
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ሥልጣናቸውን በፍቃዳቸው እንዲለቁ መጠየቃቸው ተሰምቷል።
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምክትላቸው የሆኑት ዊሊያም ሩቶ “ኬንያ ካጋጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ እንድትወጣ የሚጠበቅባቸውን አልሰሩም” በሚል ይከሷቸዋል።
የኬንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ መንግስትን ከውስጥ ሆነው መተቸት እንደሌለባቸውም ኡሁሩ ኬንያታ ተናግረዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንት ሩቶ በበኩላቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የኬንያ መንግስት ካቢኔ ተሰብስቦ እንደማያውቅ እና የመንግስት ውሳኔዎች በፕሬዚዳንቱ የስልክ ጥሪ ብቻ እንደሚተላለፉ በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
ኬንያ የፊታችን ነሃሴ ወር ላይ ከምታደርገው በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በፊት በሁለቱ መካከል ያለው የከረረ አለመግባባት ይፋ መውጣቱ ተነግሯል።
በፕሬዚዳንቱ እና በምክትል ፕሬዚዳንቱ መካከል ያለው ልዩነት ገሃድ የወጣውም የአገሪቱ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሞዋይ ኪባኪ ሞትን ተከትሎ በነበረው የሀዘን ስነ ስርዓት ላይ ነበር።
ባሳለፍነው ሳምንት አርብ በነበረው የቀድሞ ፕሬዚዳንት ስርዓተ ቀብር ላይም ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የምክትላቸውን ዊሊያም ሩቶን እጅ ለመጨበጥ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ ተመልክቷል።
ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ምክትላቸውን ከኃላፊነት የማባረር ስልጣን የላቸውም የተባለ ሲሆን፤ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ከስልጣን ሊነሳ የሚችለው ከተከሰሰ ወይም አቅም ከሌለው ብቻ ነው።
የኬንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ የፊታችን ነሃሴ ወር በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ላይ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር በእጩነት መቅረባቸው ይታወሳል።
የስልጣን ዘመናቸው ማጠናቀቂያ ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ክምክትላቸው ይልቅ ለቀድሞ ተቀናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ ድጋፍ መስጠታቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ምክትል ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፤ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ “ማንንም መደገፍ መብታቸው ነው፤ ምርጫውን ግን እኛ እናሸንፋለን” ሲሉ ተደምጠው ነበር።
የኡሁሩ ኬንያታ እና የዊሊያም ሩቶ አለመግባባት መነሻም የፊታችን ነሃሴ ወር የሚካሄደው ምርጫ ጉዳይ ሳይሆን እንዳልቀረ መላ ምቶች ተቀምጠዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 /2014