
እስራኤል፤ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭን የናዚ መሪ አዶልፍ ሂትለር “አይሁዳዊ ነው” ሲሉ የሰጡት አስተያየት ጸረ ሴማዊነት እና አደገኛ ነው ስትል ወቀሰች።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ያየር ላፒድ በእስራኤል የሚገኙትን የሩስያ አምባሳደር፤ ላቭሮቭ እሁድ እለት ከጣሊያን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስላሉት የተሳሳተ ንግግር ማብራሪያ ለመስጠት እንደሚጠሩ አስታውቀዋል።
ላፒድ ዋይ ኔት ለተባለ የዜና ድረ-ገጽ እንደተናገሩት “ይህ ይቅር የማይባል፣ አሳፋሪ መግለጫ፣ አሰቃቂ ታሪካዊ ስህተት ነው፣ እናም ከሩሲያ ይቅርታ እንጠብቃለን” ብለዋል።
እስራኤል በላቭሮቭ ንግግር እጅጉን እንደተበሳጨች በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ብትገልጽም፤ ከሩሲያ ኤምባሲ እስካሁን የተሰጠ ምንም አይነት አስተያየት የለም።
ሬቴ 4 ቻናል ከተባለ የጣሊያን ቴሌቪዥን ጋር በአንድ ጣሊያናዊ አስተርጓሚ አማካኝነት ቆይታ ያደረጉት ላቭሮቭ፤ ስለ ሂትለር የተናገሩት ጋዜጠኛው፤ ሩሲያ አሁን በዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ ዘመቻ “ዩክሬንን ከናዚ ለማዳን” የምትለው ለምንድን ነው? ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው።
ጋዜጠኛው አስከትሎ ላቭሮቭን “የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ አይሁዳዊ እንደሆኑ እየታወቀ እንዴት ከናዚዝም እናድናታለን ትላላችሁ?” የሚል ጥያቄ አቅርቦላቸዋል።
የላቭሮቭ ምላሽ ግን “ሂትለርም እኮ አመጣጡ ከአይሁድ ነው፣ ስለዚህ ምንም ማለት አይደለም” የሚል ነበር።
ይህ ብቻ አይደለም ላቭሮቭ “ጥበበኞቹ የአይሁድ ሰዎችም፤ ትልቁ ጸረ-ሴማዊነት የሆኑት እራሳቸው አይሁዶች ናቸው ይላሉ “ የሚል መከራከሪያም አቅርቧል።
የላቭሮቭ ንግግር እስራኤልን አስቆጥቷል።እስራኤል ለዩክሬን ደጋግማ እንደምትደግፍ ገልጻላች፣ ነገር ግን በጎረቤት ሶሪያ ከባድ ተጽእኖ የመፍጠር አቅም ካላት ሩሲያ ጋር ያለው ግንኙነት እንዳይበላሽ ጥንቃቄ ስታደርግ ቆይታለች።
ለዚህም ነው ምእራባውያኑ በሩሲያ ላይ ማእቀብ ሲያዘንቡ፤ እስራኤል ድርጊቱን ከማውገዝ በዘለለ ምንም ስትል ስታስፈጽም ያልታየችው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 26 /2014