትና ምርምር ለይቶ ዘርፉን ለሚመራው አካል የጥናት ውጤታቸውን እንዲያውቁት ማድረግ፣ ግንዛቤ በመፍጠርም ከፍ ያለ ሚና ይጠበቅባቸዋል። ብዙዎች በዚህ መልኩ እንደሚንቀሳቀሱ ቢታወቅም በሚያጋጥማቸው የጥናትና ምርምር የበጀት እጥረት፣ ዘርፉን ከሚመራው አካል ጋር ተናብቦ ባለመስራት፣በትኩረት ማነስና በተለያየ ምክንያት ሥራዎች እንዳልተሰሩም ሀሳብ ይነሳል።
በዚህ ረገድ በአገሪቱ አንጋፋ ከሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንዱ የሆነውን ጅማ ዩኒቨርሲቲን በማዕድን ዘርፉ በጥናትና ምርምር እያበረከተ ስላለው አስተዋጽኦና እንደአገር ስለተያዘው አገራዊ የዕቅድ አቅጣጫ ዘርፉ ስለሚኖረው ሚና በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሥር ከሚገኘው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሲቪልና አካባቢ ምህንድስና ትምህርት ክፍል ዲንና መምህር ከሆኑት ማሙዬ ሁሴን ጋር ቆይታ አድርገናል። መምህር ማሙዬ በሲቪል ኢንጂነሪንግና ኃይድሮ ፓወር ትምህርት የተማሩ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜም የአንደኛና የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማስተማርና በምርምር በማገዝ በዩኒቨርሲቲው በማገልገል ላይ ናቸው።
መምህር ማሙዬ እንዳሉት በአገር ደረጃ የአስር አመት ዕቅድ በመንደፍና ከዛም ላቅ ብሎ ለሚቀጥሉት 30 አመታት በግብርና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በቱሪዝም ኢንደስትሪ በሁሉም አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ልማትን በማፋጠን ኢኮኖሚን ለማሳደግ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው። በእቅድ አቅጣጫው ትኩረት ከተሰጣቸው ከአምስቱ ምሶሶዎች(ፒላር)ተለይተው በአገራዊ ልማት ዕቅዱ ከተያዙት መካከል አንዱ የማዕድን ዘርፍ ነው። ትኩረት መሰጠቱ ተገቢ ነው።
ኢትዮጵያ መልክአ ምድሯ(ቶፖግራፊዋ) የተለያየ ሲሆን፣ ይህም በተራራማ፣ ሜዳማና ዝቅተኛ ይገለጻል። በተለያየ ጊዜ በተካሄደ ተፈጥሯዊ የመሬት እንቅስቃሴም እሳተ ጎመራ(ቮልካኖ) ያለበት አካባቢዎችም አሏት። እጅግ በጣም ጥንታዊ የሆኑ አለቶች(ሮኮች) መገኛም ናት። በረጅም ጊዜ የመሬት እንቅስቃሴ (ሴግመንቴሽን) አፈር ሲከማችና ክምችቱም በሺዎች አመት ሲቆጠር አካባቢው ላይ የሀብት ከምችት እንዲኖር ያስችላል። ኢትዮጵያ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ስኩዌር ሜትር አካባቢ የሚገመት ስፋት ያላት ትልቅ ሀገር ናት። የመሬት ስፋቷም ከአፍሪካ ጋር ሲነጻፀር ሽፋኑ አራት በመቶ ያህል ብልጫ እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህ ሁሉ መረጃ ኢትዮጵያ ሰፊ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት እንዳላት ያሳያል። የተፈጥሮ ሀብቱ ሰፊ ከመሆኑ አኳያ መንግሥት በአስር አመቱ መሪ ዕቅድ ውስጥ በማካተት ከዘርፉ ለመጠቀም የተያዘው አቅጣጫ ተገቢነት አለው።
እስካሁን ባለው ክንውን ዘርፉ ላይ የተሰሩትን ሥራዎች መምህር ማሙዬ እንዲህ ያስረዳሉ፤ፖሊሲዎን በማዘጋጀትና ባለሀብቱን በመሳብ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም፤ አንዳንድ ማዕድናትን ጥቅም ላይ በማዋል አገራዊ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር ብዙ ሥራዎች ይጠበቃሉ። ሥራው እየተከናወነ ያለው በአብዛኛው በባህላዊ መንገድ በጥቂት የሰው ኃይል ነው። ይህ ደግሞ ከዘርፉ የሚፈለገውን ያህል ጥቅም ሳያስገኝ ቀርቷል። ይህን ለማሻሻል በመንግሥት በኩል በተለይም በማዕድን ሚኒስቴር በኩል ዘርፉን ለማዘመን የሚያግዝ ፖሊሲ ከማሻሻል ጀምሮ እየተወሰደ ያለው እርምጃ አበረታች ነው። ትምህርት ተቋማት በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች በሚችሉት ሁሉ ትብብር በማድረግ ተደራሽ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሲባል ግን የበለጠ መስራት ይጠበቃል ከሚል እንጂ በትምህርት ተቋማት አማካኝነት ተስፋ ሰጭ የሆኑ የምርምር ሥራዎች ተከናውነዋል።
የምርምር ውጤቶቹ ከኢኮኖሚ አንጻር ያበረከቱት አስተዋጽኦ፣ ወደፊትስ ምን ቢደረግ ምን ማግኘት ይቻላል፣ ዘርፉ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ እንዲችል ምን አይነት ድጋፍ መደረግ አለበት የሚል የጥናትና ምርምር ሥራዎችም ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የከፍተኛ ትምህርትን የሚመራው እንዲሁ ትኩረት በመስጠት ትምህርት ሚኒስቴርና የማዕድን ምርምር የትኩረት አቅጣጫዎች ለይቷል። በፖሊሲ ደረጃም አዘጋጅቷል። ይህም ለማዕድን ዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያሳያል።
አገራዊ የማዕድን ጥናት ምርምርና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ቦታዎች መለየት በሚል ጥናት እንዲካሄድ የተለያዩ ቡድኖችን በማቋቋም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ማዕድኖች ከመሬት ውስጥ በቁፋሮ በሚወጡበት ጊዜም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህ ሲባል ማዕድኑ የወጣበት አካባቢ እንዴት መልማት እንዳለበት እንዳይዘነጋ ነው። ምክንያቱም ማዕድኑ ጥቅም እንዳስገኘው ሁሉ ጉዳትም ማስከተል የለበትም። በመሆኑም የምርምርና ጥናት ሥራው ሁለገብ ነው መሆን ያለበት።
ጅማ ዩኒቨርሲቲም እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎች እንዲበረታቱ ነው የሚያደርገው። በዩኒቨርሲቲው የማቴሪያል ሳይንስ ኤንድ ኢንጂነሪንግ ፋካልቲ(ትምህርት ክፍል)፤ ውስጥ የሚያስተምሩ አንዳንድ መምህራን ጥናት በማካሄድ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። ለአብነትም ጅማ ከተማ ከፍተኛ የሆነ የሸክላ አፈር (ክሌይ) ክምችት ይገኛል። የሸክላ አፈር በውስጡ የተለያዩ ማዕድናት(ሚኒራል) ይገኛል። ይህ የማዕድን ሀብት ለግንባታ ለሚውል ለጡብ ምርት ግብአት ከመዋል በተጨማሪ ለምን አገልግሎት ሊውል እንደሚችልና የሀብት መጠኑን ወይንም ክምችቱን ለማወቅ ነው በዩኒቨርሲቲው መምህራን ጥናት እየተደረገ ያለው።
በጅማ ዞን ውስጥ በማዕድን የሀብት ክምችት ደረጃ ከሚጠቀሰው አንዱ የድንጋይ ከሰል ማዕድን ነው። ያለው የክምችት መጠን አገሪቱ ለሲሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች የሚያስፈልጋትን ግብአት ማሟላት የሚያስችል ሲሆን፣ ሀብቱ ከጅማ ከተማ በ44ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። በአካባቢው መኖሩ ከአስር አመት በፊት የሚታወቅና ለአካባቢው ነዋሪዎችም ከፍተኛ የሥራ ዕድል በመፍጠር አስተዋጽኦ አበርክቷል። አሁን ላይ ግን የሚገኝበት ደረጃ ለጊዜው መረጃው እንደሌላቸው የሚገልጹት መምህር ማሙዬ በተመሳሳይ ከጅማ ከተማ 180ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ጊቤ ተብሎ በሚጠራው አካባቢም ሀብቱ እንደሚገኝ መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ተናግረዋል። እንደርሳቸው ማብራሪያ በቅርቡ ከደቡብ ክልል ሥር ወጥቶ የተደራጀው በደቡብ ምዕራብ ክልል ውስጥ ቦንጋ፣ ዳውሮ፣ በተባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ የድንጋይ ከሰል ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል።
አካባቢዎቹ ለጅማ ዞን በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ። የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ምሁራንም በሥፍራው ተገኝተው ከአካባቢው አርሶ አደሮች ባገኙት መረጃና እነርሱም እንዳረጋገጡት አርሶ አደሮቹ የአካባቢውን አፈር በባህላዊ መንገድ በማቅለጥ ብረት ይሰራሉ። የዚህ ውጤት የሚያመላክተው በአፈር ውስጥ ከፍተኛ ክምችት ያለው ማዕድን(አይረን) መኖሩን ነው። ብረት(ሜታል) ሚኒራል ወይንም ማዕድን ከሚባለው ውስጥ ነው የሚገኘው። በመሆኑም በነዚህ አካባቢዎች በማዕድን የበለፀገ ማዕድን አለ ብሎ በሙሉ እምነት መናገር ይቻላል። ትኩረት በማድረግ የብረት ማዕድንን በብዛት መጠቀም ይገባል።
የማዕድን ዘርፉን በማልማት በአገር ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖረው አቅዶ መንቀሳቀስ ለመንግሥት ብቻ የተተወ ተግባር እንዳልሆነ የጅማ ዩኒቨርሲቲን ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል። መምህር ማሙዬ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ኃላፊነት አለብኝ በሚል መንፈስ ማዕድንን ጨምሮ በተለያየ ዘርፍ የአስር አመት ስትራቴጂ እቅድ ነድፏል።
ዕቅዱንም በትምህርት ሚኒስቴር አፀድቆ ነው ወደ ሥራ የገባው። ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን የማዕድን ሀብት ክምችት ባለው አቅም የመለየት ሥራ ለመሥራት ጥረት ያደርጋል። አቅም ካነሰው ደግሞ ለዘርፉ ምርምር ሥራ የሚያግዝ በኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይና በማዕድን ሚኒስቴር ሥር ብዙ ቤተሙከራዎች ይኖራሉ የሚል እምነት አላቸው መምህር ማሙዬ። ናሙናዎችን በመውሰድ በነዚህ ተቋማት መጠቀም የሚቻልበት ዕድል በመኖሩ ተግዳሮት እንደማይሆን ያምናሉ። ዩኒቨርሲቲው በማዕድን ዘርፍ የተለየ የትምህርት ክፍል ባይኖረውም የአገር ዕቅድን ለመጋራት የሚያግደው ነገር እንደሌለ ይገልጻሉ።
እንደአገር ያለውን እምቅ ሀብት ለመጠቀምና አገራዊ ዕቅድንም ከግብ ለማድረስ ዩኒቨርሲቲው በሚችለው ሁሉ ያደርጋል ብለዋል። በግላቸው የማዕድን ሚኒስቴርን ድረ ገጽ ለመጎብኘት ባደረጉት ጥረትም አዳዲስ የማዕድን አይነቶችን የማስተዋወቅና ባለሀብቶችን ለመሳብ የሚደረገው ጥረት አበረታች ሆኖ አግኝተውታል። በመገናኛ ብዙሃንና በተለያየ የመረጃ ማሰራጫ ዘዴ የበለጠ በማስተዋወቅ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ይገባል ይላሉ መምህር ማሙዬ።
በዘርፉ የሚያስፈልጉ ከፍ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም እንዲቻል ደግሞ አቅም ያላቸውን ባለሀብቶች በተለያየ አገር በተወከሉ አምባሳደሮች አማካኝነት በመሳብ መጠቀም እንደሚገባም ሀሳብ ሰጥተዋል። አንድ በዘርፉ ለመሰማራት የሚፈልግ ባለሀብት ምን ማሟላት እንዳለበት የሚያሰራ ህግ በአገር ደረጃ በመኖሩ የሚጠበቀው ህጉን መሬት ማውረድ ወይንም መተግበር ሲሉም አክለዋል።
መምህር ማሙዬ በሰጡት ምክረ ሀሳብ የማዕድን ዘርፉ የግጭት መንስኤ የሚሆንበት አጋጣሚ መኖሩን ሀብቱ ካላቸው አገሮች ተሞክሮ መውሰድ እንደሚቻል ጠቁመዋል። እንደርሳቸው ሀሳብ የማዕድን ሀብቱ የሚገኝበትን ቦታና መጠን ለማወቅ፣ ለምን አገልግሎት እንደሚውል ለመለየትና ለኢኮኖሚ ግንባታም ሊኖረው ስለሚችለው አስተዋጽኦ፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትም ስላለው አበርክቶ በምርምር ለመለየት ጥረት እንደሚደረገው ሁሉ ሀብቱ የግጭት መንስኤ ሳይሆን እንዴት ለአገር ብልጽግና ይጠቅማል። እንዴት ሰላማዊ መንገድ ያመጣሉ፣ የአካባቢው ማህበረሰብ ከዘርፉ ምን ይጠቀማል፣ በዘርፉ የሚሰማሩ ለአደጋ ሳይጋለጡ እንዴት ሥራቸውን መሥራት እንደሚችሉ ለይቶ መሥራት እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 28 /2014